- የተጠራው የአደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ ተራዘመ
- ፍርድ ቤት በተከሳሾች ላይ የዕግድ ውሳኔ ሰጥቷል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንግሥት ጋር ባደረገው ጥልቅ ውይይት ከጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረውን አጠቃላይ ችግር በመረዳት፣ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል፣ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ ማረጋገጡን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በመላው አገሪቱና በዓለም ያሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የአደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲያደርጉ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ መንግሥት ከሲኖዶሱ ጋር ውይይት ለማድረግ መስማማቱን በማሳወቁ በማሥግቱ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይቱ ተደርጓል፡፡
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የመሩት 12 ጳጳሳት የሲኖዶስ አባላት ወደ ቤተ መንግሥት ሄደው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና እንዲሁም ሌሎችም ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ሰፊና ጥልቅ ውይይት መደረጉም ተነግሯል፡፡
በሲኖዶሱና በመንግሥት መካከል ውይይት እንዲደረግና ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያደረጉት በቅዱስ ፓትርያርኩ የተመረጡ የአገር ሽማግሌዎች አማካይነት መሆኑም ታውቋል፡፡
የሲኖዶሱ አባላትና መንግሥት ያደረጉትን ውይይትና የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳብራራው፣ መንግሥት የቤተ ክርስቲያኗን አቋም ሙሉ በሙሉ ተቀብሏል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበል ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ኑሯቸውም ለፈተና፣ ለስደትና ለእንግልት፣ ለእስራት ተዳርገዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ መስማማቱን ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ አሁንም ድርጊቱ ቀጥሎ ወከባና እንግልት እየተፈጸመባቸው ያሉትን ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአኅጉረ ስብከት ሠራተኞች፣ አገልጋይ ካህናትና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለው እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የታሰሩትም እንዲፈቱና አገልግሎታቸውን በሰላምና በነፃነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ መደረሱንም አስታውቋል፡፡
መንግሥት ድርጊቱን ለማስፈጸም የሚያስችል የአፈጻጸም የድርጊት ጊዜ የሚያስፈልገው መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በመላው አገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው የአደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ ለተወሰኑ ጊዜ እንዲራዘም ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑንም አስታውቋል፡፡ የአደባባዩ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲራዘም የተደረገው ቅዱስ ሲኖዶስ የአቋም ለውጥ አድርጎ ሳይሆን፣ ቤተ ክርስቲያን በሮቿን ለሰላም ክፍት በማድረግ ያስተላለፈችውን ጥሪና ያስቀመጠችውን ቀነ ገደብ መሠረት አድርጎ መንግሥት ወዲያውኑ ችግሩን ለመፍታት ውሳኔ ላይ በመድረሱ መሆኑንም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል፡፡
‹‹ውይይቱን ያደረግነው ፍርኃት ባለበት ለይስሙላ ሳይሆን፣ መንፈሳዊ ድፍረት ባዘለ መልኩ ነው፤›› ያሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ጭፍን ጥላቻና የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደሌላት ተናግረው መነጋገሪያና አጀንዳዎቿ ሁሉ የሚያጠነጥኑት በሰላም፣ በፍቅር በመብት ጥያቄ ላይ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በነበረው ውይይት ከተነሱ ነገሮች አንዱ ሕጋዊ ሰውነትና መብት ያላት ቤተ ክርስቲያን በሕጋዊ መብቷና ሰውነቷ ድርድር ፈጽሞ እንደማይኖራት፣ ይህንን መብቷን ፍርድ ቤት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በጠበቆቿ አማካይነት ውሳኔ እንዳሰጠበት አቡነ አብርሃም አብራርተዋል፡፡
‹‹የቀረን ነገር ሳይኖር እያንዳንዱ ነገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት አስረድተናል፡፡ በክብርም ተቀብለውናል፣ ብዙ ከተወያየን በኋላ እስካሁን ድረስ የነበሩት መረጃዎች ሁሉ የተዛቡ መሆናቸው፣ ከእኛ ጋር ፍፁም ግንኙነት አለመኖሩ ብዙ ጉዳትም እንዳመጣ አስከትለናል፤›› ያሉት አቡነ አብርሃም፣ ‹‹በተለይ የተደነገገበት ታላቁ የኦሮሚያ ሕዝብ፣ ምንም እንዳልተደረገለት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኦሮሚያ ምድር ላይ እንዳልሠራች ተደርጎ የተነገረውን ሁሉ በግልጽ፣ ከበጀት ጀምሮ፣ አሿሿም፣ ምን እንደተደረገ፣ የአሿሿሙን ቁጥር ከፍ ዝቅ ያደረገው የውጭውና የአገር ውስጥ ሲኖዶስ ሲስማሙ፣ ከውጭ ከሃያ በላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሲመጡ የተፈጸመ እንጂ፣ በመጀመርያ ደረጃ ሲታይ ይመሩ የነበሩት ማንና ማን እንደሆኑ በግልጽ ተቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ዘርና ጎሳ የላትም በቋንቋው ማስተማር ሥራዋ ነው፡፡ ስለዚህ የኦሮሚያ ሕዝብ እስካሁን ቤተ ክርስቲያን በአቅሟ ልክ እንዳደረገች፣ ገና ብዙ የሚቀራትና ያቀደችው ብዙ ነገር እንዳላት፣ ያሉትንም ችግሮች ለመፍታት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
በሕግ የተያዙ ጉዳዮች የሕግ ሒደታቸውን ጠብቀው እንደሚቀጥሉ የገለጸው ሲኖዶሱ፣ ሒደቱ ትዕግሥት የሚጠይቅ በመሆኑ ምዕመኑ በፍፁም አንድነትና ኅብረት ቆሞ እንዲጠብቅ ጠይቋል፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት ፍፁም ሕገወጥ በሆነ መንገድ በመደራጀት የቤተ ክርስቲያኗን መብትና ጥቅም የሚጎዳ ተግባር መፈጸሙንና የአበው ሐዋርያ ሲመተ ኤጺስ ቆጶስነት ሥርዓት ፈጽመናል በሚል ምክንያት በተፈጠረው ውዝግብ የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊ ክብርና ልዕልና የማቃለል፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ውለታ የዘነጋ፣ ሕልውናዋንና አንድነቷን ለመናድ የተደረገ ከፍተኛ ወንጀል መፈጸሙን ሲኖዶሱ አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን የቆሙትን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ወገኖች ሁሉ አመሥግኖ፣ መንግሥትም የቤተ ክርስቲያኗን ጥያቄ ተቀብሎ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበሩና ውሳኔውንም የሚፈጽም መሆኑን በማረጋገጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው አስመሥግኗል፡፡
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዓርብ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምድብ ችሎት የዕግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የዕግድ ውሳኔ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ የሕግ አማካሪዎችና ጠበቆች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠበቃ አቶ አንዷለም በዕውቀቱ ችሎቱ ስለሰጠው ውሳኔ እንዳስረዱት በቀድሞ ስማቸው አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኤውስጣቲዎስና አቡነ ዜና ማርቆስ እንዲሁም በነሱ ተሹመዋል የተባሉ 25 ግለሰቦች ከዓርብ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜያት በኢትዮጵያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጊዜያዊ ዕግድ ተሰጥቷል፡፡
ዕግድ ተሰጠ ማለት ክስ ቆመ ማለት እንዳልሆነ ያስታወሰው የሕግ ኮሚቴው፣ የሚጠይቃቸው የወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚቀጥሉ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስና የሰላም ሚኒስቴር ዕግዱን እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ጠቅሷል፡፡