Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአርኪኦሎጂስቶች ያገኟቸው የዘመነ አክሱም ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት

አርኪኦሎጂስቶች ያገኟቸው የዘመነ አክሱም ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት

ቀን:

ጥንታዊ መዲናና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ ተመራማሪዎች እንደሚገልጿት የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ ቀጥሎም የሃይማኖት ማዕከል ብሎም ክርስቲያናዊ መንግሥት በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች ናት፡፡ በውስጧም እጅግ በጣም የተቀደሰው ጽላትና የክርስትና ሃይማኖት የተለየው መገለጫ ይገኛል፡፡

እንደ ባለታሪኩ ፍራንሲስ አንፍሬ የአክሱም መንግሥትና ከተማ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ከሚገኙት አራት መንግሥታት ከሮም፣ ከፋርስና ከቻይና ቀጥሎ አራተኛው ኃያል መንግሥት ነበረች፡፡ ለኃያልነቷ ምስክር ግዙፍ ሐውልት፣ ግዙፍ የድንጋይ፣ ጠረጴዛ፣ ግዙፍ የዘውድ መሠረታዊ ድንጋይ የተሰባበሩ ትላልቅ ዐምዶች፣ የነገሥታት መቃብር ከተለያዩ የማይዳሰሱ አፈ ታሪኮችና ባህሎች ጋር ተገኝታለች፡፡

ዜና መዋዕሏን በድንጋይ ላይ በሦስት ቋንቋዎች (በግእዝ፣ ሳባና ግሪክ) በመጻፍ  እስከ አሁን ዘመን በተላለፉት ብራናዎች ላይ ከትባ አቆይታለች፡፡

የኢትዮጵያ ጥንታዊ የመንግሥትነት ታሪክ ሲነሳ ቅድመ አክሱም የነበረውና ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአንደኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ ላይ ያከተመው፣ የአማልክቱ የአልሙቃህ ቤተመቅደስ ፍራሽ የሚገኝበት ይሓን ማዕከል ያደረገው የደአማት ሥርወ መንግሥት ተጠቃሽ ነው፡፡

ከሕገ ኦሪት (አይሁድ) ወደ ሕገ ወንጌል (ክርስትና) የተሸጋገረችው አክሱም፣ ለኢትዮጵያ ክርስትና መሠረት ስትሆን፣ ክርስትናው የገባው ደግሞ በሐዋርያት ዘመን በ34 ዓ.ም. በጃንደረባው ባኮስ አማካይነት መሆኑ፣ ሐዋርያው ማቴዎስም ማስተማሩ በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ተዘግቧል፡፡

ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸምበት የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የተገነባውም በታሪከ ነገሥት እንደተጻፈውና  ግርማ ባቱ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከጥንት – 6ኛው ክፍለ ዘመን›› መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፣ ዳግሚት ኢየሩሳሌም የተባለች አክሱም ጽዮን፣ በኢትዮጵያ የክህነትም መሠረት የሆነች፣ የአድባራትና የገዳማት እናት ታላቅና ቀዳሚት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ መንትያ ወንድማማቾቹ አብርሃና አጽብሃ (በ340 ዓ.ም.) በአክሱም ጽዮን 12 መቅደስ ያለው ባለ 72 አዕማድ ቤተ ክርስቲያን አሠሩ፡፡

በላይ ግደይ እንደጻፉት፣ ይህን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በ10ኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ከፈረሰ በኋላ በቀድሞው ፍራሹ ላይ ባለ ሰባት መቅደስ ሕንፃ ገንብቶታል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አሕመድ ግራኝ ካቃጠለው በኋላ፣ በአሁን ዘመን ቆሞ የሚታየውን ያነፀው አፄ ፋሲል ነው፡፡ የዘመነ አክሱም ግዛት ሰፊ የነበረ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ እስከ ደቡብ ዓረብ የመን፣  በደቡብም የዘለቀ ነበር፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በአሁን ጊዜ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ በዚያ ዘመን መታነፃቸው ይገለፃል፡፡

በአሁኗ ኤርትራ ሥር የምትገኘው የያኔዋ የአክሱም ወደብ አዱሊስ አብያተ ክርስቲያናት የነበሩባት መሆኑም በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ መንበረ ጳጳስ እንደነበረባትም ጭምር፡፡

በአዱሊስ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች እንደነበሩባት የሚያረጋግጡ የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

በአዱሊስ የተገኘው ምንድን ነው?

በቅርቡ በውጮቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ የወጣው መረጃ ‹‹ARCHAEOLOGISTS EXCAVATE ANCIENT CHURCHES FROM AFRICAN KINGDOM›› በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡

አንቲኲቲ/አንቲካ (Antiquity) የሚባለው የአርኪዮሎጂ ጆርናል ይፋ እንዳደረገው፣ አርኪዮሎጂስቶች (የሥነ ጥንት ባለሙያዎች) በአሁኑ ጊዜ በኤርትራ ውስጥ በምትገኘው አዱሊስ ወደብ ላይ ሁለት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን በቁፋሮ አግኝተዋል።

እንደ አንቲኲቲ ዘገባ፣ ተመራማሪዎቹ አንደኛው ካቴድራል የተሠራው ከ400 እስከ 535 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ባለ ጉልላቷ ቤተ ክርስቲያን የተገነባቸው ግን በ480-625 ዓ.ም. ነው፡፡  ሁለቱም ከአክሱማዊው መንግሥት ከመጀመሪያዎቹ  አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከዋና ከተማዋ ውጭ ከሚገኙት ጥቂቶቹ መካከል ናቸው፡፡

አክሱማዊው መንግሥት ብቅ ያለው በአንደኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በከሰመው የደአማት መንግሥት ግዛቶች ውስጥ ነው።  መንግሥቱ ከጥንት ጀምሮ በሮም እና በህንድ መካከል በነበረው አህጉር አቋራጭ የንግድ መስመር ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወቱን፣ ይህም በጥንት ዘመን ከነበሩት ቀዳሚ ግዛቶች አንዱ ለመሆን እንዳስቻለው ጥናቱ አመልክቷል፡፡

የሥነ ጥንት ተመራማሪዎች በአዱሊስ ወደብ ላይ ካገኟቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ መካከል አንደኛው ካቴድራል የጥምቀት ቤቱን የሚያሳዩ ቅሪቶች ያሉት ሲሆን፣ ሁለተኛው በመጠን ትንሽ ቢሆንም ጉልላቱን የሚደግፉ የዓምዶች ቀለበት ይዟል።

የአክሱም መንግሥት ክርስትናን መቀበሉን ተከትሎ፣ ከተለያዩ ትውፊቶች የተቀዱ ፍሬ ነገሮች ቢንፀባረቁበትም፣ ባለጉልላቱ  ቤተክርስቲያን በአክሱም ልዩ ሕንፃ ሲሆን በቢዛንታይን ኪነ ሕንፃ የተቃኘ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ካቴድራሉ በዋነኛነት በአክሱማውያን ባህል መሠረት መታነፁን ተመራማሪዎቹ አስምረውበታል፡፡

ተመራማሪዎቹ ቤተ ክርስቲያናቱ የተገነቡበት ዘመን ለማወቅ የቻሉት፣ በሁለቱ ቦታዎች የተገኙትን ቁሳቁሶችን በሳይንሳዊው ትክክለኛ የቀን ማወቂያ መንገድ በሬዲዮካርቦን አማካይነት ነው፡፡

አብያተ ክርስቲያናቱ እስልምና በአካባቢው ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አገልግሎታቸውን ያቆሙ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ ግን የሙስሊም መካነ መቃብር ቦታ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ይህም አካባቢው ወደ እስልምና መቀየሩንና የተለያዩ ባህሎች ማሳያ መሆኑ፣ ይህም ባህላዊ ክስተት የአካባቢው ማኅበረሰብ ልማዶች ከአዲሱ ሃይማኖትጋር መቀላቀላቸውን ያሳያል ይላል ጥናቱ፡፡

‹‹ይህ የክርስቲያን የተቀደሰ ቦታ በእስላማዊ ማኅበረሰብ መያዙን የሚያሳዩ ቁሳዊ ማስረጃዎች ካገኘንባቸው የመጀመሪያዎቹ አንዱ ነው፤›› ብለዋል ዶክተር ካስቲግሊያ።
እነዚህ ሕንጻዎች በአንድነት ሆነው የአፍሪካ ቀንድ ሃይማኖታዊ ታሪክ ዓለም አቀፋዊ (ኮስሞፖሊቲያን) እንደነበር፣ የተለያዩ ቡድኖችም እምነቶችን በማስፋፋት ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ያሳያሉ፡፡

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአንደኛው ሺሕ ዓመት ላይ አብዛኛው  ሰሜናዊ የአፍሪካ ቀንድ ከኢትዮጵያ እስከ ዓረብ ይገዛ የነበረው  የአክሱማውያን አፄያዊ መንግሥት በሮማ አፄያዊ ዘመን ትይዩና ዘመነኛ ነበር።

የአክሱም መሪ የነበረው ንጉሥ ኢዛና በ4ኛ ክፍለ ዘመን ክርስትናን መቀበሉ ቢታወቅም፣ በዚያ ዘመን የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ማግኘት ግን እምብዛም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዋነኛዋ የአክሱም ወደብ አዱሊስ በአሁኗ ኤርትራ የተገኙት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት  ይህን ክፍተት ለመሙላት ያግዛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...