Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቫይታሚንና ማዕድን ያልበለፀገ የስንዴ ዱቄት ለገበያ እንዳይቀርብ ሊከለከል ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቫይታሚንና በማዕድን ያልበለፀገ የስንዴ ዱቄትን በማምረትም ሆነ በማስመጣት ለገበያ ማቅረብ እንደማይችል፣ የወጣው አስገዳጅ ድንጋጌ ከሰኔ 2015 ጀምሮ ስለሚተገበር አምራቾችና አስመጪዎች ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

የምግብ፣ የመጠጥና የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ ለዱቄት አምራቾችና አስመጪዎች በላከው ሰርኩላር፣ የስንዴ ዱቄት በተመረጡ ቫይታሚንና ማዕድን ማበልፀግ አስገዳጅ እንዲሆን በተወሰነው መሠረት፣ አስገዳጅ ደረጃውን በመተግበር በተሰጠው ጊዜ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገልጿል፡፡ አምራቾች ዱቄቱን ለማበልፀግ የሚያስችላቸውን መሠረተ ልማት በተሰጠው ጊዜ አሟልተው፣ በተፈለገው ደረጃ ማምረት ካልጀመሩ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ እንደማይችሉም አስታውቋቸዋል፡፡

ቀደም ብሎ ለዚህ አስገዳጅ ደረጃ ተፈጻሚነት የሁለት ዓመት የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ አስገዳጅ ደረጃውን ያፀደቀው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ምክር ቤት በማዕድን የበለፀገ የስንዴ ዱቄት የእፎይታ ጊዜ ሁለት ዓመት የሚለው ስህተት በመሆኑ፣ ወደ አንድ ዓመት ዝቅ እንዲል ማስተካከያ በመሰጠቱ አስገዳጅ ድንጋጌው ሰኔ 2015 የሚተገበር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን ማስተካከያ በሰርኩላሩ ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ በዚሁ መሠረት አምራቾች በቀሪዎቹ ወራት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት ተግባራቸው ይግቡ ብሏል፡፡

ይህ አስገዳጅ ደረጃ ቀደም ብሎ በፈቃደኝነት እንዲተገበር የፀደቀ ቢሆንም፣ አንድም አምራችና አስመጪ ሊተገብረው ባለመቻሉ በአስገዳጅነት እንዲተገበር ሊወሰን ስለመቻሉ ታውቋል፡፡

የስንዴ ዱቄት ለማበልፀግ አስገዳጅ ደረጃን በተመለከተ በባለሙያዎች ከተሰጠ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ ይህ አስገዳጅ ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበትና በኢትዮጵያ ዘግይቶ የተተገበረ ነው፡፡ አስገዳጅ ደረጃው እስካሁን ያለመተግበሩም ቀላል የማይባል ጉዳት ያስከተለ ስለመሆኑ አኃዛዊ መረጃዎች ተጠቅሰው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን አምራቾች ለቫይታሚን ማበልፀጊያ የሚሆነውን ምርት በማስገባትና የመደባለቂያ መሣሪያውን በመትከል፣ የበለፀገውን ምርት ማምረት ግዴታቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ የማበልፀጊያ ግብዓቶቹም የተለዩ ስለመሆናቸውም ታውቋል፡፡

አገራዊ የሥነ ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይም በትንሽ መጠን ለሰውነት የሚያስፈልገው (Micronutrients) ነገር ግን ጠቀሜታቸው እጅግ ብዙ የሆኑትን የቫይታሚንና ማዕድን እጥረት ለመቀነስ፣ ምግብን ማበልፀግ አዋጭና ውጤታማ ስትራቴጂ መሆኑ ታምኖበት በተግባር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከ425 በላይ ዱቄት አምራቾች ያሉ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ ይህንን አስገዳጅ መመርያ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ በስም ዝርዝር የገለጻቸው 199 አምራቾች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች