የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ካስጠለሏቸው ስደተኞች ከ50 በመቶ በላይ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አምና የለቀቀው ‹‹ኤ ሪጅን ኦን ዘ ሙቭ 2021›› ሪፖርት ያሳያል፡፡
አገሮቹ ከሚቀበሏቸው ስደተኞች አብላጫው ሴቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚሁ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ተሰደው በየመን አቋርጠው ወደ ዓረብ አገሮች ከሚሄዱ ዜጎችም አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ድርጅቱ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ወደ ዓረብ አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ስደት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያና ከጂቡቲ በየመን በኩል የሚደረገው አደገኛ ጉዞ ዓምና የ64 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ይህንኑ ምሥራቃዊ የስደተኞች መስመር ተከትለው ከሚወጡት ውስጥ ሴቶችና ሕፃናት ብቻቸውን የሚጓዙበት መሆኑንም የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች የሚያቋርጡት ምሥራቃዊ መንገድ በዓለም ስደተኞች ከሚያቋርጧቸው መንገዶች ሁሉ የሚጨናነቅ፣ በጣም ውስብስብና አደገኛ የሚባለው ነው፡፡
ዓምና ወደ ጂቡቲ የገቡ ስደተኞች ከሃቻምናው በእጥፍ መጨመራቸውን፣ በሕመም፣ በአደገኛ ጉዞ፣ በከባድ የአየር ፀባይ፣ ባህር ውስጥ በመስመጥና በጥቃት 89 ስደተኞች መሞታቸውን ወይም መጥፋታቸውን ገልጾ፣ በርካታ ያልተነገሩ ሟቾች መኖራቸውንም አስፍሯል፡፡
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሚነሱ ስደተኞች ወደ ዓረብ አገሮች ለመግባት ምሥራቃዊውን የቀጣናው ክፍል የሚጠቀሙ በመሆኑ፣ አደገኛ የሆነውን ቀይ ባህር በሶማሊያ በሚገኘው ቦሳሶ እንዲሁም የጂቡቲ የወደብ ከተማዋን ኦቦክ ተጠቅመው ወደየመንና ወደ ሌሎች የዓረብ አገሮች እንደሚገቡም አስታውሷል፡፡
ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ለሚደረግ ስደት በአገሮቹ የሚታየው ተያያዥነት ያለው ቀውስ የደኅንነት ሥጋት፣ ግጭት፣ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታና የኢኮኖሚ ችግሮች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ እነዚህ ችግሮች አሁን ላይ ሴቶችና ሕፃናት ጭምር እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሥራ ፍለጋ በሚል በብዛት ወደ ዓረብ አገሮች አስቸጋሪ ጉዞ አድርገው የሚሰደዱት ወንዶች ቢሆኑም፣ ስደቱ ሴቶችና ሕፃናትንም ስቧል፡፡
እንደ አይኦኤም ከዚህ ቀደም ወንዶች ሚስትና ልጆቻቸውን በቀያቸው አስቀምጠውና በስደት ከሚደርሱበት አገር ሠርተው ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለመላክ ተስፋ ሰንቀው ይጓዙ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ደግሞ ሴቶች አስቸጋሪ የተባለውን በእግር የሚደረግ ሕገወጥ ስደት እየተቀላቀሉ ነው፡፡
ስደተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ለዘራፊዎች ሲሳይ ከመሆናቸውም ባለፈ ለመደፈር፣ ለጥቃት እንዲሁም ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ስደተኞች በየመን ያለውን ጦርነት ጨምሮ በስደት መንገድ ላይ ስለሚኖረው አደጋ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ናቸው፡፡
ችግሩ እየጎላ መሆኑንና አይኦኤም ስደተኞችን ለመደገፍ የሚሠራው ሥራ ላይ ጫና ማሳደሩን የገለጹት ዋና ደይሬክተሩ፣ ወደ ዓረብ አገሮች ለመግባት የየመን መንገድን የሚጠቀሙ ስደተኞችን ለመድረስ የ84 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ዓምና 2,700 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በመንገድ ላይ እያሉ በፍላጎት እንዲመለሱ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከአፍሪካ ቀንደ ብቻ ሳይሆን ከምዕራብ አፍሪካ በሊቢያ አድርገው አውሮፓ ለመግባት የሚነሱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በግጭት ውስጥ በምተገኘው የመን በርካታ ስደተኞች ታስረው እንደሚገኙ፣ ሕጋዊ የማሰሪያ ቦታዎች ቢኖሩም፣ ሕገወጥ የማሰሪያ ማዕከላት መኖራቸውንና በእነዚህ ያሉ ስደተኞች የከፋ ጥቃት እንደሚጸፈምባቸው አክለዋል፡፡
ድርጅቱ በሕጋዊ የማሰሪያ ቦታዎች ያሉ ስደተኞችን በደኅንነት አካላት በመጠበቅ የማየትና ድጋፍ የመስጠት ዕድል በተወሰነ ደረጃ ቢገጥመውም፣ ሕጋዊ ያልሆኑት ጋር መድረስ አለመቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በ2022 የመጀመሪያዎቹ አሥር ወራት 100 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
አይኦኤም አምና ሲገባደድ እንዳስታወቀው፣ ከተመለሱት 100 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ 71ሺሕ ያህሉ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጡ ናቸው፡፡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው ከኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 40,409 ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመልሰዋል፡፡
በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች በየዓመቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ደቡብ አፍሪካና አውሮፓ ይሰደዳሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጂቡቲ በኩል አድርገው ቀይ ባህርን ለማቋረጥ የሚያደርጉት ጥረት ባብዛኛው በሞት የሚቋጭ ሲሆን፣ ከዚህ አምልጠው ወደየመን ያቀኑት ደግሞ ግድያና እሥር ይጠብቃቸዋል፡፡