Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ጥቁር በለበሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸምን እስርና ድብደባ እንዲያስቆም ኢሰመጉ አሳሰበ

መንግሥት ጥቁር በለበሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸምን እስርና ድብደባ እንዲያስቆም ኢሰመጉ አሳሰበ

ቀን:

መንግሥት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈ መልዕክ መሠረት ጥቁር ልብስ በለበሱ ምዕመናን ላይ የሚፈጸሙ እስራትና ድብደባዎችን እንዲያስቆም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ አሳሰበ፡፡ ከሕግ አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ድብደባና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ የፀጥታ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶሱ በተላለፈው መልዕክት መሠረት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎችን በአንዳንድ አካባቢዎች እስራት፣ እንግልትና መዋከብ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡

ድርጊቱን አንዳንድ ተቋማት ሠራተኞች ጥቁር እንዳይለብሱ እያደረጉ መሆኑን ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳት መቻሉን ያስታወቀው ኢሰመጉ፣ ጉዳዩ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ በመሄድ ተባብሶ ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጥፋት እንዳያስከትል የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዕውቅና ያልተሰጣቸው አዲስ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ወደ አብያተ ክርስቲያናት በመንግሥት በፀጥታ ኃይል ታጅበው በመግባታቸውና ምዕመኑ ይህን ባለመቀበሉ፣ በተፈጠረው ግጭት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አካቷል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት በተተኮሱ ጥይቶች የሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጸው ኢሰመጉ፣ በያቤሎ አካባቢ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ጭምር እስራት፣ ማዋከብና ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ በእምነቱ ተከታዮችና በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ድብደባ፣ ቤት ሰብሮ በመግባት የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ እስራቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመጉ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ በዋናነት ችግሮች እየተፈጠሩበት ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ አካላት በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ያልተሰጣቸውን ኤጲስ ቆጶሳት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያን መመደብ አግባብ እንዳልሆነ በመግለጽ የተቃወሙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችን ከሕግ አግባብ ውጭ የሆነ ግድያ፣ እስር፣ ድብደባና አካል ማቁሰል እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ መንግሥት ድርጊቱን እንዲያስቆም ኢሰመጉ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3 መንግሥት በሃይማኖት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ ሃይማኖትም በመንግሥት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ እንደሚደነግግ ኢሰመጉ ገልጾ፣ የሲቪልና የፖለቲካ ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 18 ማንኛውም ሰው የሐሳብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት እንዳለው እንደሚደነግግ አስታውሷል፡፡

 መንግሥት የማኅበረሰቡን ደኅንነትና ሰላማዊ መስተጋብር የማስከበር፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 እና ከሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ አገላለጽ መረዳት ይቻላል ሲልም ኢሰመጉ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ እሑድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሀገረ ስብከት በሶዱ ዳጨ ወረዳ ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በመጣስ›› 26 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም ‹‹ሲኖዶስ አቋቁመናል›› በማለታቸው፣ ድርጊቱ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሦስት ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሳተፉ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን መለየቱ ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዛቸው ሦስቱ ጳጳሳት ግን የሾሟቸውን ኤጲስ ቆጶሳት በተሾሙበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ገብተው እንዲያገለግሉ የማድረግ እንቅስቃሴ በመጀመሩና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ድርጊቱን በመቃወማቸው፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በምዕመናን ላይ ግድያና ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት፣ በፆመ ነነዌ ጥቁር ልብስ በመልበስ ምህላና ፀሎት እንዲያዝ ትዕዛዝ ማስተላለፏ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...