Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የሽማግሌ ምክር ስሙ!

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የሽማግሌ ምክር ስሙ!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

የአገር ሽማግሌዎች፣ ጎልማሶችና ወጣቶች በሙሉ ምንድነው የምትጠብቁት? አገራችን የወገን ያለህ እያለች እጇን ዘርግታ ስታጣራ ምንድነው ዝምታው? ማን እንዲመጣ ነው የምትጠብቁት? መንግሥት የድርሻውን ይሥራ፣ ሽማግሌዎች በባህላችሁ፣ በወጋችሁና በልማዳችሁ ተነሱ፣ ለሰላም መንገድ ለመክፈት ተባበሩ። የተማረ ብቻ የሚያውቅ መስሏችሁ አትሳሳቱ፡፡ አገር የሁላችንም ነችና በያለንበት ለሰላም እንቁም፡፡ አገራችንን ከመፍረስ እንታደጋት በሉ፡፡ በየቤቱ ተቀምጦ ማውራት ብቻ በቂ አይደለምና ተነሱ ሰላምን ለማምጣት ትጉ። መንግሥትም ታውን ሐውስ (ታላቅ የስብሰባና የመወያያ) የሚሉትን ዓይነት አዘጋጅቶ ኅብረተሰቡን እየጋበዘ ቢያማክር ጥሩ ይሆናል። አንድ ወይም ሁለት ሚሊዮን የፓርቲ አባላት ብቻ መፍቴሔ ሊያመጡ አይችሉምና ሕዝቡን አሳትፉ፣ ምክርም ስሙ። ሁሉን አዋቂ እኛ ብቻ ነን አትበሉ፡፡ ገደል አፋፍ ያደረሰን ይኼው ነው። መንግሥት የሕዝብ ተወካይ እንጂ ሁሉን ፈጣሪ ሁሉን አድራጊ አይደለም፡፡ የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያዳምጥና መፍትሔ ፈላጊ እንጂ ችግር ፈጣሪ አይደለምና ጥንቃቄ ይደረግበት፡፡

በአገራችን በአሩሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌ፣ በካፋ፣ በወላይታ፣ በክስታኔ (ጉራጌ) በአማራ፣ በትግራይ፣ ወዘተ የማወያየትና የማስታወቅ አኩሪ ባህል ነበረን። ታዲያ ዛሬ የፈረንጁ ትምህርት ቅድሚያ ተሰጠውና ባህልና ታሪካችን ተረሳ፡፡ መረሳትም ብቻ ሳይሆን ተናቀ፡፡ ዋ አለማወቅ፣ ዛሬ ምዕራባውያን ‹‹Conflict Resolution›› ብለው የራሳቸው አስመስለው ዓለምን የሚያወናብዱበት ሥልት ከእኛ የተቀዳና በእነሱ አንደበት በመሆኑ ብቻ ተቀባይነት አግኝቶ የእኛነቱ ተረስቷል፡፡ ምሁራንም ያንን ተቀብለው ላይ ታች ሲሉ የአዋቂነት ዓርማ ሆኖ እየተመለከትን ነው። ወገኖቼ ወደ አገራችን መለስ ብለን ከመሠረቱ ብንመለከት ሁሉም ከእኛ የተቀዳ ነውና በሰው ወርቅ ከማጌጥ በራሳችን ብንኩራራና ብንተገብር እጅግ ውጤታማ በሆንን ነበር። ዛሬ ሚሊሺያ በመባል የታወቀው የወታደራዊ ዘርፍም ከአፄ ቴዎድሮስ እንደተቀዳ ታውቁ ይሆን? አልጠራጠርም ታውቃላችሁ።

- Advertisement -

በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪና በልማት ከመሽቀዳደም ይልቅ ለጥፋት ያዘጋጁልንን የረቀቀ ዘይቤያቸውን ይዘን በመጓዝ እስከ ዛሬ ያተረፍነውን ተመልክተን ወደ ራሳችን እንመለስ። ሁሌም የሚያልፍን ጊዜ ለማያልፍ ታሪክ ትተን እንዳናልፍ እንጠንቀቅ።                                                                                                                                   በአገራችን አሁን የምናየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን የማጥፋት ዘመቻ ዛሬ የተጀመረና በአገር ልጆች የተካሄደ ሳይሆን፣ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ጊዜ ነበር የተጀመረው፡፡ በዚያን ጊዜ ‹‹አንድ ሃይማኖት አንድ አገር ባይ›› ብቻ ስለነበረ ከጥንት ጀምሮ ሰይጣን የተጣወራቸው የአውሮፓ መነኩሴ ነን ባዮች ሰንቀው ማለያየት ስላመጡ፣ ንጉሠ ነገሥቱ እንዲህ ሲል ጠየቋቸው፡፡ ‹‹ከየት ነው የመጣችሁት?››፣ ‹‹ከአውሮፓ››፣ ‹‹በየት በኩል መጣችሁ?››፣ ‹‹በየዓረቡ አገሮች አቆራርጠን በመርከብም በእንስሳትም ጀርባ እያልን እዚህ ደረስን፤›› አሏቸው። ‹‹ታዲያ አልፋችሁ የመጣችሁበት አገር ሁሉ ክርስቲያን ወይስ እስላም›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ ‹‹አብዛኛው የእስልምና ተከታይ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ‹‹ታዲያ የክርስቲያኗን አገር ኢትዮጵያን ክርስትና ለማስተማር ከመምጣት፣ በመጀመሪያ የደረሳችሁበት የእስልምናውን አገር አታስተምሩም ነበር?›› ብለው በኃይለ ቃል ከተናገሩ በኋላ ዕርምጃ ወስደው ወደ ኢትዮጵያ ሌሎች ሁለተኛ ብቅ ሳይሉ ኖሩ፡፡

በግራኝ አህመድ በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያ ፖርቺጊዞች ከመጡበት ዘመን አንስቶ፣ ሌሎች የክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች በመጠኑም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ተከባብረውና ተዋደው ነበር የተኖረው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የሁሉም አስተባባሪና አስተናጋጅ ሆና ኖረች እንጂ ማንንም አላንገዋለለችም። የትናትናዋ ባለነዳጅ ዘይቷ ሀብታም አገር ሳዑዲ ዓረቢያ እንኳንስ ሌላ ሃይማኖት ልትፈቅድ አንድ ክርስቲያን በአገሯ ውስጥ ቢሞት በዕለቱ ከሳዑዲ አስከሬኑ ካልወጣ ወደ ባህር የሚጣልበት ዘመን እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ምናልባት ተለውጦ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንኳንስ ሃይማኖቱን አለባበሷን ያልቀየረች ሴት ንግሥትም ትሁን ቀዳማዊት እመቤትም ብትሆን አለባበሷን አስተካክላ የመቅረብ ግዴታ ነበረባት፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሹ ኃያላን አንድም ቀን በዚህ ጉዳይ ሲጨነቁና ሲጠበቡ ታይተው አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ምነው ይህንን ያህል ዋተቱ? ወገኖቼ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡ አዎን ኪስ መሙላት፣ የግል ሥልጣንና የበላይነት ለተወሰነ ጊዜ ማጠናከር ይቻላል፡፡ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን መዳንን መምረጥ የተሻለ ስለሚሆን፣ ባለጊዜ የሆናችሁ ሁሉ ትናትን ተመልከቱ። የት ነበርን፣ የትስ ነን ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ የሚሞተው ማነው፣ ገዳይስ ማን ነው ብላችሁ ራሳችሁን አደብ አስገዝታችሁ አገናዝቡ፡፡

እዚህ ላይ የ1960ዎቹን የኮንጎ ቆፍጣና ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባንና የኮሎኔል ጆሴፍ ደዚሬ ሞቡቱን ምሳሌ መከተል ይጠቅማል ብዬ አሰብኩኝ። የቤልጂየም መንግሥት ኮንጎ ነፃነቷን በማግኝቷ የነበረው የቅኝ ገዥነት ዘረፋ ስለቀረባቸውና አዲሱ መሪ ፓትሪስ ሉሙምባ ጠንካራና ለአገርና ለወገን የቆመ፣ አልፎ ተርፎ አፍሪካን አንድ ለማድረግና ነጮች ወደ ደረሱበት ለመድረስ ህልም የነበረው ወጣት ነበር፡፡ እሱን ለማስወገድ ሞቡቱን ከጎናቸው አሠልፈውና የፈለገውን ሥልጣን ሰጥተው ሉሙምባን በማስወገድ የተለመደ ዝርፊያቸውን ለመቀጠል በማመቻቸት፣ ሉሙምባን ይደግፉ የነበሩ የፓርላማ አባላትን በሙሉ አስወገዱ፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 17 ቀን 1961 ሉሙምባና ሁለት የቅርብ ወዳጆቹ የሆኑት ካታንጋ ውስጥ ተገደሉ። ሞቡቱም የማይልፍ ስም ይዞ ለልጅ ልጆቹ መልካም ስም ሳይሆን የጥቁር ጠባሳ ጥሎላቸው አለፈ። በተፈጥሮ ሀብት ከበርቴ የሆነችው ኮንጎ የነጮች ሲሳይ ስትሆን የአገሬው ልጆች ግን ከለማኝ በታች ሆነው ቀሩ።

በጣም የሚገርመውና የሚያስደንቀው ነገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሁሉም እኩል ሚዛናዊ መስሎ ይታየን የነበርን እጅግ በጣም ብዙ ስንሆን፣ ነገሩን በአንክሮ ለተመለከተ ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጀምሮ ለምዕራባውያን የቆመና በተለይም በአፍሪካ ላይ ከጠላት ያላነሰ ድርጊት የሚፈጽምና የፈጸመ ድርጅት መሆኑ አይረሳም፡፡ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት ዘመን ለአቤቱታ የቀረቡትን አፄ ኃይለ ሥላሴ ለማሸማቀቅ ከመሞከሩም በላይ፣ በግልጽ ጣሊያንን በመርዳት መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ዕቀባ አድርጓል፡፡ የንጉሡን አቤቱታ ችላ በማለት ለጣሊያን አድልኦ እንዳደረገም የዓለም ሕዝብ በትዝብት የተመለከተው ጉዳይ ነበር። በ1960ዎቹ የኮንጎ ነፃነት ታውጆ ፓትሪስ ሉሙምባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን፣ ቤልጂየሞች ሊገድሉት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ ግድያው እንዲፋጠንና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ተቆርቋሪው ሉሙምባ ደብዛው እንዲጠፋ ያበረታቱና የወንጀሉ ተካፋዮች፣ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ዳግ ሃመርሾልድና በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አይዘን አወር እንደነበሩ ‹‹The Assassination of LUMUBA›› የተሰኘውን መጽሐፍ በ‹‹LUDO DE WITT›› የተደረሰውን መጽሐፍ በዋቢነት መመልከት ይበቃል።

ይህንን የምልበት ዋናው ምክንያቴ ተመድም ሆነ ምዕራባያውያን ለጥቅማቸውና ለክብራቸው ሲሉ ማንንም በገንዘብም ሆነ በሥልጣን በማባበል የፈለጉትን በማድረግ፣ ሕዝብንና ሕዝብን በማጋጨት ሲከፋፍሉ እስከ ዛሬ ድረስ የተሳካላቸው ሆኖ እዚህ ተደርሷል፡፡ ዛሬ ወጣት ኢትዮጵያውያን ተምረውና ተመራምረው ለከፍተኛ ደረጃ በደረሱበት ዘመን እነዚያም በለመዱት መንገድ ሲሯሯጡ ለምን ብሎ በመገንዘብ፣ ሌሎች የእስያ አገሮች እንዳገለሏቸው አግልለን በራሳችን መቆም አቅቶን ለመበላላት እየተሽቀዳደምን ነው፡፡ ከእንቅልፋችን ነቅተን ሌሎች ወደ ደረሱበት በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ መሽቀዳደምና ለመብለጥ ጥረት ማድረግ ሲገባን፣ ምነው እንደ ባቢሎን ግንበኞች ውጥንቅጣችን እንዲፋጠን ተቻኮልን? አንዳንድ ጊዜም የአንዳንድ ብልህ ታላላቅ መሪዎችን ፈለግ መከተል ባንችል እንኳ ያደረጉትን የአገር ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርና ክብር መመልከት ምነው አቃተን?

እዚህ ላይ ተወዳጁና ለአሜሪካ ታላቅ ሥራ ሠርቶ ያለፈውን ፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከንን ማስታወስ ጥሩ ይመስለኛል። ባሪያ ነፃ ይውጣ አይውጣ ተባብለው ሰሜንና ደቡብ በተቃራኒ ሲወዛገቡ የተከፈተውን ጦርነት በማሸነፍ፣ ደቡቡንና ሰሜኑን አንድ አድርጎ ዛሬ አሜሪካ ላለችበት ታላቅነት ካደረሷት መሪዎቿ አንዱ አብረሃም ሊንከን ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ስሙ ለዘለዓለም እንደገነነ ይኖራል። ታዲያ ምንም ሳናጣ በሲስተም ጉድለት ብቻ ያለንን ተጠቅመን ለሌላው መትረፍ የምንችል እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም ከእጅ ወደ አፍ እንኳ መድረስ አቅቶን እንኖራለን፡፡ ወጣት ኢትዮጵያዊት ሕፃን አዝላ ዳቦ ስትለምን ያንን እንኳ ማሟላት ያልቻልን በቋንቋና በብሔር እየተከፋፈልን ለማንም ሳንሆን ከንቱ መሆናችን አያሳዝንም?

ቀጥዬ አጠር አጠር አድርጌ ለወገኖቼ የአገራችንን የዕርቅ ሥርዓት ላመላክትና ቢሻችሁ ተቀበሉኝ፣ እንደምትቀበሉኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ ለወሬ ሱሰኝነት ሳይሆን ወገኔና አገሬ ሲጠፋ ለማየት ስላቃተኝ ከቁጭትና ከአገር ፍቅር የተነሳ ነው። የአርሲንና የባሌን የዕርቅ አካሄድ ላመላክትና በየተራ የጠቀስኳቸውን ሁሉ እንዳቀርብ ፍቀዱልኝ።  በአርሲና በባሌ የዕቅር ሥርዓት ሰዎች በድንገተኛ አጋጣሚ ተጣልተው ሕይወት ቢያልፍ፣ ከሁለቱም ማለትም ከገዳይና ከሟች ወገን የአገር ሽማግሌዎች ተሰባስበው ተወያይተው ዕርቀ ሰላም ለማምጣት ብዙ ይጥራሉ፡፡ የሟች ወገን አልታረቅም ይላል፣ የገዳይ ወገን ሽማግሌዎች ባለፉት ዘመናት ያልነበረን ፀብ ወጣቶች አመጡብን ታዲያ ለብዙ ዓመታት የነበረው ወዳጅነት ሰይጣን በጫረው እሳት ነባሩ ወዳጅነት እንዴት ይበላሽ? ለነገሩ ሟች ሳይሆን የሞተው ገዳዩ ነው፣ ሟችማ አንደኛውን አርፏል፣ ገዳዩ ግን ሁሌ እንደባነነ ነው የሚኖረው። ነባሩ ወዳጅነት ተመልሶ ገዳይም ካሳ ከፍሎ ወደ አንድነት መመለስ ይገባል እንጂ፣ የሁለት ሰዎች ድንገተኛ ፀብ በፈጠረው ግድያ ምክንያት ወገን ከወገኑ መለያየት የለበትም ተባብለው ሽምግልናው ይታያል፡፡ ወገን ከወገኑ ዕርቅ አውርዶ ሰላም አምጥተው እስከ ወዲያኛው ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለው ሰላም ያሰፍናሉ፡፡ ሁለተኛም በወዳጅነት እንጂ በጠላትነት እንዳይፈላለጉ በመሃላ ተወስኖ ሰንጋ ታርዶ የገዳይ አባት ወይም ወንድም ቀርቦ፣ ገዳይም ዓይኑ ተሸፍኖ በታረደ በሬ ሆድ ዕቃ ውስጥ ሁለቱም እጅ ለእጅ ተያይዘው በደም ታጥበው ይታረቁና የዘለዓለም ወዳጅነት እንዲቀጥል ይደረጋል።

በክስታኔ (ጉራጌ) እንዳጋጣሚ በ1960ዎቹ ያየሁት አስደናቂ ሽምግልና አለ፡፡ ሁለት ወዳጃች በድንገት ተጣልተው ባልታሰበ ሁኔታ አንዱ እንዱን ገደለው፡፡ ገዳይ አገር ጥሎ ሸሸ፡፡ ከዓመታት በኋላ አንድ ታላቅ ሰው ይሞታሉ፡፡ የገዳይ ወገኖች ገዳይ የነበረውን ካለበት በአስቸኳይ በድብቅ እንዲመጣ ይልኩበታል፣ መጥቶም ይደበቃል፡፡ የታላቁ ሰው አስከሬን ለቀብር ወደ ማረፊያው ተጉዞ ደርሶ ቄሱ ግባ ወደ መሬት ሊሉ ሲዘጋጁ አንደኛው ቄስ ‹‹ሁላችንም ነን የሞትነው፣ ለዚህ መፍትሔ ሳይደረግ የግባ መሬቱ ፍጻሜ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የሟች ወገን ለገዳይ ይቅርታ ካላደረገ የእኝህ ታላቅ ሰው አስከሬን ወደ ማረፊያው አይገባም፤›› ብለው በመማፀን አቤት ይላሉ። በአካባቢው የሚታወቅ የመልካም እሴት ማሳያ ነውና አስከሬኑ ወደ ሜዳ ተመልሶ የዕርቀ ሰላሙ ሥርዓት ተደርጎ፣ ሁለቱ ባላጋራዎች ወደ ወዳጅነት እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመለሰ። ሟችም ቆመው ባያዩትም በመንፈስ ያያሉ ተብሎ ታምኖበት በክብር ሲሸኙ በማየቴ እስከ ዛሬ እገረማለሁ፡፡ መልካም ባህል እንዲህ ነው።

በካፋ አንድ ሰው ሌላውን ቢገድል በቀላሉ አይታለፍም፡፡ ነገር ግን ገዳይ በጥንቃቄ ተሸሽጎ ሕይወቱን አትርፎ ከቆየ በኋላ እንደተለመደው ሽማግሌ ይላካል፡፡ በመጀመርያ ‹‹ለምን መጣችሁ? ልጃችን ሞቶ በዋዛ የምንላቀቅ ይመስላችኋል?›› በሚል ቁጣ አዘል ግልምጫ ጭምር በሽማግሌዎች ላይ ውርጅብኝ ይደርስባቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ከተመረጡት ሽማግሌዎች አንዱ ብድግ ይሉና የሚከተለውን ግጥም ያሰማሉ፡፡

‹‹ኤሚሾ ተበሻ ተማታቼ ዎቾ                                                                                                                          ቃል ኪዳን አለብኝ ተከፈቾ ቡሾ››                                                                                                                    ይቀጥሉና ‹‹ቦረሆ ውሺያ ዎኩ                                                                                                                               ቦይጆ ቀሮና የቾ                                                                                                                                       ተየሻን ጮጦ አሎ›› 

በማለት እንደ ዘራፍ ዓይነት መሆኑ ነው ይፎክራሉ። ልተርጉምላችሁ የመጀመሪያው፣ ‹‹ፍየል ብታርድልኝ ወርች አልባል ቃል ኪዳን ያለኝ የታላቋ የካፋ ልጅ ነኝ›› ማለት ሲሆን፣ ‹‹አጋዘን አባርሬ ከአገር የማስወጣት ዱኩላ አባሪሬ ቀንዱን የምይዝ ጀግና እኔ ያልያዝኩት አውሬ የለም፤›› ይሉና የጀግንነታቸውን ደረጃ በፉከራ መልክ ካሰሙ በኋላ፣ ልተርጉምላችሁ የመጀመሪያው፣ ‹‹ፍየል ብታርድልኝ ወርች አልበላም ቃልኪዳን ያለኝ የታላቋ የካፋ ልጅ ነኝ›› ማለት ሲሆን፣ ‹‹አጋዘን አባርሬ ከአገር የማስወጣ ዱኩላ አባርሬ ከአገር የማስወጣ ዱኩላ አባርርሬ ቀንዱን የምይዝ ጀግና እኔ ያልያዝኩት አውሬ የለም፤›› ይሉና የጀግንነታቸውን ደረጃ በፉከራ መልክ ካሰሙ በኋላ፣  

‹‹እኔና ጓደኞቼ መጥተን በምን ምክንያት እንዋረዳለን?›› በማለት ያቅራራሉ፡፡                                                                                                       ‹‹ወግ ማዕረጋችን የሽምግልና ሥልታችን እንዲህ በዋዛ የሚቀር ነው?›› በማለትም ወጉን የአገሩን ታሪክ ሲዘረዝሩ ሌላው ሽማግሌ ተነስተው፣ ‹‹ወራቦ ወራቦ›› በማለት ጉዳዩን ያሟሙቁታል፡፡ ‹‹ወራቦ ወራቦ›› ማለት በአማርኛ ‹‹ለካ ለካ›› እንደሚባለው ነው።  ሦስተኛው ይነሱና ‹‹እዚህ ላይ ይብቃን ገዳይም ሟችም የእኛው ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ልንለያይ አይገባምና ወገኖቼ ሁሉንም ለእነዚህ ጀግኖችና ለታሪካችን ስትሉ ይቅር በሉ በማለት ገላጋዩ ሽማግሌ ነገሩን ወደ ሰላም ያመጡና ለቤተሰብ ምክክር ጊዜ ተሰጥቶ፣ በሳምንቱ ዕርቀ ሰላም ይወርዳል። ሰላምም ይፈጠርና ቁጣውም ሐዘኑም እዚህ ላይ ይቆማል። በወላይታም በሌሎቹም አካባቢዎች እንዲህ ዓይነት ማዕረግ ያለን ሕዝብ ነበርን፡፡ ታዲያ ሥልጣኔ ነው ብለን የፈረጆችን አጉል ልማት ተከትለን እየተለያየን ነው፡፡  ወደ ልቦናችንና ወደ ባህላችን እንመለስና በዕርቀ ሰላም ያጠፋ ተወቅሶና ክሶ ወደ ነበረበት እንዲመለስና ከኅብረተሰቡ እንዲቀላቀል የማድረግን ባህል እናበልፅግ። ሊያለያዩን በቆፈሩልን ጉድጓድ ውስጥ ዘው ብለን አንግባ። የሠለጠንን እየመሰለን ከመንገዳችን እየወጣን፣ በሰው ባህልና ቋንቋ እየተመፃድቅንና የራሳችንን እየሸሸን በውርደት ላይ እንዳንዘፈቅ እንጠንቀቅ፡፡ 

ሔኔሪ ኪሲንጀር የተባለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረ ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ውጥንቅጧን ሊያወጣ የተዘጋጀው፣ ዛሬ የምናየውን ጣሊያን መሠረት ጥሎብን የሄደውን የማለያየት ሥልት እስኪ እንይ፡፡ ሔንሪ ኪሲንጀር አሳምሮ መስመር አስይዞልን የቆየውን ሥልት የራሳችን ልጆች ሥራ ላይ በማዋላቸው አሁን ላለንበት ደረጃ አደረሰን። ይህንን በ25፣ በ50 እና በ100 ዓመታት ውስጥ በገሃድ የሚወጣውን የአሜሪካ ሚስጥር ጊዜውን ጥብቆ ማጥናትና መመርመር ስለሚቻል፣ በኢትዮጵያ የተደረጉትን ደባዎችንና ሴራዎችን መመልከት ይቻላል፣ ተችሏልም። አንዱን ለምሳሌ እነሆ ተመልከቱ፡፡ ‹‹The decline in the fortunes of the Horn nations might have been foreseen by Henry Kissinger who in 1972 as a head of nation security council, known under his direction as commute in charge of running the world,›› wrote a confidential report on the future of Ethiopia. He purportedly recommended the US policy should be to keep the Ethiopian nation in perennial internal conflict, using such vulnerabilities as ethnic, religious and other divisions to destabilize the country. Kissinger’s recommendations appear to have been followed successfully for not only for Ethiopia, but the Horn of Africa have been in the turmoil ever since.››

ወገኖቼ ይህ ቀላሉ ክፍል ሲሆን ማወቅና ማገናዘብ የፈለገ ጭራሽ መቀመቅ ሊከተን ያዘጋጀውን በሙሉ ማንበብና መረዳት ይችላል፡፡ ታዲያ ይህንን እያየን ለተደገሰልን ደባ በማያወላውል ሁኔታ ተባባሪና አስታናጋጅ መሆን ለአንድ አገር ዜጋ ተገቢ ይሆን? የሰው ልጅ በሰውነቱ፣ በአገሩና በወገኑ የሚኮራ ካልሆነና የሰጡትን የሚቀበል ብቻ ከሆነ ሰውነቱን የካደና ምንም ተስፋ የሌለው ነው የሚሆነው። ወገኖቼ ለሹመት፣ ለሽልማትና ለታላቅነት መሯሯጥ የሚቻለው አገርና ወገን ሲኖር ብቻ ነው። አለበለዚያ የባርነት እሽቅድምድም እንዳይሆን እጅግ አድርጌ እፈራለሁ። በግልጽ የተደገሰልን ሴራ እየታየ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ እንዳልሰሙ መሸምጠጡ፣ የኋላ ኋላ የእግር ውስጥ እሳት እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ በማለት የሽማግሌ ምክሬን አቀርባለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...