ራስን መደለል በእንስሳትም መካከል በጥቂቶች ላይ የተደረገ ሆኖ፤ በምሳሌ ዓይነት እንደ ተረት የሚነገር ቃል እናገኛለን፡፡ ተረቱም እንደሚከተለው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የተራበች ጦጣ ባንድ የወይን ሥፍራ አጠገብ ስታልፍ ቁመቷ ከማይደርስበትና ዘልላም ልታወርደው ከማይቻላት አስቸጋሪ ከሆነ ካንድ ከፍተኛ ሥፍራ ላይ በስሎ መልኩ ብቻ እንኳን የሚያስጎመጅ አንድ የወይን ዘለላ ተንዠርጐ ተመለከተች፡፡ ለማውረድም ሞክራ ሳይሆንላት ስለ ቀረ ፥ ልቧ እያወቀ ራሷን በማታለል ፥ ‹‹ወይኑ እኮ እንደሆን በእውነቱ ገና አልበሰለም፤ ለጊዜው የደረሰ መሰለ እንጂ ጥሬ ነው፡፡ ስለዚህ ላንድ ጥሬ ለሆነ ላልበሰለ ወይን ይህን ያኸል ምን ያደክመኛል? የሱን ዓይነት ከሌላስ ሥፍራ አጥቼ ነውን?›› በማለት ራሷን ደልላ ይኸንኑ ቃል በመደጋገም ራሷን እየነቀነቀች ነገሩን አኳስሳ ትታው ሄደች ይባላል፡፡
እንደዚሁም አንዲት ሰጐን አንድ አዳኝ ጠመንጃውን ደግኖ ሊተኩስባት ሲያነፃፅርባት እያየች፤ ሮጣ ሕይወቷን ለማዳን ከመሞከር ይልቅ፤ እዚያው ሁና ተደፍታ ዓይኖቹዋ እንዳያዩ ወደታች አቀርቅራ፤ ‹‹የት አለና ነው አዳኝ? ቢኖር ለምን አላያውም? ይኸው ምንም ነገር አላይም›› እያለች በሐሳቧ ራሷን ደልላ ከዚያው አንገቷን ደፍታ ተቀመጠች ይባላል፡፡ ነገር ግን እውነቱ ጦጣዋም ሆነች ይህችኛዋ አውሬ፤ ሁለቱም ራሳቸውን እንዲህ አድርገው ቢደልሉትም፤ ወይኑን የበሰለ መሆኑ፤ አዳኙም ከዚያ ተገኝቶ ጠመንጃውን የደገነ መሆኑ የማይቀርና የነርሱ ክህደት ነገሩን ለውጦ ሐሰት ሊያደርገው አለመቻሉ የተረጋገጠ ነው፡፡
እንግዲህ በዚህ ታሪክ ውስጥ ጦጣይቱና ሰጎኗ ራሳቸውን በመደለል ያደረጉትን ሙከራ እንመለከታለን፡፡ ሰውም ልክ እንደነዚሁ እንስሳት ይኸንኑ ዓይነት ተግባር በራሱ ላይ ሲፈጽም ይገኛል፡፡ ለዚያውም ደግሞ እነዚህ እንስሳት ይህንን ነገር ፈጽመውት ነው ማለት ሳይሆን፤ ከሰዎች ዘንድ የሚደረግ መሆኑን በምሳሌ መንገድ ለመግለጽና ለማስተማር ያኸል የሚነገር ነው፡፡ የቀድሞ አባቶቻችን፤ ሰው ያልኾነውን ነው በማለት ራሱን የሚደልል ከንቱ መኾኑን ተመልክተው «እርኩምን ሊበሉ፤ ጅግራ ነው አሉ» ብለው ይተርኩት የነበረ ቃልም ይገኛል፡፡
ስለዚህ ሰው ራሱን በራሱ እንደ ሕፃን ልጅ በመደለል በሐሳቡ የተመኘውን ነገር ሁሉ ሲፈጽም መታየቱ የቆየ እንጂ፤ አዲስ አይደለም፡፡
- የማነ ገብረማርያም (ዶ/ር) ‹‹የፍልስፍና ትምህርት ፩ኛ›› (1955)