Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከታሪክ የምንማረው መቼ ነው?

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

የዓለማችን የታሪክ እምብርትና የሥልጣኔ ቁንጮ የሆነችውን ታላቂቷን ሮማንና መላውን የአውሮፓውያኑን የቅኝ ገዥ ኃይሎች ቅስም የሰበረውንና አሳፍሮ የመለሰውን የ1888ቱን የዓድዋውን ሽንፈት ለመበቀል ነበር ከአርባ ዓመት በኋላ ፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ሠራዊቱን እስከ አፍንጫው አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ጦሩን ያዘመተው፡፡

ፋሽስት ጣሊያን በዚህ ሁለተኛ የበቀል ዘመቻው ዋንኛ ዒላማው የነበረችው ደግሞ ‹የሰው ልጆች ነፃነትና አንድነት ተምሳሌትና ትዕምርት/ሲምቦል› የሆነችው- ጥንታዊቷ፣ ሐዋርያዊቷና ኩላዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ የዓድዋውን ጦርነት ከዘመቻው እስከ ድሉ ድረስ በማስተባበርና ሕዝቡ ከፈጣሪው ለተሰጠው ነፃነት በአንድነት በጽናት እንዲቆም በማስተማሯ ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ክፉኛ ጥርሱን ነክሶባት ነበር፡፡

እናም ጣሊያንና እንዲሁም መላውን አውሮፓ/የቅኝ ገዥ ኃይል አንገት ካስደፋው ከዚህ የታሪክ ቅሌትና የሞራል ስብራት ሮማን ለመታደግ ‹‹እኔ ጀግናዋ አለሁ!›› በማለት ነበር የፋሽስቱ መሪ ለራሱና ለሕዝቡ ቃል የገባው፡፡ ሞሶሎኒ ጣሊያንና መላውን አውሮፓን ሳይወዱ በግድ የሽንፈት ጽዋ እንዲጋቱ ያደረገችውን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመበቀል ሰዓቱ አሁን እንደሆነ በሮም አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ ሲል ነበር የተናገረው፡፡

‹‹ኢትዮጵያን አምላኬ የምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ መዳፌ ሊያድናት የሚችል ከሆነ የእኔንም እግዚአብሔር ልጨምርላት እችላለሁ!››

በተመሳሳይም የምሥራቅ አፍሪካ የጣሊያን ቅኝ ግዛት ሹም- ጄኔራል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ለአለቃው ለሞሶሎኒ፡- ‹‹ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ራሷን ገጸ-በረከት  አድርጌ አቀርብልሃለሁ፤›› በማለት ነበር ኢትዮጵያን/ሕዝቦቿንና ጥንታዊቷንና ሐዋርያዊቷን የኢትዮጵያን በቤተ ክርስቲያንን ለጣሊያን በገፀ በረከትነት ለማቅረብ ፋሽስቶች በሮማ አደባባይ የተደራደሩት፡፡ የተስማሙት፡፡

ሰማይን የሚራገጥ በሚመስል ትዕቢትና ‹የታሪክ ቅሌት› በፈጠረው ብርቱ ቁጭት ኢትዮጵያን በመዳፉ ሥር ለማስገባት ከአርባ ዓመታት በኋላ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ የመጣው ፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀንደኛ ጠላቱ ብቻ ሳትሆን፣ ለቅኝ ግዛት የመስፋፋት ዘመቻው ለጣሊያንም ሆነ ለአውሮፓ አደገኛ እንቅፋት መሆኗን በማሰቡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በሕዝቦቿ ላይ ብርቱ የጭካኔ ክንዱን አሳረፈባት፡፡

ፋሽስት ጣሊያን በዚህ የበቀል ዘመቻው እስከ አፍንጫው ከታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰማይ እየሰነጠቁ ሞትን የሚተፉ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከሉ የመርዝ ጭስ አረሮችን የተሸከሙ የጦር አውሮፕላኖችን ጭምር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡

በእነዚህ በሰማይ ላይ በሚምዘገዘጉ የፋሽስት ጣሊያን አውሮፕላኖች እንግዳ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም በጊዜው በእጅጉ ተደናግጦ ነበር፡፡ በእነዚህ ሰውነትን አሳብጠውና ብጥስጥስ አድርገው በሚገድሉ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሞት ላንቃቸውን ከፍተው የእሳት አሎሎን በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች ባደረሱት ዘግናኝ እልቂት እጅጉን ግራ የተጋባው የአገሬ ሕዝብም በወቅቱ ‹‹ይህ ምን ዓይነት መዓት፣ ምን ዓይነት ጉድ ነው?›› በሚል እንዲህ መቀኘታቸውንና ፈጣሪያቸውን መሞገታቸውን የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡-

‹‹ከኢትዮጵያ ጸሎት ጣሊያኖች በለጡ፣

በአርባ ዘመናቸው ክንፍ አውጥተው መጡ፡፡››

የአምላክን መኖሪያ፣ የልዕልናው መገለጫ የሆነውን ሰማይን በተዳፈሩትና ሰማዩን እየሰነጠቁ ሞት የሚያዘንቡትን፣ የእሳት መርዝ የሚተፉትን ትንግርትና ተአምር የሆኑባቸውን የጦር አውሮፕላኖች የአገሬ ሰው በሌላኛው ቅኔው እንዲህ ሲሉ ነበር በአግራሞት የተቀኘላቸው፡- 

የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣

አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፣

አምላክ ለአንተው ፍራ፣

በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡

ይህን በአሰቃቂ ሁኔታ ሰውነትን በጣጥሶ የሚገድለውን የመርዝ ጭስ ፋሽስት ጣሊያን ለመጠቀም የፈለገው የኢትዮጵያውያንን የውጊያ፣ የመከላከል ሞራልና ቅስም በመስበር ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ኾን ብሎ አስቦና አልሞ ነበር፡፡ በወቅቱ ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ መጠቀም ስለሚገባው የመሣሪያ ዓይነት በምስጢር አስተላልፎት የነበረውን መልዕክት በተመለከተ የአሜሪካው ‹ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ› የሚገኝ አንድ ታሪካዊና ምስጢራዊ ሰነድ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

‹‹ተልዕኳችን እንዲሳካ ከተፈለገ በጠላት ላይ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ከዚህም በላይ የሞራል ስብራት የሚያስከትለውን ልዩ የሆነ ፈሳሽ ቦምብና መርዝ ሼል እንደፈለጉ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፤››

ዘረኛው የፋሽስት መንግሥት ይህን እኩይ ተልዕኮውን ከግብ ለማድረስ በማሰብም በተለይም ሕዝቡ ለነፃነቱ ሳይከፋፈል በአንድነት በፅናት ይቆም ዘንድ የሚያስተምሩትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶችንና ሊቃውንት በአደባባይ ላይ በግፍ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ አድርጓል፡፡

ለአብነትም የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም እንዲሁም ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኾኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና ምዕመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የጣሊያን ፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው እኩይ የዘረኝነት ፖሊሲው/አቋሙ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የፋሽስቱ ሞሶሊኒ ጭካኔ፣ አውሬነት በዚህ ብቻ የተገታ አልነበርም፡፡ በተለምዶው ‹‹የአካፋው ሚካኤል›› ብለን የምንጠራው የካቲት 12 ቀን በአዲስ አበባና በነዋሪዎቿ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳምና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ፋሽስቱ ግራዚያኒ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋና ዕልቂት አስመልክቶ በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ሐንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ በዓይኑ ያየውንና የታዘበውን የፋሽስቶቹን ጭካኔና ግፍ በማስታወሻው እንዲህ ገልጾታል፡፡

ኢትዮጵያውያን በየመንገዶቹና በየመኖሪያ ቤታቸው እንደ አውሬ እየታደኑ በመላ ከተማዋ ይደበደቡ፣ በጥይት ይቆሉ፣ በሳንጃ ይዘከዘኩና ነፍሳቸው እስክትወጣ ድረስም በዱላ ይቀጠቀጡ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤታቸው በሚወረወር ነበልባልና ጋዝ በማርከፍከፍ እንደዚሁም በሰዎቹ ላይ ተቆልፎባቸው ከነሕይወታቸው እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጭፍጨፋና ጭካኔ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ መነኮሳትንና ቀሳውስትንም እንኳን አልመረጠም፡፡ በሁሉም የከተማው ማዕዘናት ከአራት ሺሕ በላይ ቤቶች እሳት ስለተለኮሰባቸው ከተማው በሌሊት የቀትር ብርሃን መስሎ ይታይ ነበር፡፡ የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንም እሳት የተለኮሰበት ሲሆን ሕንፃውን ለማውደምም ሃያ ፈንጂዎች ተቀብረውበት ነበር፡፡

ይህ በአዲስ አበባና በነዋሪዎቿ የተመዘዘው የፋሽስቱ የጥፋትና የጭካኔ ሰይፍም ወደ ጥንታዊው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ዘልቆ የገዳሙ መናኒያን፣ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ተማሪዎች በግፍ እንዲገደሉ፣ እንዲጨፈጨፉና እንዲጋዙ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ ‹‹የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት›› በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የጭፍጨፋ ዕርምጃ ጣሊያዊናዊው የታሪክ ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ ‹‹Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹… የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገብረ ማርያም ወልደ ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ዓ.ም. ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ…፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

በግፍ የፈሰሰ የንፁኃን ደም ሲፋረድ!

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስቶች የፍርድ ውሳኔ ለማዕተባቸው፣ ለቃል ኪዳናቸው ታምነው ለአገራቸው በተሰውበት/ሰማዕት በሆኑባት በዛች ቀን እንዲህ ነበር ያሉት፤

…እምዬ ኢትዮጵያ… እናት አገሬ ደሜ ለነፃነትሽ፣ ለክብርሽ፣ ለአንድነትሽ ንፁሕ የፍቅር መስዋዕት ሆኖ የፈሰሰ ነውና ጽኑና ኃያል በሆነው አምላክሽ ፊት ልክ እንደ አቤል ደም ለግፉአን ፍርድን የሚሻ፣ ፍትሕን የሚጠይቅ ይሁን! ሲሉ ዓይናቸውን ወደ ሰማየ ሰማይ አቅንተው አምላካቸውን እግዚአብሔርን በዕንባ ተለማመኑት፣ ተማጸኑት፡፡

እመብርሃን፣ የጌታዬ እናት፣ ድንግል ማርያም ሆይ… ይኸው ለቃል ኪዳን ምድርሽ፣ ለአሥራት አገርሽ ለእናት ምድሬ ኢትዮጵያ እንባዬን ከደሜ ጋር ቀላቅያለሁና… ይህን በዘረኞቹ ፋሽስቶች ክንድ በሕዝብሽ፣ በአገልጋዮችሽ ላይ እየወረደ ያለውን ግፍና መከራ በልጅሽ ፊት አዘክሪ አሳስቢ፡፡

እናቴ ሆይ አዛኝቱ ያለ አንቺ ማን አለኝ፣ ተስፋዬ ልጅሽ ነውና ‹‹እግዝእትነ ስምዒ ኀዘና ወብካያ ለአገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ሲሉ የኢትዮጵያን ሰቆቃዋን፣ ጣሯንና ጭንቀቷን አሳስቢ ሲሉ ተማፀኑ… ምድሪቱም ለፋሽስት እንዳትገዛ አውገዝውና በመስቀላቸው ባርከው ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡

የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስና የጎሬው የአቡነ ሚካኤል፣ የበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ለነፃነት ክቡር መንፈስ የፈሰሰ ዕንባቸውና ደማቸው በኢትዮጵያ ተራሮች፣ ሸንተረሮች፣ ዱርና ጫካ ታላቅ የሆነ የነፃነት ደወልን አሰማ፣ አስተጋባ፡፡ ‹እምቢ ለነፃነቴ› ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የፋሽስት ጣሊያን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በሃይማኖት የመከፋፈል ዘመቻ ሳይበግራቸው ነፃነታቸውን በደማቸውና በአጥንታቸው ለማስመለስ ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ የእናት ኢትዮጵያን ሕመሟን፣ ሥቃይዋንና መከራዋን በዕንባቸውና በላባቸው፣ በደማቸውና በአጥንታቸው ታላቅ መሥዋዕትነት ይካፈሉ ዘንድ ዱር ቤቴ አሉ፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት በአገራቸው ዱርና ተራራ ተሰደዱ፣ ሌሎች ደግሞ በዕንባና በለቅሶ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከፋሽሽት ጭካኔ ይታደጋት ዘንድ ሱባኤ ገቡ፡፡ አምላካቸውን መማጸን ያዙ፡፡ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳምም ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን መናኒያን፣ መነኮሳት፣ ካህናትና አገልጋዮችም የኢትዮጵያ አምላክ ለአገራቸው ነፃነትን ይመልስላት ዘንድ በጸሎት ተጋድሎ ተወሰኑ፡፡

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትንና የፍቅር መቅደስ በደማቸው ዳግም ሊቀድሱና ሊያከብሩ በነፍሳቸው የተወራረዱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግረውም በሮም አደባባይ በደማቸው ሕያው ታሪክን ጻፉ፡፡ የኦሮሞ ምድር ፍሬ የሆኑት ጀግናው ኢትዮጵያዊ ኮሎኔል አብዲሳ አጋና ኤርትራዊው ዘርአይ ደረስ በባዕድ ምድር፣ በግዞት እንኳን ሆነው ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮዬ ይጣበቅ፡፡›› በማለት የእናት ምድራቸውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማቸውን በሮም አደባባይ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የፍቅር መቅደስ መሆኑን በደማቸው መሰከሩ፡፡

ከማይጨው ዘመቻ መልስም ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ዴር ሡልጣን ገዳምን ተሳልመውና የጥቂት ቀናት ቆይታ አድርገው መንገዳቸውን ወደ ጄኔቭ ያደረጉት አፄ ኃይለ ሥላሴም የሕዝባቸውን ግፍና መከራ በተመለከተም በሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡ ንጉሡ በንግግራቸውም የጣሊያን የፋሽስት መንግሥት በአገራቸው ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በዓለም መንግሥታት የተከለከለ መርዛማ ጭስ የአገራቸው ሕዝብ እየፈጀ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ዘግናኝና አሰቃቂ መዓት ኃያላኑ ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ በብርቱ ተማፀኑ፡፡ የሕዝባቸውንም አቤቱታ በአደባባይ አሰሙ፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቤቱታና የሕዝባቸው ለቅሶና መከራ ግን ለአውሮፓውያኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ለአንዳንዶቹ አውሮፓውያን አገሮች ራሷን ከነጭ/ከአውሮፓውያን ጋር እኩል አድርጋ ለምታስበው ኢትዮጵያ ይህ ቅጣት የሚገባ፣ ልኳን እንድታውቅ የሚያደርግ ጦርነት መሆኑን በማመን ለፋሽሽቱ ሞሶሎኒ በግልጽና በሥውር ‹‹በርታልን!›› ሲሉ ቀኝ እጃቸውን አዋሱት፡፡

በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ተግባራዊ ምላሽ ያላገኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም፣ ‹‹… ይህን የአገሬንና የሕዝቤን ግፍና መከራ ችላ ብላችሁ ብታልፉት ታሪክና እግዚአብሔር ፍርዳችሁን ይሰጣችኋል…፤›› ሲሉ ትንቢታዊ የሚመስል ታሪካዊ ንግግርን አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያን በአምባገነኑ የፋሽስት ሠራዊት መወረርና የሕዝባችንም ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮፓውያኑ አገሮች ብዙም ሳይቆይ ከጀርመን በተነሳው በናዚ ሒትለርና በፋሽስቱ መሪ ሞሶሎኒ የጦር ክተት ታወጀባቸው፡፡

አምባገነኖችን፣ ግፈኞችን በጊዜው ተዉ፣ እረፉ! ለማለት ሞራል፣ ጉልበት ያነሰውና ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› የሚል ፖለቲካዊ ስላቅን ያተረፈው ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽንም›› በዓይኑ ፊት በአምባገነኖቹ ሂትለርና ሞሶሎኒ አገሮች በግፍ ሲወረሩ የኃይለ ሥላሴ ትንቢታዊ ንግግር እየተፈጸመ እንደሆነ በወቅቱ ቀውሱን የታዘቡ ፖለቲከኞችና የታሪክ ምሁራን በሰፊው ጻፉ፣ መሰከሩም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ኢፍትሐዊ ወረራና ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮፓውያን በራሳቸው ሲመጣ ግን ለመታገስ አልቻሉም ነበር፡፡ ሳይወዱ ተገደው ወደ ጦርነት ገቡ፣ እናም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓሊፈነዳ ግድ ሆነ፡፡

የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች እንደጻፉት ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት ሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኃይል ስትወረር ያሳየው መለሳለስና ደካማ አቋም እንደ አንድ ትልቅ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል መሆኑን ያስመሩበታል፡፡ ‹‹አክሲስ ፓወር›› በሚል በጀርመኑ ሒትለር፣ በፋሽስቱ ሞሶሎኒና በቶኪዮ/ጃፓን የተባበረ ኃይል ዓለምን በራሳቸው ቁጥጥር ሥር ለማድረግ የተነሱ ጣሊያንና ጀርመንን ለመመከት እንግሊዝና ፈረንሣይ ሌሎችን አገሮችን በማስተባበር ወደ ጦርነት ከተቱ፡፡

የኢትዮጵያና የሕዝቦቿም ለቅሶ በእግዚአብሔር ፊት ታሰበ፡፡ የግፍ ጽዋም ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ እናም፣ ‹‹ስለ ድሆች፣ ስለ ምድሪቱ ግፉአን፣ ፍትሕንና ፍርድን ስለተነፈጉ ምንዱባን እግዚአብሔር አሁን ይነሳል ይላል››፣ ‹‹እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡›› ተብሎ በአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት የተነገረለት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የመዓቱን ጽዋ በአውሮፓ ምድር ላይ አፈሰሰው፡፡ አውሮፓ/ዓለም እስከ ዛሬ ዓይቶት በማያውቀው መከራና ሰቆቃ ውስጥም ተዘፈቀ፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትና የአካል ጉዳተኛ የሆኑበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሎ የናዚውን ሒትለርና የፋሽስቱን ሞሶሎኒ ታሪክ በውርደት ደመደመው፡፡ ‹‹… የትኛው አምላክ ነው ኢትዮጵያን ከኃያሉ ክንዴ የሚያስጥላት›› ያለው ሞሶሎኒም በሮም አደባባይ አይወርዱ ውርደትን ተዋርዶ የሞት ስቅላት ተፈረደበት፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ገፀ በረከት አድርጌ አቀርብልሃለሁ!›› ብሎ ለአለቃው ለሞሶሎኒ ቃል የገባው ማርሻል ግራዚያኒም- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ጽናት፣ በአገልጋዮቿ ሰማዕትነት፣ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአርበኞቻችን የነፃነት ተጋድሎ ከንቱ ሆነ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ሠራዊትም በመጨረሻ ተሸንፎ፣ አፍሮና ተዋርዶ አገራችንን ለቆ ወጣ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በልጆቿ ደም የተቀደሰው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማዋ ዳግመኛ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡

እናም የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስ፣ የአቡነ ሚካኤል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ሊቃውንት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ አንድነት፣ ለማዕተባቸው/ለቤተ ክርስቲያን ጽኑ የፍቅር ቃል ኪዳን ሲሉ በግፍ የፈሰሰው የሰማዕታቱ ደም፤

ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች የእነ አብዲሳ አጋ፣ ዘርዓይ ደረስ፣ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ፣ የራስ አበበ አረጋይ፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ የወ/ሮ ልኬየለሽ በያን፣ የእነ ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ የአፍሪካ አሜሪካዊው የኮሎኔል ጆን ሮቢንሰን፣ የጋናው ክዋሜ ንኩርማ፣ የኬንያው የጆሞ ኬንያታ… ወዘተ. በአጠቃላይ የአፍሪካ አሜሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝብ የፀረ ፋሽስት የአርበኝነት ተጋድሎና የፍትሕ ድምፅ የተነሳ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በሮም አደባባይ ሳይቀር በደማቸው ከፍ ያደረጓት ሰንደቀ ዓላማችንን በአገራችን ሰማይ ላይ ዳግመኛ በክብር ከፍ ብላ ተውለበለበች፡፡

ዳግመኛ ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው የሚያንቀላፋ እንጂ የማይሞት ጽኑና ሕያው የአንድነትና የፍቅር ውል ቃል ኪዳን መሆኑ ተበሰረ፡፡ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጽኑ ቃል ኪዳን ጋር የተገዳዳሩ፣ ሕዝቡን ለነጻነቱና ለአንድነቱ ፀንቶ እንዲቆም በምታስተምረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እጃቸውን ያነሱ ሁሉ ዕድል ፈንታቸው፣ ጽዋ ተርታቸው ድቀት፣ ውርደትና ጥፋት መሆኑ በግልጽ ታየ፡፡

የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትና የፍቅር መቅደስን ሊያረክሱና ሊያራክሱ የተነሱ ሁሉ ለድቀት፣ ለውርደትና ለአሳፋሪ ሽንፈት መዳረጋቸው የታወቀ ሀቅ መሆኑ ተመሰከረም፡፡ በምንም የማይረታና የማይሸነፍ በዓድዋ የተበሰረው ጽኑ የኢትዮጵያዊነት ታላቅ መንፈስም ዳግመኛ በፋሽስቱ ሞሶሊኒ ውርደትና ውድቀት የተነሳ ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡

ይህ የኢትዮጵያዊነት ክቡር የአንድነትና የፍቅር መንፈስ የቋራው ካሳ/ቴዎድሮስ በመቅደላ አፋፍ የተሰዉለት፣ አፄ ዮሐንስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አገርህ ልጅህ፣ ሚስትህ፣ እናትህ፣ ዘውድህ፣ ክብርህና መቃብር ናት!!›› በሚል በመተማ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጦር የሰጡለት፣ እምዬ ምኒልክ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች በዓድዋ ጦር ግንባር በደማቸው የቀደሱት፣ ያከበሩትና ያወደሱት ነው … ይህ ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያዊነት የአንድነት፣ የፍቅር ቃል ኪዳን፣ ክቡርና ታላቅ መንፈስ!

እናም እጃችሁን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነሳችሁ ሁሉ ከፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ፣ ከግራዚያኒ፣ ከዘረኞቹና ከአምባገነኖቹ ውርድትና ውደቀት ትማሩ ዘንድ ታሪክን ዋቢ አድርግን እንዲህ በድፍረት ልንነግራችሁ እንወዳለን! ሰላም ለኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles