Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቀበናን ወደ ድሮ ዝና ለመመለስ

ቀበናን ወደ ድሮ ዝና ለመመለስ

ቀን:

ከረዥም ዓመታት በፊት የቀበና ወንዝ በተለያዩ ተረፈ ምርቶችና ፍሳሾች የተበከለ ባለመሆኑ ብዙዎች ተንቦራጭቀውበታል፣ ዋኝተውበታል፡፡ ስለወንዙ ንፅህና ዘፋኞች ያንጎራጎሩበት ገጣሚዎች ስንኛቸውን የደረደሩበትም ነበር፡፡ ድምፃዊ ፀሐይ ዮሐንስ ‹‹ቢሻን ቢሻን ቀበና›› እያለ ያዜመው ሙዚቃም ቀበናን ያስታውሳል፡፡

የቀበና ወንዝ ከቅርብ ዓመታት በፊት ጎልማሳዎች ንፁህ አየር የሚተነፍሱባት ታዳጊዎች የሚዋኙበት፣ ሕፃናት የሚጫወቱበት እንደነበር ከሙዚቃው መረዳት ይቻላል፡፡

‹‹በጋም ሆነ ክረምት በፀሐይ ደመና

ከዚያም ከዚያም መጥተን ዋኝተናል ቀበና…

ፍቅር  አጠራርቶን ከፈረንሣይ ቤላ

ቀበና ታደምን ከአቧሬ እስከ ሾላ

ምንም ብንራራቅ ቢለያይ ደብራችን

ከማዶ እስከ ማዶ አንድ ነው ወንዛችን

ያ ሠናይ ዘመን የልጅነቴ ቢሻን ቀበና ነው መሠረቴ

የማልዘነጋው ቡረቃ ኩሬ የዋኘሁበት ጥንስስ ባህሬ…››

እያለ ያዜመው ፀሐይ ዮሐንስ በትዝታ ቀበናን ያስቃኛል፡፡ የድሮው የቀበና ወንዝ ለእነ ፀሐይ ትዝታ የሆነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፍሳሽ ማስወገጃ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ለዓይን አፀያፊ ሆኗል፡፡ እንደ አብዛኛው የመዲናዪቱ ወንዞች የተበከለና ለዕይታ የማይመጥን ሆኗል፡፡

 እንደ ቀድሞው ለዘፈን የሚበቃ፣ ለትዝታ የሚሰንቅ ዕይታ የለውም፡፡ ቀበናን ወንዝ ጨምሮ ሌሎች ወንዞችም አሁን ላይ ከመኖሪያ ቤቶች በሚወጡ ፍሳሽና ቆሻሻ፣ ከፋብሪካ በሚወጡ ተረፈ ምርቶች ተበክለዋል፡፡ እንደ ቀድሞው ዘመን ወጣቶች ተጠራርተው የሚዋኙባቸው፣ ልብስና ገላ የሚያጥቡባቸው አልሆኑም፡፡ እንዲያውም በሥፍራው ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች የሕመማቸውና የመዘረፋቸው ምክንያት እየሆነ መምጣቱ በነዋሪዎቹ ሲገለጽ ይሰማል፡፡

የቀበናን ወንዝ ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንዞችን ወደነበሩበት ለመመለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የቀበና ወንዝ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡

 የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የቀበና ወንዝ ልማት ፕሮጀክት በጣሊያን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ ተነስቶ እስከ ጀርመን ኤምባሲ ድረስ 2.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የወንዙን አካባቢያዊ ንፅህና ለመጠበቅና የቱሪስት መስህብ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን ያካተተ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)፣ ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ እስከ ጀርመን ኤምባሲ የሚደርሰው የቀበና ወንዝን ለማልማት ከጣሊያን መንግሥት 280 ሚሊዮን ብር (አምስት ሚሊዮን ዩሮ) ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ምዕራፍ ያለው መሆኑንና በ23 ወራት ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለበት ሁኔታ በአካባቢው ነዋሪዎች በቀጥታ በሚለቀቅ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ የተበከለ መሆኑን፣ በአካባቢው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር በወንዙ ዳርቻ የሠፈሩ ዜጎችን ለከፍተኛ የጤና ችግር ማጋለጡ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የንፅህና አጠባበቅ ዘርፍና አካባቢውን በማስዋብ ሥራዎችን አካቶ ሁለት ምዕራፎች የያዘ መሆኑንም አክለዋል፡፡  

በንፅህና አጠባበቅ ዘርፍ የግልና የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ማደስና መገንባት፣ የሰውነትና የእጅ መታጠቢያ፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቋቶች እንዲሁም የቆሻሻ ውኃ ማጣሪያ ሥርዓት የተካተቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ማስዋብ ዘርፍ ደግሞ ወሳኝ በሆኑ አካባቢዎች ድልድይ መገንባት፣ ልዩ ልዩ ጠቋሚ ምልክቶች መትከል፣ የማስዋብ፣ የሥነ ምኅዳራዊ ምህንድስና ሥራዎችን መሥራትና አረንጓዴ መስህብ መሥራት ይገኙበታል፡፡

እንደ ጀማሉ (ዶ/ር)፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዕፎይታ ከመስጠት ባሻገር፣ ለገቢ ማስገኛ ምንጭ ይሆናል፡፡

የቀበና ወንዝ ልማት ፕሮጀክትን አሰር ኮንስትራክሽንና ከሜሶሳስ ኮንትራክተሮች እንደሚሠሩት፣ አትኮን የተሰኘ ድርጅት ደግሞ በማማከር የሚሳተፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡  

የፕሮጀክቱ ሥፍራ ብዙ ነዋሪዎች እንደሌሉበት የጠቆሙት ጀማሉ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ታችኛው የፕሮጀክቱ ክፍል የተወሰኑ ነዋሪዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ነዋሪዎች በወንዙ ዳርቻ በመክተማቸው ለጎርፍ ተጋላጭ እንደነበሩ በማስታወስ፣ የኑሮ ሁኔታቸውን በማይጎዳ መንገድ አማራጮች እንደሚፈለግላቸው፣ በፕሮጀክቱ ምክንያት ምን ያህል ተነሺዎች እንዳሉ የሚታወቀውም ዲዛይኑ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀበና ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነችና በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌስ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም.  የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...