Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሚቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ፖለቲካዊ ስብራት የሚጠግን መሆን አለበት!

የሚቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ፖለቲካዊ ስብራት የሚጠግን መሆን አለበት!

ቀን:

በትርኳይ ለገሰ

  1. መግቢያ

የፌደራል መንግሥትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈራረሙት የግጭት ማስቆም ሰነድ በትግራይ ክልል የተካሄደው ምርጫ ኢሕገ መንግሥት በመሆኑ፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፈርሶ በምትኩ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ተስማምተዋል፡፡ አዲስ በሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት ዙሪያም የተለያዩ ሐሳቦች በመሰንዘር ላይ ናቸው፡፡ በባለሙያዎች የሚመራ ባለአደራ መንግሥት ይቋቋም ከሚል ጀምሮ፣ ሕወሓትን ያገለለ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት የሚሉ በርካታ አስተያየቶች በጋዜጣ፣ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መድረኮች እየሰማን ነው፡፡

በነፃነት እንዲሆን የምንመኘው አስተያየት ማቅረብ መለመድ ያለበት የዴሞክራሲ መገለጫ ልምምድ በመሆኑ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሰዎችን ማበረታታት አለብን፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበው ብዙ ሰው የተስማማንበት ሐሳብ ደግሞ አሻናፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአቶ መርስዔ ኪዳን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ በአቶ ግደና መድኅን የሚቋቋመውን ጊዜያዊ መንግሥት በሚመለከት ያቀረቡዋቸው አስተያየቶችን የማንበብ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ በጉዳዩ ላይ ደጋግሜ እንዳስብናና ያለኝን አስተያየት በጽሑፍ እንዳቀርብ ስላነሳሱኝ ሁለቱንም ሐጸፊዎች አመሠግናቸዋለሁ፡፡

አቶ መርስዔ ‹‹የባለሙያዎች ባለአደራ መንግሥት በአስቸኳይ ይቋቋም›› የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ጸሐፊው ያቀረቡት ሐሳብ በመሠረታዊ ሐሳቡ የሚያስማማ እንኳን ቢሆንም፣ ትግራይ አጋጥሟት የነበረውንና ያለውን ችግር ያላገናዘበ፣ እንደ አማራጭ ያቀረባቸው ግለሰቦች ደግሞ ከተፈለገው የባለሙያዎች ባለአደራ መንግሥት ባህሪ የማይገናኙና ትግራይ ውስጥ ለተከሰተው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ግንባር ቀደም ድርሻ የነበራቸውና ያላቸው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኝ ፖለቲከኞች መሆናቸው ነው፡፡ ግለሰቦቹ ከሕወሓት የቀድሞ አመራር ግለሰባዊ ግጭት ፈጥረው ከማኩረፋቸው በስተቀር፣ ከሕወሓት መሠረታዊ አካሄድና ፍላጎት ምንም ዓይነት ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለንተናዊ ቁመናቸው ሕወሓትና የሕወሓት አገልጋዮች የነበሩና ያሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት  የትግራይን መሠረታዊ ችግር መፍታት የሚችል፣ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰቦች ያቀፈና አዲሱን ትውልድ ያሳተፈ እንዲሆን ካለኝ ፍላጎት በመነሳት የሚከተለውን የግሌን አስተያየት ማቅረብ እወዳለሁ፡፡

  1. በትግራይ የነበረው ነባራዊ ሁኔታና ያስከተለው ቀውስ

የትግራይ ሕዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት የደረሰበት መከራና ሥቃይ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ ከሁሉም ነገር ተዘግቶ ከዓለም በሁለት ዓመት ወደኋላ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅና መልስ መስጠት ደግሞ መጪውን ጊዜ ለማስተካከል ጠቃሚ በመሆኑ ሐሳቤን ልጀምር፡፡ ትግራይ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያየናቸው መከራዎችና ሥቃዮች ለረዥም ጊዜ እየተጠራቀሙ የመጡ ችግሮች መገለጫ እንጂ ዋና ችግሮች እንዳልሆኑ መገንዘብ ይገባናል፡፡ ለዚህ ሁሉ መንስዔ ደግሞ ፖለቲካዊ ስብራት የትግራይ ዋነኛ ማጠንጠኛ እንደሆነ ነው እኔ የምረዳው፡፡

ሕወሓት ባለፉት አርባ አምሳ ዓመታት በትግራይ ብቸኛ ተመራጭ ፖለቲካ ፓርቲ፣ ብቸኛ መንግሥት፣ ብቸኛ ፀጥታ አስከባሪ፣ ብቸኛ ዳኛና ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ዕጣ ፋንታው ከሕወሓት ዕጣ ፋንታ አስተሳስሮ ቆይቷል፡፡ የረዥም ጊዜ ታሪክ ባለቤት፣ የራሱ ፊደል፣ ቋንቋ፣ ፍልስፍና፣ ባህል፣ ክብር፣ ማንነት፣ ከየትኞቹ አገሮች በፊት መንግሥት መሥርቶ ሲተዳደር ነበረ፣ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከአንድ የ48 ዓመት ጎልማሳ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጣ ፋንታ አስተሳሰረው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክ ትግራይ ሕዝብ ከተፈጠረ አጋጥሞት አያውቅም፡፡

በሌላ በኩል ሕወሓት ፓርቲ ሆኖ ለ17 ዓመታት በነበረው የበረሃ ትግል ራሱ ሠራዊት፣ የስለላ መዋቅር፣ የፍትሕ አካላት አደራጅቶ ስለነበር መንግሥት ሲሆንም እነዚህ ተቋማት ያለ ምንም ማሻሻል ይዟቸው ነው የቀጠለው፡፡ ስለሆነም የመንግሥት የሆነ ሁሉ ሕወሓት ነው የነበረው፡፡ በትግራይ ሕወሓት አንድም ብዙም ሆኖ ነው የነበረው፡፡ ፓርቲ፣ መንግሥት፣ ዳኛ፣ የፀጥታ አስከባሪ፣ ሰላይ፣ ነጋዴ፣ ዕርዳታ አከፋፋይ (በጎ አድራጊ) በአጠቃላይ ሁሉም ነበር፡፡ ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ላምባዲና የነበረውን ሕወሓት፣ ሁሉም ነገር በእጁ የነበረውን ሕወሓት ሄዶ ሄዶ ወደ ጥፋት በማምራቱ በድጋሚ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይገባል እላለሁ፡፡ ትግራይ ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በአምሳለ ሕወሓት ተቀርፆ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ዘልቋል፡፡ በመሆኑም ትግራዋይ ሌላ መንገድ መኖሩን ማየት እንዳይችል ስለተደረገ የሕወሓት ውድቀትና ጥንካሬ፣ ጭቆናና ፍትሕ የትግራይ ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ጦርነት ዓመታት እንኳን እንደ መነሻ ወስደን ካየን ሕወሓት ተሸንፎ ወደ በረሃ ሲወጣ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አባባል የሃይማኖት አባቶች ሸሽተው የሃይማኖት ተቋማት የተዘጉበት፣ የሕክምና ባለሙያዎች ሸሽተው የትግራይ እናቶች ሐኪም አጥተው የሞቱበት፣ መምህራን ሕወሓት ከሌሌ አናስተምርም ብለው ጠፍተው ትምህርት ቤቶች የተዘጉበት፣ የውኃ ባለሙያዎች መስመሩን ዘግተው የተደበቁበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ስለሕዝባዊ ፖሊስ፣ ስለሚሊሻ፣ ስለቀበሌ አመራሮች፣ ስለመንግሥት ሠራተኞች እንተውና ከላይ የተገለጹ በችግር ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሥራ ዘርፎች እንኳ ከፖለቲካ ስለተደባለቁ ራሳቸውን ለይተው ሕዝብ ማገልገል አልቻሉም፡፡

የሃይማኖት መሪዎች ውግንናቸው ለምዕመናን እንጂ ለአንድ ርዕዮተ ዓለም መሆን አይገባውም፡፡ በወልዲያ የነበሩ አባትን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ እኚህ አባት መንግሥት ሲነዛ ነበረውን ፕሮፓጋንዳ ችላ ብለው የእምነት ልጆቻቸውን በማፅናናት የረዱትን ሕዝብ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የሃይማኖት ተቋም ወይም መሪ መካሪና ዘካሪ መሆን ይገባዋል እንጂ፣ ከአንድ ፖለቲካ ድርጅት ጋር ተጣብቆ ሕዝብ ገደል ሲገባ ዝም ብሎ ማየት አይገባውም ነበር፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ጉዳይም በተመሳሳይ ማየት ይገባናል፡፡ ለምሳሌ በሶሪያ የዓለም ኃያል አገሮችን የቦምብ ውርጂብኝ ሲፈጽሙ ሶሪያውያን ሐኪሞች ደግሞ ሕዝብ መሀል ሆነው እየሞቱ ሕዝብ አድነዋል፡፡ እውነት ነው ሐኪምም ነፍስ አለው፣ ይሁንና ግን እንደ ተራ ካድሬ ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ከሸሸ አጠቃላይ መዋቅሩና የሥራ ሥምሪት ችግር እንዳለ ምስክር ነው፡፡ ስለሆነም በአጠቃላይ ትግራይ ውስጥ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ለረዥም ጊዜ ስለነበርና ስብራቱም የመጨረሻ ደረጃ ደርሶ ስለፈራረሰ ከዚህ በኋላ የሚመሠረተው የሽግግር፣ ጊዜያዊ ወይም የባለአደራ መንግሥት ከዚህ በፊት የነበሩ ስብራቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ የሚያስችል ሊሆን ይገባል፡፡

  1. ምን ዓይነት መንግሥት ይመሥረት?

በእኔ እምነት ከላይ የተገለጹ ችግሮች ትግራይን ከማፍረስ አልፈው መላ ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ ያስገቡ ልምዶችና ፖለቲካዊ ባህሎች ለማረም ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም የፌደራል መንግሥት ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምሁራን ጋር በጥልቀት በመወያየት በትግራይ የሚከተለውን ዓይነት መንግሥት ማቋቋም አለበት፡፡

3.1. የፀጥታ መዋቅር

በትግራይ ውስጥ ያለው ፀጥታ መዋቅር በቀጥታ በረሃ ከነበረው መዋቅር የሚቀዳ ነው፡፡ የበረሃ መዋቅር ደግሞ የሚያስተዳድረው ሕዝብ፣ የሚከፈለው ደመወዝና የሚኖርበት የግል መኖሪያ ስላልነበረው ታዛዥነቱ ለአንድ ፖለቲካ ድርጅት ብቻ ነበር፡፡ ከተማ ገብቶ የተዘረጋ የፀጥታ መዋቅርም ለይምሰል ካልሆነ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ‹‹ውድብና›› እያለ፣ ታማኝነቱና አገልግሎቱ ለአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በትግራይ የተካሄዱ ምርጫዎችና ሌሎች የሕዝብ ጥያቄዎችን ሲያፍን የነበረውም ለዚህ ነው፡፡

ይባስ ብሎም በተከሰተው ፖለቲካዊ ግጭት ሰለባ ሆኖ ብዙ ኢንቨስት የተደረገበት የፀጥታ መዋቅር እንዲፈርስ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥትን መሠረት በማድረግ ለሕዝብና ለሕግ ታማኝ የሆነ የፀጥታ መዋቅሮች ማቋቋም ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ሌሎች ክልሎች ሁለት ዓይነት የፀጥታ መዋቅር ይኖራሉ፡፡ አንደኛው ሕዝባዊ ፖሊስ ሲሆን አንዳንድ ማስተካከያዎች ብቻ በማድረግ የነበረውን ፖሊስ መጠቀም ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዋናው እዚህ ላይ ትኩረት መደረግ ያለበት ተቋሙ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አገልጋይና ሕዝብ ላይ ተጭኖ የነበረ በመሆኑ፣ እንደ አዲስ መሠረታዊ የአገልጋይነት ሥልጠና መስጠትና ሥልጠናውን መሠረት ያደረገ የሥራ ሥምሪት ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ የገለልተኝነት መርህ እስኪለማመድና እውነተኛ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በፌደራል ፀጥታ መዋቅር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡

ሌላው በክልሉ መደራጀት የሚገባው የፀጥታ መዋቅር ልዩ ኃይል ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት በአገር ደረጃ ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት እንኳን ቢሆንም፣ በሌሎች ክልሎች እስካለ ድረስ በትግራይም መኖሩ አጠያያቂ አይመስለኝም፡፡ ልዩ ኃይል በአገር ደረጃ የሥራ ድርሻው ግልጽ ያልሆነ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የለውም ስለሚባል፣ የባለሥልጣን ጠባቂና የሕዝብ ጥያቄ ማፈኛ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ዕሙን ነው፡፡ በመሆኑም በክልሉ የነበረውን ልዩ ኃይል ለሌሎች ትምህርት በሚሰጥ መንገድ ግልጽ በሆነ አሠራር ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ልዩ ኃይሉ በተግባር እንደታየው በትግራይ ለደረሰው አስከፊ ሥቃይና መከራ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለሕወሓትም የልብ ልብ ሰጥቶት ወደ አስከፊ ጦርነት እንዲገባ ያደረገው ይህ የሥራ ድርሻው በውል ያልታወቀ ኃይል ነው፡፡

ስለሆነም በሕግና በሥርዓት የሚመራ በትግራይ ለሚንቀሳቀሱ ፖለቲካዊ ኃይሎች እኩል የሚያገለግል በሕዝብ ተመረጠ መንግሥት እስኪመሠረት፣ ለፌደራል ፖሊስ ተጠሪ የሆነ ልዩ ኃይል እንዲቋቋም ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ተቋሙ እንደ አዲስ ፈርሶ የነበሩ አባላትም ተሃድሶ ወስደው ፈቃደኛ የሆኑ፣ የሕዝብ ሉዓላዊ መብት የተቀበሉና በፍላጎት የተመሠረተ አዲስ ምልመላና ቅጥር በማድረግ ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ በትግራይ የሚቋቋመው ልዩ ኃይል የሚታጠቀው መሣሪያ፣ የሥራ ድርሻው፣ አመላመልና ሥምሪት ሥርዓቱ በግልጽ ተቀምጦ ከተሠራበት ሌሎች ክልሎችንም ለማስተካከል ትምህርት ሊወሰድበት ይችላል፡፡

የፌደራል መንግሥት በቅንነት ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃ የሆነ የፀጥታ መዋቅር ማደራጀት ከቻለ፣ ትግራይ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት አጋጥሟት የነበረውን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ገለልተኛ የሆነ የፀጥታ መዋቅር ከተገነባ ሦስት መሠረታዊ ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ጥቅሙ መሪ ድርጅት ፖለቲካዊ ቀውስ ሲገጥመው ክልንም ሆነ አገርን በማስቀጠል ላይ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ሕዝብና አገር ለማገልገል የተደራጀ ኃይል እስካለ ድረስ በጊዜያዊ ፖለቲካ ሽኩቻ አይሸበርም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ ሽኩቻው ወደ መንግሥትና ሕዝብ እንዳይዛመት በመከላከል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ያለፈውን ታሪክ ይደግማል ማለት ነው፡፡

ሁለተኛ ጥቅሙ መንግሥት ለመሆን ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፀው የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ማገልገል ያስችለዋል፡፡ ‹‹ውድብና› የሚል የፀጥታ መዋቅር ባለበት አካባቢ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡ ላለፉት ስድስት ምርጫዎች በትግራይ ምርጫ ነበር ለማለት አያስደምፍርም፡፡ የነበረው አካሄድ የፀጥታ መዋቅሩ የእኛና የሌላ ብሎ ለይቶ ባስቀመጠበት ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሠራር ውጤቱ ምን እንደሆነም ዓይተነዋል፡፡ ስለሆነም የውድድር ሜዳው ለሁሉም እኩል እንዲሆን ገለልተኛና የፀጥታ መዋቅር ማደራጀቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እዚህ ላይ የትግራይ ሕዝብ ቆም ብሎ ማሰብ የሚገባው እኩል ጥበቃ የሚደረግላቸው በሐሳብ ብቻ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች አሉ ማለት፣ ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙ ችግሮች ለመሻገር በጣም ወሳኝ መሆኑ መረዳት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ያጋጠመው ችግር መንስዔው በራሱ የመጣው በፖለቲካ ስብራት መሆኑ መገንዘብ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ አንድ ፓርቲ፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አንድ ዓይነት አካሄድ መከተል ውጤቱ አስከፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች የሚደመጡበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ የሚወዳደሩበትና ገለልተኛ ተቋም ቢኖሩ ኖሮ ብዙ በጣም ብዙ መውጫ መንገዶች ነበሩ፡፡ የፌደራል መንግሥትን ገለልተኛ ፀጥታ መዋቅር በትግራይ ማደራጀት በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካ ስብራት የፈረሰች ትግራይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከጫፍ ደርሳ እንደነበር መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ሦስተኛው የገለልተኛ የፀጥታ መዋቅር ማደራጀት ጥቅሙ የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ብቃቱ ነው፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ የሆነ የፀጥታ መዋቅር ትኩረቱ ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡ በትግራይ የሆነውም እስካሁን እየሆነ ያለውም እንዲህ ነው፡፡ የትግራይ ልዩ ኃይል ለሕወሓት ፖለቲካዊ ዓላማ ብሎ ወደ ሕዝብ ተኩሷል፣ ሴቶች ደፍሯል፣ የሃይማኖት ተቋማትን አርክሷል፡፡ ይህ የሚያሳየው ለሕዝብ ምንም ዓይነት ርህራሔ እንደሌለው ነው፡፡ ስለሆነም ገለልተኛ ሕዝባዊ ፀጥታ መዋቅር ማደራጀት ብዙ ጥቅም እንዳለው ተገንዝበን በትግራይ የሽግግር፣ ባላደራ ወይም ጊዜያዊ መንግሥት ሲመሠረት የፀጥታ መዋቅር አደረጃጀት ትኩረት ያስፈልገዋል ባይ ነኝ፡፡

ከዚህ አንፃር የፌደራል መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ገለልተኛ የፀጥታ መዋቅሩ ማደራጀት ይገባዋል፡፡ ትግራይ አሁን ለሁሉም ነገር ምቹ ሁኔታ አላት፡፡ ለጥፋትም ለልማትም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባትም ኢዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመከተልም፣ ገለልተኛ ተቋማት ለመገንባትም በተቃራኒው ለመሄድም፡፡ ስለሆነም መንግሥት ይህንን በውል ተገንዝቦ ትግራይለ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው በማለት በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

3.2. የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት

በትግራይ ነበረው መንግሥት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ስለፈረሰ፣ ሕጋዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አዲስ ጊዜያዊ መንግሥት መቋቋሙ የማይቀር ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ጊዜያዊ መንግሥት እንዴት ይደራጅ የሚለው ነው፡፡ አደረጃጀቱን በሚመለከት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ እንሰማለን፣ ብዙ ጽሑፎችም አንብበናል፡፡ በአብዛኛው የሚቀርቡ ጽሑፎችም ሆኑ አስተያየቶች የዓለምን ልምድ መሠረት ያደረጉ እንጂ በትግራይ ውስጥ የነበረውንና ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ከግምት ያስገቡ አይደሉም፡፡ በቱኒዚያ እንዲህ ነበር እንደዚህ ሆነ፣ በሚያናማር እንዲህ ነበር እንደዚህ ሆነ ከማለት ውጪ በተጨባጭ የአገሮቹንም ሆነ የአካባቢውን ሁኔታ የሚናገር የለም፡፡

ስለሆነም በትግራይ ውስጥ ምን ነበር? ምን አለ? እንዴትስ ይሁን? የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ መሆን የሚገባው፡፡ ትግራይ ውስጥ ባለፉት 32 ዓመታት የነበረውን በሕወሓት ዘመን በአገር ደረጃ ፌደራላዊ ሥርዓት የነበረ ቢመስልም በትግራይ ውስጥ ግን ፍፁም አሀዳዊ፣ ውድባዊ ጥርነፋ የበዛበት፣ አውራጃዊ በሽታ የሰፈነበት፣ የሰው ኃይል ሥምሪቱና አደረጃጀቱ ፍትሐዊነት የጎደለው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም የሚመሠረተው መንግሥት እንዲህ ዓይነት ችግሮችን የሚቀርፍና በሕጋዊ ምርጫ ለሚመሠረተው መንግሥት የተደላደለ መሠረት አስቀምጦ የሚያልፍ መሆን አለበት፡፡ እንዴት? በመጀመሪያ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ ያልተሳተፈበት በሁሉም ወረዳዎች በሕዝብ ነፃና ግልጽ ምርጫ በማካሄድ ከጣቢያዎች የተውጣጡ አባላት ያለው ጊዜያዊ ምክር ቤት ማቋቋም፡፡ ይህ ምክር ቤት የወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት የማቋቋምና ወረዳውን ወክለው ለዞን ምክር ቤት የሚሆኑ ተወካዮች እንዲመርጥ ይደርጋል፡፡ የዞን ምክር ቤት ደግሞ የዞን አስተዳደር በመመሥረት ለክልል ምክር ቤት የሚሆኑ ተመራጮችን በመመልመል ይልካል፡፡ በዚህ መንገድ የሚመሠረት ጊዜያዊ መንግሥት ከዚህ በፊት የነበሩ ሦስት ዓይነት የፖለቲካ ስብራቶችን ያስተካክላል፡፡ እንዲሁም ለመጪው ጊዜ ጥሩ ልምድ ትቶ ማለፍ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የተሳለጠ የመንግሥት አሠራር እንዲኖር ያደርጋል፡፡

በመጀመሪያ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ራስን በራስ የማስተዳደር ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ትግራይ ውስጥ ፌደራላዊ ሥርዓት ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ቅሬታ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ አንዱ ታማኝ አንዱ የማይታመን ሆኖ ትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች ሰዎች ብቻ መፈንጫ ሆና ለ50 ዓመታት ዘልቃለች፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሠራር ደግሞ መጨረሻው ተያይዞ መጥፋት ካልሆነ፣ የሚያስገኘው ጥቅምም ሆነ የሚያመጣው ልማት አለመኖሩን ዓይተናል፡፡ ስለሆነም ከታች ወደ ላይ የሚደረገውን የምክር ቤቶች አደረጃጀት የራስና የጋራ አስተዳደር ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

ሌላው የሚያስገኘው ጠቀሜታ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ነው፡፡ በተለይ ከሥልጣን ክፍፍል ጋር ተያይዞ ነበረውን የፍትሐዊነት ጉዳይ በትግራይ ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ ችግሩ እስከ ፌደራል መንግሥትም መስፋፋት ችሎ ነበር፡፡ ስለሆነም የጣቢያ፣ የወረዳና የዞን ብዛትና ስፋት መሠረት ያደረጉ ምክር ቤቶች ማቋቋምና ከሁሉም ዞኖች በፍትሐዊነት የተውጣጡ አባላት ያሉት የክልል ጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋም ይገባል፡፡ ትግራይ የሁሉም ትግራዋይ ናት፣ በመሆኑም ሁሉም እኩል ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ዓጋመታይ፣ ወልቀታይ፣ ራያታይ፣ ሽረታይ፣ አኽሱምታይ፣ ቴምበንታይ፣ እንደርታይ፣ ኩናማታይ፣ ኢሮበታይ፣ ወዘተ የሌለው መንግሥት ትግራይ ሊሆን አይገባም፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሚያስተካክለው ስብራት ያልተማከለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ከላይ እስከ ታች በአንድ ለአምስት የተጠረነፈ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተጫነው መንግሥት ነው የነበረው፡፡ በመሆኑም መንግሥታዊ አገልግሎቶች ኢፍትሐዊና ፖለቲካዊ ውግንናን መሠረት ያደረጉ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ዜጋ በመሆንህ ብቻ ማግኘት የምትችለው መታወቂያ እንኳን የውድብ፣ወጣቶች፣ የሴቶች ወይም የገበሬዎች አባል ካልሆንክ ማግኘት አትችልም፡፡ ሌላው ዜጎች አንድ ለአምስት ተደራጅተው በነፃ አስበው ሕዝባችንና አካባቢያቸውን እንዳያገለግሉ ተደርጓል፡፡  የወጣቶችንና የተማሪዎችን የምርምር መንፈስ የሚገድል አሠራር ተዘርግቶ ነበር፡፡ ስለሆነም የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት በሕዝብ ያልተማከለ ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሚያሰፍን የትምህርት፣ የጤናና የመንግሥታዊ ተቋማት ያለ ምንም ዓይነት ጥርነፋ ሕዝብ የሚያገልግሉ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከየአካባቢው በሕዝብ ቀጥታ ምርጫ የሚቋቋም የመንግሥት መዋቅር ለሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ከራሱ ክሕዝብ በቀጥታ የሚመረጥ በመሆኑ በየወረዳው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመራደት አያስቸግረውም፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የነበረውን መፍትሔ አሰጣጥ ለደቡብም ለምዕራብም፣ ለሰሜኑም ለምሥራቁም፣ ለማዕከሉም ለዳሩም ተመሳሳይና ያው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምዕራብ ማዳበሪያ ከወሰደ ምሥራቅም መውሰድ አለበት፣ ደቡብ ሆረዮ ከሠራ ሰሜንም መሥራት አለበት እየተባለ ሲሠራበት ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን አስወግደው እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ያልተማከለ አስተዳደር መመሥረት ለሕዝብና ክልል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ የጊዜያዊ መንግሥት ጊዜ በጣም አጭር ቢሆንም፣ ለተመራጭ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ መቆየት ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያሉ የሕግና የአደረጃጀት ክፍተቶች በሚቋቋሙ ምክር ቤቶች አማካይነት ማስተካከል ይገባል ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በሕዝብ የሚወጣ በመሆኑ የትግራይ ሕገ መንግሥት እንደ ገና ታይቶ ለሕዝብ ቀርቦ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡

ጊዜያዊ መንግሥት በመመሥረት የፌደራል መንግሥት ድርሻ ትልቅ ስለሆነ፣ ከሕዝብ ጋር ተመካክሮ የትኛውም ፖለቲካዊ ፓርቲ ያልተካተተበት በሕዝብ የተመረጡ ጊዜያዊ ምክር ቤቶችና መንግሥታዊ መዋቅር መዘርጋት ይገባል፡፡ ይህ ማለት በትግራይ ያሉ መንግሥታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ይፈርሳሉ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ተቋማቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃ የሆኑ ባለሙያዎች እንዲመሩዋቸው ተደርገው አገልግሎታቸውን በተጠናከረ መንገድ እንዲሰጡ ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ጊዜያዊ መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ግን ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ከቀበሌ/ጣቢያ ጀምሮ የሚያደራጅ አካል ተሰይሞ፣ በቂ ኦሬንቴሽንና ሥልጠና ተሰጥቶት ወደ ሥራ መገባት ይገባል፡፡ ጊዜያዊ መንግሥት ከፖለቲካ፣ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች አንፃር መሥራት የሚገባውና የማይገባው በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ ከአጎራባች ክልሎች፣ ከፌደራል መንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዓለም ዓቀፍ ዕርዳታና ድጋፍ ድርጅቶች የሚኖረው ግንኙነትና አሠራር በግልጽ በፍኖተ ካርታው መቀመጥ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአደራጅ አካል በሚመች መንገድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው የሚቋቋሙ ምክር ቤቶችና አስተዳደሮች የሥራ ልምድ፣ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የትምህርት ዝግጅት የመሳሰሉ መሥፈርቶች የያዘ ሰነድ መዘጋጀት ይገባል፡፡

3.3. የፖለቲካ ፓርቲዎች

ከ2010 ዓ.ም. በፊት ከሕወሓት ውጪ በትግራይ ሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ ይንቀሳቀስ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ዓረና ፈቃድ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ትግራይ ውስጥ በነፃነት እየተንቀሳቀሰ አልነበረም፡፡ ሕወሓት ጠቅልሎ መቐለ ከገባ በኋላ ግን አራትና ከዚያ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ ነበሩ፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲ አንፃር ሲታይ ከምንም ወደ ስድስትና ከዚያ በላይ በትግራይ ብቻ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረታቸው ትልቅ አብዮት ተካሂዷል ማለት ይቻላል፡፡ ይሁንና ግን የሕዝብና የሕወሓት ፖለቲካዊ ልምድ አላንቀሳቅስ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በትግራይ አለን ከማለት ውጪ፣ ሕዝቡን ከመከራ ሊያተርፉት አልቻሉም፡፡ የሕወሓት መንገድ ተከትለው ነው ገደል ገቡት፡፡ ሁሉም በትግራይ መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም ሕወሓትና ብልፅግናን ጨምሮ በጊዜያዊ መንግሥት በፓርቲ ደረጃ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ሳይኖራቸው ሕጋዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ራሳቸውን የሚያደራጁበት፣ ከሕዝብ የሚተዋወቁበትና አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች የሚቀርፁበት ሆኖ እንዲያልፍ ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ ልምድ የላትም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጊዜያዊ መንግሥት ከገቡ ከዚህ በፊት እንዳየነው እርስ በእርስ ከመካሰስ ውጪ ለትግራይ ሕዝብ ውጤት ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በእርግጥ ለአዳዲሶቹ ልምድ ለማግኘት ይጠቅማቸው ይሆናል፡፡ ግን አጠቃላይ ጠቀሜታው ሲታይ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጊዜያዊ መንግሥቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ እንዳይሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ ፓርቲውን ሳይሆን በግሉ የተመረጠ የጊዜያዊ መንግሥት አካል የሆነ አባል ይኖራቸው ይሆናል እንጂ በፓርቲ ደረጃ እንዳይሳተፉ ማድረግ ግን ያስፈልጋል፡፡

እንዲህ ዓይነት አሠራር የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን የሚያደራጁበትና ከሕዝብ የሚተዋወቁበት ጊዜ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ፣ በፖለቲካ ፓርቲ የማይመራ ሲቪል ሰርቫንትና የፀጥታ መዋቅር ማደራጀትና ልምምድ ማድረግ ደግሞ ለትግራይ ትልቅ ዕፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡ ከፖለቲካ አሠራር ያልተጣበቀ መንግሥታዊ መዋቅር ዘላቂ እንዲሆን የመሆን ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳየነው በሕወሓት ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሲቃኝ የነበረውን መንግሥታዊ መዋቅር ሕወሓት ስትቆም አብሮ ነው የቆመው ግን መሆን አይገባውም ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከሕወሓት ፖለቲካዊ ተሳትፎ አንፃር ብዙ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰሙ እሰማለሁ፡፡ ሕወሓት ከትግራይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መወገድ አለባት የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ ይሁንና አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መወገድ አለበት ብሎ ነገር ተረኛ ሕወሓት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ስለማይኖረው፣ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ያለ ምንም ተፅዕኖ ተንቀሳቅሶ በሕዝብ ከተመረጠ እንደገና ክልል የማስተዳደር ዕድል የማግኘት መብቱ የተጠበቀ መሆን ይገባዋል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በኃይል ሳይሆን በሐሳብ በልጦ በሕዝብ ተቀባይነት እንዳይኖረው በማድረግ ብቻ ነው ማሸነፍ የሚቻለው፡፡ ዋናው እዚህ ላይ መስተካከል ያለበት የምርጫ ሜዳውና የፀጥታና መንግሥታዊ መዋቅሩ ለሁሉም በእኩል የሚያገለግል እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጊዜያዊ መንግሥት ሳይካተቱ የራሳቸውን ሥራ ብቻ እንዲሠሩ በማድረግ ፓርቲ፣ መንግሥትና ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸውን ልምድ ማግኘት ይገባል፡፡

  1. ማጠቃለያ

በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገው ስምምነት መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት ለትግራይ የዓለም ልምዶች መውሰድ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ዋናው ግን ከተጨባጭ የትግራይ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ጠቅለል ሲደረግ የፖለቲካዊ ሰብራት በአመዛኙ ትልቅ ስለሆነ በሕዝብ ለሚመረጠው ሕጋዊ መንግሥት ጥሩ መደላድል አዘጋጅቶ ከመቆየት አንፃር የፀጥታ፣ የሲቪል ሰርቫንትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናና አደረጃጀት ተለይቶ መቀመጥ አለበት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል tirquaylegesse@gmail.com አድራሻቸው  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...