Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየተራዘመ የሥልጣን ትንቅንቅ - ከዚያስ በኋላ?

የተራዘመ የሥልጣን ትንቅንቅ – ከዚያስ በኋላ?

ቀን:

በአንዳርጋቸው አሰግድ

በኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥት ታሪክ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተፈጸመ ከተባለ አንዱና ብቸኛው፣ ከአፄ ምኒልክ ወደ ንግሥት ዘውዲቱ የተከናወነው ሽግግር ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ከአቤቶ አያሱ ወደ ራስ ተፈሪ፣ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ወታደራዊ ደርግ፣ ከወታደራዊ ደርግ ወደ አብዮታዊ ሰደድና ኢሠፓ አገዛዝ፣ ከኢሠፓ አገዛዝ እስክ ኢሕአዴግ አገዛዝ ድረስ የመንግሥታዊ ሥልጣን ለውጦችን አየች። እነዚህ ሁሉ ለውጦች የተከናወኑት አንፃራዊ የተራዘም የሥልጣን ትንቅንቆችን አስተናግደው ነበር። ሁሉም ትንቅንቆች የተቋጩትም፣ አንዱ ወይም ሌላው ጎራ ወታደራዊ የበላይነትን ከተቀዳጀ በኋላ ነበር።

በአቤቶ ኢያሱና በራስ ተፈሪ ወገኖች መካከል በተካሄደው የሥልጣን ትንቅንቅ፣ የራስ ተፈሪ ወገኖች በሰገሌው ጦርነት ባገኙት ድል ተቋጨ። ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሐፋቸው በአንድ የሰገሌ ጦርነት ብቻ የደረሰውን ዕልቂት እንደዘገቡት፣ ‹‹በውጊያው ላይ ከሁለቱም በኩል የሞተው ወታደር 15 ሺሕ፣ የቆሰለው 20 ሺሕ ያህል ነው። ይህም በዓድዋ ጦርነት የሞተውንና የቆሰለውን በቅርብ ሒሳብ እጥፍ ያደርገዋል። በዓድዋ ጦርነት ከኢትዮጵያዊያን በኩል ሰባት ሺሕ አምስት መቶ ስድሳ እንደሞተና አሥር ሺሕ እንደቆሰለ ባለ ታሪኮች ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር ማነፃፀር ነው፡፡››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሁለቱ ጎራዎች ከሰገሌ በፊት በተካሄዱት ውጊያዎች የደረሰው ዕልቂትና የቁስለኛ ብዛት ቢታከል፣ በብዙ ያሻቅባል። ይህም እንግዲህ፣ ቀደም ሲል በተካሄዱት ውጊያዎችና በሰገሌው ጦርነት የደረሱት ውድመቶችና መፈነቃቀሎች ሳይታሰቡ ነው።

ከ1966 ዓ.ም. አብዮት አንስቶ እስከ ኢሕአዴግ አገዛዝ መቋቋም ድረስ ስለተካሄዱት ውጊያዎችና ስለደረሱት ዕልቂቶች፣ ውድመቶችና መፈነቃቀሎች ብዙ ስለተጻፈና ስለተነገረ በረጅም እንዲቆይበት አያስፈልግም። እንዲሁም፣ በአማካይ ከ2007 ዓ.ም. አንስቶ በተካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ላይ። በንፅፅር ግን፣ ኢትዮጵያ እንደ ዛሬው የታሪክ ወቅቷ እስከዚህ ድረስ ከተወሳሰበ፣ እስከዚህ ድረስ ከአውዳሚ፣ እስከዚህ ድረስ ከአፈነቃቃይ፣ እስከዚህ ድረስ በጥላቻና በሐሰት ተሞልቶ የሚካሄድን የተራዘመ የሥልጣን ትንቅንቅ ዘመን አስተናግዳ አታውቅም። በሰሜኑ ውጊያ ብቻ የ600 ሺሕ ሰው ሕይወት እንዳለፈ ተዘገበ። ሌሎች ከሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገምታሉ። የቁስለኞችና ለአካል ጎዶሎነት የተዳረጉት ወገኖች ብዛት አልተገለጸም። ውድመቱ በቢሊዮን ብር እየተሰላ ቢነገርም፣ ጠቅላላ ድምሩ ከቢሊዮኖች በላይ አሻቅቦ ቢገኝ የሚያስገርም አይሆንም። የተፈነቃቀሉትና ለዕለት ጉርሻቸው እንዲደረስላቸው የሚጣሩት ወገኖች ከ20 ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ ተገልጿል። ጧሪና ቀባሪ ተነጥቀው የቀሩት ወላጆች ‘ቤት ይቁጠረው’ በሚል የታለፉ ይመስል፣ ከቀመር አልገቡም።

ኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በለውጥ ማዕበል ውስጥ ገባች። ይሁን እንጂ እንኳን በታዛቢዎችና በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ቀርቶ፣ በለውጡ አመራርና በተለያዩት የተደራጁና ያልተደራጁ ተዋናዮች ዘንድም ቢሆን፣ በለውጡ ምንነት ላይ የጋራ አመለካከትና አረዳድ አልነበረም። ስለዚህም ነበር፣ በለውጡ የመጀመርያ ወቅቶች ‹‹የለውጡ ፍኖተ ካርታ ምንድነው?›› የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ሲቀርብ የነበረው። በሌላውም ወገን፣ በእጅግ የተለያዩ አመለካከቶችና አረዳዶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በእጅጉ የተለያዩ አቅጣጫዎችና ግቦች እየተነገሩና እየቀርቡ የቀጠሉት። እንደሚታወሰው ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› የሚል ጥሪ ከአንዱና ከሌላው እየተወረወረ ሰሞነኛ ሆኖ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “እኔ አሻግራችኋለሁ” እስከ ማለት ሄደው ተደምጠው ነበር። ስለዚህም ነው አምስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ቅሉ፣ በአንድ ወገን የለውጡ አቅጣጫና ግብ “አልገባኝም/አልተገለጸልኝም” የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ የቀጠሉት። መላምቶች ተበራክተው እየተነገሩ የሚሰሙት። ለምን? ዝርዝር መልሱ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪዎች የየወቅቱን ተዋናዮችና ምንነታቸውን በዝርዝር ለይተውና በማስረጃዎች አስደግፈው የሚያቀርቧቸውን ጥናቶች መጠበቅ ይኖርበታል።

ይህ አጭር ጽሑፍ፣ በአብዛኛው የሚታወቀውን የለውጡን ሒደት ለመረዳትና ለማጤን (Conceptualize) ለሚደረገው ጥረት መጠነኛ አስተዋጽኦን ለማቅረብ ከመሞከር ያለፈ ሥፍራ የለውም። የጣርኩት፣ ስለየወቅቱ ነባራዊ ሁኔታና ሒደት የነበረኝ ንባብ ወደወሰደኝ ለመሄድ ነው። እንደ ማንኛውም ጥረት ስለዚህም፣ ለሂስና ትችት የሚጋለጥ እንደሚሆን እጠብቃለሁ። ሂሶቹና ትችቶቹ የለውጡን ምንነትና ሒደት በይበልጥ ለማጤን የሚያግዙ የሐሳብ/ለሐሳብና የአመለካከት/ለአመለካከት ልውውጥ እስከሆኑ ድረስ በደስታ እቀበላለሁ። አስተናግዳለሁ።

ዋናው ምክንያት

የ2010 ዓ.ም. ለውጥ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ለውጥ፣ ለማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ባለቤትነት የሚካሄድ ትንቅንቅ ነው። ቢሆንም ግን፣ ከቀድሞዎቹ የሥልጣን ባለቤትነት ለውጦች በተለየና በዋናነት በክልሎች ገዥነት ለ30 ዓመታት ሙሉ በፈረጠሙ የብሔር ድርጅቶች መካከል የሚካሄድ በመሆኑ ዓይነተኛ ነው። ትንቅንቁ በሌላው በኩልና በበለጠም ደግሞ ግን፣ ለማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ባለቤትነት የሚካሄድ ትግል ብቻ አልሆነም። በክልል የብሔር ድርጅቶች መካከል (አንዳንዶች እንደሚሉት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በደረጁት የብሔር መሳፍንቶች መካከል) ለሀብት ምንጮች ጭበጣ (Resource Capture) የሚደረግ ትንቅንቅ በመሆኑ ጭምር ዓይነተኛ ነው። ስለሆነም በትንቅንቁ ውስጥ አንዱ ጎራ፣ የሀብት ምንጮችንና ጥቅም ለ27 ዓመታት ሙሉ ለማካበት የተጠቀመበትን የገዥነት ሰገነት ላለማጣት ከመሟሟት ውስጥ ገባ። ሌላው ጎራ ሥልጣንን አብልጦ ወደ መዝገንና የሀብት ምንጮችን አስፋፍቶ ወደ መጨበጥ ትግል አቀና። 

ይህ ሁኔታ በራሱ፣ በአንድ ወገን፣ የለውጡን ምንነትና ሒደት ለመረዳትና ለማጤን አስቸጋሪ አደረገ። በሌላው ወገን የተወሳሰበ፣ የተራዘመ፣ አውዳሚ፣ በጥላቻና በሐሰት ቅስቀሳዎች የተመላ አደረገው። ምንጩ ተደጋግሞ እንደተገለጸው፣ በ1983 ዓ.ም. የሥልጣን ባለቤት የሆኑት የብሔር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ብሔሮች መብት ስም የመሠረቱት ልዩ (Unique) የአገዛዝ ሥርዓት (System) እና ልዩ የአገዛዝ ዘይቤ (Type) ነው። ምንጩ በሌላ አገላለጽ፣ በ1983ቱ ለውጥ የሥልጣንና የሀብት ምንጮች ይዞታ የበላይ ባለቤትነትን በሕገ መንግሥት ጭምር እስከ ወዲያኛው ለራሱ የሰጠው ጎራ ላቆመው የአገዛዝ ሥርዓትና የአገዛዝ ዘይቤ “እስከ ሲዖል ድረስ ለመውረድ” የወሰነለት ትንቅንቅ ሆነ።

የሚታወቀውን ለመድገም፣ የ1983 ዓ.ም. ለውጥ መሐንዲሶች በአንድ ወገን፣ በፌዴራላዊ አስተዳደር ስም ፌዴራላዊ ያልሆነን የአስተዳደር ሥርዓት በሕገ መንግሥት ጭምር ደንግገው አቆሙ። በሌላው ወገን፣ በዴሞክራሲ ስም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ያሉትን ጠርናፊ ዴሞክራሲና “አንድ ለአምስት” ያሉትን የማኅበረሰብ ጥርነፋ አገዛዝ ዘይቤን ተከሉ። ሌላም፣ የታሪክን ትርክት እያጎሳቆሉ የታሪክ መሠረቶችን በመናድ በረቱ። ይባስም፣ በሃይማኖትና በእምነት ተቋማት ውስጥ በመግባት ጭምር ሃይማኖታዊ ግጭቶችን አቆሳቆሱ። እንዲሁም፣ የትምህርትና የዕውቀት ከፍታዎችን በማሽቆልቆል፣ “ተምሮ” የመሃይምን ትውልድ አበራክተው ፈለፈሉ። የትምህርት ሚኒስትሩ ጥር 19 ዕለት ይፋ ያደረጉት የ3.3 በመቶ አገራዊ ውጤት በራሱ ብቻ፣ የአዘቅቱን ጥልቀት ይገልጻል። በአንድ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ በር ላይ ከዓመታት በፊት የተለጠፈ አንድ ማስታወሻ፣ ‹‹አገርን ለማውደም አቶሚክ ቦምብንና ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን መጠቀም አያስፈልግም። የትምህርት ደረጃን ማሽቆልቆልና ኩረጃን ማበረታታት ብቻ ይበቃል፤›› ይል ነበር።

በሌላው ወገን፣ በነፃ ገበያና በመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ስም ብርሃኑ አበጋዝ፣ ሳራ ቮንና መስፍን ገብረ ሚካኤል በየጥናታዊ ጽሑፎቻቸው በትክክል እንዳሉት፣ በየትም አገርና መንግሥት ታይቶ የማይታወቀውን የአንድ የገዥ ፓርቲ ካፒታሊዝም ሥርዓት አደረጁ (Berhanu Abegaz, Political Parties in Business 2011 Sarah Vaughan & M. Gebremichael, Rethinking Business and Politics in Ethiopia 2011)። አይዲያ የሚባለው የስዊድን አገር ዓለም አቀፋዊ ተቋም፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የማምረቻና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዋናዮች ከሆኑ፣ የጥቅም ግጭቶች ይጨምራሉ። በፖለቲካ ውሳኔዎችና በንግድ ጥቅም መካከል ያለው መስመር ይሻራል፤›› ያለው ሽረት፣ የኢትዮጵያ እውነታ ሆኖ ተንሰራፋ (Funding of Political Parties and Election Campaigns International Institute for Democracy and Electoral Assistance (IDEA) 2014፣ ገጽ 47)። ስለዚህም ነው፣ በ1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከተመሠረተው የኢሕአዴግ አገዛዝ ሥርዓትና የአገዛዝ ዘይቤ ጋር በሩቅም እንኳን የሚመሳሰልን የአገዛዝ ሥርዓትና የአገዛዝ ዘይቤ ለአብነት እንኳን ለመጥራት የሚቻል የማይሆነው።

የሚመሳሰልበት ባህሪያት ካሉም፣ ተሰናባቹ ገዥ እንደ ቀድሞው ለመግዛት ካልቻለበት ሁኔታ ውስጥ ገብቶ የተገኘ በመሆኑ ነበር። ተገዥዎች እንደ ቀድሞው ለመገዛት ያልፈቀዱ ሆነው በመነሳሳታቸው ነበር። ተሰናባቹ ገዥ እንደ ሌሎች በርካታ ተሰናባች ገዥዎች፣ ሥልጣንና ሀብቱን ላለማጣት በጦር ኃይል ጭምር እስከመታገል የሄደ በመሆኑ ነው። ወደ ሥልጣን መንበር ያቀናው ኃይልም እንደ ሌሎች በርካታ የሥልጣን ተቀናቃኝ ኃይሎች፣ በውል የደረጀ የራስ ኃይልና አመራር ያልነበረው በመሆኑ ነበር።

ስለዚህም ለማለት ይቻላል፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀመሮ ለአምስት ዓመታት ሙሉ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሒደትም ልዩ (Unique) ሆነ። መፈንቅለ መንግሥት አንዳይባል፣ በቅፅበታዊ ዕርምጃዎች በሰዓታት/በቀናት ውስጥ አልተቋጨም። ወይም፣ የለማ ቲም የተባለው የለውጥ ኃይል በመስከረም 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ በተካሄደው የኢሕአዴግ ጉባዔ ወቅት የኢሕአዴግን/የገዥ ድርጅቱን የሥልጣን ማማዎች ለመያዝ የበቃ ቢሆንም፣ መንግሥታዊ ሥልጣንን ጠቅልሎ ለመጨበጥ የበቃ አልሆነም። ለዚህም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት አንድ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በመጀመርያዎቹ ቀናት የቢሯቸው ቁልፍ እንኳን ባለቤት እንዳልነበሩ ያሰሙት አስገራሚ ሃቅ በራሱ ብቻ ብዙ ይናገራል።

የሪፎርም ለውጥ ነው እንዳይባል በሠራዊት፣ በፀጥታና በደኅንነት፣ በምርጫ ቦርድና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ረገዶች አንዳንድ ተገቢ ሪፎርሞች የተደረጉ ቢሆንም ቅሉ፣ መሠረታዊ ሪፎርሞችን በሚጠይቁት በፌዴራሉ አስተዳደር አወቃቀርና በሕገ መንግሥቱ መሻሻል ጉዳዮች ረገድ የሪፎርም ዕርምጃዎች አልተወሰዱም። አብዮታዊ ለውጥ ነው እንዳይባልም እንደተለመዱት የአብዮታዊ ለውጦች ዕርምጃዎች፣ የቅድመ 2010 ዓ.ም. ገዥዎችን ወዲያውኑ በጡንቻ አስወግዶ፣ ሕገ መንግሥቱንና ምክር ቤቱን በአንዲት መግለጫ አግዶ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት ለመግዛት የሄደ አልነበረም።

በተጨማሪ ደግሞ ግን ተሰናባቹ ጎራ ብቻ ሳይሆን፣ የለውጥ ኃይል የሚባለው የብሔር ድርጅቶች ስብስብ አባሎችና ሌሎቹ ከአገር ውስጥና ከውጭ የገቡ የብሔር ድርጅቶች፣ የፌዴራል አወቃቀሩንና የሕገ መንግሥቱን መነካት አጥብቀው የሚቃወሙ ነበሩ። የአገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ተዋናዮቹም “ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ልትመልሱን” በሚልና “አገር ልታፈርሱ” በሚል ተከፋፍለው የሚናጩ ነበሩ።

በዚህ የመነጫጨት ድባብ ውስጥ፣ ስለጉዳዩ በሰከነ ህሊናና ሥርዓት ባለው መንገድ ለመወያየት የሚያስችል ሁኔታ ጠፋ። የለውጥ ኃይሉ፣ ‹‹ለውጡን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ብቻ እንደሚመራ›› አስታወቆ ቀጠለ። ጉዳዩን ያቆየው እስከ ወዲያኛው ይሁን በይደር አላውቅም። በነበረው መነጫጨትና ስሜታዊነት በናረበት ሁኔታ ውስጥ ግን፣ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር አምናለሁ። ስለነበርም ነበር፣ በ2013 ዓ.ም. በርካታ ፓርቲዎች  የተሳተፉበትን ምርጫ በአመዛኙ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተመራን ምርጫ ለማስኬድ የተቻለው። ቀደም ሲል እንደሚታወሰው፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ ከምርጫው በፊት በፕሬዚዳንታዊና በተመጣጠነ ውክልና ሥርዓት ይሻሻል እያሉ ሲሰብኩ ነበር። 

ስለነበርና በአጭሩ፣ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ዛሬም ዘመን የለውጥ ምንነት ግልጽ ለመሆን ያልቻለበት ዘመን የለም። እንደ ዛሬም፣ በለውጥ አቅጣጫና ግብ ረገድ ብዥታዎች የሰፈኑበት ዘመን የለም። እንደ ዛሬም፣ ባለአቅምና አቅመ ቢስ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ አብዝተው የተወናኙበት ዘመን የለም። እንደ ዛሬም አንዳንዶች፣ በግል የሬዲዮንና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ታግዘው ጭምር የቀሰቀሱበትና የቆሰቆሱበት ዘመን የለም። አንዳንድ “የሳተላይት ቦርሳ ፓርቲዎች” እና አንዳንድ ራሳቸውን በራሳቸው እያገዘፉ የሚሰብኩ ግለሰቦችም፣ አብዝተው የተወናኙበት የለውጥ ሒደት የለም። ስለሆነም ነው፣ የተዛቡ የታሪክና የሁነቶች ትርክቶች እንደ ትንተናና ዕውቀት እየተቆጠሩ ያናጩት። አንድ የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ እንዳለኝም፣ ያ እና ይኼ ድርጅት የሚሰጣቸው መግለጫዎች እንደ ፖሊሲ እየተወሰዱ ያነታረኩት።

እንደ ዛሬውም ዘመን ግን፣ የአንዳንድ ድርጅቶች ቅጥረኞች ዘመኑ በለገሳቸው የፌስቡክና የዩቲዩብ አርበኝነት እየተሞጋገሱ የቆሰቆሱበት ዘመን የለም። ደጋፊዎቻቸውና ተቃዋሚዎቻቸውም እንደ ዛሬው ዘመን አንዱና ሌላው በየቀኑ በሚፈጠረው “ዜና” እና “መረጃ”፣ አጀንዳና ሁነት በደጋፊነትና በተቃዋሚነት እየዋለሉ የዋዠቁበት ዘመን የለም። አንዳንድ የሆኑ ግለሰቦችም እንደ ዛሬው ዘመን፣ በዩቲዩብ ሥራ ንግድ ተሰማርተው የዘበዘቡበትና የተጠቀሙበት ዘመን የለም። ተከታዮች የሚሏቸውም፣ ወዲህና ወዲያ እየናወዙ የዋሉበትና ያመሹበት ዘመን የለም። ሌላም እንደ ዛሬውም ዘመን አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች በየኤምባሲዎች እየዞሩ የሰገዱበት ዘመን የለም። ሊሎችም እንደ ዛሬው ዘመን፣ “የውጭ ጦር ካልገባ” እያሉ ለባዕድ መንግሥታት ያመለከቱበት ዘመን የለም። አንዳንድ ጊዜና እንደ ዛሬውም ዘመን፣ አንዳንድ ጉምቱ ባለሥልጣናት በሚሰጡት አንዳንድ መግለጫና እንዳመጣ በሚወረውሯቸው አንዳንድ ቃላት፣ አድማጩ ታዛቢ ግር የተሰኘበት ዘመን የለም። አድማጩ ሌላም ጊዜ፣ የውይይት በሚባሉ መድረኮች ላይ እንዳመጣ በሚሰነዘሩት “አመለካከቶች” የተገረሙበትና የተጉረመረሙበት ዘመን የለም።

እንደ ዛሬውም ዘመን ደግሞ፣ የቀድሞ ገዥዎችና ተጠቃሚዎች የነበራቸውን ሥልጣንና ሀብት ላለማጣት፣ በውስጥም በውጭም ፈርጥመው ለውጥን የተፃረሩበትና የተቋቋሙበት ዘመን የለም። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችም እንደ ዛሬው ዘመን፣ በሃይማኖታዊ ሥልጣን ተከፋፍለው ከፖለቲካ ትግል ውስጥ የገቡበት ዘመን የለም። ደግሞም ደግሞ እንደ ዛሬውም ዘመን፣ የውጭ ኃይሎች ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከተባበሩት መንግሥታት እስከ የአውሮፓ ኅብረትና የዓረብ ሊግ፣ ከአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እስከ መካከለኛው ምሥራቅ አንዳንድ አገሮች ድረስ ለግልጽ ጣልቃ ገብነት ያቀነቀኑበትና የገቡበት የለውጥ ዘመን የለም። እንደ ዛሬውም ዘመን፣ የለውጥ አመራሩና የተለያዩት የተደራጁና ያልተደራጁ ተዋናዮች ለአንፃራዊ የትንበያ ግምት (Predictability) እንኳን አልጨበጥ ያሉበት ዘመን የለም። በመጨረሻ እንደ ዛሬውም ዘመን ደግሞ፣ የአካዳሚው ማኅበረሰብና የምሁራኑ ክፍል በበርካታ የውይይት መድረኮች እየተሳተፈ በርካት ሐሳቦችንና ምክረ ሐሳቦችን ያቀረበበት ዘመን የለም። ተደምጠው እንደሁ አላውቅም። ዝምተኛው ብዙኃን የሚባለውም፣ እንደ ዛሬውም ዘመን ግራ የተጋባበትና ፀጥ ያለበት ዘመን የለም።

የተመለከቱት ሁኔታዎች ድምር ይመስለኛል፣ በአንድ ወገን የለውጡን ምንነትና ሒደት መረዳትንና ማጤንን አስቸጋሪ አድርጎት የከነፈው። በሌላውም ወገን፣ ኢትዮጵያን ከተራዘመ የሥልጣን ትንቅንቅ ሁኔታ ውስጥ ቀርቅሮ አሰቃቂ ዕልቂትን፣ በግፍና በገፍ መፈነቃቀልንና ከእጅግም በእጅግ የሰፋ ውድመትን ያስከተለው። ሲከፋም፣ ኢትዮጵያን የሐሰትና የጥላቻ ቅስቀሳዎች መናኸሪያ ያደረጋት። ተማምኖ በጋራ የመቆምን እሴቶችና ጥበቦች የሰረሰረው። የጋራ ወደፊትን ራዕይ የሸበበው።

የተራዘመ የሥልጣን ትንቅንቅ

የ2010 ዓ.ም. ለውጥ በመሠረቱና በቅድሚያ፣ በኢሕአዴግ አባልና አጋር የብሔር ድርጅቶቹ መካከል የተካሄደ የሥልጣን ሚዛን ሽግሽግ (Internal Power Rebalancing) ነበር። ላለፉት አምስት ዓመታትና እስካሁን በተለያዩ መንገዶች እየተካሄደ ያለው ትንቅንቅም በመሠረቱ፣ በ2010 ዓ.ም. ያልተቋጨው የኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሚዛን ሽግሽግ ትንቅንቅ ቅጥያ ነው።

የተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ በአጠቃላይ ፀረ የኢሕአዴግ አገዛዝ ቢሆኑም የቄሮ፣ የፋኖ፣ የእጄቶ ወዘተ. እየተባሉ ቢሰየሙም፣ ግልጽ የአገራዊ ፖለትካ ማኅበራዊ ለውጥ ግብ፣ ፕሮግራምና አጀንዳ ቀርቶ፣ በአንፃራዊ የተዋሃደ ድርጅትና በውል የተደራጀ ግልጽ አገራዊ አመራር የነበራቸው አልነበሩም። እንዲያውም ቢባል የተሻለ ነው፣ በርካታ የተለያዩ ድርጅቶች፣ ግለሰብ ተዋናዮችና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባለቤት የሆኑ ቡድኖች ሳይቀሩ፣ ራሳቸውን የለውጡ መሪ አድርገው ከማስተዋወቅና ከመሪነት ዕውቅና ሻሞ ውስጥ ገብተው የተወናኙበት የለውጥ ክንዋኔ ነበር።

ኢሕአዴግ የለውጡን ማዕበል በአንድ በኩል በጉልበትና በሌላም በኩል “ተሃድሶና ጥልቅ ተሃድሶ” ባለው የፖለቲካ መንገዱ ለመቆጣጠርና ለመግራት ሞከረ። ሕዝባዊ እንቅስቃሴው አመራር ኖረው/አልኖረው፣ ወይም ያኛውም ሆነ ይህኛው ራሱን እንደመሪ እያወጀ ተወናኘ/አልተወናኘ በራሱ ኃይል እየሰፋና እየገፋ ሄደ። የኢሕአዴግ መሪ ድርጅት የነበረው ሕወሓት የዚያኑ ያህል ወደ ጥግ ተገፋ። ሕዝባዊው እንቅስቃሴ ውሎ አድሮ “የሕወሓት የበላይነት” የተባለውን የበላይነት በግልጽ ወደ መታገል ሲያቀና፣ የኢሕአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ ሰዓት እንደ ደወለ ያመለከተ እጥፋት ሆነ። ብዙም አልቆየ፣ በመስከረም 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ በተካሄደው የኢሕአዴግ ስብሰባ ላይ የኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሚዛን ሽግሽግ ተፈጸመ። ወይም የኢሕአዴግ ውስጥ ድርጅታዊ ሥልጣን ሚዛን፣ ከሕወሓት የበላይነት የለውጥ ኃይል ወደ ተባለው ጎራ ተደፋ።

የኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሚዛን ሽግሽግ ቢጠናቀቅም ግን፣ በመንግሥት ሥልጣን ደረጃ የተጠናቀቀ አልነበረም። አምስቱ ዓመታት ከላይ እንደተባለው፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ባለቤትነት በሚካሄደው ትግል ተካረው የቀጠሉበት ዓመታት ናቸው። በሌላውም ወገን፣ በአንድ በኩል ብልፅግና በተባለው ፓርቲ ውስጥ በተደራጁት በቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ አባላትና አጋር የብሔር ድርጅቶች መካከልና፣ በሌላውም በኩል በየብሔሩ ውስጥ እይተበራከቱ በተፈለፈሉት የብሔር ድርጅቶች መካከል የሚካሄዱት የሥልጣን ትንቅንቆች ወደአደባባይ ወጥተው የተስፋፉበትና የቀጠሉበት ዓመታት ናቸው።

የመጀመርያው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ግዛቶች ከተካሄዱት አሰቃቂና አውዳሚ ጦርነቶች አንስቶ እስከ ፕሪቶሪያ የዘለቀውና ዛሬም እየተካሄደ እስካለው ትንቅንቅ ድረስ ወሰደ። የኋለኛው፣ በብልፅግና ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ለበለጠ የሥልጣን ዘገናና ለበለጠ የሀብት ምንጮች አፈሳ በመካሄድ ላይ የነበረውን ትንቅንቅ አጎላ። እንደዚሁም፣ በየብሔሩ ውስጥ ያሉት የተለያዩ የብሔር ድርጅቶች ከየክልሎቻቸው ገዥ የብሔር ድርጅቶች ጋር በሚያደርጉት ትግል ተስፋፋ። እንዲህም ደግሞ፣ እየተመሠረቱ ባሉት አዳዲስ የአስተዳደር ክልሎችና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ማንነት ረገድ በሚነሱት ጥያቄዎች እየተገለጸ ቀጠለ። ይባስ ብሎ የአንዲት የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የክልል ሲኖዶሶችን እስከ ማቋቋም ዘልቀው፣ ከሃይማኖታዊ ሥልጣንና ከሀብት ክፍያ ሻሞ ውስጥ የገቡበት ዘመን እስኪታይ ድረስ ዘለቀ።

ለውጡ የግዴታና በግድ ሥርዓታዊ ከመሆን ሌላ አማራጭ የነበረው አልነበረም። ማለትም፣ ፌዴራላዊ ያልሆነውን የአስተዳደር ሥርዓት በቁመናና በአግድሞሽ ፌዴራላዊ ከማድረግ ሌላ፣ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነውን የአገዛዝ ዘይቤ ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ሌላ፣ መንግሥታዊ ካፒታሊዝም ያልሆነውን የገዥ ፓርቲ ካፒታሊዝም የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ካፒታሊዝም ከማድረግ ሌላ አማራጭ የሌለው አልነበረም። አንዳንድ ሪፎርሞች የተደረጉ ቢሆንም ቅሉ ግን፣ የለውጡ አውራ ጥያቄዎች ሳይነኩ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። ለምን?     

ተሰናባቹ ጎራ በብሔር ድርጅት ስም የሚወናኝና እወክልሃለሁ የሚለውን ብሔር በውድም/በግድም ከጀርባው ያሠለፈ ነበር። በሠራዊት አቅሙ የፈረጠም ነበር። ለ27 ዓመታት በገነባው የፀጥታና የደኅንነት ግንብ የተቆላለፈ ነበር። በነፃ ገበያና በመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ስም ያደረጀው የአንድ የገዥ ፓርቲ ካፒታሊዝም ሥርዓት ባስገኘለት ትርፎች የከበረና በፋይናንስ አቅሙ የደለበ ነበር። በጥቀመኝ/ልጥቀምህና በሙስና ትስስር በተተበተቡት አጋሮቹና ተጠቃሚዎቹ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተደገፈ ነበር። ከውልደቱ ጀምሮ በገዥነት ዘመኑ በመላ በገነባው የውጭ ግንኙነት የናኘ ነበር። ሌላም፣ አንዳንድ የብሔር ድርጅቶችና ግለሰብ ተዋናዮች በሚለግሱት ድጋፍ የተበረታታ ነበር። በመጨረሻም፣ “ፌዴራሊስት ኃይሎች” ብሎ የሰየማቸው ተዋናዮች በዙሪያው የሚዳሩለት ነበር። ውሎ አድሮም፣ ራሳቸውን ነፃ አውጭ ብለው ከሰየሙ “ነፃ አውጭዎች” ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ጭምር ያቀናጀ ነበር።

ሕወሓትን በኢሕአዴግ ደረጃ አሸንፎ ከቤተ መንግሥት የገባው የለውጥ ኃይል ግብና አጀንዳ ምንም ይሁን ምን፣ የተገለጸውን የደነደነ የተሰናባች ገዥ ጡንቻ የሚመጥንና በእርሱ ሥር የሆነ የድርጅታዊም ሆነ የጦርና የፀጥታ ኃይል፣ የፋይናንስም ሆነ የውጭ ግንኙነት ጉልበት የነበረው አልነበረም። የተረከበው ሠራዊት፣ ደኅንነት፣ ፀጥታና ቢሮክራሲ የብሔር አስተዋጽኦ በሚል የተተበተበ፣ የክህሎት ከፍታው የወረደና በሙስና ባህር ውስጥ የተዘፈቀ ነበር። ወይም፣ ቢሮክራሲውን አሹሮ ለማዘዝና ለማሽከርከር የሚያስችለው የራሱ ወገን የሆነ የሰው ኃይል አልነበረውም። ዲፕሎማቶች የሚባሉትም ከኢትዮጵያ መንግሥት ይልቅ፣ የሕወሓት ተወካዮች ነበሩ። የተረከበው የመንግሥት ካዝናም የተራቆተ ነበር።

በተጨማሪ ደግሞ ግን፣ የለውጥ ኃይሉ የሕወሓትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ “መደመር” በተባለው “ፍልስፍና/ርዕዮት” ለመተካት ቢጥርም፣ የፖለቲካ ማኅበራዊ ሥር የያዘለት አልሆነም። ብልፅግና የተባለውን ፓርቲ ቢያቋቁምም ከኢሕአዴጉ የብሔር ድርጅቶች ስብስብ በተለየ፣ በአንድ የፖለቲካ ማኅበራዊ ግብና በአንድ አገራዊ/ብሔራዊ ፕሮግራም ዙሪያ ተማምነው የተሰባሰቡ የግለሰቦች ስብስብ አልሆነም። ይህ ሁኔታም ታክሎ ነው፣ ለመንግሥታዊ ሥልጣን የሚካሄደውን ትንቅንቅ በተጨማሪ የተራዘመና አውዳሚ ያደረገው። የትንቅንቁን ጉዞ በሚታወቁት አራት ዋና ዋና ወቅቶች ለይቶ ለመመልከት ይቻላል። በሚከተለው ክፍል በአጭር በአጭሩ በማጠቃለል አመላክታለሁ።

አራት የትንቅንቅ ወቅቶች

የመጀመርያው ወቅት ከላይ እንደተወሳው፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የተከናወነው የኢሕአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሚዛን ሽግግሽ የተካሄደበት ወቅት ነበር። ትንቅንቁ፣ የለውጥ ኃይል በተባለው ጎራ ሠፈር አሸናፊነት ተዘጋ። ሁለተኛው ወቅት፣ ተፋላሚዎቹ ጎራዎች የውስጥና የውጭ ደጋፊና ተባባሪ ወገኖችን ለማሰባሰብ የተንቀሳቀሱበት ውቅት ነበር።

ሕወሓት ወደ ክልሉ አፈግፍጎ፣ በአንድ በኩል እንደ አንድ ሉዓላዊ መንግሥት ተወናይ፣ በሌላ በኩል የውስጥና የውጭ ደጋፊዎችንና ተባባሪዎችን በማሰባሰብ ተንቀሳቀሰ። በውስጥ “ፌዴራሊስት ኃይሎች” ያላቸውን ለማሰባሰብ ጣረ። ነባር የሠራዊት፣ የፀጥታ፣ የደኅንነትና የፋይናንስ ትስስሩን በመጠቀም ሠራ። በውጭ ደግሞ ነባርና ታዋቂ መሪዎቹን በሰሜን አሜሪካና በጄኔቫ አሰማርቶና ራሳቸውን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ “ሊቃነ ሊቃውንት” አድርገው የሚቆጥሩ ፈረንጆችን አስከትሎ ተንቀሳቀሰ። ከደደቢት ዘመኑ ጀምሮ ሲደግፉት የኖሩትን የአሜሪካ ባለሥልጣናትንና ሎቢስቶችን (አንዳንዶች እንደሚያንቆላጵሷቸው፣ የደደቢት ዘመን የሕወሓት የጡት እናቶችን) ከረድፍ አስገብቶ በዓለም መድረኮችና ሚዲያዎች ላይ ናኘ። ሄዶ ሄዶ በመጨረሻም ምርጫ ያለውን “ምርጫ” በክልሉ አካሄደ። በዶ/ር ደብረ ፅዮን አናት ላይ አክሊል እስከ መድፋት ደረሰ። ነገር ግን የለውጥ ኃይል የሚባለውም ጎራ፣ የውስጥና የውጭ ሠፈሩን ለማሰባሰብ የሰነፈ አልነበረም።

ከቤተ መንግሥት እንደገባ በአንድ በኩል ከኢሕአዴግ ውጭ ሊሰበስብ የሚችለውን የውስጥና የውጭ ወገን ሁሉ ወደ መሰብሰብና ማሰባሰብ አቀና። የማሰባሰቡ ንቅናቄ፣ አቶ ለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ካሉት አንስቶ የመስቀል አደባባይን አልብሶ እስከታየው ሰፊ የሕዝባዊ ድጋፍ ትዕይንት ድረስ ደራ። በአሜሪካና በአውሮፓ በተካሄዱት የድጋፍ ስብሰባዎች ተስፋፋ። በአንድ ቃል ቢገለጽ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ አደባባዮችንና አዳራሾችን እያጨናነቀ በለገሰው ድጋፍ፣ የሕወሓት የፖለቲካ ማኅበራዊ መሠረት እንደሟሸሸ በገሃድ አሳየ። አሰማ።

በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታቱና የሃይማኖት ፊተናዎችን ለማስማማት ባደረገው ጥረት ተሞገሰ። በካቢኔው ውስጥ በርካታ ሴቶችን በማካተቱም። በውጭ የሚገኙ የታጠቁና ያልታጠቁ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ አገር እንዲገቡ ሲፈቀድ ደግሞ፣ ፀረ ኢሕአዴግ ሰፈሩ ተበራከተ። የብልፅግናን ፓርቲ በመመሥረት ድርጅታዊ ቅርፅና መሠረት እየያዘ እንደ መጣ አበሰረ። የሠራዊት፣ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን ሪፎርምና ግንባታ ሲያስከትል፣ የመንግሥታዊ ሥልጣን መደላደሉን ወደ ማደርጀትና ማጠናከር እንደ ተሻገረ ግልጽ ሆነ። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቋማት በሚባሉት የፍትሕ፣ የምርጫ ቦርድና የሰብዓዊ መብቶች መሥሪያ ቤቶች አኳያ መሠረታዊ የአመራርና የአሠራር ሪፎርሞችን ሲያደርግም፣ የነፃና የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዘመንን ወደ መከፈት እንዳቀና ተደርጎ ተነበበ።

የውጭ ድጋፍን በሚመለከተው፣ ገና ከኅዳር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የጎረፉትን የቅርብና የሩቅ መንግሥታትና የፋይናንስ ድርጅቶች መልዕክተኞችን አስተናገደ። ከኤርትራ መንግሥት ጋር አዲስ የወዳጅነት ግንኙነትን መሠረተ። ከዚያም በሳዑዲ ሳሎን የተፈረመውን የኢትዮ/ኤርትራ የሰላም ስምምነት ፈጸመ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ቀንድና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ባደረጓቸው ጉዞዎች፣ ራሳቸውንና መስተዳደራቸውን አስተዋወቁ። በኢኮኖሚ ፖሊሲ ረገድም በወቅቱ “ወደኒዮ ሊበራላዊ ሥሪት (Model) ያዘመመ” እየተባለ የተተቸውን ፖሊሲ አስተዋወቀ። የተወሰነ የዕርዳታና የብድር ገንዘብም ይፈስለት ጀመር።

ሦስተኛው ወቅት ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሰሜን ጦር ዕዝ ላይ በፈጸመው ውጊያ ተከፈተ። ውጊያው ወደ አማራና አፋር ተስፋፍቶ ቀጠለ። ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ እስከተደረገው ስምምነት ድረስ ዘለቀ። አራተኛው ወቅት፣ የድኅረ ፕሪቶሪያ ወቅት በሚል ሊጠቃለል ይቻላል።

በቅድሚያ ግን፣ ከላይ የተባለውን ሁሉ ማለት በለውጡ አመራር ረገድ ስህተቶች አልተፈጸሙም ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በማዘግየት፣ ሌላም ጊዜ ሁለት ዕርምጃ ወደፊትና ሦስት ዕርምጃ ወደኋላ በመመላለስ፣ ደግሞም አንዱንና ሌላውን አብዝቶ በማስታመም፣ ደግሞም ደግሞ ግልጽነትን በማውሸልሸልና የመሪ ግለሰብን ሥፍራና ሚና አብዝቶ በማጫወት፣ ወዘተ. በርካታ ስህተቶች ተፈጽመዋል። ብዙም አስከፍለዋል። ዝርዝሩን የማጥናትና የማካፈል ድርሻ በተለይም የውስጥ አዋቂዎች ፈንታ ነው።

ከፕቶሪያስ በኋላ

በኢትዮጵያ የአፄያዊ ግዛት ግንባታ (Empire Building) ዘመንም ሆነ በድኅረ አፄያዊ አገዛዝ ዘመን፣ የውጭ ኃይሎች ያልገቡበት ጊዜ የለም። በአፄ ልብነ ድንግልና በአህመድ ኢቢን ኢብራሂም አል ጋዚ (ግራኝ አህመድ) ዘመን፣ ፖርቲጊዞችና ኦቶማኖች ገብተው ነበር። ቅኝ ገዥዎች ይስፋፉ በነበረበት በአፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒልክ፣ አቤቶ ኢያሱና አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም፣ ከግብፅና ሱዳን እስከ እንግሊዝ፣ ከፈረንሣይ እስከ ከኢጣሊያ፣ ከጀርመን እስከ ቱርክ ገብተው ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ የኢሠፓና የሕወሓት ዘመንም የዘመኑ የምሥራቅና የምዕራብ ዓለም ጎራዎች የየወገናቸውን ለመደገፍ በእጅግ ገብተው ነበር። የዛሬው የድኅረ 2010 ዓ.ም. ጣልቃ ገብነት ከዚህ አንፃር፣ አዲስ ክስተት አይሆንም።   

ሆኖም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም አቀፋዊ አሠላለፍና ዓለም አቀፋዊ የኃይል ሚዛን የቀድሞው አይደለም። ወይም በ90ዎቹ ከደረሰው የሶቪየት ኅብረት መፍረስ ወዲህ፣ ዓለማችን ለአሃድ ዋልታ (Uni-polar) የበላይነትና ለብዝኃ ዋልታ (Multi-polar) ተቻችሎ መኖር በቆሙት ኃያላን ጎራዎች መካከል ተከፍላ፣ ኃያላኑ አክርረው የሚፎካከሩባት ዓለም ሆናለች።

የምዕራቡ ጎራ፣ የሶቪየት ኅብረትንና የዩጎዝላቪያን መንግሥታት ወደ በርካታ ትንንሽ አገሮች የመከፋፈል ስትራቴጂውን አጠንክሮ ተገበረ። የአበባ አብዮት ያለውን “አብዮት” አስፋፍቶ አቀጣጠለ። ሶቪየት ኅብረት ወደ 15 አገሮች ተሰነጣጠቀች። ዩጎዝላቪያ በሰሜን አትላንቲኩ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅት የጦር ኃይል ጭምር ተደቁሳ፣ ወደ ሰባት ትንንሽ አግሮች ተሰነጣጠቀች። የአውሮፓ ኅብረት ከአምስት ወደ 27 አባላት አደገ። የሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅትም ከ12 ወደ 30 አባል አገሮች አድጎ እስከ ሩሲያ ጠረፍ ድረስ ተስፋፋ። በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ አፍጋኒስታንን፣ ኢራቅን፣ ሶሪያን፣ የመንንና ሊቢያን በከፍተኛ የተዳቀለ ጦርነት (Highbrid War) በሚባለው የዘመናዊ የጦር፣ የፕሮፓጋንዳና የዕቀባ ጦርነት ኃይል አደቀቀ። ቻይናን የቲያናንሜን ተቃውሞ በተባለው የ1981 (1989) እንቅስቃሴ ለመተናኮስ ሞከረ። የኮቪድ-19 ቫይረስ ከምርምር ጣቢያዎቿ እንዳፈተለከም በብዙ አተተ። የደቡብ አሜሪካን ግራ ዘመም መንግሥታትን “የአባባ አብዮት” በሚባልና በምርጫ ስም በተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥቶች አፈነቃቀለ። የኢራን፣ የሩሲያ፣ የቻይናንና የቱርክን ኢኮኖሚዎች በበርካታ ዕቀባዎች ወደማዳሸቅ ተሻገረ። በሩቅ ምሥራቅም ታይፔን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ ጃፓንን፣ ፊሊፒንስንና አውስትራሊያንን አስከትሎ፣ ቻይናን ወደ መገዳደር አመራ።

ይሁን እንጂ፣ የብዝኃ ዋልታውም ጎራ ተመልካች አልነበረም። ብሪክስ (BRICS) የተባለውን የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የህንድ፣ የቻይናና የደቡብ አፍሪካ የፋይናንስ ኅብረት እ.ኤ.አ. በ2002 (2010) አቋቋመ። እ.ኤ.አ. በ1936 (1944) የብሬቶን ውድስ ስብሰባ ተወስኖ የነበረውን የዶላር የበላይነት ሥፍራ ወደ መፋለም አቀና። የምዕራቡ ዓለም በብሬቶን ውድሱ ስምምነት መሠረት በዶላር ብቻ እያለ ጨቡዶ የያዘውን የዓለም አቀፍ ንግድ ልውውጥ ሥርዓት ለመገዳደርም፣ አዲስ የዓለም አቀፍ ንግድ ልውውጥ ሥርዓትን በተጓዳኝ መሠረተ። የመጀመርያው ምዕራፍ በአገሮች መካከል የሚካሄደውን ልውውጥ በዶላር ሳይሆን፣ በዓይነት የማድረግ ነበር። ዕርምጃው በብዙ እንደተነገረው በዓለም አቀፍ ግብይት ውስጥ የዶላርን ሥፍራ የጎሸመ ብቻ አልነበረም። የምዕራቡን ዓለም የዕቀባ ጡንቻ ለማልፈስፈስ የበጀም ነበር።

የዶላርን የበላይነት ለማሽመድመድ የሚካሄደው ትንቅንቅ ስዊፍት (SWIFT-Society for Worldwide Interbank Financial Telecommunications) የሚባለውን የአሜሪካንን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላለፊያ መረብ በማጥቃት ቀጠለ። ሩሲያ ከ1996 ዓ.ም. (2004) ጀምሮ ኤስፒኢፋኤስ  (SPFS-System for Transfer of Financial Messages) የተባለውን የራሷን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላለፊያ መረብ ገነባች። ቻይናም ሲአይፒኤስ (CIPS-China International Payments System) የተባለውን መረብ ዘረጋች። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ በሁለቱ መንገዶች የሚፈጸመው የንግድ ልውውጥ ከዓለም አቀፋዊ ንግድ ውስጥ እስከ 15 በመቶ የደረሰ ሆነ። አሁን አሁን፣ ፔትር ዶላር የሚባለውም በፔትሮ ዩሃን እየተተካ ጭምር መፈጸም ጀመረ። ይህ እየጨመረ የሄደውን ያህል፣ የዶላርን የበላይነትና የዕቀባ ጡንቻ እያሟሸሸው እንደሚሄድ እየተዘገበ ነው። የቻይና የኢኮኖሚ ጡንቻ የአሜሪካን ኢኮኖሚ፣ የህንድም ኢኮኖሚና የጃፓንን የሚያልፉበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ እየተዘገበ ቀጥሏል። ዕውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም፣ የአሜሪካ ዶላር የገዥነት ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን እያስታወቁ ናቸው።

የምዕራቡ ዓለም ዩክሬይንን የውስጥ ጦርነት ለማስቆም በ2007 (2015) በኪዬቭና በሞስኮ መካከል የተፈረመውን የሚኒስክ ውል ጥሶና የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ጦሩን ወደ ዩክሬይን አስገብቶ ለመስፋፋት አኮበኮበ። ሩሲያ “አሁንስ ከልክ አለፈ” እንደማለት ብላ፣ የጦር ኃይሏን ዩክሬይን አስገባች። በዋልታዎቹ ጎራዎች መካከል የሚካሄደው ዓለም አቀፋዊ ትንቅንቅ ከጫፍ ደረሰ። ትንቅንቁን አንዳንድ አሳቢያን “የሦስተኛው የዓለም ጦርነት መጀመርያ ሊሆን ይችላል” እያሉ ሲያነቡት፣ ሌሎች “እንዲያውም ተጀምሯል” እያሉ እስከማንበብ ድረስ ሄደው እየተሰሙ ናቸው። 

በዚህ የኃያላኑ ትንቅንቅ ውስጥ አፍሪካም ደግሞ ደግሞ የኃያላኑ ሌላ ዙር ትንቅንቅ መፏከቻ አኅጉር ሆነች። የምዕራቡ ዓለም በአፍሪካ መንግሥታት ላይ የሚፈጸመው ግፊትና ጫና በተለይ የባይደን አስተዳደር ከመጣ ወዲህ ተጠናክሮ መካሄድ ያዘ። አፍሪካን ያልጎበኝ አንድም የኃያል አገር መልዕክተኛ የለም። የአፍሪካን መሪዎች ወደ አገሩ ያልጋበዘ አንድም ኃያል መንግሥት የለም። የጦር ሠፈሩን በአንዱ ወይም በሌላው የአፍሪካ አገር ላይ ያልመሠረተ አንድም ኃያል መንግሥት የለም። አንዱን ወይም ሌላውን የአፍሪካ መንግሥት መስተዳድር አጋር ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍና ብድር ያላፈሰሰ አንድም ኃያል አገር የለም። አንድም ያልተገባ ቃልም የለም። ከ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ለውጥ ወዲህ ደግሞ፣ የምዕራቡ ዓለም ግፊትና ጫና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ጠንከሮ ቀጠለ።

ከላይ በተመለከቱት በአራት ወቅቶች ዘመን የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን በሚመለከት የተከተለው ፖለቲካ ሁልጊዜም አንድና ያው አልነበረም። እንዲያውም ቢባል ወደ እውነታው ይጠጋል፣ እንደ ተፋላሚዎቹ ጎራ ወቅታዊ የኃይል ሚዛን የሚለዋወጥ ነበር። የተለዋወጠውም፣ የጎራዎቹን ጡንቻ ከአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ግቡና ጥቅሙ አንፃር እየሰፈረ ይመዝን ስለነበር ነው። በሁለተኛው ወቅት ለምሳሌ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የምዕራቡን ድጋፍ እየተላበሱ የመጡ መስሎ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤልን የሰላም ሽልማት ሲሸለሙ ደግሞ፣ የምዕራቡ ዓለም ድጋፍ ተጠቃሎ እንደተቸራቸው የተረጋገጠ መስሎ ነበር። ይህ ግን የሕወሓት ሁለተኛ ዙር ውጊያ እስኪጀምርና እስኪፍም ድረስ የቆየ ነበር።

ስለነበረም በሁለተኛው ወቅት የሕወሓትን ጎራ ጠንካራው አድርጎ ወሰደው። ድጋፉን የዚያኑ ያህል ወደ ሕወሓት አዞረ። አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መስተዳድር ላይ በፕሮፓጋንዳና በዕቀባ ሊጭኑ የሚችሉትን ጫና ሁሉ ጫኑ። በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያን ወጥረው ያዙ። ግብፅና ሱዳን “የዓባይ ዕቅድ” ያሉትን ወታደራዊ ውል ተፈራረሙ። ሱዳንም የኢትዮጵያን ግዛት ወረራ ያዘች። ሕወሓት ደብረሲና ሲደርስ ደግሞ፣ ዲፕሎማቶቻቸውና ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዙ። አዲስ አበባ በሕወሓት ጦርና ኦነግ ሸኔ በሚባለው ቡድን ሥር የምትወድቅበትን ቀን ወደ መቁጠር ተሻገሩ። ጀኔራል ፃድቃን፣ ‹‹አልቋል እኮ! ከማን ጋር ነው የምንደራደረው?›› እያሉ፣ ሕወሓት የድሉን ፅዋ ተረክቦ እንዳበቃ አስታወቁ። የምዕራቡም ዓለም፣ “ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ትናዳለች” ያለውን ንፅፅር አብዝቶ ነፋ።

አንድ ባሮኔስ አርሚንካ ሄሊች የሚባሉና የእንግሊዝ መስተዳድር የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ለመሆን የበቁ ሴት፣ በሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕለት (August 2 2021) ባሠራጩት ጽሑፍ ‹‹የዩጎዝላቪያ የገደል ማሚቱ በኢትዮጵያ ምድር እየጮኸች ነው›› እያሉ የማይነፃፀረውን እስከማነፃፀር ሄዱ። ሌሎችም እንደ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ እንደነበሩት አሌክስ ሮንዶስና በኅዳር 1988 ዓ.ም. (November 12, 1995) የዩጎዝላቪያን መሰነጣጠቅ ያተመውን የዴይተን ስምምነት ካረቀቁት ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩት ማርክ ሜዲሽ፣ “ኢትዮጵያን እንደ ቦዝኒያ መሸንሸን ነው” (Bosnification of Ethiopia) እያሉ መከሩ።

አሁንም ይህ ግን የኢትዮጵያው ጎራ መቀሌን ለቅቆ ከወጣ በኋላ መልሶ እስኪደራጅና ከመከላከል ወደ ማጥቃት እስኪሻገር ድረስ የሰነበተ ነበር። ሌላም ሕወሓትም ሆነ ምዕራባዊያኑ ባልጠበቁት የብሔራዊ ክተት ዘመቻ እስኪንቀሳቀስና ወደ ማጥቃት እስኪሠለፍ ድረስ ነበር። በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ “#በቃ” (“#NO MORE”) በተባለው እንቅስቃሴ እስኪነሳሳና አደባባዮችን እስኪያጥለቀልቅ ድረስ ነበር።

በዚህኛው ሁለተኛ ዙር በተባለው የውጊያ ወቅት፣ ሕወሓት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተሸንፎ ወደ ክልሉ ተገፋ። ሆኖም ጥቂት ቆይቶ ሦስተኛ ዙር የተባለውን ውጊያ ወደ አማራና አፋር አስፋፍቶ ከፈተ። አሁንም ደግሞ ግን፣ ጥምር ኃይል በተባለው ኃይል ክፉኛ ተሸንፎ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ክልሉ ተመለሰ። ስለዚህም ቢባል እውነታ ነው፡፡ ለሕወሓት ከእንግዲህ የቀረው ምርጫ የአራተኛው ወቅት ከፋች ወደሆነው ወደ ፕሪቶሪያ ማቅናት ብቻ ሆነ። ለምዕራቡ ዓለም የቀረውም አማራጭ “ለአፍሪካ ችግሮች፣ አፍሪካዊ መፍትሔ” የተባለውን የአፍሪካ ኅብረት መርሆና አቋም ተቀብሎ፣ ረድፉን ከአፍሪካ ኅብረት ጋራ ማስተካከል ብቻ ሆነ። የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈረመ። ዶ/ር ዓብይም ከእነ ጭራሹ፣ ከባይደን ሳሎን ገብተው የቴሌቪዥን ተመልካች ሆኑ። የአሜሪካና የአውሮፓ መልዕክተኞች መጉረፍ ያዙ። የገንዘብ ዕርዳታና ድጋፍንም መለቀቅ ተጀመረ። መለስ ብሎ ያስታወሰ፣ ሕወሓት ‹‹የዓብይን መስተዳደር ከመጪው መስከረም በኋላ አላውቀውም። ሕጋዊነት የለውም፤›› ያለበትን ጊዜ አሰበ። ተመሳሳይ አቋም ሲያስተጋቡ የነበሩትን ድርጅቶችና ግለሰቦች መቁጠር ያዘ።

‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባይደን ሳሎን ስለገቡ ግን፣ የምዕራቡ ጫናና ግፊት ተለሳለስ ማለት አይደለም። ጫናው አሁንም ባልተነሳው የአጎዋ ዕቀባ እንደቀጠለ ነው። የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ወጥቷል/አልወጣም በሚል ምልልስ እንደቀጠለ ነው። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ጥር 22 ዕለት ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ‹‹የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪዎች ለግብፅ የህልውና ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ያስፈልጋል›› በማለት የሰጡት ማሳሰቢያም፣ የጫናውን መቀጠል ያመለክታል። የኢትዮጵያን የህልውና ጥያቄ ከመጤፍ አለመቁጠራቸውም፣ የባይደን አስተዳደር የሚሄዱበትን ዕርቀት ያመለክታል። ሌላም ስለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስንት ሲሉ የነበሩት ምዕራባዊያን መንግሥታት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሚዲያዎች፣ ኦነግ ሸኔ የሚባለው “ነፃ አውጭ” በገፍ ስለሚፈጽማቸው ጥሰቶች ትንፍሽ አለማለታቸው፣ ይህ ሁሉና ከውጭ ያለው የማያውቀው ሌላም ብዙ ብዙ በእኔ ዕይታ የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን አስጎንብሶ ለመዳከም በሚያካሂደው የአስጎንባሽ ፖለቲካ ውጤቱ፣ ገና ገና ያልረካ መሆኑንና ገና ገና በተለያዩ ጫናዎች እንደሚቀጥል ነው።

ማጠቃለያ

የድኅረ ፕሪቶሪያው ትንቅንቅ በመሠረቱ ከቅድመ ፕሪቶሪያው የተለየ አይደለም። የሰሜኑ፣ በሕወሓትና በኢትዮጵያ መስተዳድር ገና ለረጅም ጊዜ በሚካሄዱት የእሰጥ/አገባ ከፍ/ዝቅ የሚወሰን ይሆናል። ይህም በዋናነት በአንድ ወገን፣ ሕወሓት ከእንግዲህ በትግራይ ውስጥ ባለው ወይም በሌለው ጉልበት የሚወሰን ይሆናል። በሌላውም ወገን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተቃዋሚ ሕወሓትያን ባላቸው ወይም በሌላቸው ጉልበት የሚወሰን ይሆናል። ነገር ግን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ መስተዳድር በሚወስደውና በማይወስደው ዕርምጃም። የመጨረሻ መጨረሻ የሚወሰነው የትግራይ ሕዝብ በሚዘምበት አቋም ይሆናል።

በሌላ በኩል በብልፅግና ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ለበለጠ የሥልጣን ዘገናና ለበለጠ የሀብት ምንጮች አፈሳ የሚካሄደው ትንቅንቅ ይበልጥ እየጎላ ይመጣል። እንዲሁም በየብሔሩ ውስጥ ያሉት የተለያዩ የብሔር ድርጅቶች ከየክልሎቻቸው ገዥ የብሔር ድርጅቶች ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ። እንዲሁ ደግሞ፣ እየተመሠረቱ ባሉት አዳዲስ የአስተዳደር ክልሎችና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ማንነት ረገድ በሚነሱት ጥያቄዎች ረገድ። እንዲሁም ደግሞ ጥር 14 ቀን የተቀሰቀሰው የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ውስጣዊ ትንቅንቅ በሚስተናገድበት ወይም በማይስተናገድበት መንገድና አፈጻጸም።

የተመለከቱት ጉዳዮች በራሳቸው አስጨናቂና አስጊ መሆናቸው ሳያንስ፣ በአንድ ወገን የፌስቡክና የዩቲዩብ ባለቤቶች “ሰበር መረጃ” እያሉ በየሰዓቱ በሚለቁት “መረጃ” እና በሌላውም ወገን መስተዳድሩ አንዳንዶች “ገዳይ ዝምታ” (Killing Silence) ባሉት መንገድ በመሄዱ፣ ጭንቅና ሥጋቱ ተበረታታ። ብዙዎች ምን ሊመጣ ነው? ብልፅግና ፓርቲና ሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶቹና ተዋናዮቹ ወዴት እየወሰዱን ነው? እያሉ ከመቆዘም ገቡ። ሌሎችም፣ በብልፅግና ድርጅት ውስጥ ሌላ ድርጅት አለ ወይ? በፌዴራሉ መንግሥትና በተለይም በኦሮሞ ክልል መንግሥት ውስጥ ሌላ ጥልቅ መንግሥት (Deep State) የሚባለው መንግሥት አለ ወይ? እያሉ ጠየቁ። በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ሁከት ሰሞን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ “የተደራጀውን ቡድን” ምንነትና ማንነት ባይገልጽም፣ “ትምህርት ቤቶችን የሁከት ማዕከል ለማደረግ የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ቡድን እንዳለ” ሲያስታውቅ ጥርጣሬው አየለ።

በዚህ አኳያ በአንድ ወገን ምንነቱ የማይታወቅ “ነፃ አውጭ” የግድያ፣ የዕገታ፣ የዝርፊያ፣ የማፈነቃቀልና የአውዳሚ አድማሱን አስፍቶ ሲንቀሳቅስና መንግሥት በሌላው ወገን አንዴ “ደመሰስኩ” እያለና ሌላም ጊዜ “ጠንካራ ዕርምጃ ወሰድኩ” እያለ ሲመላለስ በመደመጡ ጥርጣሬው ተጠናከረ። መንግሥት አለ ወይ? የሚለው ጥያቄ ተስተጋባ። ከጥር 14 ወዲህ በአንድ እግዚአብሔር ቤት ዜጋ፣ ብሔር፣ ዘር፣ ድንበር፣ ጠረፍ፣ ወሰንና ክልል የለም ቢባልም በብሔር ስም የብሔር ክልል ሲኖዶስ ምሥረታ እንቅስቃሴ ሲነሳ ደግሞ የጥርጣሬው አድማስ ሰፋ። አንዳንዶች የራሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የአቶ ሽመልስ አብዲሳን ሥፍራና ሚና እስከ መጠየቅ ሄዱ። ሌሎችም ኸርማን ኮኸን ገና ጳጉሜ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. (07/09/2022) በሰደዱት ትዊት፣ ‹‹የኦሮሞ ብሔር ለብዙ ትውልድ ከፖለቲካ ሥልጣን ተገልሎ ነበር። አሁን በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር እንቅስቃሴ፣ የኦሮሞን ድምፅ መሰማት ያረጋግጣል፤›› እስከ ማለት ድረስ ሄደው መነበባቸውን እያስታወሱ፣ የውጭ ኃይሎችን ሥፍራና ሚና ወደ ማውጣት/ማውረድ አቀኑ። ኢትዮጵያ እንደ ዛሬው በየጎራቸው የከቸቹ የሥልጣን ተፋላሚዎች ገጥመዋት አታውቅም። ከእንደ ዛሬውም ዓይነት አደገኛና ማብቂያው ከማይታወቅ ዘመን ውስጥ ገብታ አታወቅም። 

አባቶች ምንም ነገር/ሁነት ያለተቃራኒው አይኖርም የሚባለውን፣ “ክፉ ከሌለ ደግ የለም” እያሉ ያስተምራሉ። እንቅስቃሴውን ከዚህ አንፃር የዘገዩትን የቤተ ክህነት ሪፎርሞች ለማሳለጥ የደረሰ ዕድል አድርጎ ለመመልከት ይችላል። የፖለቲካና የቤተ ክህነት ተዋናዮቹ በዚህ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታ ውስጥ ልብ ገዝተውና ሰክነው የኢትዮጵያን ሕዝቦች ዓለማዊና መንፈሳዊ ህልውና በጋራ ወደፊት መንፈስና ራዕይ ለማቆም እስካልበቁ ድረስ፣ ኢትዮጵያን ለከፉ ዕልቂቶች፣ ውድመቶችና መፈነቃቀሎች የሚዳርጓት ይሆናሉ። የዕልቂትና የውድመት መጠኑንና የማብቂያውን ዘመን ለመገመት አይቻልም።

ሆኖም አንድም ዜጋና ብሔር፣ አንድም የሃይማኖት ወገንና ክልል የማይተርፍበት ዕልቂትና ውድመት እንደሚሆን ለማሰብ ነብይ መሆን አያስፈልግም። የዚህ ዓይነቱ ውጤት አራማጅ ማንም ይሁን ማን ኢትዮጵያን በዜጎቿ፣ በብሔሮቿና በሃይማኖት ወገኖቿ አናት ላይ የሚያፈርስ ይሆናል። ዋናዎቹ ተጠያቂዎች ዞሮ ዞሮ የዛሬዎቹ የፌዴራል፣ የክልሎችና የሃይማኖት ባለሥልጣናት ይሆናሉ። ነገር ግን የዛሬ ልጆችና የልጅ ልጆች ነገና ከዚያ ወዲያ “የት ነበርክ/የት ነበርሽ?” እያሉ ከሚያቀርቡት የታሪክ ተጠያቂነት ክስ የሚያመልጥ ወላጅና አሳዳጊም አይኖርም።

ለውጡ አሁንም የኢትዮጵያን “ፌዴራል” አስተዳደር አወቃቀር አገራዊ/ብሔራዊ ተቀባይነትና ቅቡልነት ባለው የፌዴራል አስተዳደር ሥርዓት አሻሽሎ የማቆም ነው። ሕገ መንግሥቱን አገራዊ/ብሔራዊ ተቀባይነትና ቅቡልነት ባለው ሕገ መንግሥት የማሻሻል ነው። ሁለቱም ማሻሻሎች ደግሞ፣ የፌዴራል ሰጥቶ/መቀበል (Federal Bargain) በሚባለው ሥርዓታዊ አካሄድና ቴክኒካል መንገዶች ሊስተናገዱና ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው። ይህም በቅድሚያና ከሁሉም በፊት፣ በአዲስት ኢትዮጵያ አብሮ የመኖርን የጋራ ወደፊት ለመቅረፅ፣ ለማቆምና ለመገንባት የቆረጡ፣ የተነሳሱና የደፈሩ የፖለቲካና የመንፈሳዊ አመራር መሐንዲሶችን ይጠይቃል።

አንዳንዶች ዛሬ በ2015 ዓ.ም. አጥብቀው እንታገላለን የሚሉት የኢትዮጵያ ልጆች  ከ50 ዓመታት በፊት ባደረጉት ትግል የሻሩትን የአፄያዊ አገዛዝ ሥርዓት ነው። ራሳቸው የብሔር ድርጅቶች ከ30 ዓመታት በፊት የሻሩትን የብሔር ጭቆና ሥርዓት ነው። ከእነዚያ ዓመታት ወዲህ ብዙ ክረምት አልፏል። የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ወንዞችን ተሻግሯል። ተዋናዮቹ አተኩረው ቢያጠኑት፣ ያለፉት ዘመናት የታሪክ አተራረክ ግድፈቶች በአዲስ የታሪክ ዕይታ አተራረክ የሚታረሙ ናቸው። ስለዚህም፣ ታሪክ ዛሬ የለገሳቸው አጋጣሚ በትላንቱ እንዲጋጩና እንዲያጋጩ አይደለም። የየጎራቸውን ተከታይ በትናንቱ ቁስል እየቆሰቆሱና በቁርሾ ማወራረድ ሒሳብ እያቦዙ እንዲያናጩና እንዲያጫርሱ አይደለም።

የዛሬው የ2015 ዓ.ም. ታሪክ ሠሪዎች እነሱው የዛሬ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። የታሪክ እጥፋት  የሰጣቸውን የታሪክ ሠሪነት ዕድል ተገንዝበው ዘመን ተሻጋሪ ታሪክን እንዲሠሩ ነው። በጋራ መክረውና ዘክረው፣ የቀደሙት ገዥዎች ያልሠሩትን የአዲሲት ኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አዋላጆችና አራማጆች እንዲሆኑ ነው። የዜጎቿና የብሔሮቿ መብቶች የተረጋገጡባትንና የአንዱ ዜጋና ብሔር መብት ከሌላው ዜጋና ብሔር መብት ድንበር ላይ የቆመባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች (Founding Fathers) እንዲሆኑ ነው። ከ”ነፃ አውጭዎች” ነፃ የወጣች ሰላማዊት ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች እንዲሆኑ ነው። ከሙሰኛና አንገላች ባልሥልጣናት ካድሬዎች የተገላገለች ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች እንዲሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተመፅዋችነት የሚወጡበትን ዘመን ከፋች እንዲሆኑ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ ተገቢ ቦታዋን ይዛ እንድትገኝ የሚበረቱ እንዲሆኑ ነው። ተቃራኒው የአፈረሰ እንጂ፣ የገነባ ታሪክ አይሆንም።

ተዋናዮቹ ለተመለከተው ከፍታ በቅተው ከተገኙ፣ ኢትዮጵያ ቴክኒካዊ መንገዱ ለሚጠይቀው የዕውቀትና የተመክሮ ሀብት ደሃ አይደለችም። በቂ የፖለቲካ፣ የሕገ መንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ የሕግ፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ. ባለሙያዎች ባለፀጋ ናት። ተዋናዮቹ በእውነትም ለከፍታው ከበቁም ከአፈረስን ይልቅ፣ የገነባን ታሪክ የሚዘመርበት ዘመን ይከፈታል። የዛሬዎቹ ልጆችና የልጅ ልጆች “የት ነበርክ/የት ነበርሽ?” የሚለውን ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዘመን ከወዲሁ ይሻራል። ወላጅና አሳዳጊን ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጥያቄ ፊት የሚያስቀረቅረው ዘመንም ከወዲሁ ተሽሮ ይተናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...