Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

ቀን:

በጀማል ሙሀመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

“ሆድ ባዶ ይጠላል…”

“ከሆድ የገባ ያገለግላል…”

ከጥቂት ዓመታት በፊት ባህር ዳር ከተማ የሚኖር ሼህ አደም የሚባል ሱዳናዊ ነበር በእናቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፡፡ “ጣት ያስቆረጥማል” የሚባሉትን የዓሳ ጥብስና ፉል በመሸጥ ነበር የሚተዳደረው፡፡ የጥብሱን ቅመም የሚያዘጋጀውም ሆነ ዓሳውን የሚጠብሰው ራሱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የእናቱን ዘመዶች ለመጠየቅ ወደ በየዳ (ሰሜን ጎንደር) ይሄዳል፡፡ በነጋታው ጎህ ከመቅደዱ በፊት የሚሰገደውን ሶላት (የፈጅርን ሶላት) እንደ ጨረሰ፣ አጎቱ (የእናቱ ወንድም) ሽር-ጉድ ማለት ጀመረ፡፡ ሁለት ትልልቅ ቅሎችንም ከጓዳ አወጣ፡፡

“የት ልትሄድ ነው?” በማለት ሼህ አደም ጠየቀ፡፡ አጎቱም ገበያ ሊሄድ መሆኑን ነገረው፡፡

ሚስቱ ከላዩ ላይ በርበሬ የተደረገበት እንጀራ በሰፌድ አቀረበችለት፡፡ ሼህ አደም ስለአጎቱ አበላል የገለጸበትን መንገድ አልረሳውም፡፡

“ወጥ የለ፣ ምን የለ በርበሬ ብቻ፡፡ እንጀራውን እየቆረሰ ደብ-ደብ፣ ደብ-ደብ እያደረገ መብላት ያዘ፡፡”

ሼህ አደም አጎቱን ጠየቀው፣ “በቅሉ ውስጥ ያለው (ለሽያጭ የተዘጋጀው) ምንድነው?”

“ቅቤ!”

“አጎቴ ሆይ! አንተ በድቁስ በርበሬ ቁርስህን እየበላህ፣ ቅቤ ትሸጣለህ?” ካለው በኋላ፣ የአንዱ ቅል ቅቤ ዋጋ ስንት እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡

ዋጋውን እንደነገረውም፣ “በቃ አንዱን እኔ ገዝቼሀለሁ፡፡ ለምግብ ተጠቀሙበት…” በማለት ሒሳቡን ከፈለው…

የሼህ አደም አጎት የግብይት ቀመር፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች የሚተገበር ቀመር ነው፡፡ ቅቤ ሸጦ ዘይት፣ ማር ሸጦ ስኳር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሸጦ ቡናና መሰል ነገሮችን መግዛት እጅግ የተለመደ የግብይት ቀመር ነው፡፡ ችግሩ ያለው፣ ምርትን ሸጦ ከቤት የሌለንና የሚያስፈልግን ነገር ከመግዛት ላይ ወይም የግድ አንዱ ሌላውን (ማር ስኳርን፣ ቅቤ ዘይትን) “ሁሌ መተካት ነበረበት” ማለት አይደለም፡፡ የቀመሩ እንከን ያለው፣ አብዛኛው ገበሬ ያመረተውን እንዳይጠቀም እስከ ማድረግ የደረሰ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡

ቀመሩ፣ በረጅም ጊዜ ሒደት ውስጥ የፈጠረውን የግብይት ባህል በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንድ ሊገኝ የሚችለውን ገንዘብ በማየት ገበሬዎች ራሳቸው ያመረቱትን የእህል፣ የፍራፍሬ፣ የአትክልት… ወይም ያረቡትንና ያደለቡትን የቤት እንስሳ ለምግብነት ከማዋል የሚያግድ ነው፣ ምግቡ ለአካላቸውም ሆነ ለጤናቸው በጣም አስፈላጊ ሆኖ እያለም ጭምር፡፡ “አሟጠው” ሊባል በሚችል ደረጃ ምርታቸውን እንዲሸጡ የሚያደርግ ነው፡፡

ሁለት ሊገኝ የሚችለውን ትርፍ በማሥላት አንድን የምርት ዓይነት በውድ ሸጦ፣ ሌላን ዋጋው ዝቅ ያለን ምርት በመግዛት ማትረፍ ወይም ብዛት ያለው እህል መግዛት የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ ጤፍ ሸጦ፣ ዳጉሳ እንደ መግዛት ያለ፡፡

የመጀመርያው የግብይት ባህል በአብዛኛው ገበሬ የሚተገበር ሲሆን፣ ከምግብ ሳይንስ ግንዛቤ እጥረት ጋር የሚገናኝ ነው (ከዚህ ዕልፍ ያለውን ምክንያት ደግሞ እያዋዛን እንመጣበታለን)፡፡ ሁለተኛው ግን ስለኢኮኖሚክስ በገበሬዎች ዘንድ ያለን ዕውቀትና ዕውቀቱን የመጠቀም ብልህነትን የሚያመላክት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡  

ለማንኛውም ይህን መሰሉ ትንታኔያችን ሼህ አደምን ከመሰሉና የገበሬዎቻችንን ባህል በወጉ ከማያውቁ ሰዎች “ለምን?” የሚል ጥያቄ ሲመጣ፣ የምንሰጠው መልስ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ጉዳዩ እምብርት ማለትም ስለምግብ ስላለን አረዳድና አጠቃቀም ትንሽ ገባ ጠለቅ ብለን ስናይ ግን የምናገኘው ትልቁ ምሥል ሌላ ሊሆን ይችላል… “ሆድ ባዶ ይጠላል…”፣ “ከሆድ የገባ ያገለግላል” መሰል ብሂሎች በረጅም ጊዜ ሒደት ውስጥ ያሰረፁት የደነደነ አስተሳሰብ ይኖራል፡፡ እሱን ሰርስሮ ማውጣት፣ ማየትና ማጥናት አስፈላጊ ነው…

በዚች ዓለም ለመኖር ከማንኛውም ነገር በፊት አየር (Oxygen) የግድ ያስፈልገናል፡፡ ከዚያ ምግብ (ውኃን ጨምሮ) ይከተላል፡፡ እርግጥ ነው በማስሎው የፍላጎት ደረጃዎች (Maslow’s Hierarchy of Needs) ውስጥ አየር አልተካተተም፡፡ የካፒታሊዝም አባዜ የአሜሪካን ምሁራንን ጭንቅላት ጭምር ስለበረዘ፣ ለሰው ልጅ በአንድ ቁጥር የሚያስፈልግ ሆኖ እያለ ስለማይሸጥና ስለማይለወጥ (ሕይወት ላለው ሁሉ በነፃ የተቸረ ፀጋ በመሆኑ ብቻ) ሳይኮሎጂስቱ ማስሎው ቢረሳው ብዙም ላያስገርመን ይችላል፡፡

ያም ሆነ ይህ ከአየር ቀጥሎ የምግብ ወሳኝነት አንድና ሁለት የሌለው የመሆኑ ጉዳይ የሚያወዛግብ አይደለም፡፡ ከርዕሰ ጉዳያችን አንፃር ዋናው ነጥብ ይህንን የመሰለ ቦታ ያለውን ጉዳይ ማለትም ምግብን “ኢትዮጵያውያን እንዴት አዩት? ምን ዓይነት ቦታስ ሰጡት?›› የሚለው ነው…

ከሦስት ወራት በፊት ነው ከመብላት ጋር የተያያዘን አንድ አባባል፣ ምሳሌያዊ አነጋገር መሆኑን ለማረጋገጥ፣ “ኦንላይን” ላይ ከሚገኝ የምሳሌያዊ አነጋገር መዝገበ ቃላት ላይ መፈለግ ጀመርኩ፡፡ በመካከሉ አንድ የሚያስገርም ነገር ገጠመኝ፡፡ “ሆድ” በሚለው ቃል ብቻ የሚጀምሩ ከ45 በላይ ተረትና ምሳሌዎች ሠፍረዋል፡፡ እንዲህ ቃል በተረትና ምሳሌ ውስጥ በስፋት የተደጋገመ ካለ ለማየት በወፍ በረር ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡ ለጊዜው አላገኘሁም፡፡ ቢገኝም ጥቂት ከመሆን አይዘልም፡፡

ሐበሾች በተለያዩ ብሂሎች (በተረትና ምሳሌ፣ በፈሊጣዊ አነጋገሮች፣ በግጥም፣ በሙሾ፣ ወዘተ.) “ለከት የለሽ” ሊባል በሚችል መንገድ የተረቱለትን፣ የደሰኮሩለትን፣ ያቀነቀኑለትን ምግብ እንዴት ነው የሚመገቡት? በሌላ አገላለጽ ከሆድ ጋር የተያያዘው የወግ ባህል ማጠንጠኛ የሆነው ምግብ፣ በወግ ባህሉ ውስጥ ያለው ትርክትና ዝማሬ ጣሪያ የነካውን ያህል፣ ዓይነቱን በማብዛትና በመቀያየር እንበላዋለን ወይ? ስለጥራቱ፣ የተመጣጠነ ስለመሆኑ መጨነቅ ይቅርና የምናስብ ስንቶቻችን ነን? 

ለዚህን መሰል ጥያቄዎች ጥያቄ “አዎ” የሚል መልስ መስጠት ይከብዳል፡፡ በድፍረት “አዎ” የሚል መልስ ብንሰጥ፣ ኩርፊያቸው ፎቅ ሊያንቀጠቅጥ የሚችል ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን የተቃውሞ ሠልፍ ባይወጡ እንኳን ይታዘቡናል፡፡

እስኪ ከፍ ሲል የጠቀስናቸውን ሁለት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ለአብነት ያህል ትንሽ በተን በተንተን አድርገን እንያቸው፡-

“ሆድ ባዶ ይጠላል…”- ይህ ብሂል የሚነግረን ሆድ ባዶ መሆን ስለማይፈልግ፣ መብላት ያለብን መሆኑን ነው፡፡ ሆድ ባዶ መሆንን ከጠላ “ምን እንብላ?” ለሚለው ጥያቄ ግን፣ በቀጥታ ቀርቶ በተዘዋዋሪ እንኳን ጠቆም የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ‹‹ምንም ይሁን ምን ብላ፣ ምንም ይሁን ምን ብዬ›› የሚል ይመስላል፡፡   

“ከሆድ የገባ ያገለግላል” ይህኛው ብሂል በበኩሉ የሚነግረን፣ ለሆድ ስንቅ የማቀበልን ፋይዳ ነው፡፡ ሆኖም መብላቱ (መግባቱ) ስለሚያስገኘው ጥቅም እንጂ፣ ስለሚገባው ነገር ዓይነት፣ ጥራትም ሆነ መጠን የሚለው ነገር የለም፡፡ ምንም ይሁን ምን ብቻ ይግባ! “ለምን?” ቢሉ፣ መልሱ “የገባ ያገለግላል” የሚል ነው፡፡

የመጀመርያው አባባል ሆድ ባዶ መሆን እንዴሌለበት ሲነግረን፣ ይህኛው ደግሞ ምንም ይሁን ምን በልተን ሆዳችን ባዶ እንዳይሆን ካደረግን፣ ከዚያ በኋላ ዕዳው ገብስ መሆኑን እያበሰረን ነው ያለው… አሰስ ገሰሱን ብቻ ሳይሆን፣ አፈሩንም ሆነ ቅጠላቅጠሉን ከምግብነት “ሜኑ” ለማስወጣት የምንችለው፣ ሁለቱን ብሂሎች፣ “ቤት ያፈራውን መብላት” በሚለው አነጋገር ከገደብናቸው ወይም ካለዘብናቸው ብቻ ነው፡፡

ይህም ሆኖ እዚህ ላይ አንድ የሚያስቸግረን ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ፣ “ሆድ ባዶ ይጠላል…” የሚለው አነጋገር ተቆርጦ የቀረ አባባል አለው “ድንጋይም ቢሆን” የሚል፡፡ ሙሉ አባባሉ፣ “ሆድ ባዶ ይጠላል፣ ድንጋይም ቢሆን” የሚል ነው፡፡ ስለሆነም “ከገባልህ ድንጋይም ቢሆን ብላ” የሚል መልዕክት እየተላለፈ ነው፡፡

ይህን ያሉት የቀድሞ ሐበሾች ለቀልድና ለቱማታ እንዳይደለ ግልጽ ነው፡፡ ችጋር፣ ቸነፈርና ርሀብ ምን ያህል ተጣብተውን ዘመናትን እንደ ዘለቁ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋ በሚያስቆርጥ ደረጃ ሲያሰቃዩን እንደ ኖሩ እነዚህና መሰል ተረትና ምሳሌዎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ 

ጅብሰም፣ የጣውላ ፍቅፋቂ፣ ወዘተ. ከጤፍ ወይም ከሌላ የእህል ዓይነት ጋር ቀላቅለው በመፍጨት ለሆቴል ወይም ለሬስቶራንት እንጀራ የሚያቀርቡት ነጋዴዎች፣ “ሆድ ባዶ ይጠላል፣ ድንጋይም ቢሆን” በሚለው አነጋገራችን ተገፋፍተው እንዳልሆነ ግን ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እነሱን ለዚህ ዓይነቱ ገልቱነት ያበቃቸው ዕምነት የለሽነት ወይም ህሊና ቢስነት ነው፡፡ ሰው ከሁለቱ አንዱን ከተነፈገ፣ ከእንስሳነት የባህሪ ድንበር ላይ የቆመ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መደርደር አስፈላጊ አይደለም፡፡

አሁን አዲስ አበባ የሚኖር አንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ የነበረ ጋዜጠኛ እንደ ነገረኝ፣ ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት እንጀራ በምግብ ቤቶች የመገኘቱ ጉዳይ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ያለ ችግር ነው፡፡ ህሊና ቢሶቹ ወይም ዕምነት የለሾቹ አይጥ እያረቡ በማረድ “ዱለት” በማለት እስከ መሸጥ ደርሰዋል (በዚህ እንደሚጥሚጣ በሚለባለብ የኑሮ ውድነት፣ “ዱለቱ” በርከት ያለ ሆኖ፣ ዋጋው ትንሽ ቀነስ ያለ “ምግብ” አዲስ አበባ ላይ በልተን ከሆነ ምናልባትም… ለማንኛውም አሁን እንዳያቅለሸልሸን…)፡፡

ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ከሆድ (ከምግብ፣ ምግብ ከመብላትና ከማብላት፣ ምግብ ከመስጠትና ከመንፈግ) ጋር የተያያዙ የአማርኛ ተረትና ምሳሌዎች፣ ፈሊጦች፣ ግጥሞች፣ ትርክቶች… ያለ ጥርጥር ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ሆድና የሆድ ነገር የሐበሻን ትርክት፣ ተረትና ምሳሌያዊ አነጋገሮች በአጭሩ የሐበሻን የወግ ባህል በስፋት ተቆጣጥረውት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ መልዕክቶቻቸውን፣ ትርጓሜያቸውን፣ አንድምታቸውንና ፍልስፍናቸውን ጭምር ጠለቅ ብሎ መፈተሽ መፈታተሹ አይከፋም… (በክፍል ሁለት እንገናኝ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...