ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹‹የፈረስ ገበያ›› ማለት ነው፡፡ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ያሉ የአውቶቡስ መናኸሪያዎች በወል በዚህ ስም ይጠራሉ፡፡ ታዲያ እኔ የለመድኩት አጠራር ‹‹ፈረስ መጋላ›› እንጂ ‹‹ፈረዝ መጋላ›› ስላልነበር ‹‹አንድ የአማርኛና አንድ የኦሮሚኛ ቃል እንዴት ቢቀናጁ ነው ‹ፈረስ መጋላን› ሊያሰኙ የቻሉት?›› በማለት ለረዥም ጊዜ ስገረም ቆይቻለሁ፡፡ የሐረሩን ‹‹ፈረዝ መጋላ›› ካየሁ በኋላ ግን አግራሞቴ መልኩን ይዟል፡፡
ፈረዝ መጋላ እንደ ስሙ ‹‹የፈረስ ገበያ›› ነበር፡፡ በተለይም ከደጋማው የጋረ ሙልአታ አውራጃ (ከሐረር ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ተራራማ አውራጃ) የሚመጡ ገበያተኞች የደራ የፈረስ ግብይት ያካሂዱበት እንደነበር የሐረሪ ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ ያ ዘመን አልፎ ተሽከርካሪ ወደ ሐረር ሲገባ ደግሞ ፈረዝ መጋላ የአውቶቡሶች የተሳፋሪ ማውረጃና መጫኛ ቦታ ሆኖ ሲያገለግል ኖረ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የከተማ ታክሲዎችና የባለ ሦስት እግሮቹ ‹‹ባጃጆች›› የሥምሪት መነሻና መድረሻ ሆኗል፡፡
በ‹‹ፈረዝ መጋላ›› ዙሪያ ‹‹አሚር አብዱልላሂ መገስ ጋር›› (የአሚር አብዱላሂ ቤተ መንግሥትና የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በርካታ ሕንፃዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነርሱ ውስጥ እኔን ያስገረመኝ ግን በጽሑፍ ምንጮች ብዙም ያልተወራለት ‹‹ካፍቴሪያ አሊባል›› ነው፡፡ ዕድለኛ ሆናችሁ ወደ ‹‹ካፍቴሪያ አሊባል›› ከገባችሁ ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ካፍቴሪያ›› ውስጥ መሆናችሁን እወቁት፡፡
– አፈንዲ ሙተቂ ‹‹ሐረር ጌይ›› (2004)
* * *