Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የወለቱ ሱቅ

ትኩስ ፅሁፎች

የወለቱ ሱቅ ከአዲስ አበባው ካራቆሬና አለምገና መካከል የምትገኝ ቦታ ነች:: ዘመኑ ቢረዝምም የወለቱ ሱቅ ዛሬም ስሟ አልጠፋም። ታክሲዎች እንደመነሻና መድረሻ ተጠቅመውባት ወለቱ ሱቅን ሲጠሯት ይሰማል። በእርግጥ የወለቱ ሱቅ ዛሬ የለችም። ያለው ስሟ ብቻ ነው። ወለቱ ሱቅ በእርግጥ ልዩ ልዩ ሸቀጥ የሚሸጥበት ሱቅ አልነበረችም::

በዘመኑ የወለቱን ሱቅ የማያውቅ ቱጃር የለም። ከሲዳሞና ከጅማ  ቡና፤ ቆዳ ፤ ማርና ቅቤ በአጋስስ ጭነው የሚመላለሱት ነጋድራሶች ከእነአሽከሮቻቸው ካስማና ተራዳቸውን አቁመው ድንኳናቸውን ተክለው ከረጅም ጉዞ ድካማቸው እፎይ የሚሉት፣ ውሎና አዳራቸውን የሚያደርጉት ከወለቱሱቅ ነበር። ወለቱ ሱቅ የሚለውን ስያሜ የሰጡት እነኝሁ ነጋድራሶች ነበሩ፡፡ ነጋድራሶቹ ከወለቱ ሱቅ የሚያርፉት ያለ ምክንያት አልነበረም። የወለቱን እንጀራ በሽሮ ወጥ ፤ ዳቦና ጠላ ለመኰምኰም ነው።

እንደዛሬው በየቦታው ጐራ ብሎ የትላንቱን ዓይነት ብሬታና አረንቻታ፣ ወይም የዛሬውን ዓይነት ልዩ ልዩ ለስላሳና ቢራ መጐንጨት በማይቻልበት በእዚያ ዘመን፣ የዶሮ አይን የሚመስለውን የወለቱ ጠላ ፣ እጅ አስቆርጥሜ ከነበረው እንጀራ በሽሮ ወጧ ጋር አወራርዶ ማለፍ የተለመደ ነበር። የወለቱን ሱቅ የሚያዘወትሩት ነጋድራሶች ብቻ አልነበሩም፤ የቅርቡና የሩቁ የአዲስ አበባ ነዋሪ በተለይም የወለቱ ሠፈር ነዋሪ የወለቱን ሱቅ ሳይረግጥ መዋል አይሆንለትም።

የነጋድራሶች አሽከሮችም ቢሆኑ ከወለቱ ሱቅ መድረስንና እረፍት ማድረግን በእጅጉ ይወዱታል። እነሱም ምክንያት ነበራቸው። እንደነጋድራሶቹ ገንዘባቸውን አውጥተው የወለቱን ጠላ፣ የሽሮ ወጥና ዳቦ ለመግዛት አቅሙ ባይኖራቸውም “ውብ” በሚጠሯት የስፌት ቦቃቸው ሊጥ አቡክተው ለዕለት ጉርሳቸውና ለቀጣይ  ብለው ጉዞ ስንቃቸው እንዲሆናቸው ቂጣቸውን የሚጋግሩበት ቦታ ስለሆነች ነው። የሚገርመው የወለቱ ሱቅ ማረፊያ ብቻ አልነበረችም፤ መቃጠሪያም ነበረች። የንግዱ፣ የሥራው፣ የፍቅሩ ወዘተ . . . ብቻ የቀጠሮው አይነቱ ብዙ ነው ለእዚህ ሁሉ ዋንኛ ተዋናይ ወለቱ ነች።

የእነነጋድራስ የጭን ገረዶችም ቢሆኑ ወለቱን ታከው ከድንኳን ዘልቀው ፍቅር ሰጥተው ፍቅር ለመውሰድ የወለቱ ሱቅ ማዕከል ነች። በዘመኑ አገላለፅ ወለቱ ሱቅ “እንጋጠም” ከተባለ ከወለቱ ሱቅ መድረስ ግድ ነው ቀጠሮም ባይኖር በአካባቢዋ ከታለፈ ከወለቱ ሱቅ ጐራ ማለት አይቀሬ ነው።

– በለጠ አበበ ‹‹ድሮና ዘንድሮ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ››

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች