Thursday, April 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር፣ አገርን ሌላ አስከፊ ቀውስ ውስጥ የሚከት የሃይማኖት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ ዕፎይ ማለት በሚገባት በዚህ ወቅት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ችግር ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ የአገር ሰላም የሚያናጋ ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ለመፍትሔው መረባረብ ይገባል፡፡ የአገርን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመግባባት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ዶግማና ቀኖና መሠረት ያጋጠመው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ዕገዛ ያድርግ፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ኃላፊነት ጣልቃ ሳይገባ ሕግ እንዲከበር ማድረግ ብቻ ነው፡፡ የአገር ሰላም እንዳይናጋና የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጠር የማድረግ ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ያጋጠማትን ችግር በራሷ እንድትፈታው ማድረግ ላይ ያተኩር፡፡ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ አደገኛ ጎዳና ውስጥ እየተገባ ስለሆነ፣ ዕልቂትና ውድመት እንዳይከተል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉትን ጭምር በማበርከት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሙያና የሲቪክ ማኅበራት ወኪሎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ አደረጃጀቶችን የሚወክሉ በሙሉ አገር ከገባችበት ቀውስ ውስጥ እንድትወጣ ዕገዛ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት በብሔርና በሌሎች ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ጠቦችና ግጭቶች ያደረሱት ጥፋት አልበቃ ብሎ፣ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ሳቢያ አስፈሪ ሥጋት አፍጥጦ ሲመጣ ቆሞ ማየት አይቻልም፡፡ አገር በሃይማኖት ምክንያት ችግር ሲገጥማት አላስፈላጊ ድርጊቶችን ወደ ጎን በማድረግ፣ በፈጣን መፍትሔ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ካልተቻለ ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ አውዳሚ ነው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ሳይገባ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ይወጣ፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም ያለ ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግራቸውን በሥርዓታቸው መሠረት ይፍቱ፡፡ አገር ሰላምና መረጋጋት የምታገኘው በሕግና በሥርዓት መምራትም ሆነ መመራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ለአገር ሰላምና መረጋጋት እንቅፋት የሚፈጥሩ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን በማይመለከተው የእምነት ተቋም ውስጣዊ ጉዳይ መፈትፈት የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ውስጥ መሽገው ጠብና ግጭት የሚያስፋፉ በዝተዋል፡፡ አንድም ቀን ለአገር ሰላምና ዕድገት አስተዋፅኦ የሌላቸው፣ ነገር ግን አገር ችግር ሲገጥማት ጋዝና ክብሪት ይዘው ብቅ የሚሉ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ ከባህር ማዶ እስከ አገር ቤት ድረስ በተዘረጋው ኔትወርካቸው አማካይነት ኢትዮጵያን እሳት ውስጥ ለመክተት ሲጣደፉ ይስተዋላሉ፡፡ የፖለቲካ ችግራቸውን ከብሔር ጋር እየሸመኑ አገርን እንቅልፍ ነስተው መክረማቸው ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ ችግር እንደ ሰደድ እሳት ለማቀጣጠል ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአገር ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ ወገኖች እንዲህ ዓይነቶቹን ለማስቆምና ሰላም ለማስፈን መተባበር ያለባቸው፡፡ የአገር ህልውና የሚመሠረተው በሰላምና በመረጋጋት ላይ ስለሆነ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድነት በመቆም ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ አገር በጥባጮች ደግሞ ሰከን ይበሉ፡፡

የአገር ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚያስፈልግባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ሃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖቶች ችግር ሲገጥማቸው መንግሥት በሕገ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ኃላፊነቱን ሲወጣ፣ ዜጎችም የአገሪቱን ሕጎች አክብረው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ አጋጣሚውን ለግልና ለቡድን ጥቅማቸው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ አካላት ሲኖሩ ደግሞ በሕግ መባል አለባቸው፡፡ ሃይማኖትንና ብሔርን በማጋመድ ክፍተት ለመፍጠር ወይም ግጭት ለመጠንሰስ የሚፈልጉ አካላትም፣ ያለ ምንም ማወላወል በሕግ ሊዳኙ ይገባል፡፡ ሕግና ሥርዓት በአግባቡ ሲከበር ከሕገወጥነት ይልቅ ሕጋዊነት ስለሚበረታ፣ ሰላም ለማደፍረስ ለሚፈልጉ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ አይፈጠርም፡፡ ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠመውን ችግር ተገን በማድረግ አገር ለማተራመስ የሚፈልጉ አካላት፣ በቀና ልቦና መፈታት ያለበትን ችግር በመለጠጥ ሰላም እንዲደፈርስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የተፈጠረው ችግር ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣና ትርምስ እንዳይፈጠር፣ መንግሥት በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ የችግሩ ምንጭ የሚደርቀውም በዚህ መሠረት ነው፡፡

ሰሞኑን የተከሰተውን ችግር በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ ምክንያት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት አልፎ አካላዊ ጉዳት ደርሷል፡፡ አሁንም አድማሱን እያሰፋ ከቀጠለ ሊከሰት የሚችለው ቀውስ ከባድ እንደሚሆን ነጋሪ አያሻም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ከርማ፣ እንደገና ሌላ ዙር ግጭት ውስጥ ዘው ብላ ለመግባት ስትንደረደር ማንንም ሊያስደነግጥ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔር፣ በእምነትና በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶች ሰልችተውታል፡፡ በከፋ ድህነት ውስጥ ሆኖ የረባ ምግብ ማግኘት ያቃተው ሕዝብ፣ ሕይወቱን የሚቀጥፍና አገሩን የሚያፈርስ ግጭት ሲጠነሰስበት ይከፋዋል፡፡ ከዚህ በፊት መለስተኛ ግጭቶችም ሆኑ አውዳሚ ጦርነት ከመከሰታቸው በፊት ተማፅኖ ሲቀርብ ችላ እየተባለ፣ ከዕልቂትና ከውድመት በኋላ የሚሰሙ የዋይታና የፀፀት ድምፆች ከንዴት በስተቀር የሚፈይዱት አይኖሩም፡፡ አሁንም ችግሩን በውል አጢኖ ለሕዝብም ለአገርም የሚበጅ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ በሃይማኖት ምክንያት የሚነሳ ቀውስ ማቆሚያ ሊኖረው ስለማይችል፣ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ተሻጋሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው አማካይነት የሚያንዣብበውን አደጋ መቀልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዚህ ዘመን ትውልድ ኢትዮጵያ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋ እዚህ የደረሰች አገር መሆኗን ለመረዳት የታሪክ ድርሳናትን ማገላበጥ ይኖርበታል፡፡ ባለፉት ዘመናት የነበሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል በአንድነት መቆም የቻሉት፣ ከልዩነቶቻቸው በላይ የሚያፈቅሯት አገራቸውን ከምንም ነገር በላይ ስለሚያስቀድሙ ነበር፡፡ የተለያዩ ገዥዎች እየተፈራረቁ ሥልጣነ መንበሩ ላይ ተቀምጠው ሲመሩም፣ ጭቆናና በደሉ ቢከፋም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሲሉ ሁሉንም ነገር ችለው ዘመናትን በጋራ አሳልፈዋል፡፡ በዕብሪታቸውና በጥጋባቸው የሚታወቁ መሪዎች እንዴት እንዳለፉም ታሪክ ይዘክራል፡፡ ታሪክን የኋሊት መለስ ብሎ ማየት የሚጠቅመው የሌሎችን ስህተት ላለመድገም ነው፡፡ ‹‹ከታሪክ የማይማር የታሪክ ማስተማሪያ ይሆናል›› እንደሚባለው፣ በዚህ ዘመን በዕርጋታና በስክነት የተፈጠሩ ስህተቶችን አርሞ ለአገር ልማትና ዕድገት በጋራ መረባረቡ ያዋጣል፡፡ ከታሪክ መማር ያልፈለጉ ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ ከተው የደረሰው ዕልቂትና ውድመት ከሚገባው በላይ ታይቷል፡፡ የዚያ አስከፊ ጦርነት ጠባሳ ሳይሽር ተመልሶ ሌላ ግጭት እንዲቀሰቀስ መፍቀድ፣ በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ መቆመር ነው፡፡ የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...