Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበናሳ የጠፈር ምርምር ተልዕኮ ዕይታ ውስጥ የገባው አስትሮይድ ‹‹ድንቅነሽ›› የሚል ስያሜ ተሰጠው

በናሳ የጠፈር ምርምር ተልዕኮ ዕይታ ውስጥ የገባው አስትሮይድ ‹‹ድንቅነሽ›› የሚል ስያሜ ተሰጠው

ቀን:

የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል (ናሳ) የሚያካሂደው ሉሲ የተባለው የጠፈር ምርምር ተልዕኮ፣ በዕይታ ውስጥ ካስገባቸው የጠፈር አካላት (አስትሮይድ) ለአንዱ ‹‹ድንቅነሽ›› የሚል ስያሜ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ አፋር ሀዳር አካባቢ በተገኘችው ‹‹ድንቅነሽ›› በተባለች ቅሪተ አካል ስም የተሰየመው የአለት ስባሪ፣ ‹‹152830›› የሚል የቁጥር መለያም እንደተሰጠው ገልጿል፡፡

ናሳ ሉሲ የተባለውን የጠፈር ምርምር ተልዕኮውን ይፋ ያደረገው እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2021 ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ሉሲ የተባለችው የናሳ የህዋ መመልከቻ፣ በተለይ ወደ ትልቁ ፕላኔት ጁፒተር ምህዋር በቅርበት ምርምርና ቅኝት ስታደርግ መቆየቷ ታውቋል፡፡

የህዋ መመልከቻዋ ግዙፉን ፕላኔት ጁፒተር ከፊትና ከኋላ አጅበው የሚሽከረከሩ አስትሮይዶችንና የጠፈር አካላትን ስትመረምር መቆየቷን ናሳ ይፋ አድርጓል፡፡

ወደ ሉሲ ዕይታ ቀድሞ የገባውን አስትሮይድ (የአለት ስባሪ) ደግሞ ‹‹ድንቅነሽ 152830›› የሚል ስያሜ እንደሰጠው ናሳ አስረድቷል፡፡ ናሳ ለዚህ የጠፈር ምርምር ተልዕኮ ሉሲ የሚል መጠሪያ መስጠቱም ሆነ ቀድሞ ለተመለከተው አለት ‹‹ድንቅነሽ›› የሚል ስያሜ ማውጣቱ፣ በቀጥታ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ከተገኘችው የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል ጋር እንዲገናኝ ታስቦበት የተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ናሳ ይፋ እንዳደረገው ጁፒተርን ከፊትና ከኋላ አጅበው ችምችም ባለ መቀነት የሚሽከረከሩት አስትሮይዶች (የአለት ስብርባሪዎች)፣ አፅናፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለአራት ቢሊዮን ዓመታት የኖሩ የጠፈር አካላት ናቸው፡፡

እነዚህን የአለት ስብርባሪዎች በቅርበት ለመመልከትና ለማጥናት መቻል ደግሞ፣ ስለአፅናፈ ዓለም አፈጣጠር ለማወቅና ያልተፈቱ በርካታ እንቆቅልሾችን ለመፍታት ከፍተኛ ዕገዛ የሚያደርግ ነው ብሎታል፡፡

‹‹የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካልን ማግኘት መቻሉ ለቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ብዙ ምላሽ የሰጠ ግኝት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ‹ድንቅነሽ 152830› አስትሮይድን የሰው ልጅ በቅርበት መመልከት መቻሉ አፅናፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው፤›› በማለት ናሳ ስለአስትሮይዱ ግኝት ገልጿል፡፡

በጁፒተር ዙሪያ የሚሽከረከረው ‹‹ድንቅነሽ 152830›› የሚል የኢትዮጵያ ቅሪተ አካል ስያሜ የተሰጠው አስትሮይድ (የአለት ስባሪ)፣ ከአንድ ኪሎ ሜትር ያነሰ ስፋት ያለው መሆኑ ተነግሯል፡፡ ‹‹ድንቅነሽ 152830›› በሉሲ የጠፈር መመልከቻ ተልዕኮ በቅርበት እየተጠኑ ካሉ 10 አስትሮይዶች አንዱ ነው ተብሏል፡፡ ሉሲ የጠፈር መመልከቻ ተልዕኮ እ.ኤ.አ. ኅዳር 1 ቀን 2023 ለምድር ምኅዋር ቀረብ ብላ ትዞራለች ተብሏል፡፡ ስለድንቅነሽና ሌሎች አስትሮይዶች በጥራት የተነሱ ፎቶዎችና ተጨማሪ መረጃዎችን ወደ ምድር ትልካለች ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም. በአፋር ሀዳር በሚባል ቦታ የተገኘችው የ3.2 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠረችው የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት መስክ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት እንደሆነች ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ካስባሉ ቅሪተ አካሎች አንዷ የሆነችው ሉሲ (ድንቅነሽ) ዶናልድ ጆንሰን በሚመሩት የምርምር ቡድን እንደተገኘች ይነገራል፡፡ ቡድኑ ቅሪተ አካሉን ባገኘበት ወቅት ‹‹ሉሲ ኢን ዘ ስካይ ዊዝ ዳይመንድስ›› የተባለ የዝነኛው ቢትልስ ባንድ ሙዚቃ ይሰማ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ለቅሪተ አካሏ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የሚል ስያሜ እንደወጣላት ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...