በኢትዮጵያ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ በቁጥር በዛ ያሉት ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ምክክርና ውይይት ለማድረግ የተቋቋመውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በተመለከተ ያላቸው መረጃ በጣም ውስንና ከሚጠበቀው በታች መሆኑን የሚያሳይ ጥናት ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሲቪክ ማኅበራት በአገራዊ ምክክሩ ላይ ያላቸውን ዕሳቤና የመረጃ ሁኔታ በተመለከተ፣ በተመረጡ 160 ድርጅቶች ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ ከአጠቃላይ መልስ ከሰጡት 140 ድርጅቶች ውስጥ 34 የሚሆኑት ብቻ ስለጉዳዩ መረጃ እንዳላቸው አሳይቷል፡፡
በኅዳር 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸው የስምምነት ፊርማ ማካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተደራሽነታቸው ሰፊ በመሆኑ ለኮሚሽኑ ሥራ ትልቅ አጋር እንደሚሆኑ በማሰብ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ከአባላትና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፍ ስላለው አገራዊ ምክክር በተመለከተ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ‹‹የነቃ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ማረጋገጥ” በሚል ርዕስ ከሰሞኑ ባካሄደው ውይይት ድርጅቶቹ ለአገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሚና ለማበርከት ያላቸው አጠቃላይ ግንዛቤና ዕውቀት አናሳ መሆኑን፣ በምክር ቤቱ የጥናትና ፕሮግራም ልማት አማካሪ አቶ ጌታነህ ሰይፉ የቀረበው ጥናት ያሳያል፡፡
በመሆኑም በብሔራዊ ምክክሩ እንዲመጣ የሚጠበቀው ውጤት የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሚወስን ነው ከተባለ፣ በተለያዩ አዳራሾች ከሚደረገው ስብሳባ ባለፈ የብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ በቂ ዕውቀት የሚሰጡ መድረኮች ሊዘጋጁ እንደሚገባና ምኅዳሩ እንዲሰፋ የሲቪክ ማኅበራት መወትወትና መጎትጎት እንዳለባቸው አቶ ጌታነህ ተናግረዋል፡፡
የሲቪክ ማኅበራቱ በጥናቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታየው የፖለቲካ ተፅዕኖና ግጭት ለምክክሩ በጣም በትልቁ ሥጋት ስለመፍጠሩ፣ የምሁራን ከቀደመ ስህተት ለመማር ዝግጁ አለመሆን፣ የመሰማማት ባህል ባለመኖሩ ለብሔራዊ ምክከሩ እክል እንደሚፈጥር መናገራቸውን በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ምክክሩ ካለው ሰፊ ባህሪ አንፃር ሁሉን አቀፍ ውክልናና የተሳታፊዎች መረጣ፣ የግልጸኝነት ችግር፣ የምሁራን እጥረት፣ ሒደቱን በተመለከተ መረጃ በየጊዜው አለመስጠት ሕጋዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባው ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል ስምምነት ላይ የመድረስ፣ ውይይት የሚያካሂዱ ሰዎች ተዓማኒነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውይይቱ የመውጣት፣ የእምነትና የፖለቲካ ተቃርኖ፣ የታጠቁ ኃይሎች፣ በሁለም ደረጃ የሚደረግ የመረጃ አሰጣጥ ክፍተት፣ የሀብት እጥረት፣ በኮሚሽኑ ከመንግሥት ጋር የሚኖረው ቅርበትና በመንግሥት የመጠለፍ ዕድል ሰፊ መሆኑን የሲቪክ ማኅበራቱ እንደ ሥጋት ማንሳታቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች በአንድ ላይ ሆነው የመሥራትና ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ የማድረግ፣ ሊፈጠር የሚችለውን የሀብት እጥረት ድርጅቶች በጋራ ሀብት የሚያመነጩባቸውን መንገዶች መፍጠር፣ በብሔራዊ ምክከሩ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ከምክክሩ እንዳይወጡ የሚረዳ ምክክር ማድረግ፣ ለምክክር ኮሚሽኑ በቂ የሰው ኃይል እንዲኖር ማድረግ እንዳላባቸው አቶ ጌታነህ አሳስበዋል፡፡
በዚሁ መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ የሰላም ምሥረታና የሰላም ግንባታ የተለያዩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም በተለይ በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ላይ የሰላም ምሥረታው እየቀደመ በላይኛውና በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ የሰላም ግንባታው መካሄድ አስፈላጊ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወዲህ እንደ አገር ፈተናው እየበዛ፣ በርካቶች የሞቱበት፣ ብዙዎች የተሰደዱበት፣ ንብረት የወደመበትና ብዙ ቁስል የታየበት ጊዜ በመሆኑ የሰላም ግንባታና የአገራዊ ምክክር ሥራው ከባድ እየሆነ ስለመምጣቱ ተናግረዋል፡፡
በርካታ አገሮች በዚህ አገራዊ ምክክር ሒደት ያለፉ፣ ነገር ግን ከገቡበት ችግር ውስጥ በምክክር መውጣት መቻላቸውን የገለጹት ዮናስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ለዚህ ጉዳይ መሳካት በቂ፣ አካታችና ጠንካራ የሆነ መዋቅር በመዘርጋትና ሀብት በመመደብ መሥራት የግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕዝቡ መካካል የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ አዳሪና ታሪካዊ ቁርሾዎች በተጨማሪ፣ ከጂኦ ፖለቲካ አንፃር ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አይኖች የበዙበት ጊዜ ስለመሆኑና ሁሉም እየመጣ ላስታጥቅህ፣ መሣሪያ ላቀብልህ የሚል ኃይል የበዛበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የሃይማኖት ብሔርተኝነት የክልል ብሔርተኝነት ጋር ተደምረው በአንድ ላይ እየመጡ መሆኑን የጠቆሙት ዮናስ (ዶ/ር) ከእነዚህን ውስብስብ ችግሮች የመውጫ መንገድ ሊዘየድ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ የተሰባበረ ሆኖ የቀጠለ ይመስላል፣ ያሉት ዮናስ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በመንግሥታዊ አሠራር እፈታቸዋለሁ በሚል የጀመራቸው ሥራዎች በተለይም የክልልነት፣ የቋንቋ፣ የድንበርና ሌሎች ግጭቶች እየፈነዱ እንደሆነ በመጠቆም መንግሥት በአስተዳደራዊ ሥርዓት እፈታቸዋለሁ በሚል የሚያስባቻውን አሠራሮች እንዴት እንደሚፈታ ግልጽ የሆነ የመፈጸሚያ መንገድ አለማስቀመጡን ጠቁመዋል፡፡
ለአብነት እንኳ መንግሥት አዲስ አበባ ውስጥ ቀላል የሚባለውን የቀበሌ መታወቂያ በአስተዳደራዊ ችግር ምክንያት ለነዋሪዎች መስጠት የማይችል ሆኖ እየታየ፣ እያለ ሌላ ግዙፍ ችግሮችን እፈታለሁ ብሎ ሲነሳ ሁለቱ የማይታረቁ ነገሮች ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ከጅምሩ የሰላም ግንባታ ሲታሰብ መደረግ ያለበት የሕዝብ ቅሬታዎችንና ተያያዥ ችግር የሚፈጥሩ የዜጎችን አቤቱታ በመፍታት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ማቲዎስ ወንዱ ከተባለ ድርጅት የመጡት አቶ ለማ አየለ የተባሉ የስብሰባው ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት፣ አገራዊ ምክክሩ ወደ ዋና ሥራው ሲገባ የልዩነት ምክንያት የሆኑ በተለይም ከሕዝቡ ውስጥ በችግሩ የሚፈላለጉት የችግሩ አመንጪና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት አካላት ሊለዩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት ያዘላቸው ባለሥልጣናት በሙሉ እውነት የኢትዮጵያን ሰላም ይፈልጋሉ ወይ? በሚል ጥያቄ የሰነዘሩት አቶ ለማ፣ ጉዳዩ በደንብ መመለስ አለበት፣ ሰላም የማይፈልግ አካል አስቀምጦ እንዴት ስለሰላም ማውራት ይቻላል? ስለዚህ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለማይቻል ሰላም የሚፈልጉ አካላትን በማቅረብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ ባለሙያው አቶ አምሃ መኰንን በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የመጣችበት የመንግሥትና የፓርቲ መስመር የጠፋበት እንዲሁም መንግሥት ራሱ ውድድርና የሴራ ፖለቲካ ውስጥ የሚገባበት ጊዜ በመሆኑ፣ በምክክሩ ሒደት መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ የታቀደ ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ብዙ ከባባድ ነገሮች እየታዩ በመንግሥት በኩል የሚታየው ትኩረት በጣም ውስን ከዚያም ሲያልፍ ምንም ዓይነት የለም ማለት ይቻላል ያሉት አቶ አምሃ፣ ዛሬ በሆነ ቦታ 200 ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለ ተብሎ እንሰማለን፣ በነጋታው እንደ ኢትዮጵያ የመንግሥት አካል ብለን የምንጠራቸው የሁለትና ሦስት አካላት ሁኔታ ሲታይ በፍፁም የሚያዝናና አዝማሚያ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ከዚህ ችግር ውስጥ በዘላቂነት ያወጣናል ወይ፣ በማለት ጠይቀዋል፡፡
በመሆኑም በየአንዳንዱ የመንግሥት እንቅስቃሴ ግልጽነት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ አምሃ፣ በተለያየ ምክንያት በሙያችን ቅርብ የሆንን ሰዎች በምንሰማውና በምናየው ተወዛግበናል፣ አብዛኛው ሰው መሸሺያ መጠጊያ አጥቷል ብለዋል፡፡
አቶ አምሃ አክለውም፣ መንግሥት ከትንኮሳ መታቀብ እንዳለበትና አንዳንዴ መነካት የሌለባቸውን ነገሮች ሲነካ እንደሚታይ፣ ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም ቦታውንና ሰዓቱን መምረጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ሕዝቡን ላልተፈለገ ስሜትና አመጽ ከሚከቱ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ እንዳለበት በመጥቀስ፣ የብሔራዊ ምክክሩ ‹‹በልመናና በምኞት›› የሚሳካ ባለመሆኑ የሚያስፈልጉ ሥራዎች ከወዲሁ መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሞገስ በቀለ የተባሉና የኢትዮጵያዊነት ዜጎች ማስከበሪያ ከተሰኘ ድርጅት የመጡ ተሳታፊ ‹‹ንዑስ ብሔርተኝነት አገራችን ሊደፋት እንደሆነ እናውቃለን፤›› በማለት የምክክር ኮሚሽኑ አጉራ ዘለል የሆነ ሐሳብ ይዘው የቆሙ አካላትን ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ሊያሳይ የሚችል የዳሰሳ ጥናት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ምክክሩ ገና ከጅምሩ የነበረው ሙቀትና ግለት አሁን ወደ መቀዛቀዝ ስለመምጣቱ የገለጹት ተሳታፊው፣ ከ80 በመቶ የሚሆነው ሕዝበ ተዛምዶ፣ ተጋምዶና ተዋልዶ የሚኖር ማኅበረሰብ መሀል ከተማ ያለውና ጥቂቱ ሕዝብ የሚባላበትና የሚጋጭበት ጉዳይ የማይገባቸው እንግዳ ቢመጣባቸው ብሔርና ቋንቋ ሳይለዩ አብልተው አጠጥተው በቤታቸው የሚያሳድሩ መሆናቸውን ገልጸዋል
ይሁን እንጂ ለዚህ ሁሉ ለሚታየው ችግር ዋናው የግጭት ጠንሳሾች ፖለቲከኞች በመሆናቸው መጀመሪያ ምሁር የሚባለውና ፖለቲከኛው ጋር ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ እንደላበት አስረድተዋል፡፡
ዮናስ አሽኔ እንደሚሉት በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መፈታት የሚችሉት ጉዳዮች እንዳይፈቱ ቁስል የሚያብሱ ነገሮች እየተከሰቱ ስለመሆናቸው አብራርተው፣ በመሆኑም በመንግሥታዊ አሠራር መመለስ ያለባቸውን ጉዳዮች ጥርት አድርጎ ፍኖተ ካርታ በማስቀመጥ ‹‹ይህን በዚህ አሠራር እፈታዋለሁ፣ ይኼኛውን ደግሞ በብሔራዊ ምክክሩ ይፈታል›› በሚል ግልጽ ያለ ፍኖተ ካርታ ማስቀማስመጥ እንደላበት ተናግረዋል፡፡
የሰቪል ማኅረሰቡ በጣም ትልቅ የተዋናኝነት ሚና ያለበት በመሆኑ የጋራ አጀንዳ አድርጎ አሁን ላይ አገሪቱ ችግር ውስጥ መሆኗን በመረዳት የቢሮክራሲ አካሄድ በማዘጋጀት የማኅረሰብ ንቅናቄ ማድረግና ስነዘዴያዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ አቶ ዮናስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡