Thursday, March 23, 2023

ኢትዮጵያውያንን ያስጨነቀው የሃይማኖትና የፖለቲካ ውጥረት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ፣ በሃይማኖት፣ ፍልስፍናና ሕግ ላይ ያጠኑት መሐመድ ግርማ ‹‹Religion Once Unified Ethiopia. It Can Again›› በሚል በአፍሪካን አርጊዩመንት ላይ ባስነበቡት ጽሑፍ፣ ሃይማኖት ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ በሰፊው ያነሳሉ፡፡ ሃይማኖት ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለማኖር እንደጠቀመ ሁሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለመከፋፈል እየዋለ ነው የሚል መላምት በዚህ ጽሑፋቸው ያቀርባሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሃይማኖት ጠንካራ የሆነባት አገር ናት፡፡ ክርስቲያኖችም ሆነ ሙስሊሞች አገሪቱ ስለታነፀችበት የሃይማኖት መሠረት የሚናገሩት አስደናቂ ታሪክ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም ታሪክ ውስጥ ጨለማ የሚባሉ የታሪክ ምዕራፎችን ተሻግራለች፡፡ ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲጠየቅ እነዚህን ጨለማ የታሪክ ምዕራፎች አገሪቱ ያለፈችው በሃይማኖቶቿ የፀና መሠረትና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሆነ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፤›› በማለት ነው ተመራማሪው የሚጠቅሱት፡፡

በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያውያን በጎበዝ አለቃዎች ተከፋፍለው፣ እርስ በርስ ሲዋጉና ሲተላለቁ መኖራቸውን፣ የአገሪቱ ህልውናና አንድነትም አደጋ ላይ መውደቁን ጸሐፊው መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡ ለሥልጣን የተራቡ የአካባቢ ገዥዎችና የጎበዝ አለቆች እርስ በርስ እየተዋጉ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ በጣሉበት ያን የዘመነ መሳፍንት ጨለማ ወቅት አልፋ ኢትዮጵያ አንድ የሆነችው ደግሞ በእምነት ተቋሞቿ ሕዝቡን አንድ የማድረግ የጎላ ሚና እንደሆን ታሪክ በማጣቀስ ምሁሩ ያቀርባሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የትግራይ ጦርነት ከተስፋፋ ወዲህ ሃይማኖት የአገርና የሕዝቦችን አንድነት ለማላላት እየዋለ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተለይተናል ያሉ የትግራይ አባቶች መኖራቸውን ያነሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውናም አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

 ‹‹ኢትዮጵያ ወዴት እያመራች እንደሆነ መፃኢ ዕጣ ፈንታዋ አይታወቅም፡፡ አገሪቱ እንዳትፈራርስና አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው ወገኖች ሚናቸውን ከወዲሁ መወጣት አለባቸው፤›› ይላሉ መሐመድ ግርማ በዚሁ ጽሑፋቸው፡፡ ጸሐፊው ይህን ሲሉም ሦስት ወሳኝ ያሏቸውን ነጥቦች ያነሳሉ፡፡

‹‹የመጀመርያው ወሳኝ ዕርምጃ የሃይማኖት ተቋማቱ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ለምን ለመከፋፈልና ለዚህ አደጋ በቃ ብለው ጠንካራ ጥያቄ ማንሳት መጀመር አለባቸው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ የእምነት ተቋማቱ ለሰላም በጋራ መቆም አለባቸው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማቱ በተቻለ መጠን ከፖለቲካው ርቀታቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ከሀቅና ከሞራል ጋር እንጂ ከፖለቲካ ጎን መቆም አይኖርባቸውም፤›› በማለት ጠንከር ያሉ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ችግር ሕዝብ ማቀራረብ፣ ማስታረቅና አንድ አድርጎ የአገር ህልውናን ከአደጋ መታደግ የመቻል አሳሳቢ አደጋ መሆኑን አቶ መሐመድ በጽሑፋቸው ያሰምሩበታል፡፡

ይህ በብዙዎች የሚነሳ ጉዳይ ይሁን እንጂ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የእምነት ተቋማቱ እንኳን የአገር ህልውና ለመታደግ የራሳቸውን ህልውና ማስጠበቅም ፈተና እንደሆነባቸው ነው የሚነገረው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ችግር ብዙዎች ለዚህ እንደ ማሳያ ያነሱታል፡፡ በተለይ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዕውቅና፣ ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግጋትና ቀኖና ውጭ የጳጳሳት ሹመት መካሄዱና ሲኖዶስ መቋቋሙ ታላቋን ቤተ እምነት ከባድ አደጋ ላይ መጣሉ በአሳሳቢነት እየተነሳ ይገኛል፡፡

ሃይማኖትና ፖለቲካ የሚኖራቸው ግንኙነትም ሆነ በመካከላቸው ያለው ርቀትና ቅርበት በዓለማችን ወጥ የሆነ መሥፈርት እንደሌለው ይነገራል፡፡ ሁለቱም ርቀታቸውን ጠብቀው ቢጓዙ የተሻለው መንገድ መሆኑን ብዙዎች ቢመክሩም፣ ነገር ግን አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ሲደበላለቁ የታዩበት አጋጣሚ እጅግ በርካታ ነው፡፡

‹‹ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው›› የሚለው ጉዳይ ከዴሞክራሲ መርሆዎች አንዱ ቢሆንም በተለያዩ የዓለም አገሮች ሃይማኖታዊ መንግሥት ወይም ወደ ሃይማኖት ያዘነበለ የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡

እስራኤል የአይሁድ አገር እንደምትባል ሁሉ በዙሪያዋ ባሉ በርካታ የዓረብ አገሮች ደግሞ እስላማዊ መንግሥታት መመሥረት የተለመደ ነው፡፡ በሼሪያ ሕግ የሚተዳደሩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በርከት ብለው ይታያሉ፡፡

ዴሞክራሲ በተንሰራፋባቸው የአውሮፓ አገሮችም ሆነ በአሜሪካ የፖለቲካ ቅቡልነትን ለማግኘት ሲባል ሃይማኖትን መጠጋት የተለመደ የፖለቲካ አሠላለፍ ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ‹‹የክርስቲያን ዴሞክራቶች›› እያሉ ራሳቸውን የሚጠሩ ፓርቲዎች ይታያሉ፡፡ የፖለቲካ ቅቡልነትን ለማግኘት የእምነት ተቋማትን ድጋፍ ማግኘት ወሳኝ የሆነባቸው እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮችም በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

ፖለቲካና ሃይማኖት ሚዛን ጠብቀው መጓዝ ካልቻሉና ውሉ በጠፋበት መንገድ ከተደበላለቀ አስከፊ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል የሊባኖስን ታሪክ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡ በርካቶች ናቸው፡፡ ከስድስት ሚሊዮን ብዙም የማይዘል ሕዝብ ባላት ሊባኖስ በሃይማኖት ስም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎቿ ቁጥር ሦስት እጥፍ መሆኑ ይነገራል፡፡ በክርስትናም በእስልምናም የሃይማኖት ግንዶች ሥር ወደ 18 የሚጠጉ የእምነት ተቋማቶች ተመሥርተዋል፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ የየራሳቸው ሃይማኖት ዘመም ፓርቲዎችን መሥርተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹የመካከለኛው ምሥራቅ አውሮፓ›› ትባል የነበረችው ሊባኖስ እርስ በርስ በመሻኮትና በየጊዜው በሚያገረሽ ግጭት ተዘፍቃ ለመኖር መገደዷን ብዙዎች ማሳያ በማድረግ ያቀርቡታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካው መስመሩን ጥሶ ከሃይማኖት ጋር አላስፈላጊ መደበላለቅና ግጭት ስለመፈጠሩ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ በቅርብ ሰሞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር የዚሁ ውጤት ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ግን ይህ ጉዳይ እንደማይመለከተው ነው ደጋግሞ የተናገረው፡፡

ለመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች፣ ለብልፅግና አባላትና አመራሮች የሚተላለፉ መልዕክቶችን የያዘ ተብሎ የተሰናዳው ሰሞነኛ የብልፅግና ሰነድ መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው ችግር ውስጥ እጁ እንደሌለበት አስቀምጧል፡፡

የፓርቲው ሰነድ እንደሚያትተው መንግሥት ከደሙ ንፁህ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ራሷ ቤተ ክርስቲያኗ ልትፈታው የሚገባ ጉዳይ ነው ይላል፡፡

ሰነዱ ይህን ቢልም መልሶ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር መነሻ ሃይማኖታዊ ብቻ አይደለም ይላል፡፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማሳካት የሚረዳ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ያላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ችግር መሆኑን ይህ የብልፅግና ሰነድ ይናገራል፡፡ እነዚህ ወገኖችም ችግሩን የፈጠረው መንግሥት ነው የሚል ትርክት በማኅበራዊ ሚዲያ መፍጠራቸውን ነው ሰነዱ የገለጸው፡፡

ይህ የመንግሥት አቋም የፀረ ሽብር የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዲሁም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ተደጋግሞ ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣቸው መግለጫዎች ላይ አቋሙን በግልጽ እንዳንፀባረቀው ከሆነ ግን ችግሩን በመፍጠር መንግሥት ተሳትፏል የሚለው ነጥብ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖተ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋት ጥሰት በመፈጸም ሕገወጥ የጳጳሳት ሲመት ያደረጉ ሰዎችና ተባባሪዎቻቸውን ቅዱስ ሲኖዶሱ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በማውገዝ ከቤተ ክርስቲያን እንደለያቸው ይፋ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉና በፅንፈኛ ፖለቲኞች እንዲሁም በሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር ጉዳዩ የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገለኛለች በማለት ነበር ሐሙስ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የወጣው የሲኖዶሱ መግለጫ በግልጽ ያስቀመጠው፡፡

መንግሥት ከደሙ ንፁህ ነኝ ቢልም ሕጋዊነት የሌለውንና በውግዘት ከቤተ ክርስቲያን እንዲነጠል ውሳኔ የተላለፈበትን ቡድን ሕጋዊ ሰውነት አላብሶ ለማቅረብ መሞከሩንም የሲኖዶሱ መግለጫ ኮንኖታል፡፡ በሃይማኖት ውስጥ አንገባም፣ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ሁለቱ ወገኖች በድርድርና በመግባባት ችግራቸውን ይፍቱ የሚል አቋም መንግሥት ማንፀባረቁ በሲኖዶሱ በጥብቅ ነው የተተቸው፡፡ የተለዩትን አካላት ሕጋዊ መብት ያላቸው ማድረጉና ከሲኖዶሱ እኩል መቁጠሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ መግለጫ በጥብቅ ተወግዟል፡፡

‹‹መንግሥት ሕግ እየጣሰና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ልዕልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስካሁን ድረስ ፍፁም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት እሑድ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም.  ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሠልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ሠልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ይወጣ፤›› በማለት ነበር የሲደኖሱ ጠንከር ያለ መግለጫውን ይፋ ያደረገው፡፡

መግለጫው በምክር፣ ተግሳጽ ብቻ ሳይሆን በቁጣና መረር ባሉ ቃላት የታጀበ መሆኑ መንግሥት ፈጥኖ የመግለጫ ምላሽ እንዲሰጥ ያስገደደ ነበር፡፡ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሠልፉ ሕገወጥ እንደሆነ የሚያትት መግለጫ ወዲያው ነበር ያወጣው፡፡

እሑድ ምን ይፈጠር ይሆን? የሚለው ጉዳይ መላው ኢትዮጵያውያንን እያሳሰበ ባለበት ወቅት ግን ዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ የተፈጠሩ ክስተቶች የነገሮችን አቅጣጫ የሚወስኑ ሆነው ብቅ አሉ፡፡

ዓርብ አመሻሽ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ማድረጉንና የተደረሱ ስምምነቶችን በተመለከተ ለቅዳሜ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠዋት ዝርዝር መግለጫ ለመስጠት ቀጠሮ በመያዝ አጭር መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡

በዚሁ ወቅት መግለጫ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶሱን በችሎት የወከለው ዓብይ የሕግ ኮሚቴ በበኩሉ ሲኖዶስ መሥርተናል ካሉ ሰዎች መካከል 29 በሚሆኑ ሰዎች ላይ በችሎት የዕግድ ውሳኔ መተላለፉን ይፋ አድርጓል፡፡

ዓርብ አመሻሽ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያኗ የተሰሙ መግለጫዎች እሑድ ምን ሊከሰት ይችላል? በሚል ሲጠበቅ የቆየውን ሥጋትና ውጥረት ያረገቡ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተገናኘ የተነሱ ውዝግቦች መፍትሔ አግኝተዋል ለማለት ጊዜው ገና ነው፡፡ ከዚሁ ጎን መንግሥት ከእምነት ተቋም ጋር የፈጠረው ፍጥጫ ገና መልስ አላገኘም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -