- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲካውን የምንመራበት መንገድ ትክክል አልመሰለኝም፣ መንገድ እየሳትን ነው።
- እንዴት፣ ለምን እንስታለን?
- ምክንያቱም ከሁሉም ጋር እየተጋጨን ነው። ሥልጣን ስንይዝ የነበረን የማኅበረሰብ ድጋፍ ተሸርሽሮ እያለቀ ነው።
- አይምሰልህ። አሁንም ድጋፋችን እንዳለ ነው!
- ክቡር ሚኒስትር፣ ከማኅበረሰባችን ምን ያህል እየተለየን እንደመጣን ላስረዳዎት እችላለሁ።
- እሺ ቀጥል።
- በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ማኅበረሰብ ጋር ተለያይተናል።
- እሱ በእኛ ምክንያት የመጣ አይደለም።
- በምንም ምክንያት ይምጣ አሁን ላይ ግን ከዚህ ማኅበረሰብ ተለይተናል። በቀላሉም የምንመልሰው አይደለም።
- ሊሆን ይችላል።
- በኦሮሚያ ሸኔ አሁንም ሊለቀን አልቻለም። በበርካታ አካባቢዎች መዋቅራችንን እያፈረሰ ከማኅበረሰቡ እየነጠለን ነው።
- የኦሮሚያ ችግር የለውም፣ ይስተካከላል።
- እርሶ እንዳሉት በቀላሉ የምንመልሰው ከሆነ ጥሩ ነገር ግን ከማኅበረሰቡ እየተነጠልን መሆኑ ግን ሐቅ ነው። በሌላ በኩል
- በሌላ በኩል… ምን?
- በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የነበረውን ችግር መፍታት ብንችልም አሁንም በእኛ ላይ ያለው ጥርጣሬ አልተቀረፈም።
- ኃይማኖትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ድጋፍ ለእኛ አይጠቅመንም።
- እንደዚያ ዓይነት ሥርዓት ገንብተን ቢሆን ጥሩ። ነገር ግን እውነቱ እንደዚያ አይደለም።
- እውነቱ ምንድነው?
- ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በእኛ ላይ ያመጣውን አደጋ ብቻ መመልከት በቂ ነው።
- ምን አደጋ አመጣብን?
- ክቡር ሚኒስትር የእውነት ሳይገባዎት ቀርቶ ነው?
- ከገባኝ ለምን እጠይቃለሁ?
- አይመስለኝም። ለማንኛውም ሰሞኑን በተፈጠረው ችግርና ከእኛ በኩል ስለጉዳዩ በተሰጠው መግለጫ ምክንያት የቀረንን ማኅበራዊ መሠረት የማጣት አደጋ ደቅኖብናል።
- ከየትኛው ማኅበራዊ መሠረታችን?
- በአማራ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሚገኘው ማኅበረሰብ ብቻ ነበር የቀረን፣ አሁን ግን ይህንንም የማጣት ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡
- ለምን? ከዚህ ማኅበረሰብ ጋር ምን ያጣላናል?
- መንግሥት ሃይማኖቴን ሊንድ እጁን አስገብቷል ብሎ አምኗል። በዚህ ምክንያት በአንድ ጊዜ የዚህን ማኅበረሰብ ድጋፍ የማጣት አደጋ ውስጥ ገብተናል።
- መንግሥት ግን እጁን አላስገባም?
- ማኅበረሰቡ ግን መንግሥት እጁ እንዳለበት አምኗል።
- ታዲያ ስህተት መሆኑን ለምን አታስረዱም?
- ሞክረናል። ነገር ግን የሃይማኖቱን ተከታይ ይቅርና የእኛኑ ፓርቲ አባሎች እንኳ ማሳመን አልቻልንም።
- ችግር የለውም። የአንዱ መሄድ ሌላውን መልሶ ያመጣል።
- እንዴት?
- የዚህን መሄድ ተከትሎ በተቃራኒ የቆመ ሌላው ማኅበረሰብ ወደ እኛ ይመለሳል።
- ክቡር ሚኒስትር ሥልጣን የያዝነው እኮ በተቃርኖ ለመምራት አይደለም። ከምንከተለው መርህም ተቃራኒ ነው።
- የትኛው መርህ?
- ‹‹መደመር››!
- አሁንም በ‹‹መደመር›› መርህ ነው እየመራን ያለነው።
- ከሁሉም የፖለቲካ ማኅበረሰብ እየተጋጨን? እንዴት ያለ መደመር ነው ይኼ?
- የመደመርን መርህ አልገባህም ማለት ነው።
- እንዴት?
- የእኛ ‹‹መደመር›› ከሒሳባዊው የመደመር ቀመር የተለየ ነው።
- እንዴት? ምን ይለየዋል?
- በእኛ ‹‹መደመር›› ውስጥ መደመር ብቻ አይደለም ያለው።
- ሌላ ምን አለ?
- መቀነስም አለ።
- እ…?
- መቀነስ ብቻ ሳይሆን ማካፈልም፣ ማባዛትም አሉ።
- ክቡር ሚኒስትር እርሶ ሌላ ዓለም ላይ ያሉ ነው የሚመስለው።
- እንዴት?
- አገሪቱ በግጭቶች ውስጥ እየተናጠችና የችግሩን ጥልቀት ያስተዋሉ አልመሰለኝም፡፡
- ችግሮቹን እኛ አልፈጠርናቸውም።
- እና ከየት መጡ?
- በውርስ።
- ምን አሉ?
- የወርሰናቸው ችግሮች ናቸው!
- ወደ ሥልጣን ላይ የመጣነው ችግሮችን ለመፍታት እንጂ ባለቤት ለማበጀት አይደለም። ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት አለብን።
- ትክክል ነው። ሥጋትህ ይገባኛል።
- ታዲያ?
- አንድ ነገር አረጋግጥልኃለው!
- ምን?
- ኢትዮጵያ አትፈርስም!
- መጀመሪያ እኛን ነው የሚያፈርሰው፣ ከጥሎ ደግሞ ተቋም ይፈርሳል። ከዚያ በኋላ…
- ከዚያ በኋላ ምን?
- ከዚያማ እርሶም በዚህ ሥልጣን ላይ መቀጠል አይችሉም።
- ለምን አልችልም?
- አይሆንማ! እንዴት ሆኖ?
- አለኝ እኮ፣ ገና ይቀረኛል።
- ምን?
- የአገልግሎት ዘመን!
[ሚኒስትሩ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ‹‹ገና ይቀረኛል›› እያሉ ያወራሉ፣ በሁኔታው የደነገጡት ባለቤታቸው ሚኒስትሩን ቀሰቀሷቸው]
- እስኪ በስመ አብ በል? ምንድነው እንዲህ ያስጨነቀህ?
- እ… አይ ጭንቀት አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው? ፊትህ ሁሉ ተለዋውጦ ስትጮኽና ስታወራ ነበር እኮ?
- ብዙ አወራሁ እንዴ? ምን እንዳልኩ ሰምተሻል?
- አልገባኝም እንጂ ደጋግመህ ‹‹ይቀረኛል›› ምናምን ስትል ነበር።
- ይቀረኛል ብቻ ነው ያልኩት?
- ‹‹ይቀረኛል›› እና ሌሎችም የማይሰሙ ነገሮችን ስትል ነበር።
- ይህን ብቻ ነው የሰማሽው?
- በዚያኛው ጫፍ የሚያዋራህ አልተሰማኝም።
- እስኪ አትቀልጂ…?
- ግን ማነው?
- ምኑ?
- እንዲህ ያስጨነቀህ? ማለቴ ጉዳዩ ምንድነው?
- ቅዠት እኮ ነው።
- በእውንህም ይህንን ነገር ስትል ሰምቼ አውቃለሁ።
- መቼ? ምን ስል?
- ሰሞኑን በነበሩህ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ይቀረኛል… ሦስት ዓመት አለኝ ስትል በቲቪ ሰምቻለሁ። ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው?
- በጭራሽ አይደለም።
- ታዲያ ከማን ጋር ነው?
- ከአንድ የውጭ አገር ባለሥልጣን ጋር እየተከራከርኩ ነበር። አዎ እንደዚያ ነው።
- በአማርኛ?
- እሱም በአማርኛ ነበር ያወራኝ የነበረው… እንደዚያ መሰለኝ።
- ወይ አስተርጓሚም ይዞ ይሆናል።
- ቅዠት ነው አልኩሽ ኦኮ። ይልቅ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ
- እሺ… እንደው ግን እንዲህ ከምትጨነቅ ብትተወውስ?
- ምኑን?
- ይቀረኛል ያልከውን?
- በፍጹም። ‹‹ይቀረኛል!››