Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ድርድር ላይ እያለን ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ብረት...

‹‹ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ድርድር ላይ እያለን ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ብረት ተሰርቋል›› አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ

ቀን:

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ የመንግሥት እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ በፌዴራልና በክልል የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማልማት፣ መከታተልና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን መጠበቃቸውን መከታተሉን በአዋጅ የተሰጠው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው፡፡ እየተገነቡ ካሉት መካከል አንዱ የሆነው የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ይጠቀሳል፡፡ ግንባታው ከጀመረ ሰባት ዓመታትን የተሻገረ ቢሆንም፣ የመጀመርያውን ምዕራፍ መሻገር ግን ተስኖታል፡፡ በበርካታ ውዝግቦች የታጀበው የስታዲየሙ ግንባታ ሒደት ከቻይናው የግንባታ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ውሉን ለማቋረጥ ከጫፍ ደርሷል፡፡ ግንባታው ሲጀመር በ5.7 ቢሊዮን ብር ውል እ.ኤ.አ. በመስከረም 2022 መጠናቀቅ ቢገባውም፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም አገሪቱ ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመግጠሙና ሥራዎች በመጓተታቸው ግንባታው ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡ በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ በአገር ውስጥ ለሚያደርገው ጨዋታ ስታዲየም በማጣቱ ‹‹ስደተኛው ቡድን›› የሚል ቅፅል ስም ተቸሮታል፡፡ በሌላ በኩል የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የሚኒስቴሩን ሕግና ደንብ ችላ በማለት ፌዴሬሽኖችን በራሳቸው መንገድ እንዳሻቸው ሲዘውሩት መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የስፖርት ዘርፍ እንቅስቃሴንና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ስፖርቱን ከሚመሩት ሚኒስትር ዴኤታ  መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሒደት ምን ላይ ደርሷል?

አምባሳደር መስፍን፡- በፌዴራል መንግሥት ከሚገነቡ ዋነኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ወይም ስታዲየም መካከል የአደይ አበባ ስታዲየም ዋነኛው ነው፡፡ የግንባታው አንደኛው ምዕራፍ በውሉ መሠረት ማለቅ የነበረበት እ.ኤ.አ. መስከረም ወር 2022 ነበር፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ በ900 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ነበር ስምምነት ላይ የተደረሰው፡፡ በአንፃሩ ሥራ ከተጀመረ በኋላ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣ የግንባታ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ተደረገ፡፡ ሥራው በመቆሙ የተነሳ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማጋጠሙ ቅድመ ክፍያ መክፈል አልተቻለም፡፡ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካለፈ በኋላ ክፍያው ተፈጽሞ ሥራውን ዳግም ለማጀመር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት፣ የቻይናው ካምፓኒ ቅድመ ክፍያ አልከፈላችሁም፣ እንዲሁም ክፍያው ባለመፈጸሙ ከውጭ ማስገባት የነበረብኝ ዕቃ ባለማስገባቴ የዓለም የዕቃ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል የሚል ቅሬታ አቀረበ፡፡ በዚህም ምክንያት ተቋራጩ የጠየቀው ተጨማሪ የዋጋ ተመን መንግሥትን በማስፈቀድ፣ 12 ሚሊዮን ዶላር ቅድመ ክፍያ በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ በኩል ከተፈቀደ በኋላ፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ገበያ ተመን ይተመንልኝ የሚል ሌላ መከራከሪያ አቀረበ፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- ምንድን ነው መከራከርያው፣ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታውን ለመጀመር ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ለድርድር መቀመጣችሁም ተገልጾ ነበር፡፡ ድርድሩ ምን ነበር?

አምባሳደር መስፍን፡- ካምፓኒው ቅድመ ክፍያው ሊከፍለኝ ይገባል ብሎ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ፣ ውይይት ተደርጎ 12 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈል ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ካምፓኒው ሌላ መከራከሪያ አቀረበ፡፡ ሆኖም ግን ካምፓኒው ቅድመ ክፍያውን ወስዶ ሁለት ዓመት አለመሥራቱን ጠቅሶ፣ ማስገባት የነበረብኝን ዕቃ አላስገባሁም በሚል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣ 5.7 ቢሊዮን ብር የነበረውን 19 ቢሊዮን ብር በማድረግ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ዓለም አቀፍ ገበያውን እያወቀ ለምን የቀረበውን ጭማሪ ዋጋ መቀበል ተሳነው?

አምባሳደር መስፍን፡- መንግሥት ዓለም አቀፍ ገበያውን ይረዳዋል፡፡ በአንፃሩ በአንድ ጊዜ የተጠየቀው ገንዘብ 19 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህ የገንዘብ መጠን የሦስት ክልል በጀት መሆን የሚችል ነው፡፡ ስታዲየም መገንባት ለስፖርቱ እንዲሁም ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ትልቁ ጉዳይ ግን አገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ ይወስነዋል የሚል ነው፡፡ አገሪቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በጦርነት፣ በጎርፍ እንዲሁም በአንበጣ ተወርራ ነው ያሳለፈችው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ያህል የገንዘብ መጠን መጠየቅ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በጉዳዩ ላይ ከተመካከርን በኋላ ከካምፓኒው ጋር ችግሩን በድርድር ለመፍታት ውሳኔ ላይ ደረስን፡፡ በአንፃሩ ድርድሩ ረዥም ጊዜ ወሰደብን፡፡ የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ካምፓኒ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ ወደ ጎን በመተው የፕሮጀክቱን ከፍተኛ ዋጋ ጠይቋል፡፡ በድርድሩም የመንግሥት አካላት ጭምር እንዲሁም በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጭምር ተካተውበት 12.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ ላይ ስምምነት ተደረሰ፡፡ ሆኖም ግን በድጋሚ በጀቱን 17 ቢሊዮን ብር አደረሱት፡፡     

ሪፖርተር፡- በድርድሩ ወቅት በ12.5 ቢሊዮን ብር ከተስማማችሁ በኋላ በምን መመዘኛ በጀቱ ሊጨምር ቻለ?

አምባሳደር መስፍን፡- ቀድሞ በመርህ ደረጃ ከተስማማን በኋላ ከስምምነቱ ጎን ተሠርቶ ለተከፈለ ሥራ ደምረው በጀቱን አሳደጉብን፡፡ ይህም ማለት ስምምነት ላይ የደረስንበትን የ12.6 ቢሊዮን ብር በጀት ድጋሚ አሳድገው ለድርድር ቀረቡ ማለት ነው፡፡ በዚህም በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን የገበያ ዋጋ እያሠሉ መምጣቱን ተያያዙት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በኮንስትራክሽን ውስጥ የተቀመጡትን አንቀጾች እየመዘዙ ጥቅማቸውን ብቻ ማሳደድ ጀመሩ፡፡

ሪፖርተር፡- በድርድሩ ወቅት ሚኒስቴሩ በውሉ መሠረት አቋም ይዞ ጥቅሙን የሚያስጠብቅ ድርድር ማድረግ ለምን ተሳነው?

አምባሳደር መስፍን፡- ካምፓኒው የውሉን የተለያዩ አንቀጾች እየመዘዘ ጥቅሙ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ጫና ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ልምድ በአግባቡ ተጠቅመውበታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ የማይቻል ከሆነ ሌላ አማራጭ ለመመልከት ሌሎች አጋሮችን ለመመልከት እንደ አማራጭ ወስደናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙን ሁለተኛ ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ሌላው የታሰበውን አማራጭ ቢያብራሩልኝ?

አምባሳደር መስፍን፡- የስታዲየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ከተጀመረ አሥር በመቶ ብቻ ነው የተሠራው፡፡ በድርድሩም ወቅት ሥራ አቁመው ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ኪሳራና በጣም የከፋው አጋጣሚ ነበር፡፡ ስለዚህ የካምፓኒው አካሄድ ጤናማ የውል አካሄድ ነው ብለን ስላላመንንና ካለን የበጀት አቅም አንፃር በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ በስምምነት ውል ለማፍረስ ጥያቄ አቀረብን፡፡ እነሱ ተቀብለዋል፣ ግን ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ የነበረውን ውል አፍርሶ ወደ ሌላ መግባት ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በዚህም መሠረት ጉዳዩን ለፓርላማ አቅርበናል፡፡ ፓርላማውም ውሉን ሙሉ በሙሉ ማፍረስ ወይም ከሌላ ካምፓኒ ጋር ውል ማሰር የሚለውን ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚኒስቴሩ አቋም ወይም ፍላጎት ምንድነው?

አምባሳደር መስፍን፡- ለእኛ ቢስማሙና ራሳቸው ግንባታውን ቢያጠናቅቁት መልካም ነው፡፡ ግን የሚስማሙ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በዚህ ዋጋ ከሌሎች ካምፓኒዎች ጋር መሥራት የሚለውን አማራጭ እንከተላለን፡፡ በአንፃሩ ውል ማፍረሱ በራሱ አሉታዊ ጎን አለው፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙ ግንባታ የመጀመርያ ምዕራፍ በስምምነቱ መሠረት ተጠናቋል ማለት ይቻላል?

አምባሳደር መስፍን፡- በአንደኛው ምዕራፍ ግንባታ ውስጥ ተካትተው መጠናቀቅ የሚገባቸው፣ በአንፃሩ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ለምሳሌ ሳር ማልበስ በመጀመርያ ምዕራፍ ውስጥ የተካተተ ሥራ ቢሆንም፣ ጣራ ባለመገጠሙ ምክንያት ወደ እዚሁ  የተሸጋገረ ነው፡፡ ችግሩ እየተባባሰ የመጣው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረውን ችግር በካምፓኒ ዓይን ከግምት ውስጥ ሊገባ አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሙን ግንባታ ለማጠናቀቅ ፍላጎት ያሳዩ ካምፓኒዎችስ አሉ?

አምባሳደር መስፍን፡- እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ከቱርክ፣ ማሌዥያና ኢንዶኔዥያ ፍላጎት ያሳዩ ናቸው፡፡ ግን ከዚህ አስቀድሞ ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ያለው ውል ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ሲቻል ነው ወደ ሌላው መግባት የሚቻለው፡፡

ሪፖርተር፡- በስታዲየሙ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ እየተከናወነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ስታዲየሙን ማን እየጠበቀው ይገኛል?

አምባሳደር መስፍን፡- መሥሪያ ቤቱ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአንፃሩ ከዚህ በኋላ ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ እስካሁን የጥበቃውን ሥራ የቻይናው ካምፓኒ ነበር ሲያደርግ የነበረው፡፡ በአንፃሩ በቅርቡ ድርድር ላይ እያለን የቻይናው ተቋራጭ ሠራተኞቹ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የብረት ስርቆት ላይ ተሰማርተው ከደረስንባቸው በኋላ፣ ጉዳያቸው በወንጀል ክስ እየታየ ይገኛል፡፡ እነሱ የእኛ ነው የሚል መከራከሪያ እያቀረቡ ሲሆን፣ በአንፃሩ ኮንትራቱ ፀንቶ ባለበት ሁኔታ የፕሮጀክት ንብረትን ከባለቤቱ ዕውቅና ውጪ የሚደረግ ተግባር ስርቆት በመሆኑ ክስ አቅርበንበታል፣ ሕግ ይዞታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የቀድሞ የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሒደት በተመሳሳይ መልኩ በመጓተቱ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ይደርሳል ቢባልም፣ በታቀደለት ጊዜ መድረስ እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡ ስለሒደቱ ቢያብራሩልን?

አምባሳደር መስፍን፡- የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ ተጠናቆ ክፍት መሆን የነበረበት በነሐሴ 2014 ዓ.ም. አካባቢ ላይ ነበር፡፡ በተያዘለት ጊዜ ማለቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ዲዛይን ሲሠራ ያልታዩ ጉዳዮች በመኖራቸው፣ ሌላው ሳሩ እንዴት ይተከል? የሚለው ጉዳይ በደንብ አልተጠናም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳር ተከላው ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ በሚገኝ የሳር ተከላ ከተደረገ ካፍ ላይቀበል ይችላል የሚል ሐሳብ በማቅረቡ ጥናት እስኪደረግ ከሦስት ወራት በላይ ወስዷል፡፡ በዚህም መሠረት ከሳር ተከላው ጋር በተያያዘ በተለያዩ አገሮች ያሉ ተቋራጮች የሚያቀርቡት ዋጋ በጣም የተጋነነ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ቀድሞ ከገባው ተቋራጭ ጋር በመመካከር ኩኩዩ የተባለ የሳር ዘር ለመትከል ተችሏል፡፡ በውሉ መሠረት አንደኛ ምዕራፍ ሥራዎችን አጠናቀናል፡፡ በአንፃሩ የአንደኛ ምዕራፍ ግንባታ ስለተጠናቀቀ ብቻ ለውድድር ዝግጁ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዲዛይኑ ሳይካተቱ የቀሩ ግንባታዎች በሁለተኛ ዙር ሲጠናቀቁ ዝግጁ ይሆናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የሁለተኛው ዙር ግንባታ መቼ ይጀምራል?

አምባሳደር መስፍን፡- ሁለተኛውን ዙር ለማጠናቀቅ በጀት ባለመኖሩ፣ ምክንያት በድጋሚ ከመንግሥት በጀት መጠየቅ ነበረብን፡፡ በዚህም መንግሥት 150 ሚሊዮን ብር ፈቀደልን፡፡ ሥራውን ለማስቀጠል ጨረታ አውጥተን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ በቅርቡ ሁለተኛው ምዕራፍ ይጀምራል፡፡   

ሪፖርተር፡- በሌላ በኩል በስፖርት ፌዴሬሽኖችና በስፖርት ማኅበራት መካከል ከፍተኛ የሆነ ቁርሾ መከሰቱ፣ አለመግባባቱም እየታየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በሌሎች በተደጋጋሚ ችግሮች እንዳሉ ይነሳል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህንን ጉዳይ እንዴት ይመለከተዋል?

አምባሳደር መስፍን፡- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በአዲሱ የመንግሥት አደረጃጀት መዋቅር፣ በአዋጅ 1263/14 አንቀጽ 37 መሠረት በተለይ ‹‹ነ›› በሚባለው ፊደል ውስጥ በተቀመጠው መሠረት፣ ለሁሉም አገር አቀፍ ስፖርት ማኅበራት መመርያ ያወጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር ማኅበራትን የመመዝገብ ሥልጣን አለው፡፡ ይደግፋል፣ እንዲሁም ቁጥጥር እንደሚያደርግ ከመንግሥት የተሰጠው ሥልጣን ነው፡፡ በዚህም ሥልጣን ብሔራዊ የስፖርት ማኅበራት መተዳደሪያ መመርያ ቁጥር 52/2014 የሚባል  ፀድቆ ለስፖርት ማኅበራት ተልኳል፡፡ አሁን ያለው ችግር በስፖርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ሰዎች የሚኒስቴሩን ሥልጣንና ተግባር ወደ ጎን በመተው ለመሄድ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሚኒስቴሩን ሥልጣን ችላ በማለት በራሳችን መንገድ ነው የምንመራው የሚሉና ለግላዊ ጥቅማቸው ብቻ የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወቅት በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈጠረውም ሕግ የማክበርና ያለማክበር ነው፡፡ ስለዚህ የስፖርት ማኅበራት በአዋጅ የተቀመጠውን ሕግ ሊያከብሩ ይገባል፡፡   

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ አካሄዶ ፕሬዚዳንቱን መምረጡ ይታወቃል፡፡ ምርጫው ‹‹ሕገወጥ ነው›› የሚሉ አሉ፡፡ ሚኒስቴሩ ምን ይላል?

አምባሳደር መስፍን፡- የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጉባዔ ከመካሄዱ ጋር በተያያዘ አካሄዱ ከመመርያውና ከሕጋችን ውጪ በመሆኑ፣ ፌዴሬሽኑን ሕጋዊ አድርገን አንቀበልም፡፡ ምርጫውም፣ አካሄዱም ሕጋዊ አይደለም፡፡ ሚኒስቴሩ የራሱን ዕርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...