Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የዓለም አቀፍ ተቋማት አጋርነት

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የዓለም አቀፍ ተቋማት አጋርነት

ቀን:

በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በየጊዜው ማስገንዘቢያዎች ተሰጥተዋል፡፡ ፖሊሲዎች ከወጡና መተግበር ከጀመሩም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ልማዱ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ሆኖም የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች ላይ በስፋት የሚተገበርና ከቀዳሚዎቹ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሚመደብ ሲሆን፣ ድርጊቱ የሴትን መብት ከመጣስም ባለፈ ከፍተኛ የጤና ችግር የሚያስከትል ነው፡፡

የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡትም፣ ግርዛት ከሚፈጥረው ጠንካራ የሕመም ስሜትና የሕዋሳት መጎዳት የተነሳ ለፌስቱላ፣ በወር አበባ ወቅት ለሚፈጠር ሕመም፣ አንዳንድ የሰውነት አካል ላይ ስሜት አልባ መሆንና መደንዘዝ፣ የሚወልዷቸው ልጆችም የቀጨጩ፣ ከሚፈለገው ክብደት በታች እንዲሆኑና በምጥና ወሊድ ጊዜ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ የሚገኘው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ወደ 30 በሚጠጉ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በእስያ በሚገኙ አገሮች ሲሆን፣ በዓለም ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናትና ሴት ልጆች ላይ በተለያየ መልኩ ግርዛት ተፈጽሟል፡፡

ኢትዮጵያም የሴት ልጅ ግርዛት በ1997 ዓ.ም. ከነበረው 74 ከመቶ፣ በ2008 ዓ.ም. ወደ 65 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጓ ቢመዘገብም፣ 25 ሚሊዮን ሴቶችና ልጃገረዶች መገረዛቸውን በተባበሩት መንግሥታት ሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) እና የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገልጸዋል፡፡

‹‹የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ማኅበራዊና ጾታዊ ጎጂ ልማዶችንወንዶችን አጋር በማድረግ ማሻሻል›› በሚል ጭብጥ የሴቶችን ግርዛትን ወደ ዜሮ ለማውረድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የዋለውን ቀን አስመልክቶ ድርጅቶቹ ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የታየው የሴቶችና የልጃገረዶች ግርዛት ቁጥር ከምሥራቅና ከደቡብ አፍሪካ ትልቁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሴቶችና የልጃገረዶች ግርዛት ከጥንቱም ሲያያዝ የመጣ ልማድ መሆኑን መግለጫው አመልክቶ፣ ይህንን ጎጂ ልማድ ለማስቀረትና ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል እየተካሄደ ላለው እንቅስቃሴ ስኬታማነት ወንዶችን ማሳተፉ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሴቶችንና የልጃገረዶችን ግርዛት እንዲሁም ያለ ዕድሜ ጋብቻን በ2025 ለማስቀረት የወጣው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ለተጠቀሰው ችግር የተጋለጡ 3.6 ሚሊዮን ልጃገረዶችን ለመታደግ እንደሚረዳ፣ ይኸው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ችግሩን ለማስወገድ የወንዶችን ተሳትፎ እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ አድርጎ መወሰድ እንዳለበት አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ የሴቶችንና የልጃገረዶችን ግርዛት አስከፊነት አስመልክቶ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከሚሰጡ አገሮች ተጠቃሽ እንደሆነች፣ በዚህም 86.7 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የሴቶች ግርዛት ወደፊት መቀጠል እንደሌለበት ማመናቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አቡበከር ካምፖ (ዶ/ር)፣ ልጃገረዶች ለግርዛት የሚዳረጉት ያለፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ጎጂ ልማድ ለማስቀረትና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የየክልሉ ተወካዮችና የዘርፍ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ከሦስት ዓመት በፊት ውይይት ባደረጉበት ጊዜ እንደተገለጸው፣ በ2011 ዓ.ም. በሶማሌና በአፋር ክልሎች ውስጥ 99 በመቶ፣ በትግራይ ክልል ደግሞ 23 በመቶ ግርዛት ተፈጽሟል፡፡   

ጎረቤት አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አኃዝ አላቸው፡፡ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በቀላሉ በመዘዋወር የሴት ልጅ ግርዛትን እንደሚፈጽሙ፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በተመሳሳይ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመሄድ የሴት ልጅ ግርዛት እንደሚከናወን ተጠቁሞም ነበር፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመቀነስም ከጎረቤት አገሮች ጋር በጋራ ለመከላከል፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሚኒስትሮች ከዚህ ቀደም የጋራ ቃል ኪዳን ተፈራርመዋል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም እየሠራች መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...