Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበማኅበር ለተደራጁ የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች 31 ሔክታር መሬት...

በማኅበር ለተደራጁ የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች 31 ሔክታር መሬት ተዘጋጀላቸው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ለሚጠባበቁ የማኅበራት ቤት ተመዝጋቢዎች፣ በሦስት ክፍላተ ከተሞች 31 ሔክታር መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. መቆጠባቸውን ያላቋረጡ የ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና የ40/60 የቤት ልማት ተመዝጋቢዎች በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንዲችሉ፣ የምዝገባና በቡድን የመደልደል ሥራ ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል፡፡

መጀመሪያ የነበሩትን ከ12 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ታሳቢ በማድረግ ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ 52 ሔክታር መሬት ተዘጋጅቶ እንደነበርና አሁን ላሉት 4,518 ተመዝጋቢዎች ግንባታ የሚሆን 31 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን፣ በቢሮው የቤት ልማትና ፋይናንስ አቅርቦት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ በቂ የሆነ መሬት ስላለ ተመዝጋቢዎችን በማኅበር ማደራጀቱ እንደተጠናቀቀ፣ በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት እንደሚቻል ኃላፊው አክለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ማሳያ በማኅበር የጋራ መኖሪያ ቤት የመገንባት ፕሮጀክት በሦስት ክፍላተ ከተሞች ላይ የሚተገበር መሆኑን፣ እነሱም አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ቆልፌ ቀራንዮ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በተጠቀሱት ክፍላተ ከተሞች የመሬት ዝግጅት እንደተደረገ ያስረዱት አቶ ጳውሎስ፣ በተዘጋጁት ቦታዎች ለማኅበራት የሚሆን ቦታ እየተሸነሸነ መሆኑንና በቀጣይ በዕጣ እንደሚተላለፍ አስረድተዋል፡፡

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የክፍላተ ከተማና የወረዳ መሬት መዋቅሮች ከመሬት ጋር ያለውን ጉዳይ እንዲከታተሉ ደብዳቤ ከመጻፍ ባሻገር፣ የሰው ኃይል እንደመደበ ፕሮጀክቱን ቶሎ ወደ ሥራ የማስገባት እንጂ ቦታው የተዘጋጀና ካርታ የወጣለት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም 12,611 ተመዝጋቢዎች በኦንላይን ተመዝገው እንደነበርና የመሬት፣ የዲዛይንና ሌሎች ዝግጅቶችም በዚሁ መሠረት ሲዘጋጅ ቆይተዋል ብሏል፡፡ ሆኖም ተመዝጋቢዎች በአካል ቀርበው በሚኖሩበት ክፍለ ከተማና ወረዳ መኖሪያ ቤት እንደሌላቸው ማረጋገጥ እንደሚገባቸው በቀረበው ጥሪ መሠረት ቀርበው ያረጋገጡ 4,518 እንደነበሩ አስታውሶ፣ ለተጠባባቂና ለጎደሉ ተመዝጋቢዎች ተጨማሪ ቀናት ተሰጥቶ ሲመዘግብ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በ57 ቡድን በመደልደል በ14ኛው ዙር የ20/80 እና በሦስተኛው ዙር የ40/60 ዕጣ የደረሳቸውና በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ ተመዝጋቢዎችን የማሟላትና ተጠባባቂዎችን የመለየት ሥራ ማከናወኑ ተገልጾ፣ ተመዝጋቢዎች በቡድን በመሆን ሕጋዊ ዕውቅና አግኝተው በቅርቡ መደራጀት እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል፡፡

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ተመዝጋቢዎች ቤት እንደሌላቸውና ሌሎች መሥፈርቶችን ከክፍላተ ከተማ የተገኙ መረጃዎችን በማጠናቀር ለማኅበራት ማደራጃ የላከ መሆኑን፣ ቢሮው ከማኅበራት ማደራጃ ጋር በነበረው የጋራ ግምገማ ተመዝጋቢዎች ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት ተግዳሮት እንዳይገጥማቸው በቂ ገለጻ እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የማብራሪያ መድረኮች እንደነበሩ፣ በቀጣይ በሚኖሩ መድረኮች በ57 ቡድን የተደለደሉት ተመዝጋቢዎች መግባባት ላይ በመድረስ ምክትል ሰብሳቢና ጸሐፊ ከተመረጡ በኋላ ተደራጅተው ወደ ሥራ የሚገቡበትን አሠራር በቀጣዮቹ ሳምንቶች እንደሚከናወን አቶ ጳውሎስ ተናግረዋል፡፡

የማኅበር ቤት አማራጭ ሲተገበር 70 በመቶ በቅድሚያ ክፍያ፣ 30 በመቶ በባንኮች አማካይነት ተመቻችቶ ነው፡፡ ከባንኮቹ ጋር የሚደረገው ዝግጀት ከተጠናቀቀ የቆየ ቢሆንም፣ የመሬት ዝግጀቱ ቶሎ አለመጠናቀቁ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤት ልማት ትግበራና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትልና ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አስታውቀው ነበር፡፡  

አቶ ጳውሎስ እንዳስረዱት፣ በተያዘው ዓመት ሁለተኛ ዙር በማኅበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት የሚገነቡ ተመዝጋቢዎችን የመመዝገብ ሥራ  ይኖራል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ምዝገባ በተለያዩ ሁኔታ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት እነዚህም ከአሠራር፣ ከመመርያ ዝግጅትና ከተቋማት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ማኅበራት እንደሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤት ዲዛይንና አቀማመጥ (ቶፖሎጂ) ከ63 እስከ 104 አባላት ያላቸው ሆነው የሚደራጁ ሲሆን፣ የግንባታ ቦታዎቹም የተወሰኑት በተመዝጋቢዎች ፍላጎት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የቅድመ ዝግጅት ሥራ ለረዥም ጊዜ ሲሠራ መቆየቱንና ወደ ትግበራ ለመግባት ጫፍ ላይ እንደተደረሰ፣ ከማኅበራት ማደራጃ ቶሎ ተመዝጋቢዎቹን ማኅበር አድርጎና ፈቃድ ሰጥቶ ሲጨርስ የዕጣ ማውጣትና የትግበራ ሥራ በአጭር ጊዜ እንደሚከናወን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...