ልብ ለልብ የተራራቁ ሰዎች በቅን ልቡና ጨዋታ ሲጫዋወቱ አንዱ የተናገረውን አንደኛው በብዙ ዓይነት መጥፎ መንገድ ከመተርጎም ብዛት የሚያቀያይም አሽሙር ያገኝበታል፡፡ ቅን መንገድ የሚከተሉ የተማመኑ ሰዎች ግን የተባረኩ ናቸው፡፡
***
ጥቂት ሽቱ የፈሰሰበት ቦታ በአፈሩ ላይ እስከ ብዙ ጊዜ ድረስ መልካም መዓዛ ይገኝበታል፡፡ ትልቅ ሙያ ያለው ሰው ሲፈጠርም እንዲሁ እንኳንስ በሕይወቱ ሳለ ከሞተም በኋላ ቢሆን የተወለደባትን አገር ሲያመሰግናትና ሲያስከብራት ይኖራል፡፡
***
ጠላት የለኝ ጠብም አልወድም ብሎ የዕለት ተግባሩን በሰላም እየሠራ ከቤቱ አርፎ የሚቀመጥ ሰው ሰላምን የሚያገኝ ቢሆን ኖሮ እጅግ መልካም ነበር፡፡ ግን ክፋቱ ያለምክንያት ጠብ ያለህ ዳቦ እያሉ እቤቱ ድረስ መጥተው ሰው ሰውን የሚበጠብጡ ሰዎች በዓለም ላይ ስለሞሉ ሰው ያለጠባዩ ታጥቆና ለጠብ ተሰናድቶ መቀመጥ ግዴታ ሆኖበታል፡፡
***
በግልጥ ከታወቀው ጠላት ይልቅ ወዳጅ እየመሰለ የጠላትነት ሥራ የሚሠራ ሰው በጣም እንደሚጎዳና ሳይታወቅበት እንደሚያጠፋ የታወቀ ነው፡፡ አንድ ሊቅ ሲናገር አምላኬ ሆይ እኔ በዙሪያዬ ያሉት ጠላቶች እንዳያጠፉኝ ስታገል አንተ ደግሞ አደራህን ከወዳጆቼ ሰውረኝ አለ ይባላል፡፡
ከበደ ሚካኤል ‹‹የዕውቀት ብልጭታ››