Thursday, April 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፋሺስት ለተፈጸመባት ጭፍጨፋ የጣሊያን መንግሥት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሳ ሊከፍል ይገባዋል!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

መንደርደሪያ

የዛሬው ዕለት የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ በታሪክ የፋሺስቶች ዘረኝነት፣ አውሬያዊ ጭካኔና አረመኔነት በገሃድ የታየበት ነው፡፡ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ አድርጎ ለአምስት ዓመታት በተቆጣጠረበት ወቅት በ1929 ዓ.ም. የካቲት 12 ዕለተ ዓርብ ነበር።

የአፄ ኃይለ ሥላሴን ወደ እንግሊዝ መሰደድ ተከትሎና የሙሶሊኒን የቅኝ ግዛት ህልም እንዲያሳካ የኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው ግራዚያኒ፣ የኔፕልሱን ልዑል መወለድ አስመልክቶ ለችግረኛ ቤተሰቦች ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ) በርካታ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከተጋባዥ እንግዶቹም መካከል የጣሊያን ሹማምንት የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ቄርሎስና ሌሎች የኢትዮጵያ መኳንንት ተገኝተው ነበር።

ብራማ በነበረችው በዚያች የወርሃ የካቲት ዓርብ የተገኙትም ኢትዮጵያውያን ከጠዋት ጀምረው አንድ በአንድ ቤተ መንግሥቱ ግቢ መሰብሰብ ጀመሩ። እስከ ረፋዱም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሦስት ሺሕ ያህል ነዋሪዎች በተገኙበት የግራዚያኒ መርሐ ግብር ተጀመረ። የዕለቱ አጀማመር ሲታይ ሊመጣ ያለውን የሐዘን ድባብ የገመተ ሰው ይኖራል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል። ጥቂት ቆይቶ እኩለ ቀን ገደማ ሊሆን አካባቢ በዋናው በር በኩል ቦንብ ፈነዳ፣ ሁለተኛም ፈነዳ። ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ከየአቅጣጫው ጩኸት አስተጋባ። ሦስተኛ ቦምብም ግራዚያኒና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ሲወረወር ግራዚያኒ ጠረጴዛ ሥር ወደቀ። የተወሰኑ የጣሊያኖቹን ሹማምንት መታ።

ቦምቡን የጣለው ከጣልያኖቹ ዘንድ በአስተርጓሚነት ይሠራ የነበረ አብርሃ ደቦጭና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የሚባሉ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ወጣቶች ነበሩ። በጥቅሉ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ወዲያው ካርቴሲ ወደ ኢትዮጵያውያኑ መኳንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመርያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ። ካራቢኔሬዎችም (የጣሊያን የሲቪል ጠባቂዎች) ምሳሌውን ተከተሉ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሦስት መቶ ሬሳዎች በዚያ ግቢ ውስጥ ተከመሩ። ኃይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር። ሽማግሌዎች፣ ዓይነ ሥውራን፣ እግር የሌላቸው ለማኞች፣ ድሆች እናቶች እስከ ልጆቻቸው ነበሩበት። ሠላሳ ያህል ሰዎች ቆሰሉ። ለሦስት ሰዓታት ያህል ያላቋረጠ በግቢው ውስጥ ተኩስ ተከፈተ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለጥቁር ሸሚዞች፣ የጣሊያን ሾፌሮች የቅኝ ግዛቱ ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን ይፈጁት ጀመር።

በወቅቱ ፋሺስት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን እጅግ አረመኔያዊ የሆነ ጭካኔና ዕልቂት በተመለከተ በወቅቱ አዲስ አበባ የነበረ አንድ አውሮፓዊ ሐኪም እንዲህ ነበር የገለጸው፣

‹‹… ምን ዓይነት አጨካከን ነው፣ ደም በመንገድ ላይ እንደ ውኃ ሲፈስ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶችና የልጆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያው ከባድ የቃጠሎ ጭስ አዲስ አበባን ፅልመት አለበሳት፡፡ የነዋሪዎች ቤት ከተፈሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጥ እንዳሉ እሳት ተለቀቀባቸው፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዚንና ዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ እሩምታ ይገድሉታል፡፡

በዓለም ጦርነት ጊዜ ቁስለኛ ለማንሳት ከግንባር ከቀደመው ጦር ጋር አምቡላንስ ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ በሌላም ጦርነቶች ውስጥ ተካፋይ ሆኛለሁ፡፡ በሕይወቴ እንደ አዲስ አበባ ያለ ዕልቂት ግን አላየሁም፤››

የፋሺስቱ ተወካይ ግራዚያኒ በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ላይ ስለወሰደው ዕርምጃ አስመልክቶ በሮማ ላለው ቅኝ ግዛት ሚኒስቴር በቁጥር 14-1154 ባስተላለፈው የቴሌግራም መልዕክት እንዲህ ነበር ያለው፡፡

‹‹እነኚህ ጥቁሮች [ኢትዮጵያውያን] የእኛን ወታደር ሲያዩ ‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉትንም ለመቀጣጫ እንዲሆኑ ሁሉንም አስጨርስኳቸው፤›› ብሏል፡፡ በዚያው ዘመን እ.ኤ.አ. በየካቲት 22 ቀን የወጣው የሮም ጋዜጣ ‹‹ዴል ፖፖሎ››፣ ‹‹የአዲስ አበባ አጋማሽ በአሰሳው ፀድቷል፣ 2,000 ኢትዮጵያውያን ተይዘው ወደ ደናኔና ወደ ሌሎች ማሰሪያ ቦታዎች ተልከዋል፤›› ሲል ዘግቦ ነበር፡፡

በተመሳሳይም ጋዜጠኛው ቺሮ ፖጃሊ ፋሺስቶች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ስላደረጉት ግፍና ጭካኔ የካቲት 13 ቀን በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሆነው ጭካኔ መሠረት አድርጎ እንዲህ ዘግቦት ነበር፡፡ ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች መደበቃቸው ስለተሰማ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ቤንዚን ተርከፍክፎ እሳት ተለቀቀበት፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅድሳት መጻሕፍትና ሥዕሎች በእሳት ነደዱ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከእሳቱ ለመሸሽ 50 ያህል ሰዎች ሲወጡ ተያዙና ከቤተ ክርስቲያኑ ጓሮ ተወስደው በቦምብ እንዲገደሉ ተደረገ፡፡››

ለአርባ ዓመታት የተደገሰ የፋሺስቶች ቂም በቀል

ፋሺስት በዓለም ሁሉ ፊት ሮማ የደረሰባትን ታላቅ እፍረትና ሽንፈት ለመበቀል እስከ አፍንጫው የታጠቀ ዘመናዊ ጦሯን በቫቲካን ጳጳሳት አስባርካ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው፡፡ የሞሶሊኒ ወደ ኢትዮጵያ የላከው ኃይል በጦር መሣሪያ ብዛትም ሆነ ዘመናዊነት በቂ ወታደራዊ ሥልጠና ከሌለው ከአገራችን የጦር ሠራዊት ጋር ፈጽሞ የማይወዳደር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ የጣሊያን ጦር ሠራዊት እስከ አፍንጫው ከታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰማይ እየሰነጠቁ ሞትን የሚተፉ የመርዝ ጭስ አረሮችን የተሸከሙ የጦር አውሮፕላኖችን ጭምር የታጠቀ ነበር፡፡

ይህን በአሰቃቂ ሁኔታ ሰውነትን በጣጥሶ የሚገድለውን የመርዝ ጭስ ፋሺስት ጣሊያን ለመጠቀም የፈለገው የኢትዮጵያውያንን የውጊያ፣ የመከላከል ሞራልና ቅስም በመስበር ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ሆን ብሎ አስቦና አልሞ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በወቅቱ ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ መጠቀም ስለሚገባው የመሣሪያ ዓይነት በምስጢር አስተላልፎት የነበረውን መልዕክት የአሜሪካው ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚገኝ ወታደራዊ ምስጢራዊ ሰነድ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

‹‹ተልዕኳችን እንዲሳካ ከተፈለገ በጠላት ላይ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ከዚህም በላይ የሞራል ስብራት የሚያስከትለውን ልዩ የሆነ ፈሳሽ ቦምብና መርዝ ሼል እንደፈለጉ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡››

ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. ለዳግመኛ ወረራው በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶና የዓድዋውን ሽንፈት በሚገባ ለመበቀል የመርዝ ጋዝ ጭስ ሳይቀር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡን በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል በአንድነቱ እንዳይቆምና እንዲሁም ስለ አንድነቱና ነፃነቱ የሚያስተምሩና በፅናት እንዲቆሙ የሚመክሩ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት ለማዳከምና ለማፍረስ ከተቻለም በሮም ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግም ከፍተኛ የሆነ ዘመቻን ከፍቶ ነበር፡፡

ፋሺስት በዚህ ዘመቻው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዋንኛ ዒላማው አድርጓት ነበር፡፡ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም እንዲሁም ደግሞ የበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የሆኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና ምዕመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የጣሊያን ፋሺስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው የከፋና እኩይ አቋሙ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ፋሺስቱ ቤኒቶ ሞሶሊኒ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ንቀትና ጥላቻ ያሳየበትና ቢቻለውም ቤተ ክርስቲያኒቱን በፋሺስት ወይም በሮማ አስተዳደር ሥር እንድትሆን የነበረውን ህልም የሚያጋልጠው እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 16 ቀን 1935 በአስመራ ለሚገኘው ለጦር አዝማቹ ለማርሻል ባዶሊዮ ያስተላለፈው ጥብቅ ምስጢራዊ ቴሌግራም እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹በቁጥር 421M እና በቁጥር 426 ዳግም ያስተላለፍክልኝን የምስጢር ቴሌግራም ደርሶኝ በሚገባ አይቼዋለሁ፡፡ የአክሱም ገዳም የተቀደሰ ሥፍራ እንደመሆኑና ካለውም ጥንታዊ ታሪክና ቅርስ አኳያ በጦር መሣሪያም ሆነ በማናቸውም ዓይነት ወረራ እንዳይነካና ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ መቆየት አለበት የሚለውን የውጭ መንግሥታት ሐሳብ ከምንም አልቆጥረውም፣ ማለትህና ወደፊትም ይህን ሐሳብ የምቀበል ሰው አይደለሁኝም ማለትህ ትክክለኛ ነህ፡፡ ጥሩም አድርገሃል፡፡ አሁን የቀረህ ደግሞ የአክሱምን ገዳም ካህናትና መነኮሳት ብዛታቸውንና ማዕረጋቸውን ጠይቀህ ካወቅህ በኋላ በገናናዋ በሮምና በሞሶሎኒ ዙፋን ሥር እንተዳደራለን የሚሉ እንደሆነም በውል አጽፈህና እያንዳንዳቸውን አስፈርመህ ቃል የገቡበትን ሰነድ ወደ እኔ እንድትልክልኝ ነው፡፡››

ፋሺስት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ግፍና መከራ እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ነገር የቫቲካን ሃይማኖት አባቶች ለሞሶሎኒ የግፍ ወረራ ድጋፍ ማድረጋቸውና ጦሩንም ባርከው መላካቸው በታሪክ የተመዘገበ የቫቲካን ካቶሊካውያን የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ እፍረትና ቅሌት የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ የእነኚህን የቫቲካን የሃይማኖት መንፈሳዊ መሪዎችንና አባቶችን ቅሌት በወቅቱ የታዘበ ኤሊክ ሲንድሩም የተባለ ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ለሮማው ፖፕ በጻፈው ደብዳቤው እንዲህ ሲል ነበር ሐዘኔታውን የገለጸው፡-

…ቅዱስ ሆይ እኔ በሰሜን አገር የተወለድሁ አንድ ፕሮቴስታንት ስዊድናዊ ነኝ፡፡ … እርስዎ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ነዎት፡፡ ካቶሊክ ማለት ደግሞ የሁሉም ማለት ናት፡፡ ዛሬ እንግዲህ የእርስዎ ቤተ ክርስቲያን በእውነት የሁሉም ናትን? እርስዎ ከሞሶሎኒ ጋር ሆነው ከሌላው ዓለም ጋር በጠብ አሉ፡፡ እርስዎ የሚመሯቸው ጳጳሳት ኢትዮጵያ ለጣሊያን ቅኝ አገር እንድትሆን የሚገባ ነው ብለው ተናገሩ፡፡ ዘመቻውንም የተቀደሰ ዘመቻ ነው በማለት ለዘመቻ የተዘጋጁትን ታንክና የጦር መሣሪያዎች ባረኩ …፡፡

እርስዎ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሰዎች አገራቸውን ለመጠበቅ ቢሰበሰቡ የጣሊያን የአውሮፕላን ቦምብ ጥርግ አድርጎ ቢያጠፋቸው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ነው ብለው ያስባሉን!? ሴቶችንና ሕፃናትን በመርዝ ጭስ ሲፈጅ እግዚአብሔርን ያገለግላሉ ብለው ያስባሉን!? እርስዎ የዓለም ሁሉ አባት ነኝ ሲሉ ሳለ የሞሶሎኒ ባሪያ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ጸሎት ልታሳርግ አትችልም፡፡ ሌላው ዓለም እንደዚሁ ወደ እርስዎ አምላክ ሊጸልይ አይችልም፡፡

እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰውዬው ለሞሶሊኒ የሚታዘዙ ሆነዋልና፡፡ እርስዎ መናገር በተገባዎ ጊዜ ዝም አሉ፡፡ አሁንም በቅርብ የገና በዓል ነው፡፡ ለግፍ ጦርነት ወርቃቸውን የሰጡ ጳጳሳትም እንግዲህ ‹‹ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በምድር ላይ ሰላም ይሁን፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ ይሁን!›› ብለው ሊዘምሩ ነው፡፡ ይኽንንም መዝሙር ሲያዜሙ በደረታቸው ላይ የወርቅ መስቀል ሳያደርጉ አይቀርም፣ ነገር ግን በጀርባቸው ላይ የእንጨት መስቀል ቢሸከሙ በተሻላቸው ነበር…፡፡

የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የጣሊያን ፋሺስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት የፋሺስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምሥራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛት ሚኒስትርሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልዕክት ‹Ethiopia and Eritrea› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፡-

…The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favorable attitude. A telegram of March 1, 1937.

ትርጉም፡- ‹‹በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ ለጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሳሱና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል…፤›››

በወቅቱ በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የግድያ ዕርምጃ ጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ ‹Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience› በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹‹…የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገብረ ማርያም ወልደ ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ…፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ፋሺስት የደብረ ሊባኖሱ ግድያና ጭፍጨፋ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት ግንቦት 12 ቀን ነበር እንዲሆን ያዘዘው፡፡ ከበዓሉ ዋዜማ፣ በበዓሉና ከበዓሉ በኋላም በገዳሙ የተገኙ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ከገዳሙ አቅራቢያና ከሩቅ አካባቢ በዓሉን ለማክበር የመጡ አገልጋዮችና ምዕመናን ሳይቀሩ የዚህ ጭፍጨፋ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ፕሮፌሰር ኢያን ካምፔል ፋሺስት በደብረ ሊባኖስ ያደረሰውን ጭፍጨፋ በገለጹበት ‹‹The Massacre at Debre Libanos Ethiopia 1937:- The Story of One of Fascism’s Most Shocking Atrocities››በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹‹በግንቦት 14 ቀን የፊንጫ ወንዝ ወደ ደም ጅረትነት ተቀይሮ እንደነበርና የፋሺስት ወታደሮችም በግፍ የገደሏቸውን ሰዎች በላያቸው ላይ አፈር ብቻ በመበተን ለአውሬና ለጅብ ራት እንዲሆኑ በየሜዳውና በየዱሩ ጥለዋቸው እንደነበር፤›› ጽፈዋል፡፡   

በወቅቱም የጣሊያን የጦር አዛዦች ከግድያውና ከጭፈጨፋው ባሻገርም የገዳሙን ቁልፍ ተረክበው በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ የከበሩ ንዋያተ ቅድሳትን፣ የብራና መጻሕፍትን፣ በተለይም ደግሞ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ገላውዴዎስ ለገዳሙ በስጦታ የተበረከተውን በወርቅ የተለበጠና በአራት ሰው ትክሻ የሚነሳውን ትልቅ የብራና ወንጌል ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ሰርቀው እንደወሰዱት የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም በገዳሙ ያገኙት ብዙ ሀብትና ቅርስ ያስገረማቸውና ዝርፊያው የጣማቸው የጣሊያን ወታደሮች የተደበቀ ወርቅና ብር እናገኛለን በሚል ተስፋ ፈጽሞ ሰብዓዊነት በጎደለው ሁናቴ የገዳሙን መካነ መቃብሮች እንኳን ሳይቀር ቆፍረውትና ንደውት ነበር፡፡

በደብረ ሊባኖስ ገዳም በግፍ ስላለቁት፣ ወደ ሶማሊያ ተግዘው በዳናኔ ወህኒ ቤት ስለሞቱት የገዳሙ ተማሪዎችና በገዳሙ ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ዕልቂትና ዝርፊያ በ2003 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ያወጣው ‹‹ዜና አብዮሙ ለሰማዕታት ዘደብረ ሊባኖስ ደቂቁ ለተክለ ሃይማኖት›› በሚል ርዕስ የታተመው መጽሔት በፋሺስት ጣሊያን በገዳሙ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለት ሺሕ ገደማ ያደርሰዋል፡፡ በእርግጥ በፋሺስት ወረራው ወቅት ከደብረ ሊባኖስና ከሌሎች የአገሪቱ ገዳማትና ቅዱሳን መካናት በግፍ የተገደሉ፣ የተጨፈጨፉ፣ የተጋዙ በርካታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ገዳማትና ቅዱሳት መካናት የተዘረፉ ቅርሶችና ንዋያተ ቅድሳትም እጅግ የበዙ ናቸው፡፡

መደምደሚያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ልዓላዊነትና በሕዝቦቿ ነፃነት ላይ ያላትን የማያወላውል ፅኑ አቋም በሚገባ የሚያውቁ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች፣ ወራሪዎችና ተስፋፊዎችም በተለያዩ ዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስና ቢቻላቸውም በራሳቸው ግዛትና ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልወጡት ተራራ የለም ማለት ይቀላል፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ ይህ ሙከራቸው ደግሞ መልኩንና ይዘቱን ቀይሮ እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ነው ማለትም ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በውጭ አገሮች ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎች ዘንድ ጥርሳቸው እንዲነከስባትና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ያጋጠማቸውን ወረራ፣ የቅኝ ግዛት መስፋፋት በማውገዝና በመቋቋም ረገድ ያደረገችውን ተጋድሎና የከፈለችውን ክቡር መስዋዕትነት የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሰው ልጆች ሁሉ ከፈጣሪ በተሰጠ ነፃነት፣ በእውነትና በፍትሕ ላይ ያላት ፅኑ የሆነ አቋም ስለ ነፃነታቸው፣ ስለ ፍትሕና ስለ ሰው ልጆች እኩልነት በሚታገሉና በሚጋደሉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተሰማ፣ ትልቅ ክብርና ዝና ያለው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአገራችን በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነፃነታቸውን በሚያፈቅሩና በሚያከብሩ የሰው ልጆች መካከል ያላት አኩሪ ታሪክ፣ ገድልና መልካም የሆነ ምስክርነት በኋላ ዘመን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ለመጡ አውሮፓውያን እንደ እግር እሳት ነበር ያንገበገባቸው፡፡ እናም ይህን ለጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን መመኪያ የሆነ ታሪክ በማጠልሸት፣ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ቅርስና ታሪካቸውን ከመሠረቱ ለመናድ፣ በሃይማኖቱ ፅኑ የሆነውንና ለነፃነቱ ቀናዒ የሆነውን ሕዝብ ለመበቀል ሲል ፋሺስት የበቀል በትሩን ዘግናኝና አረመኔዊ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ አንስቷል፡፡

ስለሆነም የፋሺስት መንግሥት ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነት፣ ለፍትሕ፣ ለፍቅርና ለሰላም በቆመችው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለፈጸመው ግፍ፣ ጭፈጨፋና ኢሰብዓዊ ድርጊት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሳ ሊከፍል ይገባዋል፡፡ ይህን ጥያቄም ቅዱስ ሲኖዶስና የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በአንድነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሊያሰሙ ይገባል፡፡

ለአብነትም ‹የኒውዮርክ ታይምስ› ከሁለት ዓመት በፊት የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ዓመት በፊት ቱርካውያን በአርመን ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ላደረሱት ጭፍጨፋ፣ ግፍና መከራ የአርመን ቤተክርስቲያን መሪና መንፈሳዊ አባት የሆኑት አቡነ አራህም አንደኛ፣ የቱርክ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል የጠየቁበትንና ያሳሰቡበትን ሰበር ዜና አስነብቦን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በተመሳሳይ ‹የይቅርታና የካሳ› ጥያቄዋን ለጣሊያን መንግሥትና ሕዝብ ማቅረብ ይኖርባታል፡፡

በማጠቃለያዬም ባለፈው ጽሑፌ እንደገለጽኩት እህት ቤተ ክርስቲያን የሆነችው የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ዓመት በፊት በቱርካውያን ለደረሰባቸው ግፍና ጭፍጨፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸውና ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ በሆኑት በአቡነ አራህም በኩል የተነሳው ጥያቄ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡

እንደ አርመናውያኑ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክና ቅርስ የሚቆረቆሩና በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ የሚገኙ ማኅበራትና ተቋማት፣ እንዲሁም ሁሉም ምዕመናን ፋሺስት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ላደረሰው ግፍና ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም ይህን ግፍ በዝምታ ያለፈችው ቫቲካንም ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢው የሆነው ካሳ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሰጣት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሊያሰሙ ይገባቸዋል፡፡

ለአብነትም የጣሊያን መንግሥት በቅኝ ግዛት ዘመን በሊቢያ ስላደረሰው ጭፍጨፋና ግፍ የአምስት ቢሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ እንዳደረገ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ሮም በኢትዮጵያውያን ላይ ላደረሰችው ጭፍጨፋ፣ ዕልቂትና ግፍ ጣልያን ገነባችው የሚባለው የቆቃ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ የጉዳቱ መጠንና ካሳ በዓለም ፍርድ ቤት ባልተዳኘ፣ ከጣሊያን መንግሥትም ሆነ ከቫቲካን ይፋዊ የሆነ ይቅርታ ባላገኘችበትና ግን ለጊዜው ወዳጅነትን ለማደስ በሚል የተሠራ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡

በበኩሌ በመጨረሻ ለመግለጽ የምወደው ነገር ቢኖር ምንም እንኳን በፋሺስት ጣሊያን፣ መንፈሳዊ መሪዎቿና በርካታ አገልጋዮቿ በግፍ የተገደሉባትና የተጨፈጨፉባት፣ በዋጋ የማይተመኑ ቅርሶቿና ታሪኳ የወደመባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፋሺስቱ ጭካኔ ሰይፍ ዋና ተጠቂና ሰለባ ብትሆንም ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆን አለበት ብዬ አላምንም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብም በአንድነት በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊያሰማ ይገባል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ አንድነት፣ በትናንትና በሕዝቦቿ የነፃነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ታሪካዊ ቅርሶቻችን የምንኮራ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳንለይ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ፣ ቁጭትና አቤቱታ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles