Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቆቦ ከተማ የመተንፈሻ አካልና የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑ...

በቆቦ ከተማ የመተንፈሻ አካልና የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባለሙያ መላክ እንደማይችል አስታውቋል

ቀን:

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ፣ የመተንፈሻ አካልና የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር በቀን ከ200 እስከ 500 መድረሱንና አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የመተንፈሻ አካልና የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር በቀን ከ200 ወደ 500 ማሻቀቡን የራያ ቆቦ ወረዳ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ብርሃኔ ተንሳው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ወደ ጤና ጣቢያ የሚያቀኑት ታማሚዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ብቻ የላይኛው የመተንፈሻ አካላ ሕመም የገጠማቸው ከሦስት ሺሕ በላይ ሕሙማን መታከማቸውን አስረድተዋል፡፡

ለሕሙማን ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹አንድ አካባቢ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ከቆየና የሞቱ ሰዎች በወቅቱ የማይቀበሩበት አጋጣሚ ካለ አየሩ ይበከላል፡፡ አየሩ በሚበከልበት ጊዜም አሁን በማኀበረሰቡ ላይ እየተስተዋሉ ያለው የበሽታ ዓይነት እንደሚከሰት ይጠበቃል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በሽታው የኮሮና ምልክት ስለሚያሳይ የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ መመርመርያ መሣሪያ ከሚመለከተው አካል ማዘዛቸውን ጠቅሰው፣ በምርመራ የበሽታውን ዓይነት የመለየት ተግባር እንዲሚያከናውኑ አመላክተዋል፡፡

የሕመሙ ስሜትም (የላይኛው የመተንፈሻ አካል ሕመም) በዋናነት አጣዳፊ ደረቅ ሳል፣ ከባድ ትኩሳትና የጉሮሮ ድርቀት መሆኑን አቶ ብርሃኔ አስረድተዋል፡፡

አጣዳፊ ደረቅ ሳልና የጉሮሮ ቁስለት እንደገጠማቸው የገለጹት የቆቦ ከተማ ነዋሪ አቶ አበራ አያሌው፣ ወደ ጤና ጣቢያ ሄደው በወረፋ ምክንያት የሕክምና አገልግሎት በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰው፣ የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. የወባ በሽታ በአካባቢው በርካታ ሰዎችን እንዳጠቃና በወቅቱ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ትልቅ ፈተና እንደሆነ የገለጹት አቶ አበራ፣ ሕክምና ለማግኘት ከሦስት ቀን በላይ ወረፋ መጠበቅ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታካሚዎች ያነሱት የወረፋ ቅሬታ ትክክል መሆኑን የገለጹት የጤና ቢሮ ኃላፊው፣ የታማሚዎች ቁጥር ከተለመደው በተለየ መልኩ ከፍ በማለቱ የመድኃኒትና የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ወረፋ ያገኘ ይታከማል ሌላው ደግሞ ይጠብቃል›› ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ በጤና ጣቢያው በአጠቃላ 100 የሕክምና ባለሙያዎች ቢያስፈልግም አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት ግን ከሚፈለገው ግማሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 ተጨማሪ ባለሙያዎች እንዲቀጠርላቸው ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሰው ሀብት አስተዳደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ምላሽ እንዳላገኙም አክለዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ዳኛቸው ዳሬ፣ ጤና ጣቢያው ‹‹ገጠመኝ›› ያለውን የባለሙያ እጥረት በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በበጀቱ መሠረት የሰው ኃይልን ማሠራጨት የወረዳው ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሙያ የመላክ ኃላፊነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የሕሙማኑ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑ አሞክሳሲሊን፣ ኦግመንቲን፣ ሲፕሮ፣ ሴፋልኤግዚን የተሰኙ የፀረ ተዋህስያን መድኃኒት እጥረት እንዳጋጠማቸው የጤና ጣቢያ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ ከመንግሥት 60 ብር ሲገዙት የነበረው አሞክሳሲሊ በግል ክሊኒክ ዋጋው ወደ 200 ብር ከፍ በማለቱንና እጥረቱም ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አጋጥሟል ስለተባለው የመድኃኒት እጥረት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የደሴ ቅርንጫፍ መድኃኒት ሥርጭት ዋና ሥራ አስኪያጅ እሸቴ ሹሜ፣ ‹‹መድኃኒት በደሴ ቅርንጫፍ አለ፡፡ መጥተው መውሰድ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...