Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነ ኤርትራ ተቃውሞ አይኖራትም›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ...

‹‹የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነ ኤርትራ ተቃውሞ አይኖራትም›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ቀን:

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ሳይጓደል ተግባራዊ ከሆነ መንግሥታቸው ተቃውሞ እንደማይኖረው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጹ። 

በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወግና በጦርነቱ መሳተፏ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችና የጦር ወንጀሎችን የአገሪቱ ወታደሮች መፈጸማቸው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትም ሆነ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተረጋግጧል። 

በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ከፍተኛ እልቂት ያስከተለው ይህንን ጦርነት በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ በተፈረመ የሰላም ስምምነት የተገታ ቢሆንም፣ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበረችው ኤርትራ የሰላም ስምምነቱ አካል አለመሆን የስምምነቱ ተግባራዊትን ሊያሰናክል እንደሚችል ተሠግቶ ነበር።

ከቀናት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በኬንያ ጉብኝትና ለመገናኛ ብዙኃን ቃለመጠይቅ የሰጡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በቅንነት ሙሉ በሙሉ ከተተገበረ ኤርትራ ምንም ተቃውሞ አይኖራትም፤›› ብለዋል።

ነገር ግን የስምምነቱ ይዘት ምንም ሳይጓደል ሙሉ በሙሉ መተግበሩ ጥንቃቄ በተሞላበት ክትትል መረጋገጥ እንዳለበት ገልጸዋል።

‹‹ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት መጥፋት አስከትሏል›› ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹ከዚህ አንፃር ጦርነቱን የቀሰቀሱት ኃይሎች ተጠያቂነት ጉዳይ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ጦርነቱን በመቀስቀስ ረገድ ሕወሓት ላይ ጣታቸውን የቀሰሩ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የአሜሪካ መንግሥት ከጀርባ ሆኖ ሕወሓት ጦር እንዲያነሳ ግፊት አድርጓል ሲሉ ከሰዋል።

‹‹በ2018 በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት በቀጣናውና ከዚያም ያለፈ ብሩህ ተስፋን አስፍኗል። ነገር ግን እነዚህ ተስፋ ሰጪ ዕድገቶች በአሜሪካ መንግሥት አስተዳዳሪዎች ላይ ጭንቀትን ፈጥሯል። በዚህም ምክንያት ሕወሓት በግዴለሽነት ወታደራዊ ጥቃት እንዲከፍት የአሜሪካ መንግሥት ከጀርባ ሆኖ ገፋፍቷል። ሌላው ሕወሓትን ወደ ጦርነት ለመግባት ያስደፈረው አሳዛኝ ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የሠራው የተሳሳተ የኃይል ሚዛን ስሌት ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ያመኑበትን አመክንዮ አስቀምጠዋል።

በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት በኬንያ ያፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ፣ ኤርትራ ዳግም ወደ ኢጋድ አባልነቷ ለመመለስ መወሰኗን አስታውቀዋል።

ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ሆነው ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ኢሳያስ አፍወርቂ፣ ‹‹የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ኤርትራ ወደ ኢጋድ እንድትመለስ ሲጠይቁኝ ምንም ጥያቄ የለውም እንመለሳለን ነው ያልኩት። አዎ፣ ይህንን ቀጣናዊ ተቋም ለማነቃቃት ውጤታማ የማድረግ ሐሳብ ይዘን ወደ ኢጋድ በድጋሚ እንመለሳለን፤›› ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አክለውም በኢጋድ ውስጥ ሪፎርም በማካሄድ ተቋሙን እውነተኛ፣ የተግባርና ውጤት ተኮር ድርጅት ለማድረግ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ጋር መስማማታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ከቀጣናዊ አሠራር ውጭ በግለሰብ ሐሳቦችና በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ውጤታማ አይደለም። በቀጣናው ውስጥ ሰፊ ውህደትን መፍጠር ካልቻልን የተናጠል ግቦችን ማሳካት አንችልም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው፣ ኤርትራ ወደ አባልነቷ ለመመለስ መወሰኗ በኢጋድ ውስጥ አዲስ መነሳሳትን እንዲሁም ቀጣናውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በመምራት ረገድ አዲስ ጥበብን ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

አክለውም፣ እ.ኤ.አ. በ2018 በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትና የአዲስ ግንኙነት ለቀጣናው መረጋጋት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አጋጣሚ መሆኑንም አውስተዋል።ይሁን እንጂ የኤርትራ ጦር እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አለመውጣቱ ይነገራል።

ይህንን አስመልክቶ በኬንያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግን ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡ አድበስብሰው አልፈውታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...