Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ባንክ በ20 ቢሊዮን ብር ወጪ የኮንቬንሽንና የልህቀት ማዕከል ግንባታ አስጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ባንክ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያስወጣውን ግዙፍ የኮንቬንሽንና የልዕቀት ማዕከል የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራ አስጀመረ፡፡ 

ባንኩ በገላን ከተማ በተረከበው 15 ሺሕ ሔክተር መሬት ላይ ለመገንባት ካሰበው የተለያዩ ግንባታዎች ውስጥ የመጀመርያውን ምዕራፍ እንዲገነባለት የመረጠው ቢያንኮ የተባለው የኮንስትራክሽን ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል፡፡ 

የዚህ ፕሮጀክት የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታ ሐሙስ የካቲት የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ በተጀመረበት ወቅት እንደተገለጸው በመጀመርያው ምዕራፍ ውስጥ የሚካተቱ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች በ18 ወሮች ውስጥ ይጠናቀቃሉ፡፡

በዚህ ግዙፍ የባንኩ ፕሮጀክት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ ጋራዦች፣ ጋለሪዎች፣ ሙዚየሞች፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ መጋዘኖች ይገኙበታል።

በተለይ የልዕቀት ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የሚገነባ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ይህ ማሠልጠኛ የመማሪያና ለሥልጠና ማደሪያ የሚውሉ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን የቤተ መጻሕፍትና የመመገቢያ ክፍሎች እንደሚኖሩትም አመልክተዋል፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት በተለይ የገላን ከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ትልቅ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን የሚፈጥር ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ለተለያዩ ንግድና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች የዚሁ ፕሮጀክት አካል በመሆናቸው ባንኩ አንድ ልዩ መንደር የሚመሠረትበት ተደርጎ የሚወሰድ ነው ተብሏል፡፡

የሚገነባው ኮንቬንሽንና የልዕቀት ማዕከል ከባንኩ አልፎ አገራዊ ጠቀሜታዎች ያሉትን የተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲያስተናግድ ተደርጎ ዲዛይኑ መሠራቱን ከፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አጠቃላይ የግንባታ ይዘቱና ዲዛይኑ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና የንግድ ትርዒቶችን ለማዘጋጀት የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ 

ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ የተለያዩ መጠን ያላቸው አዳራሾች ውስጥ በአንዴ እስከ 40 ሺሕ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽም ይኖረዋል በተባለው በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የንግድ ትርዒት ማሳያ ክፍሎችም ተካተዋል። 

ኦሮሚያ ባንክ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ሲነሳ እስከ አሥር ቢሊዮን ብር ወጪ ሊጠይቅ ይችላል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም እየታየ ባለው የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ንረት ምክንያት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪው እስከ 20 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ከአቶ ተፈሪ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በማዕከሉ ከሚገነቡት የባንክ ባለሙያዎች ማሠልጠኛና ማደሪያ ሕንፃ በተጨማሪ ባንኩ አገልግሎት የሚሰጥበት ሕንፃም በፕሮጀክቱ ውስጥ ተካቷል፡፡

በተለይ የባንክ ባለሙያዎች ማሠልጠኛው ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን በዚህ ማሠልጠኛ የባንኩ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም ይገለገሉበታል ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታ ማስጀመርያ ፕሮግራም ላይ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ባንክ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሚል ስያሜ ጥቅምት 2001 ዓ.ም. ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን 4.4 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ በተጠቀሰው የሒሳብ ዓመትም 1.2 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል፡፡ 

በ2014 መጨረሻ ላይ ያስመዘገበው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 43.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ ደግሞ 32.1 ቢሊዮን ብር እንደነበረ የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ ባንኩ በመላ አገሪቱ ከ400 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን የሠራተኞቹ ቁጥርም ከስምንት ሺሕ በላይ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች