በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ሁነቶች፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅራኔ ለመፍጠርና ለማባባስ የሚተጉ አካላት መብዛታቸውን ነው የሚያመለክቱት፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ ለመፍታት የሚበጁ መላዎችን ከማፈላለግ ይልቅ፣ በውግዘትና በክስ የተሞሉ አቤቱታዎችንና እሮሮዎችን በአየቅጣጫው በማስተጋባት ቅራኔ መለጠጥ የዘወትር ተግባር ሆኗል፡፡ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተነሳው ውዝግብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገ ውይይት ፈር ይይዛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በግራና በቀኝ እያፈተለኩ የሚወጡ የሁለት ጽንፍ መረጃዎች ግን ውዝግቡን አባብሰው የሚያስቀጥሉ ነው የሚመስሉት፡፡ በፖለቲካ ወጀብ ውስጥ ሆኖ መላ ቅጡ ያለየለት ይኸው ጉዳይ የብዙዎችን ልብና አዕምሮ ገዝቶ በያዘበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት፣ በመስኖ የበቀለ ስንዴ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ሊደረግ መሆኑ ይፋ ሲሆን ደግሞ ሌላ አጀንዳ ተከፍቶ ጭቅጭቁ ደርቷል፡፡ ከአንድ አጀንዳ ወደ ሌላ አጀንዳ በከባድ ፍጥነት ለመሸጋገር ከፍተኛ ተነሳሽነት ያለውን ያህል፣ ከኢትዮጵያ ምድር ንትርክና ዱላን ቀንሶ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት ማቃቱ ያስደንቃል፡፡
የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምሁራን በአገራዊ ምክክር መድረኩም ሆነ በሌሎች በሚገናኙባቸው መድረኮች፣ ቅራኔ ከመፈልፈል ውጪ ፋይዳ እያጣ ያለውን የፖለቲካ አካሄድ በትኩረት መርምረው መላ ካልፈለጉ የአገሪቱ ሁኔታ አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ፋታ ወስዶ መነጋገርና የተለያዩ ፍላጎቶችን በበቂ መጠን መረዳት የሚያስችል ምኅዳር መፍጠር የግድ መሆን አለበት፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ጉዳዮችና በሌሎችም ላይ የጋራ ራዕይ በሌለበት አገር ውስጥ ስለልማትና ዕድገት ማሰብም ሆነ ማቀድ አዳጋች ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ቅኝ ባለመገዛትና በታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ምክንያት በዓለም አቀፍ መድረክ የተከበረ ስም ያላት ኢትዮጵያ፣ የተማሩ ልጆቿ በእነዚህ ሁለት ድንቅ የታሪክ ክስተቶች ላይ እንኳ ተመሳሳይ ምልከታ ጎድሏቸው ይነታረካሉ፡፡ ሌሎች የታሪክ ሰበዞችማ የተለያዩ አገሮች ሰዎች ነው የሚያስመስሏቸው፡፡ አንደኛው ወገን ኢትዮጵያዊነትን በወጉ መሸከም አቅቶት አላስፈላጊ ውዝግብ ሲፈጥር፣ ሌላው ደግሞ ሊያኮራው ከሚችለው የኢትዮጵያዊነት ማንነት ጋር ጠብ ፈጥሮ ሌላ ራስ ምታት ይሆናል፡፡
የማንኛውም ፖለቲከኛ ግብ ሥልጣን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሥልጣን የሕዝብ ሉዓላዊ ሀብት መሆኑ ተረስቶ፣ ፖለቲከኞች በሚያማልሉ አጀንዳዎች የሕዝብን ልብ ከመግዘት ይልቅ ዋነኛ ሥራቸው ሴራ ሆኗል፡፡ ሕዝብ በቂ ገቢ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ፅዱና ምቹ መኖሪያ፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የትራንስፖርትና የሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝባቸው ገበያዎች፣ እንዲሁም ልጆቹ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው ከፍ ያለ ደረጃ እንዲደርሱለት ይፈልጋል፡፡ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስፈልገው በጥናትና በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ተግባር ማከናወን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ፕሮግራም ወይም ማኒፌስቶ አለን የሚሉ ፖለቲከኞች ሕዝብ ፊት ቀርበው በዝርዝር ማስረዳት ሲጠበቅባቸው፣ እነሱ ግን ከሕዝብ ዓይን ሸሽተው ከመጋረጃ ጀርባ ሴራ እየጎነጎኑ የሕዝብ ሕይወት ያመሰቃቅላሉ፡፡ ፖለቲከኞች አላስፈላጊ ቦታ ጥልቅ እያሉ እሳት እየጫሩ ዕድሜያቸውን ይግፉ እንጂ፣ ሕዝቡ እንደሆነ ምንም ጠብ የሚልለት አጥቶ ችግር ይጫወትበታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ሌላው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ዜጋ ከመንግሥት ከሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የሕይወት፣ የንብረትና የአካላዊ መብት ጥበቃ ይጠቀሳሉ፡፡ የዜጎችን ሕይወት፣ ንብረትና አካል ከማናቸውም አደጋ መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ዜጎች ለሕይወታቸው የሚፈሩ ከሆነ፣ ለንብረታቸው ዋስትና ከሌላቸውና ለአካላዊ ጥቃት እንደሚጋለጡ ሥጋት ከገባቸው የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ የአገሪቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእነዚህ መሠረታዊ መብቶች ላይ ያላቸው ምልከታ፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም መረጋገጥ አለበት፡፡ ፖለቲካውን የሚዘውሩት በአገኙት አጋጣሚ ዲስኩር ለማሳመሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከበፊት ጀምሮ እስካሁን የሰው ልጅ ሕይወት፣ ንብረትና አካል ከአደጋ ጋር እንደተፋጠጠ ነው ያለው፡፡ በየቦታው ሞት ሞልቷል፣ ዘረፋው ልክ የለውም፣ የአካል ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ኢትዮጵያን ሁሌም በዓለም አቀፍ የህሊና ሙግት ችሎት የተከሳሽ ሳጥን ውስጥ እንዳስቆማት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሁለቱም መብቶች በፊትም አሁንም በስፋት እየተጣሱ ነው፡፡ በዚህ ላይ እንኳ መግባባት አልተቻለም፡፡
ጀርመናዊው የኮሙዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም ጠንሳሽ ካርል ማርክስ፣ ‹‹…ፈላስፎች ዓለምን በተለያዩ መንገዶች ይተረጉማሉ፣ ዋናው ቁምነገር ግን ዓለምን መለወጥ ነው…›› ብሎ ነበር፡፡ ሩሲያዊው ደራሲና ፈላስፋ ሊዮ ቶልስቶይ፣ ‹‹…ብዙዎች ዓለምን ስለመለወጥ ያስባሉ፣ ራሳቸውን ለመለወጥ ግን ሲቸገሩ ይታያሉ…›› ማለቱም ይነገርለታል፡፡ ማርክስ ዓለምን ከመተርጎም በላይ የመለወጡን ፋይዳ ጠቃሚነት ሲያወሳ፣ ቶልስቶይ ደግሞ ከዚያ በፊት ራስን የመለወጥ ተግዳሮት ሲያስታውስ፣ እዚህ መሀል ያለውን ወርቅ ፈልቅቆ የማውጣት ተግባር የፖለቲካ ምሁራኑና ልሂቃኑ ሥራ መሆን አለበት፡፡ ነጋ ጠባ ሴራ ከመጎንጎንና እርስ በርስ ከመጠላለፍ አባዜ በመውጣት ለተሻለ ለውጥ መነሳት ሲገባ፣ አገርን እያደር መቀመቅ የሚከቱ ችግሮችን መፈልፈል ነው የተያዘው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ መከባበር፣ መነጋገር፣ መደማመጥና መግባባት የሚያስችል የአስተሳሰብ ለውጥ ሲኖር አንዱ ለሌላው ወዳጅ እንጂ ጠላት አይሆንም፡፡ እነዚህ መልካም ነገሮች በመጥፋታቸው ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ውሸት፣ ብሶትና ጥላቻ ብቻ ናቸው አየሩን የሞሉት፡፡ አስተሳሰብን ለመለወጥ ፈቃደኝነት ሲኖርና መቀራረብ ሲጀመር ግን ማንም የማንም ጠላት አይሆንም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ የቤት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ያልቻሉ ቂመኛ ፖለቲከኞች ግን ይህንን አይፈልጉም፡፡ አዲሱ ትውልድ ግን መንቃት ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የምትታወቀው አገራቸውን በማያስደፍሩ ጀግኖች ልጆቿ ነበር፡፡ አውሮፓውያን ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ሲቀራመቱ ብቻዋን ቆማ ያልተደፈረች አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል፣ እነዚያ አገራቸውን ከራሳቸው በላይ የሚያፈቅሩ ኢትዮጵያውያን ወደር የሌለው ታላቅ መስዋዕትነት የከፈሉበት ነበረ፡፡ ይህንን አንፀባራቂ ታሪክ የራሳቸው ያደረጉ አፍሪካውያንና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች በታላቅ ኩራት ኢትዮጵያን ሲያሞግሱ፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ጥልቅ አዘቅት ውስጥ የሚከት ግርግርና ዕብደት ውስጥ መግባት በጊዜ ካልቆመ የከፋ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ወጉ በአንድነት ለአገር መምከር፣ መወሰንና መተግበር መሆን ሲገባው በዓለም ፊት ማዋረድ ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት የምትከበረው ሌሎች ጭምር በሚመሰክሩት ሥራ እንጂ፣ ሠፈርና ሠፈር እየለዩ በሚደረግ መወጋገዝና መተናነቅ አይደለም፡፡ አንዱ ችግር አበቃ ሲባል ሌላ ብቅ እያደረጉ አገርን ጤና መንሳት ጤነኝነት ስላልሆነ፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ማውጣት ይቅደም!