Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በዚህ የጎልማሳነት ዘመኔ ብቻ ሳይሆን ከወጣትነቴ ጀምሬ ሁሌም ከቤቴ ስወጣ፣ ፈጣሪዬን ‹‹በሰላም አውለኝ›› እላለሁ፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም የለም፡፡ ሊኖር የሚችለው ውድመትና ዕልቂት ብቻ ነው፡፡ ማንም ጤነኛ ዜጋ ደግሞ ግጭትን፣ ውዝግብንና አላስፈላጊ ፀብን የሚጋብዝ ችግር ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ በውይይትና በንግግር ችግሮችን መፍታትን ይመርጣል፡፡ ከፀብ ይልቅ ሰላም በማስፈለጉ ነው ‹‹ሰላም አውለኝ›› መባል ያለበት፡፡ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ሰላማዊ ከሆነ ችግሮቻችንን በሙሉ በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት አያዳግተንም፡፡ ነገር ግን ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሲያካትት ነው፡፡ ሁሉም የተካተተበት ሰላም የሚገኘው ግን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሕገወጥት ሲነግሥ ሰላም አይኖርም፡፡

የእኔ ገጠመኝ መነሻም የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ የተፈጸመ ነው፡፡ እንዳልኳችሁ የዛሬ ሃያ ዓመት በዕለተ ሐሙስ፣ እንደተለመደው ‹‹በሰላም አውለኝ›› ብዬ ወደ ሥራዬ ስሄድ ስልኬ ጮኸ፡፡ የደወለልኝ ጓደኛዬ ስለነበር ምን ፈልጎ ይሆን በጠዋት የሚደውለው በማለት አነሳሁት፡፡ ጓደኛዬ አራት ኪሎ አካባቢ ረብሻ መነሳቱን መስማቱን ነግሮኝ ጥንቃቄ እንዳደርግ ነገረኝ፡፡ ከምኖርበት ኬንያ ኤምባሲ አካባቢ የተሳፈርኩበት ወደ አራት ኪሎ የሚሄደው ሚኒባስ ታክሲ ግንፍሌ አካባቢ ሲደርስ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል፡፡ ረዳቱ ወጥቶ ሲያጣራ አራት ኪሎ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በመረበሹ መሆኑን ነገረን፡፡ ውረዱ ተብለን እየፈራን እየተባን ወደ አካባቢው ስንደርስ ጭር ብሏል፡፡ መንገዱ ላይ ግን የተወረወሩ ድንጋዮች ይታያሉ፡፡

እንደገና ስልኬ ሲጮህ አነሳሁት፡፡ አሁንም በዓይኔ እያየሁ ስላለሁት ረብሻ ጉዳይ የሚጠቁመኝ የማስጠንቀቂያ የወዳጅ መልዕክት ነው የተላለፈልኝ፡፡ አልፎ አልፎ ከሚሰማ ጩኸት በስተቀር እንደተባለው ያን ያህል አሥጊ ነገር አይታይም፡፡ ቆየት ብሎ ግን ፖሊስ ገብቶ ረብሻውን ማስቆሙን፣ ነገር ግን በተማሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት የተጎዱ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ሰማሁ፡፡ በተማሪዎች መካከል የተከሰተው ፀብ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስጠይቅ፣ በግቢው ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች አንድን ብሔር የሚያንቋሽሹ ስድቦች በመጻፋቸው መሆኑን ተረዳሁ፡፡ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ማንም ሰው እንኳን ወገኑን ቀርቶ ሌላ ባዕድ እንኳ ቢሆን በማንነቱ ምክንያት ለምን ይሰደባል? ያውም ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች በብሔር ምክንያት ተከፋፍለው ተጋጩ ሲባል ማፈር ያለበት ማን ነው? ማን ማንን ለመስደብ መብት አለው? ማን ከማንስ ይበልጣል? መማርና ማወቅ ለእንዲህ ዓይነት ስህተት የሚዳርግ ከሆነ የትምህርት ጥቅሙ ምንድነው? በጣም የሚያሳዝን ክስተት ነበር፡፡

ምሳ ሰዓት ላይ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን የዩኒቨርሲቲውን ካምፓስና አካባቢውን ስንቃኝ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች እየተገላመጡና እየተሸማቀቁ አካባቢያቸውን ሲቃኙ ማየት ግን ያሳዝን ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከስድስት ኪሎ እስከ አራት ኪሎ ድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና መብት በጋራ እንዳልተጮኸበት፣ ብሔር መራሽ ግጭት ተከሰተበት ሲባል የዛሬን አያድርገውና በወቅቱ እጅግ በጣም የሚያናድድ ነበር፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በእዚህ ድርጊት ማፈር ሲገባው፣ በአጠቃላይ ግን እንደ አገር ማፈር ያለብን ሁላችንም ነበርን፡፡ ለግለሰብ መብት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት በሚባልበት በአሁኑ ዘመናችን፣ በብሔር ተቧድኖ እርስ በርስ እየተጋጩ በሕዝባችን ውስጥ ቁርሾ መፍጠር የኋላቀርነት መገለጫ መሆኑን፣ ከዚህም አልፎ ተርፎ የጠላት መሣሪያ መሆን እንደሚከተል ከጓደኞቼ ጋር ማውራታችን አይዘነጋኝም፡፡

አራት ኪሎ ሰላም መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ምሳ እየበላን ስለጉዳዩ ስንወያይ ድንገት ሁለት ሰዎች አጠገባችን ካለው ጠረጴዛ ወንበሮች ስበው ተቀመጡ፡፡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየተነጋገሩ ስለነበር እነሱም ይኼንኑ ጉዳይ እየተወያዩበት እንደሆነ አወቅኩኝ፡፡ አንደኛው በንዴት፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ ተማሪዎች እንዴት እንዲህ ዓይነት የብልግና ስድብ ይጻፋል?›› እያለ ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም በብስጭት፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? እዚህ አገር እኮ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ከማከም ይልቅ ቸል ማለት እየበዛ ነው…›› አለው፡፡ ያኛው እንደገና፣ ‹‹ይኼ ቸልታ ብቻ አይደለም ማለባበስና መደባበቅ የሚባል አጉል ባህል ስለተፀናወተን ነው…›› እያሉ ወጋቸውን ሲቀጥሉ፣ አብሮን የነበረው ጓደኛችን ደግሞ፣ ‹‹ሰማችሁ ይኼ ጉዳይ ስንቶችን እንደሚያሳስብ? እኔን ግን የሚታየኝ ሌላ ነው…›› አለን፡፡ ሁላችንም በአንድነት፣ ‹ምን ይሆን?› በማለት ጥያቄ አቀረብንለት፡፡ ጓደኛችን በአጭሩ፣ ‹‹ይኼ ችግራችን በጊዜ መላ ካልተበጀለት የባሰ እንደሚያመጣብን አትጠራጠሩ፡፡ ብሔርና ሃይማኖት ሲደበላለቁ ነው የሚታየኝ…›› ነበር ያለን፡፡

ያ ጓደኛችን እንደ ዘመኑ አጭበርባሪ ነብይ ተብዬዎች ወይም ጠንቋዮች አይደለም ሥጋቱን የገለጸው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ መድረሻው የት እንደሆነ የነገረን በምሳሌ ነበር፡፡ ‹‹አውሮፓ ወይም አሜሪካ ውስጥ ጥቁሮችን፣ ላቲኖችንና ዓረቦችን የሚጠሉ የነጭ ጽንፈኞች ታሪካዊ ዳራቸው ሲፈተሽ የሚፈልጉትን ለማድረግ ምንም ከመሆን ስለማይመለሱ ብዙ ትራጄዲዎችን ፈጽመዋል…›› ያለው አይረሳኝም፡፡ አሁንም በእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችን ቤተ እምነቶችን ጭምር በመዳፈር፣ ለተመልካችና ለሰሚ የሚዘገንኑ ድርጊቶችን እንደሚፈጽሙ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ የጽንፈኝነት የመጨረሻ ግቡ ዕልቂትና ውድመት ስለሆነ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ሰከን ብለው ለመፍትሔ ይተባበሩ እላለሁ፡፡

 (ጌትነት ሽመልስ፣ ከኬንያ ኤምባሲ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...