Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከዚህ በኋላ በየሠፈሩ ተደራጅቶ ለመኖር ሀብቱና አቅሙ ያለን አይመስለኝም›› ታከለ ታደለ (ፕሮፌሰር)፣ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል፣ አስተምረዋል፡፡ አሁን ደግሞ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ሲሆን የወላይታ ልማት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢም ናቸው፡፡ ታከለ ታደለ (ፕሮፌሰር) የአርሶ አደር ልጅ ነኝ ይላሉ፡፡ የሚመሩት ዩኒቨርሲቲ በግብርና መስክ ውጤታማ የሆነ የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን፣ በቅጥር ጊቢው የገነባቸውን የአቮካዶ እርሻ፣ የከብት ዕርባታና የደን ልማት ሥራዎች ያስጎበኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲያቸው በግብርና ሳይወሰን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሒዩማኒቲ ዘርፍ ተግባር ተኮር ዕውቀት ለተማሪዎቹ ለማስጨበጥ የሚሠራ ተቋም መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ ወቅታዊውን የደቡብ ሕዝቦች ክልል ምሥረታ ሕዝበ ውሳኔ፣ እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ማሽቆልቆልን በተመለከተ ዮናስ አማረ ከታከለ ታደለ (ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል በቅርቡ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ እንደ አንድ የትምህርት ባለድርሻ እርስዎ ይህንን እንዴት ታዘቡት?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- ድምር ውጤት ነው፡፡ ሰዎች ውጤት ካመጡት 3.3 በመቶ ተማሪዎች በስተቀር ሌሎች ተፈታኞች ወድቀዋል ብለው ተማሪዎቹ ላይ ብቻ ሊያተኩሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እንደ አገር ሲስተሙ ነው የወደቀው፡፡ በዚህ የፈተና ውጤት ማሽቆልቆል ተፈታኞች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ወድቀናል፡፡ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ መንግሥትም ሆነ ሁላችንም ወድቀናል፡፡  ምን ያህል ነው ስለትምህርት ጥራት ትኩረት የተሰጠው? አሁን አሁን እኮ ነው ከኬጂ ጀምሮ እስከ ላይ ይተኮርበት ተብሎ ንቅናቄ የተጀመረው፡፡ ሌብነቱና ኩረጃው እኛንም መከራችንን እያበላን ነው የኖረው፡፡ ላቦራቶሪ፣ ወርክሾፖች፣ ላይብረሪዎችና ሁሉም የትምህርት መሠረተ ልማቶች መውደቃችንን ያሳያሉ፡፡ ለዚህ ውድቀት የሁላችንም እጅ አለበት፡፡ ሚዲያም ጭምር፡፡ አንገታችንን ቀና አድርገን መሄድ የምንችለው ከታች ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ተቀናጅተን ስንሠራ ነው፡፡ አደረጃጀቱ፣ አመራሩ፣ አሠራሩ፣ ግብዓቱ፣ ምዘናውና የክትትል ሥርዓቱ በሙሉ በደንብ መገምገም አለበት፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ፖለሲ በትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ ገምግመናል፡፡ በጣም ምርጥ ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ ከወጣ ደንቦች ይወጣሉ፣ መዋቅር እስከ ታች ተዘርግቶ ይህ ሲታሽና ሲበስል የቆየ ፖሊሲ ይተገበራል፡፡ ዴሞክራሲ ቢባል የአገር ግንባታ ያለ ትምህርት ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡ ማይም በሞላበት አገር ዴሞክራሲን ማለም አይቻልም፡፡ ወንድምና እህት ሆኖ በሰመረ መንገድ መኖር የሚችል ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ያለ ትምህርት አይቻልም፡፡ ልማትም ቢሆን በቅዠትና ምኞት ሳይሆን በዕውቀት ነው የሚመራው፡፡ ፖለቲካውም ሆነ ማኅበረሰብን ማንቃትና መምራት የሚቻለው በዕውቀት ነው፡፡ መሪዎች የቱንም ያህል ቁርጠኝነት ቢኖራቸው ያለ ትምህርት ፈቀቅ አይልም፡፡

ውጤቱ የሚጠበቅና የሚያሳዝን ነው፡፡ ሆኖም ዩኒቨርሲቲ ውስጥም አለ፡፡ አሁን ሊሰጥ በታቀደው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ወቅት የእኛ የዩኒቨርሲቲዎች ጉድም የሚታይበት ቀን ቀርቧል፡፡ በእኛ ጊዜ ቦዲቲ በሚባል ትምህርት ቤት ሦስት ሰዎች ነበርን ያለፍነው፡፡ አሁን እኮ ሁሉም ሰው ዩኒቨርሲቲ እየገባ ነው፡፡ ላይብረሪውን ስታይ ባዶ ሆኖ ግቢው ውስጥ የሚንዘላዘል ብዙ ተማሪ ታያለህ፡፡ አንዳንዴ ያልታጠቀ ወታደር ነው የምናስመርቀው እላለሁ፡፡ ወታደር እኮ በዲሲፕሊን የተገራና ብረት ታጥቆ በረሃ ለበረሃ ተንከራቶ አገር የሚጠብቅ ነው፡፡ ይህኛው ግን ብረት ባይታጠቅም ዝም ብሎ እየተመረቀ ከወጣ በመጨረሻ አገር ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ መቆም ነበረበት፡፡ አሁን የተደረገው ነገርም የዚህ ውጤት ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤት ማሽቆልቆልን አሁን ዓይተናል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ነገ ወደ ዩኒቨርሲቲዎችም ይመጣል፡፡ የዚያን ጊዜ ደግሞ በትክክል ተማሪን እያስተማርን ባለመሆናችን የሁላችንም ገመና ግልጥ ይላል፡፡ በትክክል ተማሪ እያስተማርን አይደለም የሚለው ጉዳይ ለእኛ ቀድሞ ነው የተነገረን፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት አካሄዳችንን ያዝ አድርገነዋል፡፡ ጥራትን እያሻሻልን ነው፡፡  

አሜሪካ ኃያል የሆነችው በመሣሪያ ሳይሆን በትምህርት ነው፡፡ የእስያ ነብሮች የሚባሉት አገሮች ያደጉት በትምህርት ነው፡፡ ከትምህርት ውጪ ሌላ መንገድ የለም፡፡ አሁን የተጀመረው ሥራ በእኛ ዘመን ባይደርስም ለቀጣዩ ጊዜ ከደረሰ ጥሩ ጅምር ነው፡፡  እኛ 32 ሺሕ ተማሪዎች ፈትነናል፡፡ ይህን ያህል ተማሪ ፈትኑ ሲባል ከባድ መስሎ ነበር የታየን፡፡ ነገር ግን ሁሉንም አቅም በአንድ አስተባብረን በመጀመርያው ዙር 18 ሺሕ አስገብተን ፈተንን፡፡ ከዚያ ቀጣዩን አስተናግደን በብቃት ተወጣነው፡፡ አቅማችንን ካስተባበርን ትልቅ ሥራ መሥራት እንደምንችል በ12ኛ ክፍል ፈተናና በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት አይተናል፡፡ የፀጥታ ችግር አለ፣ ሌላ ቦታ ሄጄ አልፈትንም የሚል ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ሄደው ሲመጡ ብዙዎቹ እንኳን ሄድን ነበር ያሉት፡፡ ብዙኃኑ ሕዝባችን በፖለቲካ ልሂቃን ክፋት አፈር እየበላ ነው፡፡ መደብ ለቆ የሚያስተኛና ካለው ቆርሶ የሚያጎርሰው ኢትዮጵያዊ በጥቂት ሰዎች ብልሹ ፖለቲካ መልካም ገጽታው እየጎደፈ ነው፡፡ ኦሮሚያ ቢባል፣ አማራ፣ ትግራይ ወይም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመላው የአገሪቱ ጥግ ያለው ምስኪኑ ብዙኃን ሕዝብ በጎነትንና ደግነትን ያውቅበታል፡፡ ልሂቃን ግን በክፋታቸው ሕዝቡን አብሮ መኖር እንዳይችል እያደረጉት ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሒደት ብዙ ነገሮችን በደንብ አሳይቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መቼ ተመሠረተ? ምን ዓይነት ትምህርቶች ይሰጣል? ምንስ እየሠራ ይገኛል?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- ዩኒቨርሲቲያችን በ1999 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የራሱ ማንነት ያልነበረው ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ ካሪኩለሙ ኮፒ ነው፡፡ ሰው ፒኤችዲና ማስተርስ ይዞ ሲመጣ ካሪኩለም ይዞ ነበር የሚመጣው፡፡ ሁለት ሦስት ሆኖ መጥቶ ዲፓርትመንት ይከፍታል፡፡ ይህ እንደ ቢዝነስም ሲታይ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ኮፒ ፔስት፣ ሥርዓተ ትምህርቱም ሆነ የመምህራን ቅጥሩ ኮፒ ፔስት ነበር፣ አመራሩም ኮፒ ፔስት ነው፣ በጣም የተዳከመ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ዝም ብሎ ረዥም ዓመት ተጉዟል፡፡ አርሶ አደራችንም ያው ነው፣ እኛም ያው ነን፡፡ ምሁሩና አርሶ አደሩ ተለያይቶ ነው የኖረው፡፡ ወጣቱ፣ ሴቱ፣ ምሁሩ፣ አርሶ አደሩና ፖለቲካው ሁሉም ተበታትኖ እየተጓዘ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን ሳይወጡ ኖረዋል፡፡

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም በዚህ ሲፈተን ነው የቆየው፡፡ ይህ እንዲቆም፣ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስኮች እንዲለዩና ራሳቸውን እንዲያሳድጉ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ እኛም በ2013 ዓ.ም. የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ተብለን ተለይተናል፡፡ የአሥር ዓመታት ዕቅድም አዘጋጅተናል፡፡ ሦስት ካምፓሶች አሉን፡፡ ዋናው ካንዳባ ግቢ፣ ኦቶናና ዳውሮ ናቸው፡፡ ዳውሮ ከዚህ ዋናው የሶዶ ግቢ 180 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቦታ ግዙፍ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ ነው ያለው፡፡ ወደ አሥር ኮሌጆች በዚህ ዋናው ግቢ ይገኛሉ፡፡ ኦቶና ደግሞ ወደ 94 ዓመታት ያስቆጠረ በሚሺነሪ ፈረንጆች የተቋቋመ የጤና ተቋም ስላለ፣ እሱ ላይ እኛ ትንሽ ጨምረን ከስፔሻሊቲ ጀምሮ እስከ ሕክምና ዶክትሬት እያሠለጠንን ነው ያለነው፡፡ ወደ 62 ቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ያሉን ሲሆን፣ ከእነዚህ አንዱ የሕክምና ዶክትሬት ፕሮግራም ነው፡፡ አራት የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ያሉን ሲሆን ቀዶ ጥገና፣ እናቶችና ሕፃናት፣ ማህፀን ሕክምናና ውስጥ ደዌ አለን፡፡ ከጳውሎስ ቀጥሎ የኩላሊት እጥበት ሕክምና የእኛ ተጠቃሽ ነው፡፡ በቀን ስምንት ታካሚዎች እናክማለን፡፡ ብዙ ሰዎች እዚህ እየታከሙ ወደ ውጭ ከመሄድ ተገላግለዋል፡፡ በካንሰር ሕክምና ላይም ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው፡፡ በተቻለ መጠን የእኛ ሆስፒታል ሌሎች በቀላሉ ሊሰጡት የሚችሉት አገልግሎት ላይ ሳይሆን፣ እጥረት ባለባቸው እንደ ኩላሊትና ካንሰር ሕክምናዎች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ነው የምንፈልገው፡፡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለዕቃ ግዥና ለግብዓት አውለን ጥሩ ዕድገት አምጥቷል፡፡ የሰው ኃይልን በሚመለከት ዩኒቨርሲቲያችን በአጠቃላይ ወደ 1,235 መምህራን አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ምን ዓይነት እሴቶች መገንባት ላይ ነው ትኩረታችሁ?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በዋናነት አምስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አንደኛው በምርምር፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ተቋም መገንባት ነው ግባችን፡፡ ሁለተኛው ቁልፍ ተግባር ደግሞ አረንጓዴ ተቋም መገንባት ነው፡፡ አረንጓዴ ተቋም የመገንባት ሥራ ደግሞ የሚበሉና የማይበሉ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ፣ አዕምሮ፣ ልብና እጅም አረንጓዴ ወይም በጎ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ጥላቻን፣ በቀልን፣ ሌብነትንና ዘረኝነትን አንፈልግም፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አረንጓዴ ናቸው፡፡ የማይሰርቅ፣ ልቡ የሚያፈቅር፣ አዕምሮው ሐሳብ የሚያመነጭና በጎ የሚያስብ ከሆነ በእኛ ዕይታ በአረንጓዴ ተቋም ውስጥ የበቀለ ነው፡፡ ከተማሪው ጀምሮ በዚህ ልክ ነው የምናስተምረውና ማኅበረሰብ የምንገነባው፡፡ ፅዱ ግቢን መገንባት ሌላው ፍላጎታችን ነው፡፡ ግቢያችን ከዶርሚታሪዎች ጀምሮ ፅዱ የዕውቀት ማዕከል እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ጨለማን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ማሸነፍ የፅዱ ተቋም መገንቢያ መንገድ ነው፡፡ ሌላው በብሔር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ተደራጅቶ ሌብነት አለ፡፡ ይህን መጠቃቀምና መጎዳዳት ማፅዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ዕውቀት ዓለም አቀፍ ሀብት ነው፡፡ ኬሚስትሪ የትም ዓለም አለ፡፡ እኛ ግቢ በአፈር ኬሚስትሪ የሚወጣ ሰው የትም ዓለም ሄዶ ይሠራል፡፡

እኔ የበሽታ አጥኚ (ኢፒዶሞሎጂስት) ነኝ፡፡ ይህን ደግሞ የትም ዓለም ሄጄ ላስተምርበት እችላለሁ፡፡ የወላይታ ኬሚስትሪ፣ የኦሮሞ ኬሚስትሪ ወይም የአማራ ኬሚስትሪ ብሎ ነገር የለም፡፡ ከዚህ ዘር ተኮር አስተሳሰብ ትምህርትና ሳይንስ መፅዳት አለበት ነው የምንለው፡፡ ሌላው አጀንዳችን ሰላም መፍጠር ነው፡፡ ሰላም ከሁሉ የሚቀድም ሲሆን፣ ሰላም ደግሞ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ላይ ሊኖር የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች ለራሳቸው ጤነኛና ሰላማዊ ሳይሆኑ ስለሌላው ሰላምና ጤንነት ማሰብ አይቻልም፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ትንሽቷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰላም ትሻለች ነው የምንለው፡፡ ከተማሪዎቻችን ጀምሮ ለመማርና ለመልማት ሰላም ይፈልጋሉ፡፡ ፀጉር አንጨባሮ፣ ሱሪ ቀዳዶና ራሱን አጎሳቁሎ ግቢያችን ውስጥ የሚውል ተማሪ እንዲኖር አንፈልግም፡፡ ተማሪዎቻችን በኢትዮጵያዊ ሥነ ባህሪ የተገሩ ናቸው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ወይም በክልል ደረጃ ሁሌም ውጥረት ቢኖር የእኛ ግቢ ግን ኮሽታ የሌለበት ሆኖ እንዲኖር ነው የምንፈልገው፡፡ ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን መቀነስ፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበርና ሥርዓት ማስያዝ የውስጣችን ኃላፊነት ነው፡፡

ሌላው አጀንዳችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖትና በብሔር ሽኩቻ የሌለበት ዩኒቨርሲቲ መፍጠር ነው፡፡ ከአመራር እስከ ታች ባለው የፆታ፣ የአካል ጉዳተኝነት፣ የክልል፣ የብሔር፣ የሃይማኖት የሁሉም ዓይነት ስብጥር ያለው የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ እንዲኖረን ነው የምንፈልገው፡፡ ከሥራ ቅጥር ጀምሮ ምደባ በማዕከል የሚመራና ይህን ስብጥር ያገናዘበ ነው፡፡ ሠፈር ለሠፈር መሳሳብ ካንሰር ነው የሚያመጣውን አንፈልግም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹ኃይስኩል ሆነዋል›› እንዳሉት፣ የእኛም ተቋመም በእጅጉ ሲፈተን ነው የኖረው፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ለአራት ዓመታት በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራዎች ስንሠራ ነው የቆየነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ይሠራል፣ ዕውቀት ያሻግራል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችንን ወደዚህ ከፍታ ለማምጣት ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ ከአመራር ጀምሮ መምህራኖቻችንና መላው ስታፎች በእነዚህ አምስት መሠረታዊ ዓላማዎቻችን ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው በጎ ለውጦችን እያመጡባቸው ነው፡፡ እነዚህ አምስቱ ዓላማዎች በየዕለት ሥራዎቻችንን የሚከወኑ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ በምን መንገድ የሚገለጹ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እየሠራን ነው ትላላችሁ?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- በዋናነት ልዩ ትኩረት ከምንሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና ነው፡፡ ከግብርናም የእንስሳት ሀብት ልማትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በልዩነት እየሠራን ነው፡፡  ወላይታ አካባቢ ለምሳሌ ሥጋ በማንኛውም ሰዓት ይገኛል፡፡ ቁርጥ እየተበላ ግን ወተት የለም፡፡ የወተት እጥረት የመጣው በምን ምክንያት ነው ብለን በምርምር ለመፍታት የራሳችንን ከብት ልማት አደራጅተን፣ ከትምህርት ዘርፉ ጋር አቀናጅተን እየሠራን ነው፡፡ በቀን እስከ 20 ሊትር የሚታለቡ ከ16 ያላነሱ የወተት ላሞችን እያረባን ለምርምር የምንጠቀም ሲሆን፣ የራሳችን ከብት ማደለቢያና መኖ ማምረቻም አለን፡፡ ለተማሪዎችና ለመምህራን የወተት ውጤቶችን ከዚሁ ማርቢያችን እየተጠቀምን ነው፡፡ ጊደሮችን ለአርሶ አደሩ ለማከፋፈል የተዘጋጀን ሲሆን፣ ለማዳቀያ የሚሆኑ ኮርማዎችንም ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሌላው ያተኮርንበት የፍራፍሬ ግብርና መስክ በተለይ አቮካዶ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ ትልቁ ሥራ እየተሠራ ያለው አቮካዶ ፍራፍሬ ላይ ነው፡፡ በራሳችን ግቢ በጠብታ መስኖ የምናለማው ሰፊ የአቮካዶ ልማት ያለን ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል፡፡ ግብርና ማቀነባበር (አግሮ ፕሮሰሲንግ) ለማበልፀግ የሚያግዝ ነው ብለን አቅደናል፡፡ አቮካዶው በጁስ ከመቀነባበር በዘለለ የመዋቢያና የቅባት ውጤቶችን ለማምረት እንደሚውል ይታወቃል፡፡ ከናይጄሪያና ከግብፅ የሚመጡ ምርቶችን በዚሁ አካባቢ በሚመረት አቮካዶ መተካት ይቻላል ተብሎ ትልቅ ዕቅድ ተይዞ የተጀመረ ብዙ የለፋንበት ፕሮጀክታችን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዓሳ ልዩ ትኩረት የሰጠነው አንዱ መስክ ነው፡፡ በእጃችን ያለ ብዙም ያልተጠቀምንበት ወርቅ ማለት ወላይታ አካባቢ ያለው የዓሳ ሀብት ልማት ዕምቅ አቅም ነው፡፡ የጊቤ የኃይል ማመንጫ ግድብ የፈጠረው ትልቅ ሐይቅ በቅርበት በኦሞ ሸለቆ ተኝቷል፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ ትልቁ የዓባያ ሐይቅ ተንጣሏል፡፡ ከወላይታ አካባቢ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ብዙ የሰው ኃይል ፍልሰት ይታያል፡፡ ይህን የሰው ፍልሰት በሥራ ፈጠራ ማስቀረት ከሚቻልበት መስክ አንዱ ደግሞ የዓሳ ሀብት ልማት መስክ ነው፡፡ ከእነ ስሙ በተለምዶ የወላይታ ዶሮ ምርጥ ነው ይባላል፡፡ አካባቢው ለዶሮ ዕርባታም የተመቸ በመሆኑ በዚህ መስክ ዩኒቨርሲቲያችን ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ሀብትና በማዕድን መስክም ትልቅ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ዞኑ 12 ሚሊዮን ብር ሰጥቶን በቅርቡ ጥናት አድርገናል፡፡ አካባቢያችን ለፍል ውኃ የተመቸ ነው፡፡ ዲምቱ የምትባል ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ከምንገነባበት ጎን ለኢኮ ቱሪዝም የሚውል የፍል ውኃ ልማት ሥራ እያካሄድን ነው፡፡ በአካባቢያችን ከፍተኛ የኦፓል፣ የድንጋይ ከሰልና የፖታሽ፣ እንዲሁም ሌሎች ማዕድናት እንዳሉም ተረጋግጧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህን ሀብት ለመጠቀም በምርምርና በቤተ ሙከራ ሥራዎች ታግዞ እየሠራ ነው፡፡

ሌላው ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የሥነ ሰብ ጥናት ሲሆን፣ በዋናነትም ባህልና ቱሪዝም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሀላላ ኬላ ግንባታ በቅርበት አለ፡፡ በዳሞታ ተራራ ዙሪያ ብዙ የቱሪስት ሀብቶች አሉ፡፡ የንጉሥ ጦና ቤተ መንግሥት አለ፡፡ እሱን አስጠግኖ ለቱሪዝም ለማዋል እየሠራን ነው፡፡ ሁለተኛም ቦራጎ የሚባል ዋሻ በተራራው ላይ አለ፡፡ እንግሊዞችና አሜሪካኖች ከእኛ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ጋር ሆነው እያጠኑት ነው፡፡ ዋሻው ምናልባትም ጥንታዊ የሰው ዘር ከዚህ አካባቢ ተነስቶ ተስፋፍቷል የሚለውን መላምት የሚያጠናክር ሲሆን ብዙ ምርምር የሚደረግበትም ነው፡፡ ባለ አራት ኮኮብ ሆቴል ግንባታም እያጠናቀቅን ነው ያለነው፡፡ ባህል ማዕከል፣ ሙዚየምና የሆስፒታሊቲ ተቋምን ያስተሳሰረ ሥራ እሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው እያጋጠሙት ያሉ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታለት የሚፈልገው ምንድነው?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- ስለትምህርት ጥራት ስናወራ ላብራቶሪና የሰው ኃይል አስፈላጊ ነው፡፡ ከእኛ መምህራን መካከል ከፍ ያለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ካየን ከአጠቃላይ ወደ ስድስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገራዊ የፒኤችዲ ፕሮግራም ተብሎ በአንድ ጊዜ ወደ አምስት ሺሕ እናስገባ በሚል ሐሳብ ተነስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በመካከል አመራሮች ሲቀያየሩ ቆመ፡፡ በፒኤችዲ ሥልጠናዎች ብዙ ጊዜ ለሥልጠናው የሄዱ ሰዎች የማይመለሱበት ሁኔታ ችግር ነው፡፡ በፒኤችዲ ሥልጠና የምርምር በጀት የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ ለፒኤችዲ ፕሮግራም ምርምር የሚውለው የ20 እና 30 ሺሕ ብር በጀት አያንቀሳቅስም፡፡ ሰው ፒኤችዲ የመሄድ ፍላጎቱን እቀነሰ ነው፡፡ አንደኛዬን ለቅቄ ሌላ ሥራ እገባለሁ እንጂ ፒኤችዲ ሠርቼ ወደ መምህርነት እመለሳለሁ የሚል ቁጥሩ እየቀነሰ ነው፡፡ የመምህራን ልማት በተለይ የፒኤችዲ መምህራን ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥቅም ጉዳይ የሚታወቅ ነው፡፡ የመምህራን መኖሪያ፣ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ አሥር ዓመት ፕሮፌሰር የሆነና ዛሬ ፕሮፌሰር የሆነ ሰው እኩል ነው ገቢያቸው፡፡ ይህ የትኛውም አገር ላይ የሌለ ሕግ ነው፡፡ እኔ የዛሬ አራት ዓመት ፕሮፌሰር ሆኛለሁ፣ ዛሬ የሚመጣው ሰው ግን ከኔ እኩል ነው የሚታየው፡፡ አስተዋጽኦና ልምድ የመሳሰሉት አይታዩም፡፡ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ ሁሉም ሰው እየተገመገመ እንደ አስተዋጽኦው ይሰጠዋል ቢባልም፣ ያንን አሠራር ግን ሲቪል ሰርቪስ ቆልፎ ይዞታል፡፡  የመምህራን መኖሪያ ጉዳይ ለምሳሌ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ለምሳሌ ለኔ 1,000 ብር የሚታሰብልኝ ሲሆን፣ ተቆራርጦ ግን 700 ብር ነው የሚደርሰው፡፡ በሶዶ ከተማ ይህች ብር እንኳን አንድ ወር አንድ ቀን አታሳድርም፡፡ የመምህራን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በአንዴ በእጥፍና ከዚያ በላይ ይደግ እያልን አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊደረጉ የሚችሉ ቀላል ነገሮች ይታሰብባቸው ነው የምንለው፡፡ ከባንክ ጋር ተነጋግሮ ለመምህራን ብድር ማመቻቸት ቢቻልም፣ መምህራኑ ቤት የሚሠሩበት ቦታ ካላገኙ ግን አይቻልም፡፡ ቦታ እንኳ ማመቻቸት ለምን ያቅታል? እኔ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርኩት፡፡ ሰው ቁርጠኝነቱ ካለው ዋርካ ስርም ያስተምራል፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ እንዲከበር ከተፈለገ ዋና መሠረቱን መምህሩን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ አገሮች የተቀየሩት በትምህርትና በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህንን ሕንፃ በወርቅና በአልማዝ ብትሠራው ያለ ሰው ምንም ነው፡፡ ጦርነቱ፣ አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍ ችግሮች በሙሉ ተደራርበው እኛ ላይም ተፅዕኖ አሳርፈውብናል፡፡ እንደ አገር ትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ኦሮሚያና መላው አገሪቱ ሰላም ሲሆኑ ነው እኛም ሰላም የምንሆነው፡፡ የዋጋ ግሽበትም ፈትኖናል፡፡ የበጀት እጥረትም አለብን፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የመምህራን ደመወዝና መሠረታዊ ወጪያችን ከተሸፈነ ሌላው ዕቅዳችንና ግንባታችን ከጊዜ በኋላ ሁሉም ሰላም ሲሆን ይደርሳል ብለን አምነንበት እየሠራን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በወላይታና አጎራባች ዞኖች የተደረገውን ደቡብ ኢትዮጵያ የተባለ ክልል የመፍጠር ሕዝበ ውሳኔን እንዴት ታዘቡት? የሕዝበ ውሳኔው መካሄድ በምን መንገድ ለእናንተ ይጠቅማል ይላሉ?

ታከለ (ፕሮፌሰር)፡- ደቡብ ላይ ተበታትኖ መኖር ከባድ ነው፡፡ የቲቲአይ ምሁራን ያቆሙትን ግዙፍ ክልል እኛ በፒኤችዲ እንዳናሳንሰው እሠጋለሁ፡፡ ዲፕሎማ ያላቸው ሰዎች ግዙፍ ክልል ፈጥረው አስረክበውን እኛ ግን ጠብቀን ማቆየት አልቻልንም እላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያስገርመኝም ይህ ነው፡፡ ትልቁን ክልል በትነነዋል፡፡ ደቡብ ማለት ከኦሮሚያና ከአማራ ቀጥሎ ትልቅ የሚባል ክልል ነበር፡፡ ሲዳማ ወጣ ሌላው ተከተለ፡፡ አሁን በተበታተነ ኃይል ነው የቀረው፡፡ ይህ የበለጠ እየከፋ እንዳይሄድና ኃይሉ እንዳይበታተን ቢያንስ ደቡብ ኢትዮጵያ ተብሎ መለስተኛ ትልቅ ክልል ለመመሥረት መሞከሩ ጥሩ ነው፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ በሆኑ አግባቦች ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የምረዳው፡፡ ይህን ሕዝበ ውሳኔም በሰላም እንዲካሄድ የምንጠብቀው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በአንፃራዊነት ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች ቀጥሎ ትልቅ የሚባል ክልል ለመመሥረት የሚያስችል ነው፡፡

ወደፊት እያንዳንዱ አጥርና ኬላ ሠርቶ ኢትዮጵያን ማሳደግ አይቻልም፡፡ የሰው ኃይልና ፋይናንስ ያለገደብ ማንቀሳቀስ የሚቻልባት ኢትዮጵያ መፈጠር አለባት ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ለምሳሌ የዕድሜዬን ግማሽ ጎንደር ተምሬ ጎንደር ሠርቻለሁ፡፡ ሌላ ቦታም ቢሆን ሄጄ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ነፃነቱ እየጠፋ ነው፡፡ ነፃነቱ ከሌለ ደግሞ ድህነት ከላያችን አይወገድም፡፡ ይህ ትልቅ አገራዊ ቀውስ የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ እያንዳንዱ ልክ እንደ ሶማሊያ ፑንትላንድ፣ ሶማሊላንድ እየተባለ በየሠፈሩ በመደራጀት ሀብቱን ማዳረስና መጠቀም አይቻልም፡፡ እንደ በፊቱ ያለውን ሀብትና የሰው ኃይል በጋራ በመጠቀም ደበብ ኢትዮጵያ ክልልም ለመልማት አመቺ ዕድል ያገኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ በየሠፈሩ ተደራጅቶ ለመኖር ሀብቱና አቅሙ ያለን አይመስለኝም፡፡ በጦርነቱም በሌላውም ወደኋላ ሄደናል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ልማቷ እንዲፋጠን መስከን አለባት፡፡ ደርግ 17 ዓመታት፣ ኢሕአዴግ 27 ዓመታት በልተውናል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ መከራችንን ዓይተናል፡፡ ይህ ካልተለወጠ አገራችን ወደፊት መቀጠል ይከብዳታል፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ተብሎ ትልቅ ክልል መፈጠሩ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ከሚታቀፉ እንደ አርባ ምንጭ፣ ዲላና ጂንካ የመሳሰሉ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ተባብሮ ለመሥራት ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል፡፡ የክልሉን መንግሥትም ሆነ ክልሉን የምርምርና ዕውቀት ምንጭ በመሆን ለማገልገል ትልቅ አቅም ይኖረናል፡፡ ሀብታችንና የሰው ኃይላችንን በጋራ የምንጠቀምበት፣ ካፒታልና የሰው ኃይል ያለገደብ የሚንቀሳቀስበት ክልል ከሆነ ይህችን አገር ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ክልል ይሆናል፡፡ ትልቁ ደቡብ ክልል ፈርሶ ያጣነውን ዕድል አሁን ደግሞ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተመሥርቶ የምናገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...