Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእንቅስቃሴና የኢንተርኔት ዕቀባ በኢ-ኮሜርስና በፈጣን መልዕክት አገልግሎቶች ላይ የፈጠረው ዕክል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ዕቀባን ተከትሎ ከተነቃቁ የሥራ መስኮች ውስጥ የፈጣን መልዕክትና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎት (የዴሊቨሪ ቢዝነስ) ተጠቃሹ ነው፡፡ በአገልግሎቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የበሰሉ ምግቦችን ጨምሮ ሌሎች የምግብ ሸቀጦችና ቁሳቁሶንችንም ማድረስ ዛሬ ላይ እየተለመደ ሳይሆን እየተዘወተረም መጥቷል፡፡ 

ምንም እንኳን አገሪቱ ላይ የሚገኙት የፈጣን መልዕክትና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎት አቅራቢዎች ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ካለው ጋር ሲነፃፃር ገና መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ቢኖሩም፣ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲመሳከር በተለይም ምግቦችን የማድረስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር እንዳሻቀበ፣ በዘርፉም የሚሰጡ የአገልግሎት ዓይነቶች እየተበራከቱ መሆኑን ተጠቃሚዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ለአንድ አገር ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎቱ ይበልጥ እንዲዘምንና እንዲስፋፋ የተለያዩ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱን ለመስጠት ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶች እንዲሁም ማኅበራት ጋር በቅርበት መሥራት እንዲሁም ምቹ ፖሊሲዎችና መመርያዎች እንዲዘጋጁ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ በዘርፉ ውስጥ የሚሰሩ አካላት ይናገራሉ፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ ክብረ በዓሎችና እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሞተር ብስክሌቶች እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ መገደቡ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራራጥ በተለይም እየተፍጨረጨረ ባለው የፈጣን መልዕክትና አገልግሎት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን የዘርፉ ተዋንያን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

ለአብነትም በመዲናዋ የሚካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ምክንያት በማድረግ ከየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ሞተር ብስክሌትና ባጃጅ ተሽከርካሪዎችን ማሽከርከር የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባሳለፍነው ሳምንት መግለፁ ይታወሳል፡፡ 

በተለይም ሞተር ብስክሌቶችን ከየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እስከሚጠናቅቅበት የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ 12:00 ሰዓት ድረስ ማሽከርከር ፍጹም የተከለከለ መሆኑን ኤጀንሲው አሳውቋል፡፡

ክልከላው የሚመለከተው የፀጥታና የትራፊክ ቁጥጥር ሥራ አካላት ከሚጠቀሙባቸው ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ባጃጆችን፣ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶችን በኤሌክትሪክ የሚሠሩትን ጭምር በሙሉ የሚያካትት እንደሆነ እንዲሁ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ የሚደረጉ ሁነቶችን መሠረት ተደርጎ የሞተር ብስክሌት እንቅስቃሴ ዕገዳ መደረጉ በተለይም እየተስፋፋ የመጣውን የፈጣን አገልግሎት (ዴሊቨሪ ቢዝነስ) እየጎዳው ነው ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር አባላትና ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በተለይም በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳይሰጥ፣ ለምን ዕገዳ እንደሚደረግ ሳይገለጽ ድንገት ተነስቶ የሚደረግ ክልከላ ለሥራ ፈጠራ፣ ለትራፊክ እንቅስቃሴ መቀነስ እንዲሁም ለሥራ ዕድል ፈጠራ የራሱን አበርክቶ እያደረገ ያለውን አዲስ የቢዝነስ አውታር መንግሥት እንዲያድግ በሚሽትበት ልክ እንዳይጓዝ የሚያደርገው መሆኑን የማኅበሩ አባላት ይናገራሉ፡፡

አቶ ጥጋቡ ኃይሌ የእሺ ኤክስፕረስ መሥራችና የኢትዮጵያ ፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ዘርፉ ወጣቱን የሚቀጥርና ኢኮኖሚን የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን የፈጣን መልዕክት አገልግሎት በጣም አስፈላጊ መሆኑ ተዘንግቶ በተለይም ከፀጥታ (ሴክዩሪቲ) ምክንያት ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዮናታን በየነ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ‹‹በዴሊቨር ሰርቪስም ሆነ ፖስታል ሰርቪስ›› ላይ ያለው ትልቁ ችግር በመንግሥት ደረጃ በቂ ግንዛቤ (አዌርነስ) አለመኖሩ ነው፡፡ ኢ-ኮሜርስ ተብሎ በተደጋጋሚ ቢወራም የፈጣን መልዕክት አገልግሎት (Last Mile Delivery) ለሚባለው አገልግሎት በትክክል ትኩረት ተሰጥቶ እስካልተሰራበት የሚወጡት ፖሊሲዎችና መመሪዎች በተግባር ጋር ካለው የሚጋጩ ይሆናሉ፡፡

በመንግሥት በኩል በሚወጡ መመሪያዎችም ሆኑ ሌሎች የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ወቅት ዘርፉንና የዘርፉ ተዋንያንን የማሳተፍ ዝንባሌ እንደሌለ፣ ይህም መንግሥት በዘርፉ ላይ የግንዛቤ ችግር እንዲኖረው ስለማድረጉ አቶ ዮናታን ያስረዳሉ፡፡

እስካሁን በዘርፉ ለመሰማራት ከ90 በላይ ድርጅቶች ፍቃድ እንደወሰዱ ከዛ ውስጥ 60 የሚሆኑት በሥራ ላይ እንደሚገኙ በአግባቡ ደግሞ አገልግሎት እያቀረቡ የሚገኙት ከ30 የማይበልጡ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ነገር ግን ኢ-ኮሜርስና የዴሊቨሪ ቢዝነስ በህንድ፣ በቻይና የዘርፉ እንቅስቃሴ ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል የፈጠራ እንደሆነና በዚህ አገርም የዲሊቨሪ ቢዝነስን መደገፍ ካልተቻለ በአገሪቱ ኢ-ኮሜርስን ማሳደግ እንደማይቻል የሚናገሩ ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡

ማኅበሩ ለትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ስለዘርፉ ውይይት ለማድረግ ከዚህ ቀደም ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ዮናታን፣ ሆኖም እስካሁን መልስ ሳያገኝ እንደቀረ ያስረዳሉ፡፡

የሞተር ብስክሌቶች አንድ ላይ ሆነው የራሳቸው ብራንድ እንዲኖራቸው (ስታንዳርዳይዝ እንዲሆኑ) ተደርጎ፣ የዕቃ መያዣ ሳጥን (ቦክስ)፣ ባለከለር ልብስ፣ ተዘጋጅቶ ከአደጋ ሥጋት በፀዳ ሁኔታ መሥራት የሚለውን ለመወያየት በማሰብ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥረት መደረጉን የሚገልጹት የማኅበሩ አባላት፣ ከምግብ ጀምሮ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉትን የመልዕክትና ሌሎች አገልግሎቶች በዴሌቨሪ ሰርቪስ መቅረባቸው ዘርፍ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ አሁንም ልብ ሊባል ይገባል ይላሉ፡፡

ጠንካራ የኢ-ኮሜርስ ለመፍጠር ከታሰበ፣ አሊባባን ጨምሮ ሌሎች ስም ያላቸው ተቋማት ወደፊት ወደ አገር ውስጥ ገብተው ይሠራሉ ከተባለ፣ መጀመሪውኑ አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ አካላትን ማጠናከርና መጎልበት፣ በማኅበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መደገፍ ጥቅሙ ለአገሪቱ መሆኑን አገልግሎት አቅራቢዎች ይናገራሉ፡፡

በመንግሥት በኩል እስከ ሚኒስትሮች ድረስ የአገልግሎቱ አስፈላጊነት ግንዛቤ ያላገኘ መሆኑ፣ እንዲሁም የሚወሰኑት ውሳኔዎች ምንም ዓይነት ምክክር ሳይደረግባቸው የሚተላለፉ መሆናቸው ማኅበሩ እንደ ዋነኛ ችግር የሚያነሳቸው ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ይህንን ጉዳይ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀርቦ ለመነጋገር የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ ለትራንስፖርትና መሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽሕፈት ቤት አስቸኳይ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጥያቄውን በደብዳቤ አቅርቧል፡፡

የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር ለከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና ለኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን በግልባጭ በላከው ደብዳቤ በአሁኑ ሰዓት ያለው የሞተር ዕገዳ ካለምንም ማሳወቂያና ማብራሪያ ሳይኖር የተደረገ መሆኑ አግባብነት ያለው መሆኑን እንደማያምንና አስቸኳይ ውይይት ተደርጎ ዕግዱ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡

ማኅበሩ ደብዳቤውን ከላይ ለተገለጹት አካላት ገቢ እንዳደረገ የሚያስረዱት የማኅበሩ አስተባባሪ ወ/ሪት ሮዛ ካሳ፣ በተለይም በሞተር ብስክሌት አገልግሎት እስከቀረበ ድረስ ይህንን አገልግሎት የሚቀያርቡ አካላትን ያማከለና ያሳተፈ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚገባው፣ በሥጋትነት የሚነሱ ጉዳዮችም ካሉ ለእነሱ መፍትሔ ለማበጀት የጋራ ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ቅድመ ዝግጅቶችንም በዚህ አግባብ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎችን አገልግሎት የሚያቀርቡ ሞተረኞች ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅትን ወክለው የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ፣ አገልግሎቱ ቀን እየተገለጸ ለዚህን ያህል ጊዜ መንቀሳቀስ አይችልም ሲባል የሚታገደው ወይም የሚስተጓጎጓለው አሽከርከሪው ብቻ ሳይሆን የድርጅቶቹ አገልግሎት መሆኑን ወ/ሪት ሮዛ በማስረጃነት ይገልጻሉ፡፡

ብዙኃኑ የሞተር ብስክሌት ሥራ ጀማሪ የሥራ ዕድል (ስታርት አፕ) እንደመሆኑ መጠን ይህንን መደገፍ መሠረታዊና ወቅታዊ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ የሚገለጽ ጉዳይ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊ እንዳስረዱት፣ ኤጀንሲው የመፍቀድና የመከልክል ሥልጣን እንደሌለው የከተማዋን መንገድ እንደሚያስተዳድር ተቋም ከፖሊስ ኮሚሽን ከሰላምና ፀጥታ ግብረ ኃይል በመጣ መመርያ መሠረት የከተማው የትራንስፖርት ቢሮ ይህንን እንዲያስፈጽም በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

የሰላምና ፀጥታ ግብረ ኃይል ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በተጻፈ ደብዳቤ ቀን ተጠቅሶ በአዲስ አበባ ሞተር ብስክሌትና ባጃጅ ተሽከርካሪዎችን ማሽከርከር የተከለከለ መሆኑን ተከትሎ ክልከላውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ማድረጉን የሥራ ኃላፊ ያስረዳሉ፡፡ 

የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበሩ ጥያቄ ካለው መመለስ የሚችለው ፍቃድ የሰጣቸው አካል መሆኑን፣ ኤጀንሲው ግን በሚተላለፍለት ትዕዛዝ መሰረት መልዕክቱን ይፋ እንደሚያደርግና ሕጉን የተላለፉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

የትራፊክ ማኔጀመንት ኤጀንሲ መሰል መልዕክቶች ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሲደርሰው የሚያስተላልፈው መልዕክት ለሁሉም ይፋ የሚደረግና ለማኅበር የተደራጁ ወይም በሌላ መልኩ ተብሎ ለብቻ የሚገለጽ እንዳልሆነ የኤጀንሲው ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡ 

ወ/ሪት ሮዛ እንደሚናገሩት፣ በተለያየ ጊዜ ባልተጠበቀ ጊዜ የሚወጡት ክልከላዎችና ዕገዳዎች የኢትዮጵያ ፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር አባላት የሚያቀርቡት አገልግሎቶች ላይ መስተጓጓል ከመፍጠሩ ውጭ ዘርፉም እንዳያድግና እንዲቀጭጭ እያደረገው ይገኛል፡፡

ጥያቄዎችን ለትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ለትራንስፖርና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት ለጉዳዩ ሁነኛ መፍትሔ ባለመስጠቱ ሲንከበለል እንደመጣ የሚናገሩት የማኅበሩ አባላት፣ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ማኅበሩም ብቻ ሳይሆን ዘርፉ የገጠመውን ችግር መረዳትና እንዴት ማስተካከል ይቻላል የሚለውን መመለስ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች