Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውይይት በሚቀርቡት የካፒታል ገበያ መመርያዎች ላይ የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦች እንዲጤኑ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ለምታቋቁመው የካፒታል ገበያ አዋጁን መሠረት አድርገው በቀጣዩ ሳምንት ለሕዝብ ውይይት የሚቀርቡ መመርያዎች ላይ ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች ተጤነው እንዲፀድቁ ተጠየቀ፡፡

ይህ የተገለጸው አፍኤስዲ (FSD) ኢትዮጵያ (Capital Market Roadmap and the Role of Intermediaries) በሚል ርዕስ በሸራተን አዲስ ሆቴል ባሰናደው የዘርፉ ተዋንያን የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በቅርቡ ይፋ ስለሚደረገው የካፒታል ገበያ ምንነት፣ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅትና አተገባበር ዙሪያ ገለጻዎችን እያቀረበ የሚገኘው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም ከፍተኛ አማካሪዎች በመድረኩ ገለጻዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በተለይም በካፒታል ገበያ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ስለሚጠበቁት የካፒታል ገበያ ተዋንያን ሚና ላይ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በይፋ ከተመሠረተ ጥቂት ወራት ቢሆነውም፣ የሥራ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችለውን በርካታ መመርያዎች አዘጋጅቶ ለቦርድ ማቅረቡን አስታውቆ፣
በካፒታል ገበያ አዋጅ በተጠቀሰው መሠረት ባለሥልጣኑ ስምንት መመርያዎችን እንዲሁም አዋጁ በሚሰጠው ሥልጣን ተጨማሪ ሰባት መመርያዎችን በጥቅሉ 15 መመርያዎችን አዘጋጅቶ ለቦርድ ማቅረቡን የባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሕግ አማካሪዎች ባቀረቡት ገለጻ ላይ ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎችም ከሌሎች አገር ተሞክሮ በመነሳት በኢትዮጵያ እንዴት ውጤታማ የካፒታል ገበያ ሊቋቋም ይገባል? በተለይም የዘርፉ ተዋንያን እንዴት በገበያው ሙያዊ አሠራርን ተከትለው ይሠራሉ? በገበያው ላይ ዜጎች እምነት ያሳድሩ ዘንድ ተቀርፀው ለሕዝብ ውይይት ክፍት የሚደረጉ የሕግ ማዕቀፎች ከዝግጅት እስከ አፈጻጸም መሆን ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዳኪቶ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዓይነት የፋይናንስ ሪፎርሞች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ለአብነትም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ፣ ማይክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክነት እንዲያድጉ መደረጉ፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፖርት አደራረግ ስታንዳርድ እየተቀየሩ መሆናቸውን፣ እንዲሁም የካፒታል ገበያን ለመቋቋም የተጀመረውን እንቅስቃሴ ጠቅሰው፣ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሥራዎች በአግባቡ መመራት የሚጠይቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይንናስ ዘርፉ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አገሮች የፋይናንስ ሪፎርም ሲያደርጉ በአግባቡ መምራት ካልቻሉ ቀውስ ይፈጥራል፤›› በማለት የገለጹት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ የካፒታል ገበያ ሥራም ገበያ ስለሆነ ጥንቃቄን የሚሻ (ሴንሰቲቭ) መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለው ሁኔታ አንፃር ሲታይ በብዙ መልኩ ከዕውቀትም ማነስና መረጃ በአግባቡ ያለመድረስ ሁኔታ ስለሚኖር፣ እንዲሁም መረጃ አፈትልኮ ገበያው ባይሳካ መጀመርያውኑ አለማቋቋም የተሻለ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

‹‹የአዋጁን መንፈስ ካየነው ፍልስፍና አለው፡፡ አዋጁ ሲወጣ መንግሥት ሥጋትን መሠረት ያደረገ (ሪስክ ቤዝድ አፕሮች) ነው የተከተለው፡፡ ይህ ማለት ሥጋቶችን ባገናዘበ ሁኔታ ነው ሕጉ የወጣው ማለት ይቻላል፤›› ያሉት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ ያም ሆኖ አፈጻጸሙ ላይ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ ካፒታል ገበያ ማለት የአካውንቲንግ ሪፖርት ወይም ከቁጥር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም የአካውንቲንግ ሪፖርቱ፣ አስተዳደሩ ሥነ ምግባርን የተከተለ ካልሆነ፣ የአካውንቲንግ ማጭበርበሮች (ስከንዳልስ) የሚፈጥረው ችግር ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ባደጉ አገሮችም ችግር ይሆናል፡፡  

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ የካፒታል ገበያ ተዋንያን ፈቃድ አሰጣጥን፣ እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በቀጣይ ሳምንት የሚደረጉት የሕዝብ ውይይቶች የሕግ ቅደም ተከተልን ለማካተት ብቻ የሚደረጉ ሳይሆኑ፣ የባለሙያዎችን ዕይታና ግብዓት ለማካተት የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በተለይም በካፒታል ገበያ የሚሰማሩ ወይም የሚሠሩ ሰዎች (ኢንተርሚደሪስ) እንዴት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው? በሚለው ላይ ተቋሙ ለውይይቶችና ምክክሮች፣ እንዲሁም የሚቀርቡ አስተያየቶችን ለመቀበል ክፍት መሆኑን ብሩክ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች