የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ኢንተርናሽናል የመረብ ኳስ ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ፣ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ እንዲወጣ የራሳቸውን አሻራ አበርክተዋል፡፡ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተቀብለው ስፖርቱን አገልግለዋል፡፡
በመረብ ኳስ ሲኒየር ዓለም አቀፍ የቪሊቦል ኢንስትራክተር በመሆን ከ150 በላይ አገሮች በመሄድ ሥልጠናዎችን በመስጠት አገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት ችለዋል፡፡፡
ኢንስትራክተር ዓለማየሁ በተለይ ስለኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ፣ ስፖርት አደረጃጀት እንዲሁም መንግሥታዊ የስፖርት ድርሻ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለአገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች፣ ለባለድርሻ አካላት፣ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለታዋቂ የስፖርት ድርጅቶችና ክለባት እንዲሁም ለሁሉም የስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎች ጥናት ማቅረብ ችለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መረብ ኳስ አባት›› በሚል የሚታወቁት ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ ወዳጅ ዘመድ፣ ከፍተኛ የስፖርት አመራሮች፣ የሙያ ልጆቻቸውና የስፖርት ቤተሰቡ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ባለትዳርና የሁለት (ወንድና ሴት) ልጆች አባት ነበሩ፡፡