- የማይተባበሩ የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከየካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በ167 የመንግሥት ተቋማት ላይ የሙስና ሥጋት ተጋላጭነት ጥናት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ የጥናቱ ውጤት በቀጣይ ተደራጅቶ የተቋማቱን ገጽታ የሚያሳይ ፕሮፋይል ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽኑ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ላይ ያተኮረ ጥናት እንደሚያካሂድ፣ የኮሚሽኑ የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የጀመረው የዳሰሳ ጥናት ሥልጠና በወሰዱ 142 ባለሙያዎች አማካይነት በየተቋማቱ በመንቀሳቀስ፣ ከሙስና ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ የአሠራርና የአደረጃጀት መመርያዎችን በማጥናት በአሥር ቀናት ውስጥ ለኮሚሽኑ የተጠናቀረ መረጃ እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡
በሒደቱ ከባለሙያዎቹ የሚሰበሰበውን መረጃ ከተቋሙ ውጪ በገለልተኛ አማካሪዎችና በመረጃ ተንታኝ ባለሙያዎች አማካይነት ተተንትኖና ተሰንዶ፣ በመጪዎቹ አሥር ቀናት ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ተስፋዬ አክለው አስረድተዋል፡፡
በተጀመረው የዳሰሳ ጥናት የሥራ ኃላፊዎች ለባለሙያዎቹ ትብብር እንዲያደርጉ የተጠየቀ ሲሆን፣ ጥናቱ በየተቋማቱ ያሉ የበላይ አመራሮችን፣ የሕግ፣ የግዥ፣ የአይሲቲ፣ የኦዲት፣ የሥነ ምግባር፣ የሰው ኃይል፣ የቅሬታ ሰሚና ተያያዥ የሥራ ክፍሎችን በመዳሰስ የሚከናወን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሙስና ሥጋት ጥናቱ በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ የሙስና ሥጋት ችግር ሊሆኑ የሚችሉ አሠራርና አደረጃጀቶችን በመለየት፣ በቀጣይ ተቋማቱ ያሉበት ሁኔታ ታይቶ መንግሥት የተቋማቱን አደረጃጀት ሊለውጥበት፣ አሠራር ሊቀይርበት ወይም መመርያ ማስተካካል ካለበትም እንዲስተካከልና ተቋማቱ የሙስና መከላከል ዕቅድ እንዲያወጡ የሚረዳ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በዓይነቱ የመጀመርያ ያለውን ይህን ጥናት አጠናቆ ለፓርላማውና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ የሚገኘው ውጤት ተቋማቱ የሙስና ቅነሳ ስትራቴጂ እንዲያዘጋጁና እንዲተገብሩ ከማድረግ በተጨማሪ፣ የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን፣ የሙስና መከላከል ጥናት ለማካሄድ፣ የጥቅም ግጭት ለመከላከልና ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ለማወቅ የሚደረጉ ሥራዎችን ለማከናወን የመረጃ ምንጩ የሚያገልግል ይሆናል፡፡
በተጀመረው የዳሰሳ ጥናት በተቋማት ደስተኛ ላይሆኑ የሚችሉ የሥራ ኃላፊዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ ጅምሩ እንደ አገር የሚታየውን የሙስና ችግር ለመፍታት በየጊዜው ኮሚቴ ማቋቋሙ አዋጭ ስለማይሆን፣ አገራዊ የሆነውን ይህን ችግር ከሥረ መሠረቱ የመከላከል ሥራ ላይ ማተኮር ይበጃል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ጥናት ለማካሄድ ዘጠኝ አባላት ያሉት የፀረ ሙስና የጥናት ኮሚቴዎች በሥሩ ያደራጀው የባለሙያዎች የጥናት ቡድን የተቋማት መመርያ፣ አሠራር፣ ሕግ፣ አደረጃጀትና መሰል የተያያዙ ጉዳዮች ይዳሰሱበታል ተብሏል፡፡
የሚከናወነው ዳሰሳ የተቋማትን የ2013 እና 2014 ዓ.ም. መረጃ መሠረት በማድረግ የሚከናወን መሆኑን፣ ባለሙያዎች በሚሄዱባቸው ተቋማት የማይተባበሩ የሥራ ኃላፊዎች የሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡