Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሳሳቢነቱ የጎላው የኮሌራ በሽታ

አሳሳቢነቱ የጎላው የኮሌራ በሽታ

ቀን:

በኢትዮጵያ የኮሌራን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጠጠር መንግሥት እየሠራ ቢሆንም፣ አሁንም የችግሩ አሳሳቢነት አልቀረም፡፡ በተለይም የገጠራማ አካባቢ ነዋሪዎች የወንዝና የዝናብ ውኃን ለመጠጥና ለምግብ አገልግሎቶች ስለሚጠቀሙ በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

በቅርቡም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ገጠራማ ቦታዎች ላይ ችግሩ መከሰቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ድንገተኛ ጤና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ሹሚ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በክልሉ በስምንት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የኮሌራ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቢሮው ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች በ2014 ዓ.ም. ከነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ እየተስፋፋ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት በሽታው በተከሰተባቸው ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

በእነዚህም ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ ለመጠጥና ለተለያዩ አገልግሎት የሚጠቀሙት ወራጅ ውኃ በመሆኑ በሽታውን መቆጣጠር አለመቻሉን አክለው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በባሌ፣ በጉጂና በምዕራብ አርሲ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ላይ 927 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቢሮው ጊዜያዊ የሕክምና ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም ከስምንቱ ወረዳዎች ውስጥ አምስቱን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንደተቻለ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡  

በስምንቱ ወረዳዎች ውስጥ የተከሰተው በሽታ ከግል ንፅህናና የመጠጥ ውኃ አጠቃቀም ችግር ጋር የተያያዘ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ወረዳዎቹ ቆላማ የአየር ንብረት ያላቸው መሆኑ ችግሩን አጉልቶታል ብለዋል፡፡

በሽታው ሊስፋፋ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ከ88 በመቶ በላይ የሚሆነው ንፅህናውን የጠበቀ የውኃ አቅርቦት ስለማያገኝ እንደሆነና ማኅበረሰቡም ስለበሽታው በቂ የሆነ ግንዛቤ ስለሌለው በመሆኑ ጭምር ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ችግሩ የታየባቸው ቦታዎች ላይ የውኃ ማከሚያ መድኃኒት ለማኅበረሰቡ ሲሠራጭ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገመቹ፣ በተለይም ባሌ ላይ ጎሮ የሚባል ወረዳ፣ ምዕራብ አርሲ መንሰቦ በሚባለው ወረዳና በጉጂ ደግሞ ከጊርጃ በተባለ ወረዳ ላይ በሽታው አሁንም መኖሩን አስረድተዋል፡፡

እነዚህም ስምንት ወረዳዎች ድርቅ የተከሰተባቸው ቦታዎች በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የውኃ አቅርቦትና የምግብ እጥረት ችግር እንዳለባቸው፣ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ቦታዎችም ለበሽታው ተጋላጭ የመሆናቸው ነገር ከፍተኛ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ችግሮቹ ተደማምረው በሽታውን ለመቆጣጠር ማነቆ እንደሆነባቸው፣ በተለይም ደግሞ በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ ላይ ከፍተኛ የሆነ የውኃ አቅርቦት ችግር በመኖሩ የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ ሊሆን እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን፣ በባሌ ዞን በሁለት ወረዳዎች ላይ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ ከ765 ሺሕ በላይ ሰዎች ክትባት መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች ላይ የተሰጠው ክትባት 50 በመቶ በሽታውን የሚከላከል መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም በሌሎች ወረዳዎች ክትባቱን ለመስጠት ሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሦስቱ ወረዳዎች ላይ የኮሌራ በሽታ ሥርጭቱ የጨመረበት ዋነኛ ምክንያት፣ አንድና አንድ የውኃ አቅርቦት ችግር ነው ያሉት አቶ ገመቹ፣ በዚህ አካባቢም የሚኖሩ ሰዎች በተቻለ መጠን ውኃን አክመው መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት በሽታ የሚከሰተው ከበጋ ወደ ክረምት መግቢያ አካባቢ ላይ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ረዥም ጊዜ መውሰዱንና በሽታውም ሊጠፋ አለመቻሉን አክለዋል፡፡

የበሽታውንም ሥርጭት ለመቀነስ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑንና ማኅበረሰቡም የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት ንፅህናው የተጠበቀ ውኃ መጠቀም ይኖርበታል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ክልሎች ላይ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል፣ እንዲሁም ወደ ሌሎች አካባቢዎች በቀላሉ እንዳይዛመት ከተለያዩ የክልል ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሠራ እንደሆነ መረጃው ያሳያል፡፡

በኦሮሚያ፣ በባሌ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በጉጂ ስምንት ወረዳዎችና በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ሁለት ወረዳዎች በሽታው መዛመቱን፣ በእነዚህም አሥር ወረዳዎች የሚገኙ 66 ቀበሌዎችን በማካለል ሰፊ ሥራ መሠራቱን ኢንስቲትዩቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡

የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ 14 የኮሌራ ሕክምና ማዕከሎች ተቋቁመው እያገለገሉ መሆናቸውን መረጃው ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለማስቆም እንዲሁም የማኅበረሰቡ የበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ መንግሥት ከአጋር የልማት ድርጅቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ሲሆን፣ በሶማሌ ክልል በሽታው በተከሰቱባቸው ቦታዎች ላይ ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥር ማድረግ መቻሉን ተገልጿል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኮሌራ ‹‹ቫይብሮ ኮሌራ›› በተባለ ተህዋስያን አማካይነት የሚከሰትና አንጀትን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ በተበከለ ምግብና ውኃ አማካይነት የሚመጣው ተህዋሱ፣ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ምልክቶቹ ናቸው፡፡ ኮሌራ በሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ስለሚያሟጥጥና አቅም ስለሚያሳጣ ፈጥነው ካልታከሙ በሰዓታት ውስጥ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...