በአበበ ፍቅር
በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞን በፀግብጂ ወረዳ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን፣ የወረዳው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ፡፡
ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም. የወረዳው ሚሊሻዎች ተሰባስበው ባሉበት አካባቢ የሕወሓት ታጣቂዎች ከበባ በማድረግ ከባድ ተኩስ እንደከፈቱባቸው፣ የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታዊ ሹሜ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተኩስ ልውውጡም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ ሁለት ሚሊሻዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ሚሊሻዎች መቁሰላቸውን አቶ ጌታዊ አስረድተዋል፡፡
በአካባቢዎቹ በአሁኑ ጊዜ ተኩስ መቀጠሉን ገልጸው፣ የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ጥራሪ ወንዝ እየተባለ በሚጠራው አካባቢና ወዲ ገብሩ በሚባለው የአማራና የትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራ የሕወሓት ታጣቂዎች በብዛት ሠፍረው እንደሚገኙ የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹በወዲ ገብሩ አካባቢ ወታደራዊ ሥልጠና እንደሚወስዱ ለማወቅ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡
ከ450 በላይ ሚሊሻዎች ወደ ወረዳው የገቡ ቢሆንም፣ የሕወሓት ታጣቂዎች እጅግ በርካታ ከመሆናቸውም በላይ የታጠቁት መሣሪያ ዘመናዊ በመሆኑ ለመከላከል ከባድ እንደነበር ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ብሬን፣ ስናይፐር፣ ድሽቃና ሞርታር የተባሉ መሣሪያዎችን በብዛት ሲጠቀሙ እንደነበር የተገናሩት አቶ ጌታዊ፣ ትጥቅ እየፈቱ ነው የተባሉት ኃይሎች ኃይሎች ዙ 23 የተባለውን መሣሪያ ይዘው በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን አክለዋል፡፡
ቀደም ሲልም ፀግብጂና አበርገሌ ወረዳዎች ነፃ እንዳልወጡ ተናግረው፣ አሁን በሚታየው ትንኮሳ የክልሉም ሆነ የፌዴራል ኃይሎች ያደረጉት እንቅስቃሴ የለም ብለዋል፡፡
የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደበሽ በበኩላቸው፣ በአካባቢው ተከሰተ የተባለው ግጭት ቀላል የሚባል ነው ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው በረሃብና በችግር የሚሰቃዩ ወገኖቻቸውን ችግር በማየት፣ እኛስ እስከ መቼ ከቀዬአችን ርቀን በሚል ስሜት ተነሳስተው ወደ ወረዳው በገቡ የአካባቢው ሚሊሻዎችና ወረዳውን ተቆጣጥረው በሚገኙ የሕወሓት ታጣቂዎች መካከል የተነሳ ግጭት ነው ሲሉ የግጭቱን መነሻ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በወረዳው በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን መደፈር ጨምሮ የሚዘረፉና የሚወድሙ ንብረቶች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን የገለጹት የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታዊ፣ ሸሽቶ ያልወጣው ኅብረተሰብ በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ ነው ያለው ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ የአርሶ አደሩን በሬ እያረዱ እየበሉበት እንደሆነ ለማወቅ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ችግሩ ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው ነዋሪዎች ድምፃቸውን ያሰሙልናል ያሏቸውን ሰዎች ወክለው እስከ ክልሉ መንግሥት ድረስ በመሄድ ችግራቸውን ያሳወቁ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ምላሽና መፍትሔ አላገኙም ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ንብረት ከመዝረፍ ባሻገር ልጆቻችሁን አምጡ በማለት፣ ሽማግሌዎችን ጭምር በማዋከብ ላይ መሆናቸውን አቶ ጌታዊ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህና ተያያዥ ምክንያቶች ወረዳውን በመልቀቅ ወደ መጠለያ ጣቢያ የሚገባው ተፈናቃይ ቁጥር መጨመሩን ጠቁመው፣ በአካባቢው በቂ የሆነ ዕርዳታ የለም ብለዋል፡፡
እናቶች ልጆቻቸውን የሚያበሉት አጥተው በረንዳ ላይ ወድቀው በረሃብና በብርድ እየተሰቃዩ ነው ያሉት ኃላፊው፣ የክልሉ መንግሥት ያለውን ችግር በአፅንኦት ተረድቶ አካባቢውን ነፃ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከሁለቱ ወረዳዎች ተፈናቅለው ያሉትንም ሆነ በመፈናቀል ወደ ካምፕ እየገቡ ያሉትን ዜጎች ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት፣ መንግሥትን ጨምሮ ባለሀብቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡