Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተር‹‹ጠላታችሁ መብራት ኃይል አይሂድ!››

‹‹ጠላታችሁ መብራት ኃይል አይሂድ!››

ቀን:

አንድ ካስተማሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በአብዛኞቹ የተናደደ ጓደኛዬ፣ ‹‹እስክንድር ወደፊት በመሥሪያ ቤትህ አለቃ ከሆንክ የሚያስቸግርህን ሠራተኛ ከፍለህ ዩኒቨርሲቲ አስተምረው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በላይ ትልቅ ቅጣት የለምና!›› ይለኝ ነበር፡፡ እውነቱን እዚያው ዩኒቨርሲቲ ስማር በመቅመሴ ከመጀመሪያ ዲግሪዬ በኋላ ከፍሎ የሚያስተምር ጭምር አግኝቼ ዕድሉን አሳልፌያለሁ፡፡

መብራት ኃይልም ሁለቴ ያጋጠመኝ ይኼው ነው፡፡ አንዱ የመብራት ቆጣሪ ጥያቄ አቅርቤ የደረሰብኝ መጉላላትና ከአቋሜ ተዛንፌ መብቴን እንዴት እንዳስከበርኩ የማልዘነጋው ነው፡፡ ‹‹ለምን እንዲህ አደረግህ?›› የሚለኝ፣ ባለጉዳይ ሆኖ ይሂድና መቅመስ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ ህሊና ወይም ‹‹እንትን ስለሆንኩ›› ብሎ ነገር በበቀል ጭምር ያስጎዳልና!

ሰሞኑን ሞባይል ስልኬን ከኪሴ ሳወጣ ስልኬ ላይ ተለጥፎ ከወጣ በኋላ ወድቆ በጠፋብኝ የመብራት ካርድ የተነሳ ለመተካት የደረሰብኝን አሳር፣ አይደለም እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓይነት ዕርምጃ ሊያስመኘኝ ጠላቴም እንዲገጥመው አላስብም፡፡ ለነገሩ በዚህ ጉዳይ ለመሄድ ሳስብ ታውሶኝ እየፈራሁ የነበረው በጋዜጠኞቹ ግርማ ፍስሐና መኮንን ወልደ አረጋይ በሚያዘጋጁት የሸገር ሬዲዮ፣ ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› እና ‹‹ማንን ምን እንጠይቅልዎ?›› ፕሮግራሞች ላይ የሰማኋቸው የደንበኞች እሮሮዎች ናቸው፡፡ የእሮሮዎቹን እውነትነት ታዲያ ሲደርስብኝ ያረጋገጥሁበት ገጠመኝ ነው የደረሰብኝ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱንና የሰዎቹን ማንነት በማልገልጽላችሁ የመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ያመራሁት ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ በተደጋጋሚ ስመላለስ እንዳየሁት ዓይነት፣ በዚህም ቀን የገጠመኝ እኔንና ተገትረን ፊታቸው የቆምነውን ባለጉዳዮች ‹‹ምን ልታዘዝ?›› የሚል መሆኑ ቀርቶ፣ ቀና ብሎ እንኳን ለማየት የሚፀየፉ ሠራተኞች ነው የገጠመኝ፡፡ በመከራ ቀስቅሰን ማሟላት የሚገባን ነገር የተነገረን፣ ‹‹የትም ስትንዘላዘሉ እየጣላችሁ፤›› በሚል ዓይነት በቁጣ ነው፡፡ አስቀድሜ የምነግራችሁ እስከመጨረሻው በነበረኝ ምልልስ የመውጫ እንጂ፣ የመግቢያ ሰዓታቸውን አክብረው ሲገኙ ያየኋቸው ሥራ አስኪያጁንና በጣት የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ብቻ ነው፡፡

በዕለቱ ከነበረብኝ የመስክ ሥራ መልስ ሰኞ የተነገረኝን አሟልቼ ስቀርብ አርፍደው ከገቡም በኋላ ቢሆን ያጋጠሙኝ ሦስት ባለሙያዎች አማራሪ ማስተናገድን አላየሁባቸውም፡፡ በተለይ አንድ ባለሙያ እኔን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ለመርዳት የሚያሳየውን ትጋት ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ መጨረሻም ላይ በኋላ የምገልጽላችሁን ሽልማት ሰጥቼዋለሁ፡፡

የሰነዱ ጉዳይ አልቆና ለምትክ ካርድ 700 ብር ከፍዬ፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ የጨረስኩትን ጉዳይ ካርድ በመረከብ ልቋጭ ከሌሎች ጋር ብቀመጥም ካርድ ሰጪው ሠራተኛ የለም፡፡ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ስንጠብቅ የቆየነው፣ ‹‹እየመጣ ነው፤›› ተብሎ የተዋሸንን በማመን ቢሆንም፣ ሲሰለቸን ሥራ አስኪያጁን አናገርነው፡፡ ደንበኛን ለማቅረብ በማይገፋው የሥራ አስኪያጁ ኮስታራ ፊት ቁጣ ቢጤ ታክሎበት፣ ‹‹ነገ ተመለሱ፤›› ተባልንና 5፡45 ሰዓት ላይ ተመለስን፡፡

በነጋታው የተገኘሁት ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት ቢሆንም፣ የምሳ መውጫ ስድስት ሰዓታቸውን አክብረው የሚወጡት አብዛኞቹ ሠራተኞች መግባት የጀመሩት ከ2፡30 ጀምሮ ነው፡፡ እነሱ እስኪገቡ ባለ ጉዳይ በሙሉ በሠልፍ የቆመው ሕንፃው ሥር ብርድ እየጠበሰው ሲሆን፣ ከሰዓትም ከምሳ እስኪመለሱ የሚጠብቃቸው ሐሩሩ እየለበለበው ነው፡፡

በተቀጠርነው መሠረት ካርድ ሰጪው የገባው 3፡45 ላይ ነበር፡፡ ፊቱ ላይ ንቀት የሚታይበት፣ ዕድሜው በ20ዎቹ መጀመርያ አካባቢ የሚገመተው ወጣት ላረፈደበት ይቅርታ መጠየቅ ይቅርና የምንነግረውን የሚያዳምጠን በተረጋጋ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ተራዬን ጠብቄ ይሰጠኛል ብዬ ስጓጓ ተነስቶ ወጣ፡፡ ይኼኔ በሥርዓቱ ወዳስተናገደኝ ባለሙያ ተጠግቼ ስነግረው አቀብሎት የሄደውን ከዚህ ቀደም ሲል ያገለገለ ካርድ ሰጥቶኝ ከሲስተም ጋር እንዲገናኝ ተደረገ፡፡

ወደ ቤት ከመሄዴ በፊት በሥርዓቱ ስለሚያስተናግደን ባለሙያ አድናቆትና ምሥጋናዬን ለሥራ አስኪያጁ አሳውቄ ከቆጣሪው ጋር ለማገናኘት ወደ ቤት ሄድሁ፡፡ ካርዴን ከቆጣሪው ጋር አገናኝቼ ወደ ሥራ ከገባሁ በኋላ፣ ሰው ልኬ የ200 ብር አስሞላሁ፡፡ ወደ ማታ ቤት ስመለስ ካርዱን ከቆጣሪው ባገናኝም ምንም ድምፅ አያሰማም፡፡ ወደ ቆጣሪው የገባ ገንዘብም የለም፡፡ ይህ ሳያንስ ቆጣሪው ላይ የነበረው ጥቂት ገንዘብ ማምሻውን አልቆ ጨለማ አደርን፡፡

በነጋታው ካርድ ወደ ሰጠኝ መብራት ኃይል በመሄድ ከብዙ ጥበቃ በኋላ ሠራተኞቹ ሲገቡ ካርዱን ከሲስተም ጋር ወዳገናኘው ባለሙያ ቀርቤ ሳስረዳው ማሽኑ ውስጥ አስገብቶ፣ ‹‹ይሠራል፡፡ አሁን ሄደህ ከቆጣሪው አገናኘው፤›› አለኝ፡፡ ሄጄ ብሞክርም አይሠራም፡፡ እናም ተመልሼ ስነግረው የደንበኞችን ቅድመ ክፍያ ካርድ ወደምትሞላው ባለሙያ ላከኝና ካርዱን መርምራ ሁለት መቶ ብር እንዳለው ነግራኝ ወደ ቤት ብሄድም አሁንም ካርዱ አይሠራም፡፡

ምልልሱ ስለታከተኝ ተናድጃለሁና አቤቱታዬን ለሥራ አስኪያጁ ሳቀርብ፣ ማስነሻ ካርድ ወደሚሰጡ ባለሙያዎች ላከኝ፡፡ እዚያም ከስንት ማጉላላት በኋላ ሞባይል ስልኬን በመያዣነት ተቀብለውኝ ወደ ቤት ተመለስኩ፡፡ መጀመርያ ማስነሻውን፣ ቀጥሎ ደግሞ የእኔን ካርድ ባስነካም ከበፊቱ የተለየ ነገር አላገኘሁበትም፡፡ ስለዚህ ተመልሼ ወደ እዚያው ሄጄ ለውጥ እንዳላየሁ የነገርሁት ባለሙያ ማስነሻውን ካርድ ተቀብሎኝ ስልኬን ከመለሰ በኋላ፣ ‹‹ቆጣሪው መቀየር አለበት›› አለኝ፡፡ ለማስቀየር ማድረግ ያለብኝን ስጠይቅ ቀድሞ ለጠፋብኝ ካርድ ያስገባኋቸውን ሰነዶች ኮፒ ከማመልከቻ ጋር እንዳስገባ ነገረኝ፡፡ ቀድሞ ያስገባኋቸውን ሰነዶች መጠቀም እንደሚችሉ ስናገር ቁጣ ቀምሼ ወጣሁና በትኅትና ለሚያስተናግደን ባለሙያ ነገርሁት፡፡ ‹‹ሳይመረመር እንዴት ቆጣሪ ይቀየራል?›› ብሎ እንዳላስቀይር ወደ ነገረኝ ተመልሼ ‹‹ይመርመርልኝ›› እንድል መራኝ፡፡ የተባልሁትን ተናግሬ የቆጣሪ መርማሪ ስልክ ተሰጠኝና ደውዬ ስነግረው ቤት ሆኜ እንድጠብቀው አሳወቀኝ፡፡ ‹ይመጣል› በሚል ከ9፡00 ሰዓት የጀመርኩ እስከ 12፡30 ሰዓት እየደጋገምሁ በመደወል ብጠብቀው ግን ‹‹እየመጣሁ ነው›› እያለ ዝር ሳይል ቀረ፡፡

ባለሙያውን ጥበቃ ብርድ እያንገበገበኝ ሳለሁ የጎረቤታችንን ልጅ ሳገኝ፣ ‹‹ብር እንደምትሰጣቸው ካልነገርካቸው መቼም አይመጡልህም፡፡ ስለዚህ እንዲህ እንደ አንተ ሲገጥመን ከሁለት መቶ ብር ጀምሮ እያስከፈሉ የሚሠሩ ሰዎች ስላሉ አንዱን ልጥራልህ፤›› ብላ በመደወል ጠራችልኝ፡፡

በስንት ድርድር በ300 ብር ሊሠራልኝ ምሽት ላይ የመጣው ሰው ቆጣሪው ምንም ችግር እንደሌለው፣ ችግሩ ያለው ካርዱ ላይ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስጠይቀው፣ ‹‹1,000 ብር ከከፈልኸኝ ነገ እስከ ቀኑ 6፡00 ካርዱን ለውጬ አስተካክልልሃለሁ፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እኔ ነገ ሄጄ እንዲለውጡልኝ ማድረግ እየቻልሁ ለምን ይህን እከፍላለሁ?›› ስለው፣ ‹‹የሚለውጡልህ ሌላ 700 ብር አስከፍለውህ፣ ያውም ቶሎ ከሰጡህ ነው፤›› ብሎ ተስፋ አስቆረጠኝ፡፡

ሌላው የገረመኝ፣ ‹‹ለዛሬ ጨለማ ላይ እንዳታድሩ ከቀጥታ መስመር ላገናኝላችሁና ነገ ካርዱን ለመብራት ኃይል ሰዎች የሻይ ሰጥቼ ካስተካከልሁላችሁ በኋላ መስመሩን ከቆጣሪ ጋር አገናኝላችኋለሁ፤›› ሲለኝ ነው፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ወንጀል ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ተስማምቼ ባደርገው እንኳ ነገ ጠዋት መብራት ኃይሎች ቆጣሪውን ለመመርመር ሲመጡ ቢደርሱብኝስ?›› ስለው፣ ‹‹እመነኝ፡፡ እነሱ መቼም አይመጡልህም፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ለማንኛውም ጠዋት እደውልልሃለሁ፤›› ብዬው ጠዋት የሆነውን ሁሉ ለሥራ አስኪያጁ አስረዳሁት፡፡ በነገርኩት መረጃ ይበሳጫል ብዬ ስጠብቀው፣ ምንም ከቁብ ያልቆጠረው ሥራ አስኪያጁ ካርድ እንዲለወጥልኝ መራኝ፡፡ ስልኬን ይዞ ማስነሻ ካርድ ለሰጠኝ ባለሙያ እንዲመረምርልኝ የነገሩኝ ባለሙያ እንዳላየልኝ፣ ከእርሱ ይልቅ ሌላ ሰው አይቶልኝ ቆጣሪው ምንም ችግር እንደሌለበት እንደነገረኝ አስረዳሁት፡፡ ጠብቄው ወደቀረብኝ ባለሙያ እንድደውል ጠቁሞኝ ደውዬ የነገረኝ፣ ‹‹ቆጣሪውን ያየላችሁን ሰው የላክሁት እኔ ነኝ፤›› በማለት ነበር፡፡ ቴአትሩ ግልጽ የሆነልኝ ይኼኔ ነው፡፡ ማስነሻዎቹም ሆነ ዋናው ካርድ በራሳቸው በመብራት ኃይሎች አማካይነት ወጥቶ ለሠፈር ‹‹አገልግሎት ሰጪዎች›› ተሰጥቷቸዋል ወይም ራሳቸው ሠራተኞቹ የምሽት መሸቀያቸው ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ይህን ድራማ በመግቢያዬ እንዳልኳችሁ በሸገር ሬዲዮ መብራት ኃይል ካማረራቸው ሰዎች ሰምቼው ነበረና!

በዚህ ደረጃ ላይ ሳለሁ በትኅትና ሲያስተናግደኝ የነበረው ሠራተኛ ጠርቶኝ የማይሠራውን ካርድ ተቀበለኝና ካርድ ወደሚሰጠው ወጣት ይዞኝ ሲሄድ አልገባም፡፡ ሥራ አስኪያጁ ሲደውልለት፣ ‹‹እየመጣሁ ነው፤›› አለው፡፡ ከቆይታ በኋላም ትዕቢት ባዘለ አኳኃን መጣ፡፡ በነገራችን ላይ በጣም እያረፈዱ የሚገቡት ሠራተኞች ከሥራ አስኪያጁ ቁጥጥር ውጪ ስለመሆናቸው እየደወለ፣ ‹‹ሥራ አትገቡም’ዴ?›› በማለት እየተበሳጨ ሲያናግራቸው በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ፡፡

ቀድሞም እየቀፈፈኝ የተቀበልሁት አሮጌ ነበረና በአዲስ ካርድ ተለውጦልኝ ከሲስተም ጋር ካገናኙልኝ በኋላ የስንት ብር እንደምሞላ ተጠየቅሁ፡፡ ከዚህ በፊት አሮጌው ካርድ ላይ የ200 ብር ስለሞላሁ እንዲዛወርልኝ ስጠይቅ እያስተናገደቺኝ ያለችው ወጣት በቁጣ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ! ስንት ጊዜ ነው እኔ ዘንድ የምትመላለሰው!›› አለቺኝ፡፡ የእሷንም ቁጣ፣ የሌሎቹንም ማንከራተትና ማመናጨቅ፣ እንዲሁም መናቅ ባለጉዳይ ነኝና ችዬ፣ 200 ብሬንም አስበልቼ፣ ሌላ 200 ብር በመክፈል በድጋሚ ስልኬን አስይዤ ከ‹‹ዜሮ ማስነሻ›› ካርድ ጋር ተሰጥቶኝ ወደ ቤት በረርኩ፡፡ እንደደረስኩ መጀመሪያ በማስነሻው፣ ቀጥሎ በዋናው ካርድ ቆጣሪውን ሳገናኝ 200 ብር ብቻ አስገባልኝ፡፡

አንድ መሥሪያ ቤት ሄጄ በመልካም ሁኔታ ላስተናገደኝ ሁል ጊዜ የማደርገው ልምድ አለኝ፡፡ ይኼውም ያሳተምኋቸውን መጻሕፍት ከምሥጋና ጋር መስጠት ሲሆን፣ በመልካም ሁኔታ ላስተናገደኝ የመብራት ኃይል ባለሙያም ልሰጠው ያዝኩኝ፡፡ ሁለት ዓይነት መጻሕፍቴን ልሰጠው የወሰንሁበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ማን እንደሆንኩ ጭምር አውቆ እንደ እሱ ላልሆኑት እንዲነግር ጭምር ነው፡፡

ከቤት ወደ መብራት ኃይልና ከመብራት ኃይል ወደ ቤት ለአንድ ጊዜ ደርሶ መልስ 25 ብር ሳወጣ የነበረውን ምልልስ ለመጨረሻ ጊዜ የቋጨሁት ማስነሻ ካርዳቸውን መልሼ ስልኬን ከተረከብሁና መጻሕፍቴን ለሚገባው ትሁት ባለሙያ ከሰጠሁ በኋላ ነው፡፡

በማጠቃለያዬ ከሬዲዮም ሆነ ከሰዎች የሰማሁትን አንድ ወንጀል ልንገራችሁ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ቤቶች፣ በተለይም ኮንዶሚኒየሞች ከቆጣሪ ባልተገናኘ የቀጥታ መስመር ይጠቀማሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ራሳቸው የመብራት ኃይል ሰዎችና ከመሥሪያ ቤቱ ውጪ ባሉ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው ሌላ ነገር ጉቦ ተቀብለው ከቀጥታ መስመር ጋር ከሚያገናኙት በተጨማሪ ሰው የማይኖርበትን ሰዓት አጥንተው ባለቆጣሪው ሳያይ ከቀጥታ መስመር ጋር በማገናኘት ከቀናት በኋላ ጠቁመው እንደሚያስይዙ በማስፈራራት ብዙ ሺሕ ብር የሚቀበሉ ናቸው፡፡

ከዚህ ሌላ ደግሞ እንዲሁ ሠፈር ጭር ባለበት የሰዎችን ቆጣሪ በመክፈት ማስነሻ እንዲፈልግ ካደረጉ በኋላ ተደውሎላቸው ብዙ ብር በመቀበልም ያስነሳሉ፡፡

እነዚህ ሁሉ ወንጀሎች የሚፈጸሙት በራሳቸው በመብራት ኃይል ሠራተኞችና ከእነሱ ጋር የጥቅም ግንኙነት ባላቸው የሠፈር ባለሙያዎች ነው፡፡

(በእስክንድር መርሐ ጽድቅ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...