(ክፍል ሁለት)
በጀማል መሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)
‹‹ሙክክክክ…››
ሰውዬው ጎበዝ ገበሬ ነው ማልዶ ጠማጅ፡፡ አንድ ቀን እንደ ልማዱ በጠዋት ይጠምዳል፡፡ እንደ ልማዱ ቁርሱን እንኳን ሳይበላ፡፡ ወይም በእናቴ አባባል፣ ‹‹ያደረ አፉን ሳይሽር››፡፡
ሰዓቱ ከረፋድነት አለፈ የፀሐይዋም ሙቀት ጠንከረ፣ ሰውነቱ በላብ መወረዛዛት ጀመረ፡፡ አሁንም ግን የአፍላ ጉልበቱ እርሾ አላለቀም፡፡ በመካከሉ ሚስቱ ከች አለች፡፡ ሙክክ ብሎ የበሰለ የባቄላ ንፍሮ በትልቅ ሜኖ (ከሳር የሚሠራ ባህላዊ ሳህን) እና የሚጠጣ ውኃ በቅል ይዛ፡፡
በቅርብ ከምትገኝ የብሳና ዛፍ ሥር ቁጭ አሉ፣ እጁን አስታጠበችው፡፡ ንፍሮውን አቀረበችለት፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በዚያ ሰፊ የገበሬ እጁ እፍስ እያደረገ መቃሙን፣ ዛቅ እያደረ መብላቱን ተያያዘው፡፡ በመቀጠልም የዚያን የቅል ውኃ በአናቱ ለቀቀበት፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ ወደ እርሻ ሥራው ጥልቅ ነዋ!፡፡
ይህ አባወራ በነጋታውም እንደ ልመዱ በሬዎቹን ማልዶ ጠመደ፡፡ እንደ ልማዱ አፉን ሳይሽር ሰዓቱ ከመርፈድም አለፈ፡፡ ፀሐይም ጉልበቷን መፈተሽ ጀመረች፡፡ ከመወበቅም አልፋ መለብለብ ጀመረች፡፡ ላቡ ከብብቱ ሥር ኮለል እያለ ከጀርባው መሀል ሰተት እያለ ወረደ ማረሱን አላቋረጠም፡፡ ሆኖም ረሃብ ጀግናው እየሞረሞረው ያ የጠዋት አፍላ ጉልበቱ እየከዳው መሆኑ በውል ገብቶታል፡፡
የትናንትናው ሙክክ ያለ የባቄላ ንፍሮ በዓይኑ ላይ ዞረ፡፡ አሥር ጊዜ ቀና እያለ ሠፈራቸው ወዳለበት አምባ ቢያይም፣ ሚስቱ የውኃ ሽታ ሆነች፡፡ ድካሙም፣ ረሃቡንም እየጠናበት ሲመጣ ማረሱን አቋርጦ ሚስቱን በመጣራት ሊያስታውሳት እግረ መንገዱንም ትንሽ ረፍት ሊወስድ ፈለገ፡፡
ከእርሻው ዳር በኩል ቆመና ወትሮ እንደሚያደርገው ስሟን በረዥሙና በከፍተኛ ድምፅ ለቀቀው፡፡
እሷም በረዥሙና በከፍተኛ ድምፅ ወዲያው ‹‹አ…ቤ…ት!›› አለች፡፡
‹‹እንደ ትናንትናው…›› በረዥሙና በከፍተኛ ድምፅ ለቀቀው፡፡
‹‹እህህህ…›› እሷም እንደ እሱው ለቀቀችው፡፡
‹‹ሙክክክክ…››
‹‹ምናልከኝ?›› በረዥሙና በከፍተኛ ድምፅ ለቀቀችው፡፡
‹‹ሙክክክክ…››
ይህን ቃል ‹‹ሙክክክክ…›› የሚለውን በረዥሙ መልቀቅም ሆነ፣ በጩኸት ማለት ወይም ማስወጣት ግን አልቻለም፡፡ እናም ሚስቱ ቃሉንም መልዕክቱንም መስማት አልቻለችም፡፡
‹‹እንደ ትናንትናው አልኩሽ…›› በከፍተኛ ድምፅና በረዥሙ፡፡
‹‹እህህህ…›› በከፍተኛ ድምፅና በረዥሙ፡፡
‹‹ሙክክክ…››
‹‹ሙክክክ››ን በጩኸት አለማለቱን ብቻ ሳይሆን፣ ማለት አለመቻሉን ጭምር ስላላወቀ አሁንም በዚያው መንገድ ደገመላት፡፡
‹‹ኧረ ምን ምናልከኝ?›› በከፍተኛ ድምፅና በረዥሙ፡፡
‹‹እንደ ትናንትናው አልኩሽ…›› በከፍተኛ ድምፅና በረዥሙ፡፡
‹‹እህ…›› በከፍተኛ ድምፅና በረዥሙ፡፡
‹‹ሙክክክ…››
‹‹ኧረ ምን ምናልከኝ?››
‹‹እንደ ትናንትናው አልኩሽ…››
‹‹እህ…››
‹‹ሙክክክ…››
ሆድ የሚጫወትብን ዓይነቱም፣ ቅርፁም፣ ይዘቱም እጅግ ብዙ ነው፡፡ አሁን ይኼ ገበሬ ቁርሱን በልቶ ቢወጣ ኖሮ ለረሃብ ባልተጋለጠ፣ የእርሻ ሥራውን ለማቋረጥ ባልተገደደ፣ ሚስቱ ጋር በመጯጯህ ባልተዳረቀና የሥራ ጊዜውን ባላባከነ፡፡
በመኸር ወቅት በየገበሬው ቤት ይፈጫል፣ ይጋገራል፣ ይበላል፡፡ ምናልባትም በቀን ሦስት ጊዜ ምናልባትም ድግስም ይደገሳል…›› ሁሉ እኩል የመኸር ወፍጮ የምትለዋ አነጋገር፣ የምግብ ዋስትናውን ላላረጋገጠው ገበሬ ‹‹የተቀኘች›› ተረትና ምሳሌ ነች፡፡
ከዚያስ? ከፍ ሲል የጠቀስነው ዓይነት ገበሬዎች ወደ መደበኛ የምግብ አበላል ሥርዓታቸው ይመለሳሉ፡፡ ያላቸውን እህል መቆጠብ አለባቸው፡፡ የበጋውን አጋማሽና ያንን ረዥም ክረምት ላለመራብ ጭምር፡፡ እናም በርካታ ደሃ ገበሬዎች፣ ምርት ያስገቡበት የመኸር ወይም የበልግ ወቅት ከእነሱ እየሸሸ በሄደ ቁጥር ‹‹ቁምሳ’ን›› ተግባራዊ ወደ ማድረግ ይመለሳሉ፡፡
‹‹ቁምሳ›› ማለት በመንግሥት ሠራተኞች አነጋገር፣ ቁርስና ምሳን ከመደበኛ ጊዜያቸው በማፈናቀል፣ በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ መብላት ማለት ነው፡፡ ቁርስን ከጠዋት ወደ ረፋድ፣ ምሳን ከእኩለ ቀን ወደ ተሲዓት ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያም በላይ ገፋ በማድረግ መብላት ነው፡፡ የሁለቱ ጊዜ ሲገፋ የእራት ጊዜም ይገፋል፣ ይገፋና እኩለ ሌሊት ላይ ሄዶ ቁጭ፡፡ እናም ‹‹እራት›› ታስቦ ሳይሆን፣ ተረስቶ ያድራል፡፡ ‹‹ቁምሳ›› በሚለው የአዲስ ቃል ምሥረታ ውስጥ፣ የ‹‹እራት›› ፊደላት ማለትም ‹‹እ››፣ ‹‹ራ›› ወይም ‹‹ት››፣ ‹‹የመረሳታቸው›› ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡
እዚህ ላይ ግን በቀን ሁለት ጊዜ መብላትን ያስተማረ የመንግሥት ሠራተኛ/የተማረው አድርጋችሁ እንዳትወስዱት አደራ፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ገበሬ ለዘመናት የኖረበት የአመጋገብ ሥርዓት ነው፡፡ ምሁራኑ ስም አወጡለት ከሆነ ያስማማናል፡፡ መቼስ በቋንቋ ‹መራቀቅን› ማን ያህላቸዋል? (እኔንም መጨመር ካስፈለገ ‹ማን ያህለናል?›) እንጂማ፣ በሁለት በሬ ከማረስ፣ በተመሳሳይ የእርሻ መሣሪያ መሬትን ከመጫር መቼ አወጡት? በእሱና በግብርናው ስም የሚመደብ በጀት ግን ያው እንደምታውቁት ተቋርጦ አያውቅም፡፡
ጋዜጠኛ እያለሁ፣ ‹‹ዶክመንተሪ›› ለመሥራት በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ወደሚገኝ የግብርና ምርምር ማዕከል ከባልደረቦቼ ጋር ሄድኩ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ኃላፊና ባለሙያዎች አንድ የሚያስደስት ብሥራት ነገሩን በአንድ በሬ ማረስ የሚያስችል ማረሻ መሥራታቸውን በጣም ደስ አለን፣ ማረሻውን አስጎበኙን፡፡ (‹‹ዘጋቢ ፊልም›› የሚለውን መጠሪያ አውቄ ነው የተውኩት፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎች ለፖለቲካ ዱላ እየተጠቀሙበት ስሙን ክፉኛ ሳያጠለሹት ቀሩ ብላችሁ ነው?)
‹‹ማረሻው ተገጥሞ ሲታረስበት ማየት አለብኝ›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፣ ወደ እርሻው ቦታ ሄድን፡፡ የካሜራ ባለሙያችን መቅረጫ መሣሪያውን አዘጋጀ፡፡ ድምፅ ስሰማ ወደ ኋላ ዞር አልኩ፡፡ በሬው እየመጣ ነው ጎምላሌው በሬ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ ገምሸር፣ ገምሸር እያለ፡፡ አንዲት ነፍስ ብቻ ስለያዘ ነው እንጂ መባል ያለበት ‹በሬ› ሳይሆን፣ ‹በሬዎች› ነው፡፡ በመካከለኛ የበሬ መጠን እናስላው ከተባለ፣ ያለማጋነን የሦስት በሬዎች ጥምር ብላችሁ ውሰዱት፡፡ የተቆጣ ቀን የአንድን ገበሬ ቤት ከሥሯ ሰቅስቆ አንስቶ፣ በአፍጢሟ መድፋት የሚችል ዓይነት፣ ይሄማ ሁለት ማረሻ ቢገጠምለትም ላያቅማማ ይችላል፡፡ ዋናው ጥያቄ አብዛኛው የእኛ አገር ገበሬ የዚህ ዓይነት በሬ አለው ወይ? የሚለው ነው…
በአጭሩ ማረሻው የአገራችን ገበሬዎች ለእርሻ ሥራ የሚጠቀሙባቸውን በሬዎች መጠን፣ ጉልበትና አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ባለሙያዎቹ ማረሻውን ያዘጋጁት ሌላ አገር ላሉና የደለበ በሬ ላላቸው ወይም ለማያውቋቸው ገበሬዎች ነው፡፡ የምን ቀረፃ ነው የካሜራችንን ኮተት ሸካክፈን ውልቅ፡፡
በነገራችን ላይ የከተማውም ሆነ የገጠሩ ቁምሳ ዓላማው አንድ ነው፡፡ ምግብ መቆጠብ፡፡ ወይም የከተማው የመንግሥት ሠራተኛ በተለይ መስክ ሥራ ላይ ለምግብ ሊያውለው የነበረውን ገንዘብ ሲቆጥብ፣ የገጠሩ ሰው ለምግብ ሊያውለው የሚችለውን እህል ይቆጥባል፡፡
ሆድ እየተራበም ቢሆን ወይም ደግሞ ብልጠት በተሞላበት መንገድ መደበኛ የምግብ መብያ ወቅቶችን አዛብቶ፣ እንደ ሕፃን ልጅ ሆድን በማረሳሳት ቁምሳን ሥራ ላይ በማዋል፣ ዛሬ ሊበላ የሚችልን ምግብ (የበሰለም ሆነ ያልበሰለ) ወደ ነገ የማሸጋገሩ ብሂል በሥነ ቃል ጭምር እስከ መሞካሸት የደረሰ ነው፡፡ እንዲህ በማለት፣
የሥራ ነገ ያደናግራል፣
የመብል ነገ ያገለግላል።
ሥራ መዋል ማደር የለበትም፡፡ ሥራ ካደረ ከነገው ጋር ስለሚደረብ ብዛቱ መደነጋገርን ያስከትላል፡፡ ምግብ ለነገ ማደሩ ግን ይፈለጋል ከነገው ጋር ስለማይደረብ አያደናግርም፡፡ ለምን? የዛሬው ማደሩ ከታወቀ፣ ለነገ ስለማይበሰል ቢበሰልም ወደ ነገ ወዲያ ይሸጋገራል፡፡
ይህ ብሂል ሥራ የሚሠራው የምግብ ፍላጎትን ለማሟላት ጭምርና ‹ያደናግራል› የተባለውንም ሥራ፣ በቀለጠፈና ውጤታማ በሆነ መንገድ መሥራት የሚቻለው፣ በቂ የሆነ ምግብ በመመገብ መሆኑን ለመዘንጋት የሞከረ ይመስላል፡፡ ይመስላል ማለቴ ያለ ነገር አይደለም፡፡ የብሂሉ ቀማሪ ወይም ቀማሪዎች ስለሥራና ስለመብል እየነገሩንና ከሁለቱ ለማን ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት አበክረው እየመከሩን፣ ምግብ ከሥራ አንፃር ያለውን ሚና ይዘነጉታል ማለት ትንሽ ያስቸግራል፡፡
እዚህ ላይ ያለው ጥያቄ ለምን የዘነጉት ለመምሰል ሞከሩ የሚለው ነው፡፡ ሁለት መላ ምቶችን መሰንዘር ይቻላል፡፡ አንዱ ምክንያት ስለምግብ ካለን ጠቅላላ ባህል የሚመነጭ ሊሆን ይችላል፡፡ “እረኛ ቢቆጣ ምሳው እራቱ ነው››፣ ‹‹ነገም ሆድ አለ››፣ ‹‹እራት በእንቅልፍ ያልፋል›› መሰል አነጋገሮች የመብላትና የመመገብ ፋይዳን ሳይሆን፣ ማንኛውንም አጋጣሚ ተጠቅሞ ምግብን በመቆጠብ ሆድን መቅጣት ወይም ባዶ ማሳደር ጥሩ መሆኑን የሚሰብኩ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የእህል ወይም ሰብል ለአብዛኛው የገጠር ሰው የሁለ ነገሩ እምብርት ነው፡፡ ገበሬው ለበርካታ ነገሮች (ለልብስ፣ ለቤት ፍጆታ፣ ለሕክምና…) ወጪ የሚያደርገውን ገንዘብ በአብዛኛው የሚያገኘው ያመረተውን እህል ሸጦ ነው፡፡ በሬ እንኳን ቢሞትበት፣ በሬ የሚገዛው እህል ሸጦ ነው፡፡ ተበድሮ በሬ ቢገዛም እህል ሸጦ ነው ብድሩን የሚከፍለው፡፡ እናም እህል መቆጠብ ያለበት እሴት ነው፡፡ ሆድ ደግሞ ይኼንን እሴት በየጊዜው ከመቀነስ ውጪ ሌላ ሥራ የለውም፡፡ ስለሆነም ሆድን በተወሰነ ደረጃ እያባበሉም ሆነ መቆጠብ የሚያስገኘውን አጓጊ ውጤት እያሳዩ መቆጣጠር አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም፡፡
(ሳምንት ክፍል ሦስት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡