Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት ከፍ ማለቱን ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጥር ወር የነበሩ በዓላት ወርኃዊ የዋጋ ግሽበቱን ቀደም ሲል ከነበረበት አኃዝ ከፍ ብሎ እንዲመዘገብ ማድረጋቸውን፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በሸማቾች መመዘኛ ሪፖርቱ አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ይፋ ያደረገው የጥር ወር የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በጥር 2015 ዓ.ም. በነበሩ ሁለት ታላላቅ የሃይማኖት በዓላት ምክንያት የምግብ የኢንዴክሱ ዋጋ ግሽበት በመጠኑ ጨምሯል፡፡

የዋጋ ግሽበት ብዙ ጊዜ ከሚባባስባቸው አንዱና ዋናው ምክንያት በዓላት መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ በዓላትን ተከትለው የሚመጡ የዋጋ ጭማሪዎች በተለይም የምግብ ዋጋ ግሽበትን ከፍ እንደሚያደርጉት ያስረዳሉ፡፡

አብዛኞቹ እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ሥጋ፣ ወተት፣ ዓይብና ዕንቁላል በጥር ወር መጠነኛ ጭማሪ ከማሳየታቸው በተጨማሪ፣ ምግብ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች  ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ በተመሳሳይ ጭማሪ መታየቱን በአገልግሎቱ ሪፖርት ተገልጿል፡፡

የጥር 2015 ዓ.ም. የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 33.6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች ከቀደመው ወር ጋራ ሲነፃፀር በ1.4 ነጥብ በመቶ ጭማሪ መመዝገቡ ታውቋል፡፡

የስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው፣ በጥር ወር 2015 ዓ.ም. በአንዳንድ እህሎች ማለትም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡ በሌላ በኩል ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ከውጭ የሚገባው የምግብ ዘይት፣ ቡናና ለስላሳ መጠጦች ላይ መጠነኛ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥር 2014 ዓ.ም. አንስቶ ከሰላሳ ቤቶች ውስጥ ዝቅ አለማለቱን ሪፖርተር የተመለከተው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ገላጭ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በጥር 2015 ዓ.ም. ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.9 ከመቶ የተመዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ወር የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.8 ከመቶ ተመዝግቦ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የምግብ ክፍሎች ዋጋ ግሽበቱ ከታኅሳስ ወር ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ1.4 ነጥብ በመቶ ጭማሪ መመዝገቡ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ34.4 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም ልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች (ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ ነዳጅ፣ ሕክምና፣ የትምህርት መሣሪያዎችና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የነበረው የዋጋ ለውጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ የዋጋ ንረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁንም የሸማቾች መሠረታዊ ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍላጎትን ያገናዘበ በቂ ምርት ኖረም አልኖረም በዘፈቀደ በምርቶችና በሸቀጦች ላይ የሚጫን ዋጋ ገበያው እንዳይረጋጋ አድርጎታል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ባለሙያዎች አክለውም ገበያን አገናዝቦ ዋጋ ለመስጠት የሚሻ እንደሌለ፣ የተትረፈረፈ ምርት ቢኖር እንኳን ከነበረው ዋጋ ቀንሶ ለመሸጥ ያልተለመደ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል ይላሉ፡፡ 

ከበዓል ማግሥት በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው ዋጋ እያንሰራራ እንደሚገኝ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሸማቾች ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ከበዓላት አስቀድሞ በሃምሳዎቹ ውስጥ ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ጤፍ በአሁኑ ጊዜ ከ70 እስከ 75 ብር፣ ስንዴ ደግሞ 60 ብርና ከዚያ በላይ ዋጋ እየተቆረጠለት መሆኑን ሸማቾች አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ስኳር ቀድሞ ከነበረበት በኪሎ 40 ብር ዋጋ አሁን 54 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ፣ በደረቅና በፈሳሽ ሳሙና ላይ ከአሥር ብር እስከ መቶ ብር የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ሸማቾች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች