በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል በሦስት ምዕራፍ ተደርጎ በነበረው ጦርነት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸው ተቀጥፏል፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አረጋውያን፣ ሕፃናት ወጣቶች፣ ጎዳና ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተከሰቱት የአገሪቱ ሰላም በመደፍረሱ መሆኑ ይታመናል፡፡ ነገሩም ሥር ሰዶ የተለያዩ ችግሮች ቢከሰቱም በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ስምምነት ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር በቅርቡ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ ግጭት መፈጠሩ ብዙዎችን ከማወዛገብም ባለፈ የኢትዮጵያ ሰላም ሊታወክ ችሏል፡፡
ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ ፖለቲካዊ ቅርፅን መያዙን በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይሁን እንጂ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ‹‹ዓለም አቀፍ የማነቃቃት አገልግሎት›› የተሰኘ ድርጅት ቅዳሜ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኩል ተወክለው ከመጡ ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዓለም አቀፍ የማነቃቃት አገልግሎት ድርጅት ዳይሬክተር ዳንኤል ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደፈረሰ የመጣው የሰላም ሁኔታ ዕልባት እንዲያገኝና በሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመቅረፍ ትኩረት ተደርጎ መሠራት ይኖርበታል፡፡
በተለይ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል በተላለፈው መልዕክት የተነሳ፣ በርካታ ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መከናወኑንና የኢትዮጵያም የሰላም ሁኔታ ደፍርሶ እንደነበር ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ መሠረት የተላለፈውን መልዕክት በመቀበል ለሦስት ቀናት ጥቁር ልብስ በመልበስና ፆም ፀሎት ሲያከናውኑ በነበሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የደረሰው ድብደባ ከፍተኛ መሆኑን፣ ይህንንም በመቃወም የመገናኛ ብዙኃን፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ሰፋ ያለ መግለጫ እንደሰጡበት አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሰላም መደፍረስና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ተቋሙ ሰፊ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ዳንኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የደረሰውን በደል ማውገዛቸውንና መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አጽንኦት መስጠታቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ተቋሙ እየሠራ እንደሆነ፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መንግሥት አንድ ወጥ የሆነ አሠራር መዘርጋት እንደሚኖርበትም አስረድተዋል፡፡
ከሁሉም በላይ አንዱ የሃይማኖት ተቋም የሌላውን የሃይማኖት ተቋም የመንቀፍ ሁኔታ ሲታይ እንደነበር፣ ይህም የኢትዮጵያን የሰላም ሁኔታ ከማደፍረስም በላይ እርስ በርስ ጥላቻን ሊፈጥር እንደሚችል አክለዋል፡፡
በቅርቡም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት በኩል ተላልፎ የነበረውን ትዕዛዝ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በሚገባ ደረጃ ተቃውሞት እንደነበር፣ በወቅቱ ችግሩ ፖለቲካዊ ቅርፅ ሊይዝ መቻሉን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ጉዳዩ ወደ ሌላ መንገድ ማምራቱንና አብዛኛውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው መዘገብ ሲኖርባቸው፣ ወደኋላ ማፈግፈጋቸው ብዙዎችን ማስቆጣቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኩል የተፈጠረው ችግር በርካታ የሃይማኖት ተቋሞችን ያስቆጣ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተዳደርና ፋይናንስ መምርያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ እሸቴ ተናግረዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የራሷ የሆነ አሠራር እንዳላትና ምንም በማይታወቅ መንገድ ራሳቸውን በመሾም የሃይማኖት ክብር ዝቅ ያደረጉ ‹‹ምዕመናን ነን›› ባዮች ቦታ መስጠቱ የአገሪቱን ሰላም ሊያደፈርሰው መቻሉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት በጣም የቆየች ተቋም፣ ጠንካራ መዋቅር፣ ብዙ ሊቃውንት ያላት ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ችግሯን በራሷ መንገድ መፍታት እንደምትችልና በዚህ ጉዳይ ላይም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ጉዳይን ከሕግም አንፃር እንኳን ብናየው የራሱ የሆነ መሥፈርት እንዳለው፣ ይህም ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ከሰሞኑ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ የተከሰተውን ችግር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች አሠራር ያፈነገጠ ነው ብሏል፡፡
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ የአደረጃጀት ችግር መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን፣ በተለይ እንደ እነዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋሞች ገለልተኛ ሆነው መዘገብ እንደሚኖርባቸው ጋዜጠኛ ጥበቡ ገልጿል፡፡
ጉዳዩን ተከታትለው ያልዘገቡ የመገናኛ ብዙኃን በአደባባይ ወጥተው ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በወቅቱ ተነስቶ የነበረው ችግር በርካታ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ላይ ድብደባ ከመድረስም አልፎ ሕይወታቸውን ያጡ መኖራቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡