Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚጥል በሽታ ተጠቅተዋል

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚጥል በሽታ ተጠቅተዋል

ቀን:

የሚጥል ሕመም (ኤፕለፕሲ) በማንኛውም ሰውና የዕድሜ ክልል ሊፈጠር የሚችል ድንገተኛ ከቁጥጥር ውጪ የሆነና የአዕምሮ ተግባርን የሚያውክ ክስተት ሲሆን፣ የሚከሰተውም የአንጎል ነርቭ ኤሌክትሮኒካዊ ንዝረት ጊዜያዊ መረበሽ ሲኖርበት ነው፡፡

ስምንተኛው ብሔራዊ የሚጥል ሳምንትን አስመልክቶ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አዜብ አዲስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ወደ 1.2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዚህ ሕመም ተጠቅተዋል፡፡ ከተጠቀሱት ሕሙማን መካከል 79 በመቶ ያህሉ የሚገኙት በኦሮሚያ፣ በአማራና በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ውስጥ ነው፡፡

አብዛኞቹ የሕመሙ ተጠቂዎች ወደ ሕክምና እንደማይሄዱና አገልግሎትም እንደማያገኙ አማካሪው ገልጸው፣ በዚህም እንደ ምክንያት የጠቀሱት ማኅበረሰቡ ስለሕመሙ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ሕሙማን ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው መገለልና አድልኦ፣ እንዲሁም በሕመሙ ዙሪያ ያሉ ልማዳዊ አስተሳሰቦች ወደ ተሳሳቱ አመለካከቶችና መሸማቀቅ በማምራት በጊዜ የመታከም ዕድልን ማሳጣታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በወሊድ ጊዜ በጨቅላ ሕፃናት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ፣ በራስ ቆዳ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ፣ የልብ በሽታዎችንና ስትሮክን መከላከል፣ እንደ ማጅራት ገትርና ወባ የመሳሰሉት በሽታዎች ላይ የሚሠሩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች በሽታውን ከመከላከል አንፃር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹በመንገድ ትራፊክና ከሥራ ጋር በተያያዙ የሚያጋጥሙ ጉዳቶች እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ልብ፣ ኩላሊት በሽታዎች) ለሚጥል በሽታ አጋላጮች ናቸው፤›› ያሉት ደግሞ፣ የነርቭ ሐኪምና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኒውሮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ ዘነበ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ አባባል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለኤፕለፕሲ አጋላጭ ሊሆኑ የቻሉት አንጎል ላይ በሚፈጠሩት ቁስለት የተነሳ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሕመሙ ችግር ከፆታዊ አንፃር ሲታይ በወንዶችና በሴቶች መካከል ብዙም ልዩነት የለውም፡፡

ከዕድሜ አኳያ ሲታይ ግን በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል፣ ከዚህ አኳያ አንድ ጨቅላ ሕፃን ከተወለደ የመጀመርያው አንድ ዓመትና ከዚያም እስከ አምስትና አሥር ዓመት ያለው የዕድሜ ክልል ለዚህ ሕመም ተጋላጭ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡

የዚህም ዋናው ምክንያት ብዙ እናቶች የሚወልዱት በቤት ውስጥና በባህላዊ አዋላጆች በመታገዝ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ አወላለድ ደግሞ ልጁ የመታፈን ዕድል ሊያጋጥመው እንደሚችልና ምንም ዓይነት ድጋፎችም ሳይደረግለት እንደሚቀር፣ በዚህም የተነሳ ለልጅነት የሚጥል በሽታ ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከቱት፡፡

ዕድሜው በታዳጊ ወጣት ክልል ሲደርስ ወይም በጎልማሳ ዕድሜ ክልል አዲስ ነገር ከመሞከር አንፃር ይኼውም የአልኮል መጠጥና አደገኛ ዕፆችን የመጠቀም ሱስ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም በመደባደብ የተነሳ ከጭንቅላት ጋር በተያያዙ ጉዳቶች የሚጥል በሽታ እንደሚያስከትል፣ ዕድሜ እየጨመረ ወደ 66ዎቹ ሲጠጋ የበሽታው መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡

ሕመሙ የያዘው ሰው ከበሽታው ባሻገር ተያይዘው ለሚመጡ ጫናዎች ተጋላጭ እንደሚሆን፣ ከጫናዎቹም መካከል ወደ ሥራ እንዳይሄድና አምራችም ላይሆን እንዲሁም የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጥገኛ ሊያደርገው እንደሚችልም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከያሬድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በበሽታው ጫና ዙሪያ እ.ኤ.አ. በ2019 የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በዓለም ውስጥ 50 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከሚጥል ሕመም ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ በየዓመቱም አምስት ሚሊዮን ሰዎች ለሕመሙ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡

ከበሽታው ጋር አብረው ከሚኖሩት መካከል 80 በመቶ ያህሉ የሚገኙት በማደግ ላይ፣ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ሕክምና አያገኙም፡፡ ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላም መንገድ ለሕክምና ተደራሽ ሆነው መድኃኒቱን በሥርዓት ከመውሰድና ተገቢውን ክትትል ካደረጉ ጤናማ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ ነው ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የሚጥል ሕመም ያደረባቸው ሰዎች ሥራ የማግኘት ወይም የመቀጠር፣ የመማር፣ ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት፣ ተመጣጣኝ መብቶቻቸውን በተለይ መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ማክበርና ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

ኬርኢፕለፕሲ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ እናት የእውነቱ እንዳመለከቱት፣ የሕመሙን ባህሪ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር በማቆራኘትና እንደ እርግማን በመቁጠር በርካቶች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ በሕመሙ ዙሪያ ያሉ ጎጂና ልማዳዊ አመለካከቶችና ድርጊቶች ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና እንዳይሄዱ፣ መገለልና አድልኦ እንዲደረስባቸውና ባልተገባ ሥነ ልቦና ጫና እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡

‹‹በጋራ በሚጥል ሕመም ላይ ያለውን መገለልና አድልኦ እናስቁም!›› በሚል መሪ ቃል እስከ ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን ድረስ በሚዘልቀው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጥ፣ ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ሥፍራዎች በራሪ ወረቀቶችን በመበተን፣ ፖስተሮችን በመለጠፍ፣ በዘጋቢ ፊልም የተደገፈ ማስገንዘቢያ እንደሚከናወን ነው ዋና ሥራ አስኪያጇ የገለጹት፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...