Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያ በምታሰናዳው የቴኒስ ሻምፒዮና 28 አገሮች ይሳተፋሉ

ኢትዮጵያ በምታሰናዳው የቴኒስ ሻምፒዮና 28 አገሮች ይሳተፋሉ

ቀን:

ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ኢንተርናሽናል ጁኒየር ሠርኪውት የቴኒስ ውድድር ላይ 28 አገሮች እንደሚሳተፉ ተገለጸ፡፡

ከየካቲት 4 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ በሚከናወነው ሻምፒዮና ላይ ከአውሮፓ አሜሪካና እስያ፣ ከአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተጫዋቾች አዲስ አበባ በመክተም ይሳተፋሉ፡፡

በሻምፒዮና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተወዳዳሪዎች የሚካፈሉበት ሲሆን፣ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ከ50 በላይ ተጫዋቾች እንደሚካፈሉበት የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ሰብሳቢና የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሚካኤል ንጉሤ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሻምፒዮናው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፍ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር እንደሚሰናዳ ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ ቴኒስ ፌዴሬሽን ውድድሩ እንዲሳካ የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ ሎጅስቲክስ የመጫወቻ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ዳኞች በማስመጣት ሻምፒዮናውን እንዲከናውን ማድረጉን አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል፡፡ ሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታ የሚከናወን ሲሆን፣ የዓለም አቀፉን የውድድር ቅርፅ ተከትሎ ይከናወናል ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት የካቲት 4 እና 5 የማጣሪያ ውድድር እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን ከእስራኤል፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ ብራዚል፣ አሜሪካ፣ እንዲሁም ከናምቢያ፣ ኬንያና ሞሮኮ የተውጣጡ ተጫዋቾች ተካፋይ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከወራት በፊት ዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ የግምገማ ቡድን ልኮ አጠቃላይ የመጫወቻ ሜዳውን፣ እንዲሁም የተለያዩ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን መገምገሙ ተጠቅሷል፡፡

ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን የቴኒስ መጫወቻ ሜዳ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ በዙር የሚደረገውን ውድድር የማሰናዳት ዕድል ለማግኘት መቻሏን አቶ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴኒስ የዳኞች እጥረት እንዳለ የሚያነሱት አቶ ሚካኤል፣ ከዚህ ቀደም ከኬንያ ዳኞችን ሲያስመጡ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በአንፃሩ አሁን ፌዴሬሽኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከውድድሩ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ለኢትዮጵያውያን ዳኞች ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ለ14 ቀናት የሚዘልቀው ሻምፒናው በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፣ የሜዳ ጥበት ከመጣ በግሪክ ክለብ ውድድሩ እንደሚቀጥል አቶ ሚካኤል አንስተዋል፡፡

ቴኒስ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን (1881 – 1909) የባቡር ሐዲድ ግንባታ ላይ በተሰማሩ ፈረንሣዮች አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ እንደገባ የሚነገር ሲሆን፣ ስፖርቱ በፌዴሬሽን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ፣ የተፈለገውን ያህል መንገድ መጓዝ አልቻለም፡፡ በተለይ ስፖርቱ የሀብታም ተደርጎ መቆጠሩና ቁሳቁሶቹም ውድ መሆናቸው በዋነኛነት እንደ ምክንያት ይነሳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ባላት አቅም ስፖርቱን በልጆች ላይ መሥራት ቢቻልም፣ ከዓለም አቀፍና ከአፍሪካ ቴኒስ ፌዴሬሽኖች ጋር በትብብር መሥራት አለመቻሉ ለስፖርቱ መቀዛቀዝ ችግር ተጠቃሽ መንስዔ ነው፡፡

ከሠላሳ ዓመታት በፊት ስፖርቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደነበርና ምድር ጦርና  አየር ኃይል የነቃ ተሳትፎ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አኅጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረው የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን፣ ስፖርቱ ሳይንሳዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አቶ ሚካኤል ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡም ፌዴሬሽኑ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ተናግረዋል፡፡   

ከዚህም ባሻገር ፌዴሬሽኑ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጀምሮ የቴኒስ ስፖርት እንዲያዳብሩ ጁኒየር ቴኒስ ኢኒሼቲቭ የተባለ መርሐ ግበር ቀርፆ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ለክልሎችም የአሠልጣኞችና የዳኞች ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተነስቷል፡፡ በየዓመቱም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እየተካሄ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ስፖርቱ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖር የማስገንዘቢያ ሥራ ለመሥራት ዕቅድ በመያዝ እየተንቀሳቀስ መሆኑና ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቆ በራሱ እንዲቆም ለማድረግ መወጠኑንም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...