በጤና እንክብካቤ፣ በሕክምና መገልገያዎች እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ‹‹ኢትዮ ኸልዝ›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ከየካቲት 16 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ለማካሄድ ቅድመ ዝግጀቱን ማጠናቀቁን ፕራና ኤቨንትስ አስታውቋል፡፡
የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በሰጡት መግለጫ፣ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አቅራቢዎችን አገር ውስጥ ከሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በማጣመር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ዓውደ ርዕዩም ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ ወኪሎችና አገልግሎት ሰጪዎች በአንድ ጊዜና ቦታ በሺዎች ለሚቆጠሩ የጤና ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት መሆኑን አቶ ነብዩ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የሕክምና አገልግሎት ፍላጎት ለማሳካት ይህ ኩነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ከባንግላዴሽ፣ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከጆርዳን፣ ከህንድ፣ ከሱዳን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኩባንያዎች ኩነቱ ላይ መሳተፋቸው በዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን ችግር በተወሰነ ደረጃ ሊቀርፈው ይችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮ ኸልዝ በጤና ዘርፍ የተሰማሩ የንግድ ማኅበረሰብ አካላትና ጤና ባለሙያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የጤና እንክብካቤ አገልግሎትን ተደራሽነት ማረጋገጥ ያለመ ሲሆን፣ በዘርፉም ለተጋረጡ ፈተናዎች የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ገንቢ ውይይት የሚደረግበት ጭምር መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩም በርካታ የጤና ባለሙያዎችና ከመቶ በላይ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው ኩነት በዲጂታል ጤና ላይ የተዘጋጀ ጉባዔ መኖሩን ይኼም ጉባዔ የጤና ዘርፍ ዘመናዊነት በተላበሰ መልኩ የተሳለጠ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩ በተለያየ የጤና ሴክተር የሚሠሩ ባለሙያዎች እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለችግሮቻቸው ተገቢውን የሆነ መፍትሔ የሚያገኙበት መድረክ ነው ያሉት የላይፍ ሳይንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ምስክር ካሳሁን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
አሥራ አንድ የሕክምና ሙያ ማኅበራት የሚሳተፉበት የኢትዮ ኸልዝ ጉባዔ ዋናው ዓላማ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ዕውቀት የሚቀስሙበት፣ እንዲሁም ክህሎታቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ይሆናል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩም ሃያ ነጥብ የሚያሰጥ የሙያ ማጎልበቻ ትምህርትና ሥልጠና በሕክምና አገልግሎት ልህቀት፣ በታላሚ ደኅንነት፣ በራዲዮሎጂ ሕክምና፣ የመጀመርያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ በመድኃኒትና በሌሎቹ ጉዳዮች ላይ ከ11ዱ የሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር የሚሠራ እንደሆነ ምስክር (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡