Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዛሬዋ መራራ ቀን

የዛሬዋ መራራ ቀን

ቀን:

ወርኃ የካቲት ከአሥራ ሦስቱ ወራት የተለየ የሚያደርገው፣ ከቅርቡ ከግማሽ ምታመቱ ብንነሳ እንኳ ዘውዳዊው ሥርዓትን አነቃንቆ ለክስመት ያበቃው ‹‹የሕዝብ ንቅናቄ››፣ በኋላ ላይ ‹‹አብዮት›› የተሰኘው የተወለደበት መሆኑ ነው፡፡ ዘንድሮ ላይ የየካቲቱ አብዮት፣ እንበል አመፅ ከባተ 49ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡

በሌላ በኩል የባዕድ ወራሪን ስናስብ በተለይ የጣሊያን ኮሎኒያሊስት ኃይልን ዓድዋ ላይ በ1888 ዓ.ም. ድል የተመታው በየካቲት ወር ነው፡፡ የ40 ዓመት የሽንፈት ቂሙን ለመወጣት በ1928 ዓ.ም. በፋሺስት ፓርቲው አማካይነት ወረራ ፈጽሞና ፋሺስት ጣሊያን ተሰኝቶ ለአምስት ዓመት በወረራ በቆየበት ወቅት ከፈጸማቸው ዘግናኝ ግድያዎችና ውድመቶች መካከል አንዱ በወርኃ የካቲት 12ኛ ቀን፣ 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የፈጸመው ነው፡፡

የዛሬዋ መራራ ቀን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ለሰማዕታቱ ክብር የቆመው ሐውልት

በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውና 30 ሺሕ ሕዝብ ያለቀበት 86ኛ ዓመት ዛሬ እሑድ የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ በሚገኘው የየካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልትና አደባባይ እየታሰበ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሰማዕታቱ አፅሞች ተለቅመው በክብር ባረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም በጸሎተ ፍትሐት የታሰበው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) አማካይነት በ1934 ዓ.ም. በካቴድራሉ አፀድ ውስጥ በተተከለው መካነ ሰማዕታት ላይ ነው፡፡

ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ የፍዳውን ዘመን የሚያስታውስ ነው፡፡

 ‹‹ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓ.ም …››::

ይህ የአፅሞች ማረፊያ በጣሊያን ፋሺስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው፣ በሚል የሚንደረደረው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣ በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከእንግሊዝ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ሥፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው፡፡

በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በቆመው ሐውልት ግርጌ የሠፈረ ግጥም የሚከተለው ነው፡፡

ራስን ከአንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ
ሰውን ከእነቤቱ አብሮ እያቃጠለ
ማነው እንደ ፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ?
ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡
ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ
አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን
ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡
እላንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ
በኃይለ ሥላሴ ትንሣዔ አገኛችሁ፡፡

የሰማዕታቱ ዜና ስንክሳር

የዓይን እማኙ ‹‹ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12›› የተሰኘ ጽሑፍ የጻፉት ተመስገን ገብሬም እንዲህ ጽፈዋል፣ ‹‹ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሺስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው፡፡ ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው ‹እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል፡፡ ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፣ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል!› የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ፡፡ ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡ ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ፡፡ ካምዮኑም እየፈጠነ ጎተታቸው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው፡፡ እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል፡፡ ከዚያም መሀል ጨመሩን፡፡

‹‹ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል፡፡ በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገድለዋቸዋል፡፡ አስከሬናቸው ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ፡፡ እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ፡፡ ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች የአንዳችንን እጅ ከአንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን፡፡ አስረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ፡፡ የእሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ፡፡ ፋሽስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፣ ሕፃናቶችን ከአባትና ከእናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል፡፡ እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምራቄ ደረቀ፡፡ በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን፡፡ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር፡፡››

ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት፣ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በወቅቱ የነበረውን የፋሺስት ጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡-

‹‹…ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ፡፡ … በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም፡፡ ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ሥውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር፡፡››

‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው ባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሺስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከእነ ነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በአገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...