ለሕግ የበላይነት መከበር እሠራለሁ ከሚል አንድ የመንግሥትና አስተዳደር ሥርዓት ቀዳሚ መርሆች መካከል በሕግ አውጪው፣ በሕግ አስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው መካከል የሚኖር ግልጽ የሆነና መስመሩን የለየ የሥልጣን ክፍፍል መኖር ወሳኝና ቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ አሠራር ባለሥልጣናት በሕጉ መሠረት እንዲሠሩ ከመገደብ ባለፈ ሥልጣን የሕግ ልጓም እንዲኖረውና የእነሱ የመወሰን ሥልጣን በሕግ በማጥበብ፣ ያላግባባ በሥልጣን የመጠቀምን አሠራር በእጅጉ የሚገደብና በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል አንዱ ሌላውን በሕግ አግባብ ተጠያቂ የሚደርግበት የክትትልና ቁጥጥር አሠራር እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡
ስለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 የፓርላማ አባላት ተገዥነታቸው ለሕዝቡ፣ ለሕገ መንግሥትና ለህሊናቸው መሆኑን ያብራራል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት እንደማይከሰስና አስተዳደራዊ ዕርምጃም እንደማይወሰድበት ይገልጻል፡፡
የፓርላማ አባላት የአስፈጻሚ አካል ላይ ከሚኖራቸው የተቆጣጣሪነትና የጠያቂነት ሥልጣን ባለፈ፣ በመንግሥት አካላት መካካል እንዲኖር የሚጠበቀው የተጠያቂነት ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ በምትከተለው የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ውስጥ በቀደመው ጊዜም ይሁን በአሁኑ የብልፅግና ፓርቲ፣ በፓርላማው የገነነ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የተነሳ ለፓርቲ ዕሳቤ በሚደረግ ተገዥነት፣ በሕግ አውጭውና በአስፈጻሚው መካከል የሚታየውን የተጠያቂነት (Check and Balance)፣ እንዲሁም በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ነፃነት (Independence) ጥያቄ ውስጥ የከተተ ጉዳይ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡
በቅርቡ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ስብሰባ፣ አንድ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹የሕዝብ ውክልና ሥራ ስናከናውን የመረጠንንም ያልመረጠንንም ማካተትና ማገልገል እንዳለብን ግልጽ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ የሚታየው ክፍተት የጎላ ነው፡፡ እኔ እንደ አዲስ አበባ ተወላጅ በከፍተኛ ቁጥር ስመረጥ ምንም ቢሆን ፍትሐዊ ሆና ድምፃችን ታሰማለች በሚል ብዙ የሠፈሬ ልጆች በምርጫው ተሳትፈዋል፤›› በማለት ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን የማይመጥን መልስ በመስጠታቸው፣ በርካቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልተገባ መልስ ሰጥተዋል በማለት ወቀሳ አቅርበው ነበር፡፡
በወቅቱ ከፓርላማ አባሏ ለተነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኔ የአዲስ ሕዝብ መርጦኝ የሠፈሬ ልጆች አግዘውኝ ያሉት ስህተት ነው፡፡ እርስዎን የመረጠም ያገዘም የለም፡፡ ሕዝቡ የመረጠው ብልፅግናን ነው፡፡ እርስዎን ማን ያውቅዎታል? ብልፅግና ነው እንደ ፓርቲ የተወዳደረው እንጂ፣ ግለሰቦች በግል ውድድር አይደለም የገባነው፤›› የሚል ነበር፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ሞገስ ደምሰው (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በመርህ ደረጃ በተለይ የፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈጻሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳለው ከብዙ አገሮች ተሞክሮ ልምድ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ይህን አሠራር በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም ፓርላማው ራሱ አድጓል ወይም ተለውጧል? ምን ያህል አቅም አዳብሯል? ሲባል ለዓመታት በተግባር እዚህ ግባ የሚባል አቅም ባለመፍጠሩ አስፈጻሚ አካሉን የመቆጣጠር አቅም አላካበተም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የሕግ አውጭውና የሕግ አስፈጻሚው ውክልናዎች የተያዙት በአንድ ፓርቲ የበላይነት በተያዘው መንግሥት በመሆኑ ሁለቱም ሊያራምዱት የሚችሉት ርዕዮተ ዓለም፣ የሚይዙት አቋምና አመለካከት ተመሳሳይ ሰለሆነ፣ በዚህ ሒደት አንዱ ሌላኛውን ይደግፋል እንጂ ቁጥጥር ውስጥ ይገባሉ ማለት ከባድ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ይህ የቁጥጥር ሥርዓት የሚተገበረው ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወይም ተገዳዳሪና ተመጣጣኝ የፖለቲካ ኃይል ባላቸው አገሮች በመሆኑ፣ በአንድ ፓርቲ የበላይነት በተያዘ ፓርላማ ላይ ቁጥጥር መዘርጋት ማለት፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ላድርገው ብትል ብልፅግናን ብልፅግና ተቆጣጠረው ማለት በመሆኑ በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› ብለው፣ በዚህም የተነሳ ሁለቱም ተመሳሳይ አመለካከት የሚያራምዱ መሆናቸው ከአቅም ማነስ ጋር ተዳምሮ፣ አስፈጻሚውን ገፍቶ በመሄድ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
የፖለቲካ ሥርዓታቸው አድጓል በሚባሉ አገሮች የፓርቲ አባላት በትክክለኛው የፖለቲካ ዕውቀትና አስተሳሰብ የተገነቡ በመሆናቸው፣ ለፓርቲው ታማኝ ቢሆኑም እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ለምክንያታዊ ሐሳብና ለሕዝብ ብቻ መሆኑን ሞገስ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡
የፖለቲካ ክትትልና ቁጥጥር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባላደጉ አሮች ለመተግበር ጠንካራ የፖለቲካ ባህል መገንባት አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚናገሩት ምሁሩ፣ የአንድ ፓርቲ አባል ሆኖ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ማራመድ መቻል የፖለቲካ ዕድገት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ፓርቲ አባል ሆኖ የተለያዩ አቋሞችን መከተል የሚያስከትለው ዕርምጃ ጠንካራ መሆኑን፣ ከላይኛው መዋቅር አንድ አቋም ሲመጣ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያንን ነገር ካላስተገበረ መዘዙ ከፍ ሊል እንደሚችል፣ ይህ ደግሞ ከአገሪቱ የፖለቲካ ዕድገት ጋር የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ለውጥ በረዥም ጊዜ ሒደት የሚመጣ መሆኑን የገለጹት ሞገስ (ዶ/ር)፣ በዋነኝነት ጠንካራና ተገዳዳሪ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢደራጁ፣ በዚው ልክ አባላትን ቢያንቀሳቅሱ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱና ተከታዮቻቸውን በሆነ ባልሆነው የሚከፋፍሉ ሳይሆኑ ወደ አንድነት ማምጣት የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሒደት እየተፈጠሩ ቢሄዱ፣ ጠንካራና ተገዳዳሪ ፓርላማ ተፈጥሮ አስፈጻሚውን ለመጠየቅና ለመቆጣጠር አዳጋች እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህ ዓይነቱ ፓርላማ ሲመሠረት ደግሞ በርካታ የሕዝብ ድምፆች ይንፀባረቃሉ፡፡ ፓርላማውን አስፈጻሚውም የመቆጣጠር አቅሙ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ፓርላማው በተለያዩ ፓርቲዎች ካልተያዘና አስፈጻሚና ፓርላማው ጋብቻ ካልፈጠሩ እርስ በርሳቸው የመቆጣጠርና የመጠያየቅ ሥርዓት ይፈጥራሉ፣ ተጠያቂነትም እየሰፋ ይሄዳል፤›› ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአንድ አገር ውስጥ ትክክለኛ የመንግሥት አሠራር አለ የሚባለው ሦስቱ የመንግሥት አካላት ገለልተኛ በመሆን አንዱ በአንዱ ላይ ጣልቃ ሳይገባ ክትትልና ቁጥጥር ሲኖር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጥሩ የፖለቲካ ሥራ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገር ሲታይ ሦስቱም ገለልተኛነታቸውን አልጠበቁም፡፡ ፓርላማውም የተሰጠውን ሥልጣን እየተወጣ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ እንዲያውም በተገላቢጦሽ ሥራ አስፈጻሚው ፓርላማውን እያዘዘና አስፈጻሚው በሕግ ተርጓሚው ላይ ጣልቃ ለመግባትና ለመቆጣጠር እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከጅምሩ ሕገ መንግሥቱ ለፓርላማ ትልቅ ሥልጣን ቢሰጠውም የተሰጠውን የመቆጣጠርና የመጠየቅ፣ ባለሥልጣናትን የማውረድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመጥራትና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሥልጣን የማውረድ ሥልጣን እየተጠቀመበት ነው ወይ ሲባል አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹ስለዚህ በመንግሥት አካላት መካከል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በወረቀት እንጂ በተግባር አልተጀመረም፤›› የሚሉት መብራቱ (ዶ.ር)፣ ይህ ሊሆን የቻለው አገሪቱን እየመራ ባለው የፓርቲ አሠራር ምክንያት ማለትም አብዛኛው ሥራ አስፈጻሚውን የሚሾመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲው በላይ በመሆኑ፣ ገለልተኛ ተብለው የሚታሰቡ ተቋማት ኃላፊዎች በፓርላማው ይሾማሉ ተብሎ ተቀመጠ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርጦ ለምክር ቤቱ ለአሠራሩ ብቻ በመላኩ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በእዲህ ዓይነት ሥርዓት ውስጥ ፓርላማው ራሱን ችሎ ይንቀሳቀሳል ማለት እንደማይቻል የተናገሩት መብራቱ (ዶ/ር)፣ በሌላ በኩል የክልል የፀረ ሙስና ኃላፊዎች ተጠሪነት ለክልል ፕሬዚዳንት መሆኑን፣ በዚህ አሠራር ፕሬዚዳንቱ ሙስና ቢፈጽምና ይህ የፀረ ሙስና ኃላፊ በፕሬዚዳንቱ ላይ ላጣራ ብሎ ቢጀምር ወዲያውኑ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ሊያነሳው እንደሚችል ምሳሌ አጣቅሰዋል፡፡
ተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ያሉበት የደቡብ አፍሪካ ፓርላማን የጠቀሱት የጋራ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ፕሬዚዳንት የራሳቸው ፓርቲ አባላት በተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርቡባቸው መታየቱን ተናግረዋል፡፡ ይህን በማየት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ፣ ፓርላማው ማብራሪያ ሲፈልግ በጠራቸው ጊዜ ሁሉ ቀርበው የተጠየቁትን መመለስ እንደሚጠበቅባቸው አሰረድተዋል፡፡
‹‹ይሁን አንጂ በቅርቡ በፓርላማ እንዳየነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገላቢጦሽ ነው የቀረቡት፡፡ እኔም እንደ አንድ ፖለቲከኛ ይህ አሠራር አልተመቸኝም፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተቋማትን ኦዲት አድርጎ ብዙ ችግር አለባቸው በማለት ክስ ያቀረበባቸው ተቋማት፣ በኦዲት ግኝቱ መሠረት ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም የሚሉት መብራቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጉዳዩ ሁሌ ይወራል፣ በቴሌቪዥን ይተላለፋል፣ እንፈጽማለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሲፈጸም ዓይተነው አናውቅም፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የምክር ቤት አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በምክር ቤቱ የአሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት በቋሚ ኮሚቴ አማካይነት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንዲሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴዎቹ ወደ እዚህ ሥራ ሲገቡ ስለሚገመግሙት ተቋም ሙሉ መረጃ ይዘው አስፈላጊውን ግምገማ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚታዩ እጥረቶች ቢኖሩም ከቀደመው የኢሕአዴግ ሥርዓት ጋር ሲነፃፀር ግን አሁን ለማሻሻል ጥረቶች ስለመኖራቸው አስረድተዋል፡፡
የማይካዱ ክፍተቶች ስለመኖራቸው የሚናገሩት አብርሃም (ዶ/ር)፣ ለአብነት እንኳ የተለያዩ ሚኒስትሮች በዚህ ዓመት በቀደመው ዓመት ያቀረቡትን አፈጻጸም ደግመው ሪፖርት ሲያቀረቡ እንዳስተዋሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፓርላማው በተግባር የታየውና እስካሁን የሚነሳው ችግር ምክር ቤቱ አንድ ሚኒስትር ጥፋት አጥፍቷል፣ አልቻለም፡፡ በሙስና ተዘፍቋል፣ የተበጀተለትን በጀት በአግባቡ አልተጠቀመም በሚል ከሥልጣን የተነሳ ወይም የተፈረደበት አካል ወይም ባለሥልጣን አለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ከሥልጣን ማንሳት ወይም እንዲቀጣ ማድረግ የግድ መሆን ያለበት ባይሆንም፣ በገሃድ የሚታዩ ችግሮች ለአብነት እንደ ኑሮ ውድነትና የሙስና መባባስ ከጅምሩ ተቋምን በአግባቡ ባለመምራት የተፈጠሩ ክፍተቶች በመሆናቸው፣ ይህ ክፍተት ደግሞ ከጅምሩ ብቃት ያላቸው አመራሮች ባለመሾማቸው እንደሆነና ምክንያቱም ይህ የአስፈጻሚ አካል ሲሾም ብቃት እንጂ ሌላ መለኪያ መሥፈርት ሊመጣ አይገባም ብለዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሒደት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በትክክል ቦታ ያልተቀመጡ አመራሮችንና በአፈጻጸማቸው የወደቁትን ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በሙስና የተዘፈቀ ከሆነ መነሳት ካለበት መነሳት አለበት፣ ይህ ርስት አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ግን ገዥው ፓርቲ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለበት የገለጹት አብርሃም (ዶ/ር)፣ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይሁን ሌላ ሚኒስትር በመጥራት ማብራሪያ ሊጠይቅ እንደሚችልና ይህም መለመድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በጉዳዩ ዙሪያ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ማውጣት፣ የአስፈጻሚውን ሥራ መከታተልና መቆጣጠር፣ የውክልና ሥራ መሥራትና የፓርላማ ዲፕሎማሲን መሠረት አድርጎ የሚሠራ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፓርላማው አስፈጻሚውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በምክር ቤቱ ውስጥ በተደራጁ 13 ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት በየዘርፉ ያሉትን ሥራዎች የመቆጣጠርና የመከታል ሥራ የሚሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ አሁን ምክር ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ራሱን ችሎ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
የቁጥጥርና የክትትል ሥራውን ጠንካራ ለማድረግ በምክር ቤቱ ያሉ አራት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ ስለመደረጉም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቶች በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ ማለት ማንኛውንም ሐሳብ መደገፍ ወይም መቃወም ሳይሆን፣ ሁሉም በተሰጣቸው ሥልጣን ልክ ምክንያታዊ ሆኖ መደገፍና መቃወም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህ ሥርዓት የመገንባትና ለውጥ የማምጣት ሒደት በመሆኑ በቀጣይ እያደገ እየጎለበት ይሄዳል እንጂ፣ ፍፁም የሚባል ሥራ የለም፡፡ ነገር ግን ከለውጥ በኋላ የተጀመረው ጅምር በጣም ጠንካራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ በሕግና በሕግ ብቻ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሆነ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ የዚህ ዓላማም ነገ አንድ ነገር ቢፈጠር ምክር ቤቱ ከዜሮ የሚጀምር ሆኖ መቀጠል ስለሌበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹የፓርላሜንታዊ ሥርዓት በሚገነቡ አገሮች ወሳኙ ፓርቲው ነው፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ መጀመሪያውኑ ተወዳዳሪዎች ብልፅግናን ወክለው ሕዝቡ ዘንድ ቀርበው ምረጡኝ ሲሉ ብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ አቅርቧል፡፡ ስለዚህ ብልፅግናን የምትመርጡ ከሆነ የብልፅግና ተወካይ እኔ ነኝ፣ እኔን ከመረጣችሁ ይህን ለማስፈጸም እሠራለሁ ብሎ የሚመረጥ መሆኑን ተናግረዋል፡
ስለዚህ ፓርቲን ወክለው የተመረጡና ምክር ቤት የገቡ አባላት ፓርቲዎች የነደፏቸውን የፓርቲ ማኒፌስቶ ዓይቶ ሕዝቡ የመረጣቸው በመሆኑ፣ በዚህ አካሄድ ፓርላማው ውስጥ የገባው አባል ሊያደርግ የሚችለው ማኒፌስቶ ላይ በተቀመጠው መሠረት ጉዳዩ እየተፈጸመ ነው ወይ የሚለውን መቆጣጠርና መከታተል እንጂ፣ ጭልጥ ያለ የግልና የተወሰነ ቡድንን ፍላጎት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ፓርላማው ላይ ያንፀባርቃል ከተባለ ይህ ሌላ ጉዳይ ነው የሚሆነው ማለት ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡