ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር መሀል መርካቶ ቅርንጫፍ በአካውንቱ በቂ ገንዘብ ለሌለው ግለሰብ የ45 ሚሊዮን ብር ሲፒኦ (CPO) ማዘጋጀቱ እያወዛገበ መሆኑ ታወቀ፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው ሲፒኦ እንደሚያሳየው፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ለተባለ ድርጅት አቶ ሀበን ግዑሽ ከተባሉ ግለሰብ አካውንት ተቀናሽ ተደርጎ እንዲከፈለው፣ 45 ሚሊዮን ብር መጠን ያለው ሲፒኦ በሲፒኦ ቁጥር 60389434 ተሠርቶ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ኦላ ኢነርጂ የተባለው ድርጅት ታኅሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቅርንጫፉ ገንዘቡ ተቀናሽ ተደርጎ መግባቱን ማረጋገጫ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ የባንኩ ቅርንጫፍ መልስ ሲሰጥ፣ አንድ የባንክ ብድር ለመውሰድ ሒደት ላይ የነበረ ኩባንያ የቅድሚያ ዝግጅት ሒደቱ ሲያልቅለት ወደ አቶ ሀበን ሒሳብ 45 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዲደረግ አዝዞ እንደነበረ ይገልጻል፡፡
‹‹ኩባንያው በአካውንቱ ከሚለቀቅለት ጠቅላላ ብድር ውስጥ ወደ አቶ ሀበን ግዑሽ ሒሳብ 45 ሚሊዮን ብር እንዲተላለፍ፣ እንዲሁም አቶ ሀበን ግዑሽ በዕለቱ ለኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ 45 ሚሊዮን ብር ሲፒኦ እንዲዘጋጁ›› ማዘዛቸውን በቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ደምሴ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ለኦላ ኢነርጂ ያሳውቃል፡፡
ደብዳቤው በማስከተልም ብድር ሊወስድ የነበረው ኩባንያ እንደ ማስያዣ ንብረት ማሳገድ ሒደቶችን ባለማጠናቀቁ ምክንያት ‹‹የተዘጋጀው ሲፒኦ የተሰረዘ መሆኑንና ከባንኩ ወጪ ሆኖ ለደንበኛው ያልተሰጠ መሆኑን እናረጋግጣለን፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ምንም እንኳን ቅርንጫፍ ገንዘቡ ወጪ ተደርጎ አለመከፈሉንና መሰረዙን ቢገልጽም፣ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን የያዘ ሲፒኦ መሥራቱን ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡
በተያያዘም ከንብ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት የሪቴልና ኤስኤምኢ ባንኪንግ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ታደሰ ተፈርሞ ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የወጣ ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ከላይ በተጠቀሰው የሲፒኦ ቁጥርና የገንዘብ መጠን ለአቶ ሀበን ግዑሸ ‹‹የተሰጠ የክፍያ ሰነድ ወይም ሲፒኦ የሌለ መሆኑን፤›› ያስረዳል፡፡
የንብ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለሪፖርተር እንዳስረዱት ባንኩ ሲፒኦውን ወጪ ያላደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን ከቅርንጫፉ በወሰዱት መረጃ ለአንድ የነዳጅ ኩባንያ ቀደም ሲል ተፈቅዶ የነበረው የ45 ሚሊዮን ብድር እንደነበረና የዕግድ ሥነ ሥርዓት ላይ እያለ ሲፒኦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
‹‹ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ቅርንጫፉ ሲፒኦውን አዘጋጅቶት ነበር፡፡ ተዘጋጅቷል ማለት ግን ለደንበኛው ተሰጥቷል ማለት አይደለም፤›› ያሉት የባንኩ ሴንትራል አዲስ አበባ ዲስትሪክት ማናጀር አቶ አሸናፊ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡
አቶ አሸናፊ አክለው ለሪፖርትር ሲገልጹ፣ ሲፒኦ ማዘጋጀት አንደኛው ሒደት እንደነበረና የብድሩ ዕግድ ሥርዓትን ጠብቆ ስላልመጣ ገንዘቡም ፈሰስ አልተደረገም፣ በመሆኑም ‹‹ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ የነበረው ሲፒኦ ተሰርዟል›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ ሲፒኦውን እንደ ባንክ አልሰጠንም፡፡ የዚህ ሲፒኦ ዋና ቅጂ ተሰርዞ በእጃችን ነው የሚገኘው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ክፍያ የተፈጸመበት ሲፒኦ እንደ ማስረጃ ሆኖ ከሌሎች ሰነዶች ጋር በአቶ ሀበን ግዑሽ አቤቱታ አቅራቢነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታኅሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሄደን የሐራጅ ሽያጭ እንዲሰረዝ ተጠይቆበታል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው ታኅሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጻፈው አቤቱታ እንደሚያትተው፣ የፍርድ ባለመብት ኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ከፍርድ ባለዕዳ አቶ ሀበን ግዑሽ ላልተከፈላቸው 54 ሚሊዮን ብር ፍርድ ቤት በወሰነው ውሳኔ መሠረት ታኅሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት የተካሄደው የፍርድ አፈጻጸም ፍትሐዊ እንዳልነበረ ነው፡፡ አቤቱታ አቅራቢው የፍርድ ባለዕዳ የነበረበትን ገንዘብ ለፍርድ ባለመብት እስከ ጨረታው የተካሄደበት ቀን ድረስ በተለያዩ ሲፒኦዎች ሲከፍል እንደነበር በአቤቱታው ጠቅሶ የነበረ ሲሆን፣ በማስረጃነት ከቀረቡት ሲፒኦዎችም አንደኛው ይህ በንብ ባንክ የተዘጋጀው ሲፒኦ ነበር፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ በቀረበበት ቀን ታኅሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ያስተላለፈው ትዕዛዝ፣ የፍርድ አፈጻጸም ያካሄደው የሐራጅ ሒደት ከፍርድ ቤቱ ‹‹ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ባለበት ሁኔታ ታግዶ እንዲቆይ፤›› የሚል ነበር፡፡