Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

አቅም ለሌላቸው የካንሰር ሕሙማን አቅም የሚፈጥረው ተስፋ አዲስ

በኢትዮጵያ ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ በካንሰር በሽታ ተይዘው የሚሰቃዩ ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም የችግሩ አሳሳቢነት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን እየፈተነ ይገኛል፡፡ እነዚህም ሰዎች ልጆቻቸው ታመው ለማሳከም ቢፈልጉም እንኳን፣ አቅም ስለሌላቸው ብቻ የሰው ፊትን ለማየት ተገደዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት (ታፕኮ) እየሠራ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ሳራ ኢብራሂም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ ተስፋ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት እንዴት ተመሠረተ?

ወ/ሮ ሳራ፡- ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት የተመሠረተው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ ድርጅቱም የተቋቋመው በተወሰኑ ወላጆች አማካይነት ነው፡፡ እነዚህም ወላጆች ልጆቻቸው በካንሰር በሽታ ተይዘው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማስታመም ላይ እያሉ፣ ያለውን ችግር በማየት ድርጅቱን ሊመሠርቱ ችለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ድርጅቱ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸው ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠረ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?

ወ/ሮ ሳራ፡- ድርጅታችን የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ በፌዴራል መሥሪያ ቤቱ ሕግና ደንብ መሠረት በአዋጅ ቁጥር 621/2009 መሠረት ተቋቁሞ መሥራት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ2,000 በላይ ታካሚዎች ሕክምናቸው እንዳይቋረጥ አድርጓል፡፡ ከማደሪያ አንስቶ እስከ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ትራንስፖርት፣ የሥነ ልቦና ምክርና ሌሎች አገልግሎቶችን ሊሰጣቸው ችሏል፡፡ በተለይም በዋናነት የሕፃናት ካንሰርን በሽታ ለመከላከልና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከጥቁር አንበሳ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ የካንሰር ሕሙማን አገልግሎቱን እያገኙ ነው፡፡ ድርጅቱም በገንዘብ ምክንያት የሕክምና አገልግሎቱን ሳያገኙ ለሚሄዱ ሕሙማን በፍጥነት በመድረስ ሕክምና እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ የሕክምና አገልግሎቱንም ፈልገው የሚመጡ ሕሙማንን ወላጆቻቸው በፍጥነት ወደ ተቋሙ ካመጧቸው የመዳን ዕድላቸው ሰፊ ሲሆን፣ አንዳንድ ወላጆች ግን ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸውና ከረፈደ በኋላም በመምጣታቸው የተነሳ ልጆቻቸው ለከፋ ችግር ሲጋለጡ ይታያል፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ሕሙማንን ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ እንዲያገግሙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ ከሩቅ ቦታ መጥተው ልጆቻቸውን ለሚያስታምሙ ወላጆች ተቋሙ ከሕክምና ጀምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?

ወ/ሮ ሳራ፡- በእርግጥ በሥራችን ላይ የተለያዩ ችግሮች ይገጥሙናል፡፡ በተለይም ደግሞ ለሕሙማን የሚሆን መድኃኒት እጥረት በመኖሩ ፈተና ሆኖብናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ተቋሙን ተገን አድርገው ለመነገድ የሚሞክሩ በመኖራቸው ሥራችን ላይ እንቅፋት ሊሆኑብን ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕክምና አገልግሎቱ በሚሰጥበት ጊዜ ራዲዬሽን ለመትከል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ ብቻ በመሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ሕሙማን ችግር ውስጥ ሊወድቁ ችለዋል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎቱ ሲሰጥ አብዛኛውን ጊዜ ለሕክምና የሚሆነው ማሽን ስለሚበላሽ ሕሙማንን ችግር ላይ ሲወድቁ ለማየት ችለናል፡፡ ነገር ግን በቅርቡም ይኼው የሕክምና አገልግሎት በጅማ ሆስፒታል በመጀመሩ ችግሩን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሊቀረፍ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህም በቂ ነው ማለት ትንሽ ነገሩን አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ሌላው ተቋሙ የራሱ የሆነ ተሽከርካሪ ስለሌለውና ተከራይቶ ስለሆነ፣ ሕሙማንን የማመላለስ አገልግሎት የሚሰጠው ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ ነው፡፡ ይህንንም መቅረፍ ከተቻለ በርካታ ሕሙማንን መታደግ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራታችሁ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?

ወ/ሮ ሳራ፡- ተቋማችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ከጤና ሚኒስቴርና እንደኛው ዓይነት መሰል ሥራዎችን ከሚሠሩ ተቋማት ጋር ቁርኝት በመፍጠር እየሠራን ነው፡፡ በተለይ የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሙን ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የመድኃኒትና ሌሎች ነገሮች በቀላሉ ያቀርቡልናል፡፡ ሙል ሙል ዳቦ የተሰኘው ድርጅትም ሕሙማንን በባዶ ሆዳቸው መድኃኒት እንዳይወስዱ ዕንቁላል፣ ዳቦና ወተት ያቀርብልናል፡፡ ኤምባሲዎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጉልናል፡፡ የሕክምና አገልግሎቱን የሚያገኙት ልጆች ወደ ተቋሙ የሚመጡበት የራሱ የሆነ አሠራር አለው፡፡ ተቋሙም በዚህ ችግር የወደቁ ሕሙማንን በመታደግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ አገልግሎቱን የሚያገኙት ዕድሜያቸው ከጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ሳራ፡- ተቋሙ በቀጣይ የተሻለ የሆነ አገልግሎት ለመስጠትና በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ ሌላው ጅማ ላይ የሚገኘው ማዕከላችን 500 ካሬ ሜትር መሬት ከመንግሥት በኩል የተበረከተልን ስለሆነ፣ መሬቱ ላይ አንድ ሰፊ የሆነ ማዕከል ለማቋቋም ዕቅድ ይዘናል፡፡ የሕክምና አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድ በጎንደርና በሌሎች ቦታዎች ላይ ማዕከሎችን ለማቋቋም እንቅስቃሴዎች ጀምረናል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦትና የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ በቀጣይ የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?

ወ/ሮ ሳራ፡- በመንግሥት በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በተለያየ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት ተቋሙ እየሠራ ያለውን ሥራ ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ መሠረት የተለያዩ ድጋፎችን ያደረጉልን ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር የካንሰር ሕክምና ኬም ቴራፒ በነፃ እየሰጠን ይገኛል፡፡ የካንሰር መድኃኒት የሆነው ኬም ከትንሽ ጀምሮ እስከ ትልቅ ድረስ ያለ ሲሆን፣ ዋጋው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ ሕክምና ሒደትም ለአንድ ሰው በትንሹ ከ20 ሺሕ ጀምሮ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ይህም በጣም ከፍተኛ ስለሆነ የመንግሥት ድጋፍ እጅግ የላቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

መንግሥት በግማሽ ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ያህል ቀጥታ ብድር መውሰዱ ታወቀ

የአገር ውስጥ ብድር ከ1.6 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል የብሔራዊ ባንክ...

ብልጽግና ፈተና ሆነውብኛል ያላቸውን አምስት ተግዳሮቶች ይፋ አድርጎ የአግዙኝ ጥሪ አቀረበ

ብልፅግና በነፃነት ስም በሚፈጸም ወንጀል ምክንያት በትግሉ ያገኘውን ነፃነት...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...

በደብረ ብርሃን ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ያስጠለሉ ተቋማት ክልሉ እንዲያስለቅቅላቸው ጠየቁ

በአበበ ፍቅር በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ...