Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት እራቴን እየበላሁ ቴሌቪዥን ሳይ አንድ አዲስ የሚጀመር ተከታታይ ድራማ ማስታወቂያ ላይ ዋና ገጸ ባህሪ ሆኖ የሚተውን ወጣት አየሁ፡፡ ይህንን ወጣት አውቀዋለሁ፣ ነገር ግን እሱ ነው ወይስ ወንድሙ ወይስ ተመሳሳይ ሰው ይሁን አላወቅኩም፡፡ ማስታወቂያው በጣም በፍጥነት ስለሚተላለፍ ልለየው አልቻልኩም፡፡ በነጋታው ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገኘው ካፌ ስገባ ያ የማውቀው ወጣት እንደተለመደው በደማቅ ፈገግታ ሲቀበለኝ፣ የአዲሱ ድራማ ተዋናይ እሱ ወይስ ሌላ እንደሆነ ወዲያው ጠየቅኩት፡፡ እሱም ራሱ መሆኑን ነግሮኝ የመጀመሪያው ሥራው እንደሚሆን ከትምህርት ዝግጅቱና ከሌሎች መለስተኛ ልምዶቹ ጋር አያይዞ አስረዳኝ፡፡ እኔም አበረታትቼው አዲሱን ድራማ ለመከታተል ቃል ገባሁለት፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ካፌ እያስተናገደ በጥረቱ ለማደግ የተዘጋጀን ማን ዝም ይላል ታዲያ፡፡

የሕይወት ክብደት በሁሉም የኑሮ ትግል ውስጥ ዘወትር የሚያጋጥም መደበኛ ተግዳሮት በመሆኑ፣ ይህንን ጭነት ተጋፍጦ ነገን በአሸናፊነት ለመረከብ ውጣ ውረዱን በፅናት መቋቋም የብርቱዎች የተለመደ ተግባር መሆኑን አምናለሁ፡፡ በግልም ይሁን በአገር ደረጃ አስከፊ ጊዜያት ሲያጋጥሙ አጋጣሚዎችን ወደ መልካም ከመለወጥ ይልቅ፣ ውሉ የማይታወቅ ቅራኔ ውስጥ ሰጥሞ ተዓምር መጠበቅም ሆነ የተሻለ ነገር ማሰብ ለማንም አያዋጣም ባይ ነኝ፡፡ ዓለም የሁሉም ዓይነት ትግሎች መድረክ በመሆኗ የተሻለውን ትግል መርጦ አሸናፊ ለመሆን ጥረት ማድረግ የግለሰቡ ውሳኔ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢከኖሚና በማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ብቁ ተዋናይ ለመሆን የሚቻለው ለዚያ የሚመጥን ቁመና መገንባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ቁመና ጡንቻ የሚያሳዩበት ሳይሆን የአዕምሮ ጭማቂ ውጤት የሚያስመዘግቡበት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በእኛ አገር በሁሉም ነገሮች መጨቃጨቅና ለገላጋይ የሚያስቸግር ጠብ መፍጠር በጣም ቀላሉ ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን ለራስም ሆነ ለአገር ጠብ የሚል አስደሳች ነገር ማግኘት ግን የኤቨረስት ተራራን የመውጣት ያህል ከባድ ነው፡፡ በአግባቡ በመማር በሥራ መለወጥን የመሰለ መልካም ባህል ተዘንግቶ፣ የአቋራጭ መንገድ ፍለጋው ላይ የሚንከራተቱ ወጣቶችን ብዛት መቁጠር እያታከተ ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ከጠቅላላ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ብቻ እንዳለፉበት ሲያስታውቅ፣ በጣም ጥቂት ከሚባሉ ሰዎች በስተቀር ብዙኃኑ በኩርፊያ ወይም በቀልድ ውስጥ ሆነው መነጫነጫቸውና መሳለቃቸው የችግራችን አንዱ ማመላከቻ ነው፡፡ ለማንም የማይጠቅምና እንደ ሰጎን ራስን አሸዋ ውስጥ የመደበቅ አባዜ በሉት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ድሮ መምህራን በየክፍለ አገሩ በእግር፣ በጋማ ከብቶችና ሲገኝም በጭነት መኪኖች እየተጓዙ ያስተምሩ እንደነበር ከበቂ በላይ ሰምቻለሁ፡፡ በጉዞአቸው ወቅት አቀበትና ቁልቁለት፣ የውኃ ሙላት፣ የዱር አውሬ፣ ቀማኛ ሽፍታ፣ ወባና መሰል የበረሃ በሽታዎችና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠው ከባድ መስዋዕትነት ይከፍሉ ነበር፡፡ ወታደሮች፣ ሐኪሞች፣ መሐንዲሶች፣ ፖስተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወዘተ በዚህ መሰሉ ከባድ ሕይወት ውስጥ እያለፉ አገልግሎት ያበረክቱ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ዛሬም ያንን መሰል መስዋዕትነት የሚከፍሉ አገር ወዳዶች እንዳሉ አይካድም፡፡ ነገር ግን ብዙ ነገሮች ተበለሻሽተው ዘመናችን አጉል ሆኗል፡፡

ፈተና በደቦ መፈተን ወይም በኩረጃ ማለፍ፣ ጥቅም የሚገኝበት መሥሪያ ቤት በዘመድ አዝማድ መቀጠር፣ ከቤት ወይም ከሥራ ቦታ እየተጠሩ የባንክ ብድር፣ መሬት፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልና የመሳሰሉት ሳይቀሩ የሚበተንላቸው በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡ ዘመድና ተቆርቋሪ የሌላቸው ግን የልማት ባንክ ያወጣውን የሥልጠና ዕድል ለማግኘት፣ ለቀናት ፀሐይና ቁር ላይ ተሰጥተው የወጪ ወራጁ ዓይን ማረፊያ ሆነው መሰንበታቸው አይዘነጋም፡፡ በየቦታው ባለ አድሎአዊነት ምክንያት ከሚሠራው ይልቅ ሳይሠራ ሀብት የሚያግበሰብሰው እየበዛ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የብሔር ፖለቲካው መልካም መደላድል ፈጥሯል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት ይመስለኛል ዕድሜው በግምት አሥር የሚሆነው ከወላይታ አካባቢ የመጣ ታዳጊ፣ “ጋሼ ጫማ ልጥረግ…” ብሎ ዓይኖቼን በልምምጥ ማየት ጀመረ፡፡ እኔም አንድ ጥግ ወስጀው ደገፍ ካልኩ በኋላ አንድ እግሬን ዘርግቼ ሥራውን እንዲቀጥል ነገርኩት፡፡ ከዚያም እኔ እየጠየቅኩት እሱም በቋንቋ ችግር ምክንያት እየተደነቃቀፈ መልስ እየሰጠኝ ብዙ አወራን፡፡ ከልጁ ጋር በነበረኝ ቆይታ እንደተረዳሁት፣ እሱ ከመጣበት የገጠር ቀበሌ አንድም ወጣት ወይም ታዳጊ የተረፈ አይመስልም፡፡ ታዳጊዎቹ ትምህርታቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ በመሸሽ ለቀን ሥራ ራሳቸውን አሳልፈው ሲሰጡ፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎችም ሆኑ የፖለቲካ ሰዎች ዝም ብለው ማየታቸው አገራችን በእንቆቅልሽ እንድትሞላ ያደረጋት መሰለኝ፡፡ የዝምታቸው ምክንያቱ ግልጽ አይደለማ፡፡

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንገታቸውን ደፍተው በጨዋነት አገራቸውን የሚያገለግሉ ያሉትን ያህል፣ ይህንን መልካም ባህል ተፀይፈው “ሁሉም ነገር ወደ ዘረፋ ግንባር” ያሉ መብዛታቸው ሲታሰብ መጪው ጊዜ ያስፈራል፡፡ ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ተንደው ከላይ እስከ ታች ደጋፊን ለማሰባሰብ ሲባል ጥቅማ ጥቅም መስጠትም ሆነ መቀበል ልማድ ሲሆን፣ የነገው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ከወዲሁ ያሳስባል፡፡ የካፌ አስተናጋጅነት እየሠራ ተከታታይ ድራማን የሚያህል ትልቅ ፕሮጀክት ላይ መሪ ተዋናይ ሆኖ ለመሥራት የበቃ አንድ ጠንካራ ወጣት በማወቄ ብፅናናም፣ እንዲህ ዓይነት አርዓያነት ያላቸው ወጣቶች በብዛት ማግኘት ካልተቻለ ነገ ያስፈራኛል፡፡

(ሙራድ መሐመድ፣ ከቦሌ ሆምስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...