Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የትግራይ ክልልን ሊጎበኙ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቀጣዩ ሳምንት የትግራይ ከልልን እንደሚጎበኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ገለጹ።

ሪፖርተር ከዲፕሎማቲክ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመጪው ሳምንት መገባደጃ ቀናት አዲስ አበባ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ዋና ምክንያት በመጪው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመታደም ሲሆን፣ ከጉባዔው በኋላም በትግራይ ክልል በአካል ተገኝተው ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳትና ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚመለከቱ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹ ገልጸዋል። 

በትግራይ ክልል ቆይታቸው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎትና የአቅርቦት ሁኔታን እንደሚመለከቱና ከሕወሓት አመራሮች ጋር ተገናኝተው በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ እንደሚወያዩ ምንጮቹ ጠቁመዋል።

ከትግራይ ክልል ጉብኝታቸው በተጨማሪ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን እንደሚጎበኙም ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል።

ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጎቴሬዝ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ማኅበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም የፌዴራል መንግሥት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የትግራይ ጦርነት ከሁለት ዓመት በኋላ ባለፈው ኅዳር ወር በፕሪቶሪያ በተደረሰ የሰላም ስምምነት የተቋጨ ሲሆን፣ በጦርነቱ የተሳተፉት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት የፈረሙትን የሰላም ስምምነት የመፈጸም ሒደት ጀምረዋል።

በእስካሁኑ ሒደትም የፌዴራል መንግሥት የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ የጀመረ ሲሆን፣ ሕወሓት በበኩሉ ከባድ የጦር መሣሪያዎቹን ለፌዴራል መንግሥት አስረክቧል። 

የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚነት ያደናቅፋል የሚል ሥጋት በብዙዎች ዘንድ ፈጥሮ የነበረው የኤርትራ ጦርም ከበርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወጥቷል። ነገር ግን አሁንም በኤርትራ ጦር የተያዙ የትግራይ አካባቢዎች እንዳሉ ሕወሓት ከሰሞኑ አሳውቋል።

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች