በዳግም መርሻ
ሰሞኑን የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ታዲያ ይህ ምን አዲስ ነገር አለው? ሊባል ይችላል። በርግጥም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ተፈታኝ ተማሪዎቹን፣ አለፍ ሲልም ወላጅን ጨምሮ የቅርብ ቤተሰብ አባላትን ካልሆነ በስተቀር እንዲህ እንዳሁኑ የሕዝቡን ትኩረት በትልቁ ስቦ አያውቅም። ጉዳዩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሊሆን የቻለው ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል የማለፊያውን ነጥብ፣ ማለትም ከ50 በመቶ በላይ አምጥተው ያለፉት ተማሪዎች እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መሆኑ ነው። የተመዘገበው ውጤት ምን አንደሚነግረን ወደ መዘርዝር ከማለፋችን በፊት ስለትምህርት ምንነት/ፋይዳ፣ እንዲሁም ስለመጣንበት ሒደት በጨረፍታ ማየት ጥሩ ይመስለኛል።
የትምህርት ጉዳይ ለአገርም ለሕዝብም ትልቅና መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በሌላ አነጋገር ትምህርት የአንድን አገር መፃኢ ዕድል ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ትምህርት የሰው ልጆችን ኑሮ ለማቅለል፣ የአገር ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ታሪክን፣ ባህልንና ዕውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገልግል መሣሪያ ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል።
የተለያዩ አካላት ትምህርት ዓለምን በመለወጥ ረገድ ያለውን ፋይዳ በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በሕዝቦችና በአገሮች መካከል የሥልጣኔ ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገውም እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ አገር ለትምህርት በሚሰጠው ትኩረት፣ ትምህርትን ለማስፋፋትና በትምህርት ለማነፅ ባለው ቁርጠኝነት መሆኑን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል፡፡ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚነገርላቸው የአገር መሪዎችም በተለያየ አጋጣሚ ለሕዝባቸው ንግግር ሲያደርጉ የትምህርትን አስፈላጊነት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ከዚህ አንፃር ቶሎ ብሎ ወደ አዕምሮ የሚመጣው የዓለም ሕዝብ በነፃነት ታጋይነታቸው የሚያከብራቸው የህንዳዊው ማኅተመ ጋንዲ የማይዘነጋ ጥቅስ ነው። ማኅተመ ጋንዲ፣ ‹‹ፍፁም የሆነ ሰላም ለዓለም እንዲሆን የምንሻ ከሆነ ሕፃናትን በሚገባ በማስተማር መጀመር አለብን፤›› በማለት የትምህርትን አስፈላጊነት ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ የነፃነት መሪውና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላም፣ ‹‹ትምህርት ዓለምን ለመቀየር ከሚያስችሉ መሣሪያዎች ሁሉ ከፍተኛ አቅም ያለው ነው፤›› በማለት ትምህርት ዓለምን ለመቀየር ምን ያህል አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ትምህርት የሚለውን ቃል፣ ‹‹ዕውቀት፣ ክህሎት፣ እሴቶች፣ አመለካከቶችና ልማዶች የምንጨብጥበት መንገድ ነው፤›› ሲል ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት ትምህርት ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በብቁና በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረ ገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ የሆኑ በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ እናገኘዋለን። እነዚህ የሰው ልጅ ብቃቶች የሚገኙት በዘመናዊ ትምህርት ብቻ ነው።
የትምህርት ጉዳይ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ጉዳይ የትምህርት ጥራት ነው። ከዚህ አኳያ ትምህርት ተገቢና ተግባራዊ መንገዶችን ባሟላ ሁኔታ መሰጠት እንዳለበት ከማስገንዘቡ ጎን ለጎን፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት፣ የትምህርት ግብዓት፣ የትምህርት መሣሪያ (ቁሳቁስ) መሟላት ወሳኝ መሆኑን ዩኔስኮ ይገልጻል፡፡
የአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገትና የሕዝቦቿ የኑሮ ደረጃ በሚኖራት የሰው ኃይል አቅም ይወሰናል፡፡ ዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በልፅገው በአገራቸው ልማትን በማምጣት የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አገሮች ልምድ የሚያሳይን ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ኃያላኑ እነ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ካናዳና በርካታ የስካነዲኔቪያን አገሮች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በቅርብ ዓመታት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ እመርታ በማምጣት የዓለምን ቀልብ እየገዙ ያሉት እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት ለትምህርት በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ነው።
በተቃራኒው ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በተለይም አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉት የትምህርት ሥርጭትና ተደራሽነት፣ የአግባብነትና የጥራት ጉደለት የመሳሰሉት ዋና ዋና ችግሮች ጎልቶ የሚታባቸው አገሮች እንደሆኑ በስፋት ይነሳል። ይህ ደግሞ በልማትና የዕድገት ጉዟቸው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
ዘመናዊ ትምህርት በአገራችን ከተጀመረ ከአንድ ምዕት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ዘርፍ ነው። ይሁን እንጂ ያለፉት መንግሥታት ይከተሉት በነበረው የተሳሳተ ፖሊሲ ሳበያ፣ አገሪቱ ላሉባት ውስብስብ ችግሮች ትርጉም ያለው ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት በቅቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በተለይም የቀድሞው የኢሕአዴግ አስተዳደር ለአገሪቱ ምሁራንና በአጠቃላይም ለትምህርት ጥራት ይሰጥ የነበረው ትኩረትና ግምት የወረደ የነበረ በመሆኑ አገሪቱ በብዙ ሁኔታ ትልቅ ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል። ይህ ማለት ግን በደፈናው ትምህርት ለአገሪቱ ምንም ነገር አልፈየደም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ምንም እንኳን ሌሎች አገሮች በሄዱበት ፍጥነት እኩል ባንሄድም፣ አገር በብዙ ሁኔታ ከትናንት ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መመስከር ይችላል። ለዚህ ደግሞ የዘመናዊ ትምህርት ትሩፋትን የመቋደስ ዕድል ያገኙ ዜጎች ድርሻ የሚናቅ አይደለም።
ሆኖም መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር የትምርት ሥርዓቱ ጠንካራ፣ በተግባር የተፈተሸ፣ በቂ ዕውቀትና ክህሎትን የተካነ ትውልድ ጥራትን ማዕከል ባደረገ አግባብ ከማፍራት ይልቅ፣ ለሥርዓቶቹ እንዲመች ተደርጎ መለዋወጡና በየጊዚው የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ አንዲሆን መደረጉ፣ ትውልድን በጥራት ከማፍራት አንፃር የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል።
በእርግጥ ባለፉት ዓመታት የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት፣ የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት በማጎልበት በኩል በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከእነ ብዙ ችግሮቹ በተለይ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በየክልሉ በመገንባታቸው፣ ብዙ ዜጎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዲማሩ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ አገሪቱ ሰፊ የተማረ የሰው ኃይል እንዲኖራት አስችሏል፡፡ ሆኖም ለትምህርት ተደራሽነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለጥራቱ አለመሰጠቱ የትምህርቱ ዘርፍ ዋና ግቡን ሳያሳካ በውድቀት ጎዳና እንዲዳክር ተገዷል። ይህንን ተከትሎም በተለያየ ደረጃ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ዜጎች የቁጥራቸውን መብዛት ያህል፣ የሚጨብጡት የዕውቀት መጠንና የክህሎት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የሚገባና አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ለአብነትም በቅርቡ ራይዝ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ በ168 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ በዘጠኝ ሺሕ ተማሪዎች ላይ የተሠራው ጥናት እንዳሳየው፣ 68 በመቶ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎችና 51 በመቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ያመላክታል። በተመሳሳይም ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባጠናው ጥናት መምህራን በሚያስተምሩበት የትምህርት ዘርፍ ተፈትነው 50 እና ከዚያ በላይ ያገኙት ከ30 በመቶ እንደማይበልጡ፣ 90 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርት እንደማያሟሉ፣ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ተምረው ሲጨርሱ ማንበብና ቁጥር ለመለየት እንደሚቸገሩ በግኝት መረጋገጡ የውድቀቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።
ከትምህርት ጥራት ችግር ጎን ለጎን ለትምህርት ሥርዓቱ እየተዳከመ መምጣት እንደ ምክንያት የሚወሰደው፣ ፈተናዎቹ የፖለቲካና የብሔር መልክ እየተሰጣቸው የመምጣቱ ሁኔታ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ከቅርብ ዓመታት ወዲሀ በስፋት እየተስተዋለ የመጣው ኩረጃ፣ ስርቆት፣ ፈተናን በደቦ መሥራትና የተማሪዎች የሥነ ምግባር ችግር ነው። በዚህም ምክንያት የፈተናው ሥርዓት በትምህርት ሚኒስቴር፣ በተማሪዎችና በወላጆች እምነት እንዳይጣልበት ከማድረጉም ባሻገር በመጪው ትውልድ ህልውና ላይ ሥጋት ደቅኖ ቆይቷል። ሰሞኑን ከዚህ በፊት ከነበረው የተለመደው አሠራር ወጣ በማለት ተማሪዎች ለፈተና የተቀመጡበት የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት፣ ይህንኑ የትምህርት ዘርፍ ገመና ግልጥ አድርጎ አሳይቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር ለሕዝብ ይፋ ባደረገው ስታትስቲክሰ መሠረት ዘንድሮ የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናውን የወሰዱት ተማሪዎች ቁጥር 896,520 ያህል ሲሆን፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለመማር የሚያስችለውን ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 3.3 ወይም 29,909 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳው ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች በሙሉ ያሳለፉ ሲሆን እነዚህም ትምህርት ቤቶች ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ኦዳ አዳሪ ልዩ ትምህርት ቤት፣ ባህር ዳር ስቴም ትምህርት ቤት፣ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት፣ የጎንደር ማኅበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤትና ከግል ትምህርት ቤት ደግሞ ለባዊ ትምህርት ቤት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ተማሪዎቻቸውን ለፈተና ካስቀመጡ 2,959 የመደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል 1,161 የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችም ውጤታቸው ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውጤት አኃዝ መሠረት አማካይ የተፈታኞች ውጤት በአማካይ 29.25 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው ኬሚስትሪ በአማካይ 33 በመቶ፣ እንዲሁም ዝቅተኛው ሒሳብ በአማካይ 25.5 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። በሌላም በኩል በማኅበራዊ ሳይንስ ከ500 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር በመላ አገሪቱ አሥር ብቻ ሲሆኑ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ከ500 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ደግሞ በመላ አገሪቱ 263 ብቻ መሆናቸውን የወጣው መረጃው ያመለክታል፡፡
ከዘህ በመነሳት የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎችና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ዜጎች ውጤቱ ምን እንደሚያሳይና ምን አንድምታ እንዳለው ሲተነትኑና ሐሳብ ሲለዋወጡ ሰንብተዋል። በዘርፉ ውስጥ እንዳሉ አብዘኞቹ ምሁራን ከሆነ ውጤቱ እንደ አገር የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት/ሲስተም ምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳለ በቂ ማሳያ ነው።
ለተማሪዎቻችን ውጤት ማነስ በርካታ ዝርዝር ምክንያቶችን መጥቀስ ፣ በጥቅሉ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲጠራቀሙ የመጡት ብልሹ አሠራሮች ውጤት መሆኑ ይወሳል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት መምህር ከበደ ገነቴ (ዶ/ር) እንደሚሉት የተመዘገበው ውጤት ከትምህርት ግብዓትና ከመማር ማስተማር ሒደቱ ጋር ተያይዞ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ የተለያዩ ችግሮች ተደማምረው የፈጠሩት ነው። ለዚህም ከመምህራን እጥረት፣ ከመምህራን ብቃትና ተነሳሽነት፣ ከሥልጠናን ጉዳይ፣ ከተረጋጋ የመማር ማስተማር ሁኔታ፣ ከምዘናው ሥርዓት፣ ከትምህርት መሠረተ ልማት መሟላት፣ ከወላጆች ክትትል እንዲሁም ከተማሪው ተነሳሽነት/ቀናዒነት ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን እንደ ምሳሌ በማቅረብ ይሞግታሉ።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ የውጤቱን ማነስ በአገሪቱ ከነበረው አለመረጋጋት፣ ተማሪውን የሚያዘናጉ ሁኔታዎች እየበረከቱ መምጣትና አቋራጭ መንገድ ከመፈለግ ዝንባሌ ጋር ያያይዙታል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በጉዳዩ ዙሪያ ሲናገሩ፣ ‹‹የፈተናው ውጤት ስለትምህርት ቤቶቻችን፣ ተማሪዎች ለትምህርት ስለሚሰጡት ትኩረት፣ ስለተማሪና መምህራን ግንኙነት፣ መምህራኖቻችንን ስላዘጋጀንበት፣ ስላሰማራንበት፣ ስላተጋንበት፣ ተጠያቂነትን ስለረጋገጥንበት፣ የትምህርት መዋቅሩ ለትምህርት ጥራት ያለበትን ኃላፊነት ምን ያህል እንደዘነጋ፣ ወዘተ አሳይቶናል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ።
ይሁንና በቀጣይ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ ከተሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል፣ አብዛኞቹ የልማት ማኅበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ማኅበረሰቡ ትኩረት ሰጥተው በከፈቷቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ዘንድሮ ካስመዘገቡት ውጤት እንደታየ ሳሙኤል (ዶ/ር) ይገልጻሉ። በአንድ በኩል ውጤቱ አስደንጋጭ ቢሆንም በሌላ ጎኑ በቀጣይ ማን ምን መሥራት እንዳለበት፣ እንዲሁም ችግሩ የት ጋ እንዳለ የሚጠቁም በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ውጤቱ ምን አሳየን በሚለው ጉዳይ ላይ፣ በሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል (ዶ/ር) በተነሳው ሐሳብ ይስማማሉ። እንደ እሳቸው አገላለጽ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት የሚመለከተው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የተገነባበትን አግባብና ተማሪዎችን ከማብቃት አንፃር ያለበትን ግዙፍ ችግር ነው። ይሁንና ግኝቱ ቀጣዩን ትውልድ ኮትኩቶ ለማውጣትና ወደ የሚፈለገው መንገድ ለመጓዝ እንደ ማንቂያ ደወል የሚሆን ጥሩ ገጠመኝ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር የመጨረሻውን ርቀት ሄዶ ለረዥም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የፈተና ስርቆትና ኩረጃ እንዳይቀጥል ለማድረግ የወሰደው ቆራጥ ዕርምጃ ይበል የሚያሰኝና ለሌሎችም ተቋማት አርዓያ የሚሆን ተግባር ነው። ይህ ጅማሮ ፈተናን በራስ ጥረትና ውጤት ብቻ ማለፍ የሚለው ሥነ ልቦና በተማሪዎች፣ በወላጆች፣ በትምህርት አመራሮችና በማኅበረሰቡ ውስጥ ማስረፅ እስከሚቻልበት ጊዜ ድረስ ዘላቂ ሆኖ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ይህ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሥራ ነው።
በአጠቃላይ ዓመታትን ቆጥሮ ኩረጃን ባስቀረ ጥብቅ የፈተና አሰጣጥ ሒደት የተገለጠው የዘንድሮ የተማሪዎች ውጤት የሚነግረን ነገር ቢኖር የትምህርት ሥርዓቱ ትልቅ ስብራት ላይ ያለ መሆኑን ነው። ለዚህ ስብራት የፖለቲካ አመራሩ፣ ማኅበረሰቡ፣ ወላጅ፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የትምህርት አመራር፣ ወዘተ ሁሉም የተጠያቂነት ድርሻውን ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ለዚህ ዋናውን ኃላፊነት የሚወስደው መምህሩ ነው። ምክንያቱም ተማሪዎቹን በዕውቀት አንፆና በሥነ ምግባር ኮትክቶ ለስኬት የሚበቃው መምህሩ ነውና። ተማሪው ብቃት የሚኖረው መምህሩ ብቃት ሲኖረው ነው። በመሆኑም ትውልዱን በተገቢው ሁኔታ በመቅረፅ የተሻለች አገር መፍጠር የሚያስችል የትምህርት ፖሊሲና የትምህርት ሥርዓት አገርን ከስብራት በሚያድን መንፈስ መተግበር ያስፈልጋል። ከዚህ እኩል በትምህርት ትግበራው ውስጥ ተዋናይ የሆኑትን የመምህራንን አቅም ማሳደግ፣ ማብቃትና መደገፍ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመማር ማስተማር ሒደቱን ምቹና ስኬታማ የሚያደርጉ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቃል።
በዚህ አግባብ የመጣውን ውጤት መሠረት በማድረግ ከዚህ ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርት ሥርዓት የፈጠረውን ሕመም ምክያንቱን ከሥር መሠረቱ (Root Cause) በዝርዝር በማጥናት፣ መፍትሔው ላይ መወያየትና ችግሩን ዘላቂ በሆነ መንገድ ማከም ያስፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው dagimmersha@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡